Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

እውን ሠዕለባ ሙናፊቅ ነውን?

እውን ሠዕለባ ሙናፊቅ ነውን?

ሠዕለባህ ኢብኑ ሓጢብ አልበድሪ አልአንሷሪ ከነቢዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ምርጥ ሶሐቦች አንዱ ነው፡፡ እሱን የሚመለከት በተለያዩ ቦታዎች በተለያዩ አጋጣሚዎች የሚነሳ አንድ ታሪክ አለ፡፡ ብዙዎቻችን እንደሰማነው አስባለሁ፡፡ ለማስታወስ ያክል የታሪኩ ጭብጥ ቃል በቃል ሳይሆን እንዲሁ ባጭሩ ይህን ይመስላል፡፡
ሠዕለባህ ደሃ ሰው ነበር፡፡ አላህ ገንዘብ እንዲሰጠው ዱዐ እንዲያደርጉለት ነብዩን ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ይጠይቃቸዋል፡፡ እሳቸውም “ጥቂት አላህን የምታመሰግንበት ገንዘብ ብዙ ሆኖ ከማትችለው ይበልጥብሃል” ብለው ይቅርብህ ይሉታል፡፡ “በሐቅ በላከህ ጌታ እምላለሁ አላህ ገንዘብ ከሰጠኝ ባለሐቅ ለሆነ ሁሉ እስጥ ነበር” እያለ ሲጠይቃቸው ዱዐ ያደርጉለታል፡፡ ለመስጂድ ካለው ቅርበት የተነሳ “የመስጂድ እርግብ” ሲባል የነበረው ሠዕለባህ መዲናን ማጨናነቅ የያዙትን በጎቹን በመከተል ከጀማዐ መዘናጋት ያዘ፡፡ የተወሰኑ ወቅቶች ላይ ብቻ ሆነ የሚገኘው፡፡ ቀስ በቀስም ጁሙዐ ብቻ ሆነ የሚመጣው፡፡ እያለም መዲና አልበቃቸው ያሉትን በጎቹን ተከትሎ ከናካቴው ከመስጂድ ጠፋ ከከተማም ራቀ፡፡ ይባስ ብሎም አላህ ከሰጠውና ከመስጂድ ለመራቅ ሰበብ ከሆነው ሀብቱ ዘካ ለመስጠት ነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ሰው ቢልኩበት ፈቃደኛ ሳይሆን ቀረ፡፡ እሱን አስመልክቶም የቁርኣን አያዎች ወረዱ፡፡ በዚህ የተደናገጠው ሠዕለባህ ወደነቢዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም በመምጣት ተውበት ለማድረግ ቢጠይቅ ሳይቀበሉት ቀሩ፡፡ በአቡበክርም፣ በዑመርም፣ በዑሥማንም የኺላፋ ዘመን በመምጣት ተውበት ቢጠይቅ ሳይቀበሉት ቀሩ፡፡…
ታሪኩ በተለያዩ የተፍሲር ኪታቦች ላይ ተጠቅሷል፡፡ ነገር ግን ይህን ታሪክ ውድቅ የሚያደርጉ ብዙ ምክኒያቶችን ምሁራን ይጠቅሳሉ፡፡ ከነዚህም ውስጥ
  1. ቀዳሚው ምክኒያት የሐዲሡ ደካማ መሆን ነው 
በርካታ ሙሐዲሦች ታሪኩን “ደካማ/ዶዒፍ” ነው ሲሉ አጣጥለውታል፡፡ ለምሳሌ፡- ኢብኑ ሐዝም፣ በይሀቂ፣ ቁርጡቢ፣ ኢብኑልአሢር፣ ዘህቢ፣ ዒራቂ፣ ሐይሠሚ፣ ኢብኑ ሐጀር፣ አልመናዊ፣ ሲዩጢ፣ ኢብኑልወዚር፣ አሕመድ ሻኪር፣ አልባኒ፣ ሙቅቢል አልዋዲዒ፣ እና ሌሎችም…፡፡ እንደሚታወቀው  የመረጃዎችን ድክመትና ጥንካሬ በመገምገም በኩል የሙሐዲሦች ውሳኔ ከሌላው ቀዳሚ ነው፡፡ ታሪኩ ምንም ሳያጣሩ ያገኙትን ለጆሮ እንግዳ የሆኑ ቂሳዎችን ይዘው በየሄዱበት በሚያራግቡ ደስኳሪዎች በሰፊው በመራገቡ የተነሳ ከብዙዎቻችን ጆሮ ደርሷል፡፡ ነገሩ ከመደጋገሙ የተነሳ አንዳንዶቻችን ጋር የማይነቃነቅ እውነታ እስከሚመስል ደርሷል፡፡ በዚህም የተነሳ የዚህ ቂሳ ደካማነት ሲነገራቸው ብዙ የሚገረሙ ብዙ የሚደነግጡም አሉ፡፡ ቢሆንም ነፍስያችንን እንርገጥ፡፡ “ቀድመን የሰማነው ሁሉ መነካት የለበትም ባይጣራም ይቀመጥ” እንዳንል፡፡ አንድ ታሪክ ደጋግመን ብንሰማውም፣ እጅጉን ቢማርከንም፣ ስንሰማው ቢጣፍጠንም በዘርፉ ምሁራን ተፈትሾ መስፈርት ካላሟላ ይወድቃል፡፡ ነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም “ብለውታል” እየተባለ የሚወራ ግን በሐቂቃ የሳቸው ንግግር ያልሆነ ስንት አለ፡፡ ሐበሻን የሚያንቋሽሽ፣ ቱርኮችን የሚሳደብ፣ ጥቁሮችን በጅምላ የሚወነጅል ስንት ሐዲሥ አለ፡፡ በሙሐዲሦች ሲፈተሸ ግን መሰረተ-ቢስ ቅጥፈት እንደሆነ የተደረሰበት፡፡
ሠዕለባን የሚወነጅለው ታሪክም ልክ እንዲሁ መስፈርት የማያሟላ ደካማ ታሪክ ነው፡፡ የሰነዱ ደካማ መሆን ታሪኩን ከመሰረቱ ይንደዋል፡፡ ከዚህ በኋላ የሚጠቀሱ ምክኒያቶች የታሪኩን ድክመት ይበልጥ አጉልቶ ለማሳየት እንጂ ሐዲሡ ደካማ ነው ሲባል ሁሉም ያከትማል፡፡
2. ሠዕለባ በድር ላይ የተካፈለ ታላቅ ሰሐብይ ነው

ነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም “በድርና ሑደይቢያ ላይ የተካፈለ አንድም ሰው እሳት አይገባም” ብለዋል፡፡ እውነታው እንዲያ ከሆነ በድር ላይ የተካፈለው ሠዕለባ ቂሳው ላይ እንደተተረከው ሙናፊቅ ነው ማለት ከባድ ነገር ነው፡፡ ጌታችን አላህ በቁርኣኑ ((መናፍቃን ከእሳት የመጨረሻው አዘቅት ውስጥ ናቸው)) ይላል፡፡
ለዚህም ነው ኢማም አልቁርጡቢ “ሠዕለባህ በድር ላይ የተካፈለ አንሳሪ ነው፡፡ አላህና መልእክተኛው በኢማን ከመሰከሩላቸው ነው፡፡ ስለሱ የተወራውም ትክክል አይደለም” ይላሉ፡፡ ስለዚህ ይህን ያክል ታላቅ ቦታ ያለውን ሶሐቢይ ቀርቶ ማንንም ቢሆን ባልተረጋገጠ ወሬ በኒፋቅ መወንጀል ከባድ ነገር ነው፡፡
3. ታሪኩ ዘካ ከከለከለ ሰው በግድ መወሰድ እንዳለበት ከሚያዘው መርህ ጋርም ይጋጫል
ዘካ የከለከለ ሰው በሐዲሥ እንደተጠቀሰው በሀይል ይወሰድበታል እንጂ ዝም ብሎ አይተውም፡፡ ሠዕለባህ ላይ የሆነው ግን ይሄ አይደለም፡፡ ይስተዋል ሙናፊቅ ነው ብንል እንኳን ሙስሊሞችን የሚመለከተው የዘካ ህግ ይመለከታቸዋል፡፡ የዘካ ህጉ የፈቀደን በፈቃዱ እምቢ ያለን በግዱ መቀበል ነው፡፡ አቅም ካለ እስከ ጦርነት ይደርሳል እንጂ “አልሰጥም” ስላለ ማንም አይተውም፡፡ “አንሰጥም” ስላሉ ቢተውማ አመፀኞች የፍላጎታቸው ይሆን ነበር፡፡ “ዘካ አልሰጥም” ያለ ሁሉ ቢታለፍማ አቡ በክር አሲዲቅ ረዲየላሁ ዐንሁ “ዘካ አንሰጥም” ያሉ ሰዎች ጋር ስንተ ሰሐቦች ያለቁበት መሪር ጦርነት ባልገጠሙ ነበር፡፡ ለዚያም እኮ ነው “ለነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ይሰጡት የነበረውን - ሌላ ቀርቶ -  ገመድ ቢከለክሉኝ እሱን ለማስመጣት እዋጋቸዋለሁ” ያሉት፡፡ ታዲያ ገመድ ለማስመጣት የሚዋጋ ሰው ነው በፈቃዱ “ዘካ ልስጥ” የሚልን እምቢ የሚለው? መታወቅ ያለበት ዘካ በሀብታም ገንዘብ ላይ የተጣለ የድሃ ሐቅ እንደሆነ ነው፡፡ እራሱን እንደሙስሊም የሚያቀርበው ቀርቶ ዘካ ከወጀበበት በኋላ የከፈረ ሰው እራሱ የዘካው ገንዘብ ሊወሰድበት ይገባል ይላሉ ሻፊዒያዎች ኢማሙ ነወውይ ረሒመሁላህ እንደሚሉት፡፡
4. “አይ ዘካውን ያልተቀበሉት ስለከፈረ ነው” ከተባለም ታሪኩ የከፈረ ሰው መገደል እንዳለበት ከሚያዘው ኢስላማዊ መርህ ጋር ይጋጫል
ሠዕለባህ የሸሪዐ ህግ በሚተገበርበት በወርቃማው የኢስላም ዘመን ነው የኖረው፡፡ እንደሚታወቀው ሸሪዐዊ ህግ ባለበት ሀገር ውስጥ ከኢስላም የወጣን ሰው ሸሪዐው እንዲገደል ያዛል፡፡ ነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም “ዲኑን የቀየረን ግደሉት!” ብለዋልና፡፡ 
5.  “አይ ሠዕለባ ቀድሞ ሙስሊም ስላልነበረ ነው እርምጃ ያልተወሰደበት” ከተባለ
አንደኛ ነገር ሙስሊም ካልሆነ ለምን ዘካ ይጠየቃል? ሁለተኛ ሙስሊም ካልሆነ ዑመር ሙሽሪኮችን ከሀገር ሲያባርር ለምን እሱን ቶወው? ነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም “በህይወት ከቆየሁ በውስጧ ሙስሊሞችን ብቻ አስቀርቼ የሁዶችንና ነሳራዎችን ከዐረቢያ ልሳነ-ምድር አስወጣቸዋለሁ” ማለታቸው ይታወቃልና፡፡ ይሄ እንግዲህ ምናልባት “ቀድሞ ሙስሊም አልነበረም” የሚል ካለ ነው፡፡ ያለበለዚያ ሙስሊም እንደነበር ታሪኩም በደንብ ይጠቁማል፡፡ ቀድሞ “የመስጂድ እርግብ” የሚባል መሆኑ፤ ለአላህ ቃል ገብቶ የነበረ መሆኑና ከምንም በላይ ደግሞ በድሪይ መሆኑ ቀድሞ ሙስሊም እንደነበር ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፡፡
6.  ታሪኩ ኢስላም ካለው የተውበት መርህ ጋርም ይፃረራል
ተውበት ተቀባይነት የማያገኘው በደሊል እንደመጣው አንድ ሰው ወይ ሳይቶብት ቆይቶ የሞት አፋፍ ላይ ከደረሰ በኋላ የሚደረግ ተውበት ነው አለያ ደግሞ ፀሃይ በምእራብ ስትወጣ ነው፡፡ ነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም “ፀሀይ በመግቢያዋ እስካልወጣች ድረስ ተውበት አይቋረጥም” “አሸናፊና የላቀው አላህ ጣእረ-ሞት እስካልደረሰ ድረስ የባሪያውን ተውበት ይቀበላል” ብለዋል፡፡ 
7.  ታሪኩ በኢስላም ከየትኛውም ወንጀል ተውበት ያደረገን ሰው እንደሚማር ካለው መርህ ጋርም ይጣረሳል
((“በነፍሶቻቸው ላይ ገደብ ላለፉ ባሪያዎቼ “ከአላህ እዝነት ተስፋ አትቁረጡ፡፡ አላህ ወንጀሎችን በሙሉ ይምራልና፡፡ እነሆ እርሱ እጅግ መሃሪና አዛኝ ነው” በል፡፡)) (አዝዙመር፡ 53) በሐዲሠልቁድሲም ጌታችን አላህ እንዲህ ብሏል፡- “የአደም ልጅ ሆይ! እስከለመንከኝና ተስፋ እስካደረግብኝ ድረስ ላለብህ ወንጀል ደንታ ሳይኖረኝ እምርልሃለሁ፡፡ የአደም ልጅ ሆይ! ወንጀሎችህ የሰማይ ደመና ቢደርሱም ምህረትን ከጠየቅከኝ ጣጣ የለበኝም እምርልሃለሁ፡፡ የአደም ልጅ ሆይ! ምድርን ሊሞሉ የቀረቡ ወንጀሎችን ይዘህ ብትመጣና ብትገናኘኝ በኔ ላይ ምንም ካላጋራህ ምድርን ሊሞላ የቀረበ ምህረትን ይዤ እቀርብሃለሁ፡፡” አልባኒ “ሠሒሕ” ብለውታል፡፡
“አይ ሠዕለባ ሙናፊቅ ስለሆነ ነው ተውበቱ ተቀባይነት ያላገኘው” ከተባለም አያስኬድም!! ምክኒያቱም አላህ ለሙናፊቆቹም ከቶበቱ እንዲህ ሲል በሩን ክፍት አርጎላቸዋልና፡፡ ((መናፍቃን ከእሳት የታችኛው አዘቅት ውስጥ ናቸው፡፡ ረዳትም አታገኝላቸውም፡፡ እነዚያ የተመለሱት (ተውበት ያደረጉት)፣ ያሳመሩትም፣ በአላህ የተጠበቁትም፣ ዲናቸውን ለአላህ ያጠሩትም ሲቀሩ፡፡ እነዚያ ከአማኞቹ ጋር ናቸውና፡፡ አላህ ደግሞ ለአማኞቹ ታላቅ የሆነ ምንዳን ይሰጣል፡፡ ካመሰገናችሁና ካመናችሁ እናንተን በመቅጣት አላህ ምንም አያደርግም፡፡ አላህ አመስጋኝና አዋቂ ነው፡፡)) (አንኒሳእ፡ 145-147) በሱረቱተውባ፡ 74 ላይም የሙናፊቆችን ክህደትና ጥፋት ካነሳ በኋላ ((ቢመለሱ (ተውበት ቢያደርጉ) ለነሱ መልካም ነው)) በማለት የተውበት በር እንዳልተዘጋባቸው ያስረዳል፡፡
8. በታሪኩ ውስጥ ሠዕለባህ እንደሙስሊምም እንደካፊርም አልተያዘም፡፡
በታሪኩ ውስጥ ሠዕለባ ወይ እንደሙስሊም ተቆጥሮ ዘካውን አልተወሰደም ወይ እንደ ካፊር ተቆጥሮ እርምጃ አልተወሰደበትም፡፡ይሄ በኢስላም ያልተለመደ አሰራር ነው፡፡
9.  ሠዕለባህ የሞተበት ጊዜ በትክክል አለመታወቁ ነው
እንዳውም የተለያዩ የተራራቁ ዘገባዎች ናቸው ያሉት፡፡ ለምሳሌ እዚህ በኒፋቅ የተወነጀለበት ታሪክ ላይ በዑሥማን ጊዜ እንደሞተ ተጠቅሷል፡፡ ነገር ግን ይህን ታሪክ ሰነዱ ውድቅ ነው በማለት የዘርፉ ምሁራን ሙሐዲሦች ከመሰረቱ ንደውታል፡፡ በሌሎች ዘገባዎች ደግሞ “የኡሑድ ጦርነት ላይ ሸሂድ ሆኗል” የሚል አለ፡፡ ኢብኑ ዐብዲልበርና ኢብኑ ሐጀር ባወሱት ደግሞ የኸይበር ዘመቻ ላይ ሸሂድ ሆኗል የሚል አለ፡፡ ተመልከቱ! የኡሑድም የኸይበርም ዘመቻዎች የተደረጉት ነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም በህይወት እያሉ ነው፡፡ እውነት ሠዕለባ የሞተው ከነዚህ ጦርነቶች ባንዱ ከሆነ ሠዕለባ ከነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ቀድሞ ሞቷል ማለት ነው፡፡ የሞተበትን ትክክለኛ ዘመን አላህ ይወቅ፡፡ ብቻ ጉዳዩን ይህንን ከግምት አስገብተን ቆም ብለን ካየነው ሳያጣሩ በደካማ ታሪክ ተሞርክዘው ሠዕለባን ለሚወነጅሉ ሰዎች ይበልጥ አስደንጋጭ ይበልጥ አስፈሪ ነው፡፡
10. ዘካ መጄ ነው የተደነገገው?
ታሪኩ ላይ ሠዕለባ አለቅጥ በዝተው የሚርመሰመሱ በጎቹን ተከትሎ ከመዲና ከወጣ በኋላ ዘካን የምትደነግገዋ አያ እንደወረደች ያትታል፡፡ ያስተውሉ ለመውረዳቸው ሠዕለባ ሰበብ የተደረገባቸው ስለሙናፊቆች የሚያትቱት አንቀፆች አገባባቸው የሚያሳየው በተቡክ ዘመቻ ወቅት እንደወረዱ ነው፡፡ የተቡክ ዘመቻ ደግሞ ዘካ ከተደነገገበት አመት ዘግይቶ ከሂጅራ በኋላ በ9ኛ ዓመት ነው የተካሄደው፡፡ እንዲህ አይነት ህፀፆችን በመመልከት ነው አንዳንዶች ታሪኩን ከመሰረቱ ታላቁ የነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ሰሐባ ሠዕለባ ላይ የተፈፀመ አይን ያወጣ ቅጥፈት ነው ያሉት፡፡ በዚህ አጋጣሚ ሸይኽ ኢብኑ ዑሰይሚን ስለዚህ ቂሳ አንስተው እንዲህ ይላሉ፡- “በርካታ ሙፈሲሮች የሚጠቅሱትና ብዙ ደስኳሪዎች እንደሚያራግቡት ይቺ አንቀፅ በሠዕለባ ላይ ነው የወረደችው የሚለው፣ ደካማ ነው መሰረት የለውም፡፡ እንዳውም ተመላሽ ከየትኛውም ወንጀል ቢመለስ አላህ ተውበቱን እንደሚቀበለው ከሚታወቀው ግልፅ እምነታዊ መርህ ጋርም የሚፃረር ነው፡፡” (ኡሱሉትተፍሲር)

ሼር በማድረግ ከነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ክብር እንከላከል፡፡