«በቁርኣን ውስጥ አላህ ከፍጥረታቱ በላይ እንዳለ የሚያመለክቱ አንድ ሺህ ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ መረጃዎች አሉ!»
[ከአንጋፋዎቹ የሻፊዒያህ መዝሀብ ሊቃውንት የአንዱ ንግግር ነው። (“መጅሙዑ’ል-ፈታዋ” ጥራዝ 5 ገፅ 121 ይመልከቱ።)]
የዚህ ፅሑፍ አላማ የአላህን የበላይነት የሚያረጋግጡ መረጃዎችን መዘርዘር አይደለም።
ነገር ግን ይህንን እውነታ የማይቀበሉ ወገኖች የሚያነሱትን አንድ “ዝነኛ” ብዥታ ጠራርገው የሚያፀዱ ሸሪዓዊና አእምሯዊ ምላሾችን መጠቆም ነው። እንዲያውም የጥያቄያቸው ትክክለኛ ምላሽ የበላይነቱን የሚያፀና መሆኑን በስተመጨረሻ እናያለን!
በትዕግስት ያንብቡት!
#ጥያቄ፦
«“አላህ በዐርሹ ላይ ነው!” ካላችሁ ዐርሽን ከመፍጠሩ በፊት የት ነበር?!»
- በርግጥ አላህ ከዐርሽ በላይ የመሆኑን ብሩህ እውነታ በእንዲህ ያለ ጥያቄ መጋፈጥ እንደሚቻል የሚገምቱ ወገኖች ይህንን ጥያቄ የሚቀምሩት እንደሚከተለው ነው፦
«አላህ ዐርሽም ሆነ ሌላ ቦታ ሳይፈጠር የነበረ ጌታ ነው፤ እርሱ የማይቀያየር ጌታ በመሆኑ ዛሬም እንደያኔው ያለ ቦታ ነው ያለው!» ይላሉ።
[ይህ በተለያየ አገላለፅ የሚደጋግሙት ሀተታ “ዋነኛ መጋፈጫቸው” ነው፤ እንደ ምሳሌ፦ “አሽ-ሸርሑ’ል-ቀዊም” የተሰኘውን የዐብዱ’ላሂ አል-ሀረሪ መፅሐፍ ገፅ 212 (በአምስተኛው እትም መሰረት) መጥቀስ ይቻላል።]
#መልስ ፦
ይህን ድፍን ሙግት ከነመንደርደሪያው አንኮታኩተው የሚጥሉ ምላሾችን በሁለት መንገዶች ማቅረብ ይቻላል።
የመጀመሪያው መንገድ የጥያቄውን ስልት በጥቅሉ የተመለከቱ መሰረታዊ ምላሾችን ያካተተ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በሙግቱ አሰካክ ላይ የሚያነጣጥሩ ዝርዝር ምላሾችን ያቀፈ ነው።
#አንደኛው_መንገድ፦ ስልቱን የተመለከቱ አምስት ጥቅል ምላሾችን ይዟል፤ እነሆ!
(1-1) እውነታ በውዥንብር አይረታ!
የአላህ ከበላይ መሆን በሸሪዓዊና አእምሯዊ አስረጆች የተረጋገጠ ብቻ ሳይሆን ፈጣሪ በሰዎች ተፈጥሯዊ ዝንባሌ ውስጥ ያሰረፀው አማራጭ የለሽ እምነት በመሆኑ ምንም አይነት ጥያቄን የሚያስተናግድ አይደለም!
ልብ ይበሉ! በፅኑ መረጃዎች የፀደቀ እምነትን በማጠራጠሪያ መጠይቆች መጋፈጥ አይቻልም! ሙግት ደግሞ ማስረጃ አይሆንም! ማስረጃም በመላምት አይፈርስም! እውነታም በውዥንብር አይረታም።
› ይህ ሙግት አል-ኢማም አዝ-ዘሀቢይ እና ሌሎች በትክክለኛ ሰነድ የዘገቡትን አንድ ተያያዥ ክስተት ያስታውሰናል፦
قال أَبُو جَعْفَر بن أبي عَليّ الْحَافِظ: سَمِعت أَبَا الْمَعَالِي الْجُوَيْنِيّ وَقد سُئِلَ عَن قَوْله {الرَّحْمَن على الْعَرْش اسْتَوَى} فَقَالَ: كَانَ الله وَلَا عرش وَجعل يتخبط فِي الْكَلَام فَقلت قد علمنَا مَا أَشرت إِلَيْهِ فَهَل عنْدك للضرورات من حِيلَة فَقَالَ مَا تُرِيدُ بِهَذَا القَوْل وَمَا تَعْنِي بِهَذِهِ الْإِشَارَة فَقلت مَا قَالَ عَارِف قطّ يَا رباه إِلَّا قبل أَن يَتَحَرَّك لِسَانه قَامَ من بَاطِنه قصد لَا يلْتَفت يمنة وَلَا يسرة يقْصد الفوق فَهَل لهَذَا الْقَصْد الضَّرُورِيّ عنْدك من حِيلَة فنبئنا نتخلص من الفوق والتحت وبكيت وَبكى الْخلق فَضرب الْأُسْتَاذ بكمه على السرير وَصَاح ياللحيرة وخرق مَا كَانَ عَلَيْهِ وانخلع وَصَارَت قِيَامَة فِي الْمَسْجِد وَنزل وَلم يجبني إِلَّا يَا حَبِيبِي الْحيرَة الْحيرَة والدهشة الدهشة فَسمِعت بعد ذَلِك أَصْحَابه يَقُولُونَ سمعناه يَقُول حيرني الْهَمدَانِي
=› አል-ሓፊዝ አቡ ጀዕፈር ኢብኑ አቢ ዐሊይ አል-ሀመዛኒ (በ531 ዓመተ-ሂጅራ ያረፉ) እንዲህ ይላሉ፦ «አቡ’ል-መዓሊ አል-ጁወይኒ (478 ዓ.ሂ) “አር-ረሕማን ከዐርሹ በላይ ከፍ አለ” ስለሚለው የአላህ ንግግር ተጠይቆ “አላህ ዐርሽ ሳይኖር የነበረ ነው..” እያለ በንግግሩ ሲዘላብድ ሰማሁት! ከዚያም “ያመላከትከውን ነገር አውቀናል፤ ታዲያ ስለ “ዶሩሪያት” (እንድናረጋግጠው የግድ ስለሚለን ፅኑ እውነታ) መላ ቢጤ አለህን?” አልኩት። “በዚህ ንግግርህ ምን ፈልገህ ነው? በዚህ ጥቆማህስ ምን ወጥነህ ነው?” አለኝ። እኔም፦ “ማንኛውም አዋቂ ‘ጌታዬ ሆይ..!’ ካለ ገና ምላሱ ከመንቀሳቀሱ በፊት በውስጡ ፅኑ ስሜት ማደሩ አይቀሬ ነው፤ ወደ ቀኝ ወይም ወደ ግራ ሳይዞር እላይን ያስባል! ለዚህ ፅኑ እውነታ መላ አለህን? አሳውቀንና ከ‘ላይ’ እና ከ‘ታች’ እንገላገል!..” አልኩትና አለቀስኩ! ሁሉም አለቀሱ! መምህሩም (አል-ጁወይኒ) በእጅጌው አግዳሚ ቆጡን መታና “ወይ ግራ መጋባት!” ሲል ጮኸ! ልብሱንም ቀዶ ጣለ! በመስጂዱም ቂያማ ቆመ (ተረበሸ)! ከዚያም ወርዶ “ወዳጄ ሆይ! ኧረ ግራ መጋባት..! ኧረ መርበትበት..!” ከማለት ሌላ መልስ አልሰጠኝም። ከዚያም በኋላ ተማሪዎቹ “ ‘አል-ሀመዛኒ ግራ አጋባኝ!’ ብሎ ሲናገር ሰማነው!” ሲሉ ሰማኋቸው።»
[አዝ-ዘሀቢይ - “አል-ዑሉዉ ሊል-ዐሊይ-ዪ’ል-ገፍ-ፋር” ገፅ 259 ቁጥር 582 እንዲሁም “ሲየሩ አዕላሚ’ን-ኑበላእ” ጥራዝ 18 ገፅ 477፤ ኢብኑ ተይሚ-ያህ - “በያኑ ተልቢሲ’ል-ጀህሚይ-ያህ” ጥራዝ 1 ገፅ 51-52 ፤ አል-አልባኒ “በሑፋዞች ሰንሰለት የተያያዘ ትክክለኛ ሰነድ” እንደሆነ መስክረዋል። (“ሙኽተሰሩ’ል-ዑሉው” ገፅ 277 ይመልከቱ።)]
በጥቅሉ ስፍር ቁጥር በሌላቸው ማስረጃዎች የፀደቀውን የአላህ የበላይነት በመሰል ፀጉር ስንጠቃ መጋፋት ለአላህና ለመልዕክተኛው ንግግር ተገቢውን ቦታ ከመስጠት ጋር የሚጣረስ ነው!
---
(1-2) ልዩነቱ ብርቱ!
ሌሎች ሙስሊሞች የአላህን የበላይነት ሲያፀድቁ እጅግ ብዙ ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ ቁርኣናዊና ነብያዊ አስተምህሮቶችን እያጣቀሱ ነው! እነዚያ ሙግተኞች ግን “አላህ ቦታ ሳይፈጠር የነበረ ነው፤ ዛሬም ያለ ቦታ ነው ያለው..» የሚለውን የዘወትር መፈክር የሚያትቱት በየትኛውም የቁርኣን ወይም የሐዲሥ መረጃ ወይም የሰሓቦች ንግግር ላይ አግኝተውት አይደለም! ይህን ማወቅ ብቻ ሙግታቸው ውድቅ መሆኑን ያረጋግጣል።
በርግጥ ይህንን ሙግት እንዲጠግን የተቀጠፈ መሰረተ ቢስ “ዘገባ” አይጠፋም!
ለምሳሌ፦ ታዋቂው የሐዲሥ ጠቢብ አል-ሓፊዝ ኢብኑ ሐጀር (852 ዓ.ሂ) «አላህ - ከርሱ ውጭ ምንም ነገር ሳይኖር ነበረ..» የሚለውን አል-ቡኻሪይ ዘንድ በቁጥር 3191 ላይ የሚገኘውን ሐዲሥ ባብራሩበት አጋጣሚ እንዲህ ብለዋል፦
تَنْبِيهٌ: وَقَعَ فِي بَعْضِ الْكُتُبِ فِي هَذَا الْحَدِيثِ: كَانَ اللَّهُ وَلَا شَيْءَ مَعَهُ، وَهُوَ الْآنَ عَلَى مَا عَلَيْهِ كَانَ! وَهِيَ زِيَادَةٌ لَيْسَتْ فِي شَيْءٍ مِنْ كُتُبِ الْحَدِيثِ! نَبَّهَ عَلَى ذَلِكَ الْعَلَّامَةُ تَقِيُّ الدِّينِ بْنُ تَيْمِيَةَ، وَهُوَ مُسَلَّمٌ فِي قَوْلِهِ وَهُوَ الْآنَ إِلَى آخِرِهِ
=› «ማሳሰቢያ፦ በሆነ መፅሀፍ ውስጥ በዚህ ሐዲሥ ላይ “አላህ - ከርሱ ጋር ምንም ሳይኖር ነበረ፤ ‘እርሱ አሁንም ያኔ በነበረበት ላይ ነው!’ ” የሚል (ገለፃ) ሰፍሯል! ይህ በየትኛውም የሐዲሥ መፃህፍት ላይ የማይገኝ ጭማሪ ነው! ይህንን ታላቁ ዓሊም ተቂይ-ዩ’ድ-ዲን ኢብኑ ተይሚይ-ያህ አስገንዝቧል። ይህም “..እርሱ አሁንም ያኔ በነበረበት ላይ ነው!” የሚለውን አስመልክቶ እጅ የሚሰጥለት ነው..»
[ኢብኑ ሐጀር - “ፈትሑ’ል-ባሪ” ጥራዝ 6 ገፅ 289] [በተጨማሪም “መጅሙዑ’ል-ፈታዋ” ቅፅ 2 ገፅ 272 እንዲሁም “ከሽፉ’ል-ኸፋእ..” የተሰኘውን የአል-ዐጅሉኒ መፅሃፍ ቁጥር 2011 ይመልከቱ።]
በተመሳሳይ መልኩ ታላቁ ሰሓቢይ ዐሊይ ኢብኑ አቢ ጣሊብ ይህን መሰል ቃል እንደተናገሩ የሚወራ ቅጥፈት አለ፦
قد كان ولا مكان، وهو الآن على ما كان
ትርጉሙም፦ «በርግጥ ቦታ ሳይኖር ነበር፤ እርሱ አሁንም ያኔ በነበረበት ላይ ነው!»
ይህ ንግግር የአሽዐሪያህ አቀንቃኙ ዐብዱ’ል-ቃሂር አል-በጝዳዲይ [አል-ኸጢብ አል-በጝዳዲይ (463 ዓ.ሂ) አለመሆኑን እያስተዋሉልኝ!] «አል-ፈርቁ በይነ’ል-ፊረቅ» በተሰኘው መፅሀፍ ገፅ 321 ላይ ያለ ምንም የሰነድ ልጓም ያሰፈረው ልቅ ወሬ ነው! ዐሊይ የሞቱት በ40ኛው አመተ ሂጅራ ሲሆን ዐብዱ’ል-ቃሂር አል-በጝዳዲይ የሞተው ደግሞ በ429 ዓመተ ሂጅራ ነው። ስለዚህ በመካከላቸው ከሞላ ጎደል የአራት ክፍለ ዘመናት ክፍተት አለ፤ ወሬው ደግሞ ይህ ሰፊ የምእተ አመታት ርቀት የሚያያዝበት የዘገባ ሰንሰለት የለውም!
› ታላቁ የኢስላም ሊቅ ዐብዱ'ላህ ኢብኑ'ል-ሙባረክ (181 ዓ.ሂ) እንዲህ ይላሉ፦
«الْإِسْنَادُ مِنَ الدِّينِ، وَلَوْلَا الْإِسْنَادُ لَقَالَ مَنْ شَاءَ مَا شَاءَ»
=› «"ኢስናድ" (ሐዲሥ ወይም ሌላ ዘገባ ከአንድ ሰው ወደሌላ የሚተላለፍበት የቅብብሎሽ ሠንሠለት) የዲን አካል ነው፤ "ኢስናድ" ባይኖር ኖሮ ማለት የፈለገ ሁሉ ያሻውን ባለ ነበር!»
በተጨማሪም እንዲህ ብለዋል፦
بَيْنَنَا وَبَيْنَ الْقَوْمِ الْقَوَائِمُ - يَعْنِي: الْإِسْنَادَ-.
=› «በኛና በሌሎቹ መካከል (የሚዳኝ) "ኢስናድ" አለ!»
[ሁለቱም በሶሒሕ ሙስሊም መግቢያ ላይ (ጥራዝ 1 ገፅ 15) የሰፈሩ ትክክለኛ ዘገባዎች ናቸው!]
አዎን! የላይኛው ቅጥፈት እውነተኛ ምንጮች በተለያዩ የእምነት አጀንዳዎች ላይ ግልፅ ክህደትን በማራመድ እንዲሁም ውሸቶችን በማቀናበርና በመንዛት የሚታወቁት “ራፊዷዎች” ስለመሆናቸው አንዳንድ መፅሐፎቻቸው ይመሰክራሉ። [ለምሳሌ “አል-ካፊ” የተባለውን የኩለይኒ መፅሐፍ ቅፅ 1 ገፅ 90 ይመልከቱ።]
ትክክለኛ ሐዲሦችን “ኣሓድ” (በበርካታ መንገዶች ያልተዘገቡ) በመሆናቸው ብቻ በእምነት ርእሶች ላይ ከመቀበል እየታቀቡ በአንፃሩ ትክክለኛ ሊሆኑ ይቅርና ለደካማነት እንኳ ባልበቁ ውዳቂ አፈ ታሪኮች ላይ እምነታቸውን ይመሰርታሉ! አልፎም ሸሪዓዊ እውነታዎችን ይፃረራሉ! አላህ እውነታውን ይግለጥላቸው!
--
(1-3) ቢድዓ ነው!
በእምነት ጉዳይ ላይ ይህ አይነቱን ጥያቄ ማንሳት የተወገዘ ፈጠራ (ቢድዓህ) ነው! ምክንያቱም የህዝበ-ሙስሊሙ አርዓያ የሆኑት ቀደምት ትውልዶችና ታላላቅ መሪዎች ይህን መሰል ጥያቄ አንድም ቀን አንስተው አያውቁም!
ጥያቄውን ማንሳት ለእምነት የሚፈይድ ቢሆን እነርሱ በቀደሙን ነበር! ያኔ ያልነበረ የእምነት ድርሻ ስለማይተርፍልን በነርሱ ፋና ላይ ከመጓዝ ያለፈ አማራጭ የለንም።
› አል-ኢማም ማሊክ (179 ዓ.ሂ) እንዲህ ብለዋል፦
إياكم والبدع، قيل: يا أبا عبد الله وما البدع؟ قال: أهل البدع الذين يتكلمون في أسماء الله وصفاته وكلامه وعلمه وقدرته، لا يسكتون عما سكت عنه الصحابة والتابعون
=› «ቢድዓዎችን አደራችሁን! (ተጠንቀቁ!)» ሲሉ «የዐብዱ’ላህ አባት ሆይ! ቢድዐዎች ምንድናቸው?» ተብለው ተጠየቁ። እርሳቸውም፦
«የቢድዓህ ባለቤቶች! እነዚያ ስለ አላህ ስሞችና ባህሪያት፣ ስለ ንግግሩ፣ እውቀቱና ችሎታው የሚናገሩና ሰሓቦችና ታቢዒዮች በዝምታ ያለፉትን በዝምታ የማያልፉ!» ብለው መለሱ።
[አቡ ዑሥማን አስ-ሷቡኒ - “ዐቂደቱ’ስ-ሰለፍ ወአስሓቢ’ል-ሐዲሥ” ገፅ 244 ፣ አቡ ኢስማዒል አል-ሀረዊ “ዘም-ሙ’ል-ከላሚ ዋህሊሂ” ቅፅ 5 ገፅ 70 ቁጥር 858]
ስለሆነም ቀደምት አበው በአላህ ባሕሪያት ላይ የሚነሱ የ“እንዴት?” እና “ለምን?” ጥያቄዎችን ሁሉ ሲኮንኑ እንደነበሩ መዛግብት ይመሰክራሉ።
› አንድ ግለሰብ በአንድ አጋጣሚ ወደ አል-ኢማም ማሊክ (179 ዓ.ሂ) መጣና የሚከተለውን ቁርኣናዊ አንቀፅ አንብቦ አንድ ጥያቄ አቀረበላቸው፦
ٱلرَّحۡمَٰنُ عَلَى ٱلۡعَرۡشِ ٱسۡتَوَىٰ [طه: ٥]
= «አር-ረሕማን በዐርሹ ላይ ሆነ።» [ጧሃ 5]
“አላህ በዐርሹ ላይ የሆነው እንዴት ነው?” አላቸው!
ይህንን ሲሰሙ ፊታቸውን ደፉ፤ ላብም አጠመቃቸው፤ ከዚያም እንዲህ ብለው መለሱ፦
الاِسْتِوَاءُ غَيْرُ مَجْهُولٍ، وَالْكَيْفُ غَيْرُ مَعْقُولٍ، وَالْإِيمَانُ بِهِ وَاجِبٌ، وَالسُّؤَالُ عَنْهُ بِدْعَةٌ.
=› «የአላህ ከዐርሽ በላይ መሆን (“ኢስቲዋእ”) የማይታወቅ አይደለም (ግልፅ ነው)። ‘እንዴት?’ (የሚለው ጥያቄ መልስ) በአዕምሮ የሚደረስበት አይደለም፤ በዚህ (በተጠቀሰው ባህሪ) ማመንም ግዴታ ነው፤ ስለዚህ መጠየቅም ፈጠራ “ቢድዓ” ነው!» ከዚያም (ጠያቂውን)፦ «የቢድዓህ አራማጅ ትመስለኛለህ!» ካሉት በኋላ ከመስጂዱ እንዲወጣ ትዕዛዝ አስተላለፉ!
[አል-በይሀቂይ - “አል-አስማኡ ወስ-ሲፋት” ጥራዝ 2 ገፅ 150-151፣ እንዲሁም “አሊ’ዕቲቃድ” ገፅ 56፣ አድ-ዳሪሚይ - “አር-ረድ-ዱ ዐለ’ል-ጀህሚያህ” ገፅ 33፣ ኢብኑ ዐብዲ’ል-በር - “አት-ተምሂድ” ጥራዝ 7 ገፅ 151፣ አቡ ኑዐይም - “ሒልየቱ’ል-አውሊያእ” ቅፅ 6 ገፅ 325-326፣ አል-ላለካኢይ - “ሸርሑ ኡሱሊ’ዕቲቃዲ አህሊ’ስ-ሱን-ነቲ ወል-ጀማዐህ” ጥራዝ 2 ቅፅ 3 ገፅ 398 ቁጥር 664፣..በሌሎችም በርካታ መዛግብት ሰፍሯል። ይህ በበርካታ ሰነዶች የተረጋገጠ ዘገባ ሲሆን የተለያዩ ሊቃውንት ትክክለኛ ስለመሆኑ መስክረዋል፤ አንድም ታዋቂ ዓሊም በዚህ እውነታ ላይ የሚያጠራጥር ቃል አልተናገረም!]
በተመሳሳይ መልኩ የርሳቸው መምህር የነበሩት አል-ኢማም ረቢዓህ ኢብን አቢ ዐብዲ’ር-ረሕማን (136 ዓ.ሂ) ይህ ጥያቄ ሲቀርብላቸው እንዲህ ብለው ነበር፦
الاِسْتِوَاءُ غَيْرُ مَجْهُولٍ، وَالْكَيْفُ غَيْرُ مَعْقُولٍ، وَمِنَ اللهِ الرِّسَالَةُ، وَعَلَى الرَّسُولِ الْبَلَاغُ، وَعَلَيْنَا التَّسْلِيمُ
«የአላህ ከዐርሽ በላይ መሆን (“ኢስቲዋእ”) የማይታወቅ አይደለም (ግልጽ ነው)። ‘እንዴት?’ (የሚለው ጥያቄ መልስ) በአዕምሮ የሚደረስበት አይደለም፤ መልዕክቱ ከአላህ ዘንድ ነው፤ በመልዕክተኛው ላይ ያለው (ሀላፊነት) ማድረስ ነው፤ በእኛ ላይ ያለው (ግዴታ) መቀበል ነው።»
[አል-በይሀቂይ - “አል-አስማኡ ወስ-ሲፋት” ጥራዝ 2 ገፅ 151፣ አል-ላለካኢይ - “ሸርሑ ኡሱሊ’ዕቲቃዲ አህሊ’ስ-ሱን-ነቲ ወል-ጀማዐህ” ጥራዝ 2 ቅፅ 3 ገፅ 398፣ አል-ዒጅሊ - “ታሪኹ’ሥ-ሢቃት” ገፅ 158 ቁጥር 431፣ አዝ-ዘሀቢይ - “አል-ዑሉዉ ሊል-ዐሊይ-ዪ’ል-ገፍ-ፋር” ገፅ 129 ቁጥር 352]
ይህን ይበልጥ የሚያጎላው ደግሞ ተከታዩ ነጥብ ነው፦
---
(1-4) መለኮታዊ ርዕሶች በንፅፅራዊ አመክንዮ አይለኩም!
በእምነት ጉዳዮች ላይ ንፅፅራዊ አመክንዮ መጠቀም እንደማይፈቀድ ቀደምት የኢስላም ሊቃውንት ተስማምተዋል።
› ታላቁ የፊቅህ ምሁርና የአቡ ሐኒፋ ቅርብ ተማሪ አል-ኢማም አቡ ዩሱፍ (182 ዓ.ሂ) እንዲህ ብለዋል፦
وَلَيْسَ التَّوْحِيدُ بِالْقِيَاسِ لأَنَّ الْقِياسَ يَكُونُ فِي شَيْءٍ لَهُ شَبَهٌ وَمَثَلٌ، وَاللَّهُ لَا شبه لَهُ وَلا مثل
=› «ተውሒድ በንፅፅራዊ አመክንዮ አይሆንም፤ ምክንያቱም ንፅፅር ቢጤና አምሳያ ላለው ነገር ብቻ የሚሆን ነው። አላህ ደግሞ ቢጤም አምሳያም የለውም!»
[ኢብኑ መንዳህ - “አት-ተውሒድ” ጥራዝ 3፣ ገፅ 306፣ ቁጥር 890፤ አቡ’ል-ቃሲም አት-ተይሚይ - “አል-ሑጅ-ጃህ ፊ በያኒ’ል-መሓጅ-ጃህ” ጥራዝ 2 ገፅ 122]
› እንዲሁም አል-ኢማም አሕመድ (241 ዓ.ሂ) እንዲህ ብለዋል፦
وَلَيْسَ فِي السُّنَّةِ قِيَاسٌ, وَلَا تُضْرَبُ لَهَا الْأَمْثَالُ, وَلَا تُدْرَكُ بِالْعُقُولِ وَلَا الْأَهْوَاءِ, إِنَّمَا هِيَ الِاتِّبَاعُ وَتَرْكُ الْهَوَى
=› «ትክክለኛው ፈለግ ወስጥ ንፅፅራዊ ልኬት የለም፤ ምሳሌም አይበጅለትም! በአእምሮና በግላዊ ዝንባሌ የሚደረስበትም አይደለም! መከተልና ግላዊ ዝንባሌን መተው ብቻ ነው።»
[አል-ላለካኢይ - “ሸርሑ ኡሱሊ’ዕቲቃዲ አህሊ’ስ-ሱን-ናህ..” 1ኛው ጥራዝ፣ ቅፅ 1 ገፅ 156]
› እንዲሁም ታላቁ ሊቅ ኢብኑ ዐብዲ’ል-በር (463 ዓ.ሂ) እንዲህ ይላሉ፦
لَا خِلَافَ بَيْنَ فُقَهَاءِ الْأَمْصَارِ وَسَائِرِ أَهْلِ السُّنَّةِ، وَهُمْ أَهْلُ الْفِقْهِ وَالْحَدِيثِ فِي نَفْيِ الْقِيَاسِ فِي التَّوْحِيدِ
=› «በተውሒድ ጉዳይ ላይ ንፅፅራዊ ልኬት ውድቅ ስለመሆኑ የየከተሞች ሊቃውንት እንዲሁም የፊቅህና የሐዲሥ እውቀት ባለቤት የሆኑት ሌሎች አህሉ’ስ-ሱን-ናዎች መካከል ምንም ውዝግብ የለም!»
[ኢብኑ ዐብዲ’ል-በር - “ጃሚዑ በያኒ’ል-ዒልሚ ወፈድሊሂ” ጥራዝ 2 ገፅ 887]
በመሰል ርዕሰ-ጉዳዮች ላይ የሚነሱ ውዝግቦችን ሊቋጭ የሚችለው ብቸኛው ፍርድ ከበላይ የሚመጣ አምላካዊ ብይን ነው! ሁሉም በራሱ አእምሯዊ ሚዛን የሚዳኝ ከሆነ ግን የሰዎች አእምሮ እንደ መልካቸው ዥንጉርጉር ነውና ስምምነት ላይ አይደረስም!
ደግሞም ትክክለኛ አእምሯዊ አስረጆች የጌታን የበላይነት እንደሚያፀድቁ አለፍ ብለን በምሳሌ እናያለን።
---
(1-5) ያልተገለጠው እውነታ የተገለጠውን አይሽርም!
እኛ በቁርኣንና በሐዲሥ መረጃዎች የተረጋገጡ እውነታዎችን ያለ ምንም ቅሬታ እናፀድቃለን፤ በዝምታ የታለፉ ጉዳዮችን ደግሞ በዝምታ እናልፋለን! በእውቀት እንናገራለን፤ አሊያም ዝም! ይህ ነው የደጋጎቹ አበው መንገድ!
እናም አላህ ሰማያትንና ምድርን ፈጥሮ ሲያበቃ በዐርሹ ላይ ከፍ ማለቱን ነገረን እንጂ ዐርሹን ከመፈጠሩ በፊት የት እንደነበረ አላሳወቀንምና በመላ ምት አንዘላብድም!
› አል-ቡኻሪይ እና ሌሎች እንደሚያስተላልፉት ታላቁ ታቢዒይ ሱለይማን አት-ተይሚይ (በ143 ዓ.ሂ ያረፉ) እንዲህ ብለዋል፦
لَوْ سُئِلْتُ أَيْنَ اللَّهُ؟ لَقُلْتُ: فِي السَّمَاءِ، فَإِنْ قَالَ: فَأَيْنَ كَانَ عَرْشُهُ قَبْلَ السَّمَاءِ؟ لَقُلْتُ: عَلَى الْمَاءِ، فَإِنْ قَالَ: فَأَيْنَ كَانَ عَرْشُهُ قَبْلَ الْمَاءِ؟ لَقُلْتُ: لَا أَعْلَمُ! قَالَ أَبُو عَبْدِ اللَّهِ: وَذَلِكَ لِقَوْلِهِ تَعَالَى: {وَلَا يُحِيطُونَ بِشَيْءٍ مِنْ عِلْمِهِ إِلَّا بِمَا شَاءَ} يَعْنِي: إِلَّا بِمَا بَيَّنَ
=› «“አላህ የት ነው?” ተብዬ ብጠየቅ “በሰማይ!” እላለሁ፤
“ከሰማይ በፊት ዐርሹ የት ነበር?” ቢለኝ “በውሃ ላይ!” እላለሁ፤
“ከውሃ በፊት ዐርሹ የት ነበር?” ቢለኝ “አላውቅም!” እላለሁ።»
አቡ ዐብዲ’ላህ (አል-ቡኻሪይ - ከዘገባው ቀጥሎ) እንዲህ አሉ፦ «ይህም፦ {ከእውቀቱም እርሱ የሚሻውን እንጂ ምንም አያካልሉም (አል-በቀራህ 255)} በሚለው የአላህ ቃል (መሰረት) ነው፤ ማለትም፦ የገለፀውን እንጂ (አያውቁም)!»
[አል-ቡኻሪይ - “ኸልቁ አፍዓሊ’ል-ዒባድ” በተሰኘው መፅሐፋቸው 2ኛው ጥራዝ፣ ገፅ 38 ፣ ቁጥር 64፤ እንዲሁም አል-ላለካኢይ - “ሸርሑ ኡሱሊ’ዕቲቃዲ አህሊ’ስ-ሱን-ናህ..” 2ኛው ጥራዝ፣ ቅፅ 3 ፣ ቁጥር 671 ፤ ኢብኑ ቁዳማህ - “ኢሥባቱ ሲፈቲ’ል-ዑሉው” ገፅ 165 ቁጥር 75]
ስለዚህ ያላወቅነውን አለማወቃችን ያወቅነውን እንድናስተባብል ምክንያት ሊሆነን አይችልም! በድብቁ ምክንያትም ከግልፁ አንታወርም!
ያስተውሉ! ዐርሹ ከመፈጠሩ በፊት ስለነበረው ሁኔታ አለማወቃችን ከዚያ በኋላ ስላለው እውነታ በማስረጃዎች የፀደቀውን እምነት እንድናስተባብል አያደርገንም።
›አል-ኢማም ዐብዱል-ዐዚዝ ኢብኑ’ል-ማጀሹን (በ164 ዓ.ሂ ያረፉ) እንደሚከተለው ብለዋል፦
«..فأَمَّا الَّذِي جَحَدَ مَا وَصَفَ الرَّبُّ مِنْ نَفْسِهِ تَعَمُّقًا وَتَكَلُّفًا فقَدِ اسْتَهْوَتْهُ الشَّيَاطِينُ فِي الْأَرْضِ حَيْرَانَ، فَصَارَ يَسْتَدِلُّ بزَعَمِهِ عَلَى جَحْدِ مَا وَصَفَ الرَّبُّ وَسَمَّى مِنْ نَفْسِهِ بِأَنْ قَالَ: لَا بُدَّ إِنْ كَانَ لَهُ كَذَا مِنْ أَنْ يَكُونَ لَهُ كَذَا! فَعَمِيَ عَنِ الْبَيِّنِ بِالْخَفِيِّ، وجَحَدَ مَا سَمَّى الرَّبُّ مِنْ نَفْسِهِ، بصَمْتِ الرَّبُّ عَمَّا لَمْ يُسَمِّ مِنْهَا..»
=›«..ጌታ ከራሱ ባህሪያት የገለፀውን ጠልቆ በመፈላፈልና በመፍጨርጨር ያስተባበለውማ ግራ የተጋባ ሆኖ ሰይጣኖች (አታልለው) በምድር ላይ መንገድ አስተውታል፤ በመሆኑም “እንዲህ ያለ ነገር ያለው ከሆነማ የግድ እንዲህ ያለ ነገርም ይኖረዋል..!” በማለት ጌታ ከራሱ ባህሪያት የገለፀውንና የሰየመውን ለማስተባበል በርሱ ቤት መረጃ ማቅረብ ያዘ! በድብቁ የተነሳ ከግልፁ ታወረ! ጌታ ስለ ራሱ ሳያወሳ በዝምታ ባለፋቸው (ዝርዝሮች) ምክንያትም ስለ ራሱ (በግልፅ) ያወሳውን ካደ!»
[ኢብኑ በጥ-ጠህ - “አል-ኢባነህ” (ሶስተኛው ክፍል) ጥራዝ 3 ገፅ 64፣ አዝ-ዘሀቢይ “አል-ዑሉዉ ሊል-ዐሊይ-ዪ’ል-ገፍ-ፋር” ገፅ 142 ቁጥር 386]
- በርግጥ ለጥያቄው ቀጥተኛ መልስ ሊሆን የሚችል መልዕክትን ያዘለ አንድ የሐዲሥ ዘገባ አለ። እርሱም እንደሚከተለው ይነበባል፦
عن أَبِي رَزِينٍ، قَالَ: قُلْتُ: يَا رَسُولَ اللهِ، أَيْنَ كَانَ رَبُّنَا - عَزَّ وَجَلَّ - قَبْلَ أَنْ يَخْلُقَ خَلْقَهُ؟ قَالَ: "كَانَ فِي عَمَاءٍ؛ مَا تَحْتَهُ هَوَاءٌ، وَمَا فَوْقَهُ هَوَاءٌ، ثُمَّ خَلَقَ عَرْشَهُ عَلَى الْمَاءِ".
=› «አቡ ረዚን እንዲህ ይላሉ፦ “የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! ጌታችን ፍጥረታቱን ከመፍጠሩ በፊት የት ነበር?” አልኩኝ።
እርሳቸውም፦ “ ‘ዐማእ’ ውስጥ ነበር፤ ከላዩም ባዶ፣ ከስሩም ባዶ! ከዚያም ዐርሹን በውሃ ላይ ፈጠረ።” አሉ።» በአንደኛው የ“አል-በይሀቂይ” ዘገባ ላይ ደግሞ «ከዚያም በዐርሹ ላይ ሆነ!» የሚል ጭማሪ አለ።
[አሕመድ (ቁጥር 16188)፣ አት-ቲርሚዚይ (ቁጥር 3109)፣ ኢብኑ ማጀህ (ቁጥር 182)፣ አል-በይሀቂይ - “አል-አስማኡ ወስ-ሲፋት” ቁጥር 801 እና 864 እና ሌሎችም ዘግበውታል።]
“ዐማእ” ወይም “ዐማ” የሚለውን ቃል አንደኛው የሐዲሡ አስተላላፊ አል-ኢማም የዚድ ኢብኑ ሃሩን “ከርሱ ጋር ምንም ነገር የሌለበት” ሲሉ እንዳብራሩት አት-ቲርሚዚይ አያይዘው ጠቅሰዋል። ይህን ትርጓሜ የመረጡ እንዳሉ ሁሉ ከዚህ የተለየ ትርጉም የሰጡትም አሉ። [ለምሳሌ፦ “አል-አስማኡ ወስ-ሲፋት” ከቁጥር 864 ቀጥሎ፣ “አል-ተምሂድ” ጥራዝ 7 ገፅ 138፣ እንዲሁም “አን-ኒሃየቱ ፊ ገሪቢ’ል-ሐዲሥ” ጥራዝ 3 ገፅ 304 ይመልከቱ።]
- ሆኖም ይህ ዘገባ ጤናማ መሆኑ ያጠራጥራል፤ ምክንያቱም ሐዲሡን ከአቡ ረዚን (ለቂይጥ ኢብኑ ዓሚር) ያስተላለፈው የወንድማቸው ልጅ “ወኪዕ ኢብኑ ሑዱስ” (አንዳንዶች “ዑዱስ” ይሉታል) ሁኔታው ያልተጣራ “መጅሁል” እንደሆነ በርካታ የሐዲሥ ጠቢባን ፈርደዋልና። [ለምሳሌ፦ “ተህዚቡ’ት-ተህዚብ” የተሰኘውን የኢብኑ ሐጀር መፅሀፍ ጥራዝ 11 ገፅ 131 ይመልከቱ።]
ስለሆነም ምላሻችንን በመሰል አጠራጣሪ ወይም ደካማ ሰነድ ላይ አንመሰርትም። ይብላኝ ለነርሱ እንጂ!
*********
#ሁለተኛው_መንገድ (የሙግቱ አሰካክ ላይ ያነጣጠረ ዝርዝር ምላሽ)
«“አላህ በዐርሹ ላይ ነው!” ካላችሁ ዐርሽን ከመፍጠሩ በፊት የት ነበር?!» «ዐርሽም ሆነ ሌላ ቦታ ሳይፈጠር የነበረ ጌታ ነው፤ እርሱ የማይቀያየር በመሆኑ ዛሬም እንደያኔው ያለ ቦታ ነው ያለው!»
የሚለውን የሙግት አሰካክ በታትነን እንመርምረው፦
(2-1) በቅድሚያ «“አላህ በዐርሹ ላይ ነው!” ካላችሁ ዐርሽን ከመፍጠሩ በፊት የት ነበር?!» የሚለው ቃና ራሱ ስህተት ነው፤ ምክንያቱም “የት” የሚለው ጥያቄ መልስ የሚያገኘው ለገለፃ የሚያግዝ መነሻ (reference) ሲኖር ነው! ለዚህም ነው “አላህ የት ነው?” ሲባል፦ “ከዐርሹ በላይ፣ ከፍጥረተ-ዓለሙ ውጭ፤.. ወዘተ” የምንለው። በዚህ ገለፃ ላይ ዐርሽን ወይም አጠቃላይ ፍጥረተ አለሙን እንደ መነሻ በማጣቀስ የአላህ የበላይነትን አውስተናል። ሆኖም ዐርሽም ሆነ ሌላ ፍጡር ጭራሽ ባልነበረበት ሁኔታ አላህ የት እንደነበር በምን ቋንቋ መመለስ ይቻላል? ከምንስ በላይ ነበር ይባላል?
ልብ ይበሉ! የህልውናው የበላይነት (ዑሉው) ከማንነቱ የማይነጠል የዝንተ አለም መገለጫው ነው! ዐርሹን ከፈጠረ በኋላ በርሱ ላይ መሆኑ (ኢስቲዋእ) ደግሞ ይህንን የሚያጎላ አድራጎታዊ መገለጫ ነው።
- ደግሞም ከላይ እንደተብራራው የማናውቀው እውነታ የምናውቀውን አይሽርም!
---
(2-2) «አላህ ዐርሽም ሆነ ሌላ ቦታ ሳይፈጠር የነበረ ጌታ ነው!..» የሚለውን መነሻ ከመልዕክት አንፃር ስንፈትሸው ደግሞ፦
- ይህ በመሰረቱ የውዝግብ ርዕስ አይደለም፤ ሆኖም አላህ ከዐርሹ በላይ ከመሆኑ እውነታ ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚጋጭ ባለመሆኑ በዚህ ሂደት መጠቀሱ ምንም አይፈይድም!
ይህን ይበልጥ የሚያብራራው ደግሞ ቀጣዩ ነጥብ ነው፦
---
(2-3) «እርሱ የማይቀያየር ጌታ ስለሆነ..» የሚለውን ገለፃ በተመለከተ ደግሞ ጥቂት ነጥቦችን አብረን እንቃኝ፦
#ሀ- በቁርኣንና በሐዲሥ የተረጋገጡትን የጌታ ባህሪያት በሚያጠራጥር ወይም በሚያሳቅቅ ቃል መግለፅ እውነታውን አይቀይረውም፤ ልብ ይበሉ!
› አል-ኢማም አሕመድ (241 ዓ.ሂ) እንዲህ ብለው ነበር፦
..وَلَا نُزِيلُ عَنْهُ صِفَةً مِنْ صِفَاتِهِ لشَنَاعَةٍ شُنِّعَتْ..
=› «የሚፀየፍ ተፀይፎ ስላወገዘ (ብለን) ከባህሪያቱ አንዱንም አናስወግድም!»
[ኢብኑ በጥ-ጠህ - “አል-ኢባና” ጥራዝ 3 ገፅ 326፣ ኢብኑ ቁዳማህ - “ዘም-ሙ’ት-ተእዊል” ገፅ 22]
#ለ- “መቀየር” ፣ “መለወጥ” እና መሰል ቃላት በዚህ ሂደት የሚፈለግባቸው ፍልስፍናዊ ይዘታቸው እንጂ ቋንቋዊው መልዕክታቸው አለመሆኑን ማወቅ የግድ ይለናል። በዚህም መሰረት የላይኛው ሙግት ባለቤቶች የአላህን ከዐርሹ በላይ መሆን ብቻ ሳይሆን እርሱ በሚሻ ጊዜ የሚፈፅማቸውን አድራጎታዊ መገለጫዎች በሙሉ በ“መቀየር” እና በ“ክስተት” ስም ውድቅ ያደርጋሉ!
ለምሳሌ፦ በፈለገው ጊዜ መናገሩን “‘ክስተት’ ነው!” በማለት ያጣጥሉታል፤ በቁርኣኑ እንዳፀደቀው በእለተ-ቂያማህ ለፍርድ መምጣቱን “እንቅስቃሴ ነው..!” ሲሉ ያስተባብሉታል። ምክንያቱን ሲያብራሩ ደግሞ «መንቀሳቀስም ሆነ አለመንቀሳቀስ ሁለቱም ክስተት ናቸው! ክስተት ደግሞ መቀየር ነው! ፈጣሪ ደግሞ አይቀየርም!..» ይላሉ።
- በመሰረቱ እኛ በቁርኣንና በሐዲሥ የሌሉ አሻሚ ገለፃዎችን በአዎንታዊም ይሁን በአፍራሽ መልኩ አንጠቀምም! በቃ! በእምነታችን ላይ የቁርኣንና የሐዲሥ ገለፃን አንተላለፍም! እንደ “ክስተት” እና “መቀየር” ያሉ ቃላት እውነታን በሚጥስ መልኩ ለሚታለመው ውጤት እንዲውሉ የሚቆለመሙና ከቋንቋዊ ይዘታቸው የወጡ መልዕክቶች የሚታጨቁባቸው አሻሚ ገለፃዎች ናቸውና!
- በዚህ ላይ ደግሞ መናገርም ይሁን መንቀሳቀስና አለመንቀሳቀስ “መቀየር” መሆናቸው የነሱ ፍልስፍናዊ አጠራር እንጂ ሌሎች ባለ አእምሮዎች የሚስማሙበት እንዳልሆነ ግልፅ ነው!
- እንደሚታወቀው በየትኛውም ቋንቋ አንድ ነገር “ተቀየረ” የሚባለው ከቀድሞው ይዘቱ የተለየ አዲስ መገለጫ ሲኖረው ነው።
ለምሳሌ፦ አንድ ሰው በበሽታ ምክንያት ሲከሳ ወይም ሲጠቁር ፣ ወይም አርጅቶ ፀጉሩ ሲሸብት አሊያም በምቾት ሲወፍር ወይም ሲቀላ “ተቀየረ” ይባላል። ስነ ምግባሩ ሲሻሻል ወይም ሲበላሽም “ተቀየረ” ይባላል።
የአየሩ ሙቀት ከተለመደው በላይ ከፍ ወይም ዝቅ ሲል እንዲሁም ምግብ ሲሻግት ወይም ጠረኑ ሲለወጥ አሊያም የመጠጥ ቀለም ይዘቱን ሲለቅ እንደዚሁ “ተቀየረ” ይባላል። ወዘተ...
በአንፃሩ ደግሞ አንድ ሰው መናገር ሲጀምር ወይም ተናግሮ ዝም ሲል፣ ወይም ሲቆም አሊያም ሲቀመጥ፣ በጥቅሉ ሲንቀሳቀስና እስቅስቃሴውን ሲተው ከልማዱ እስካልወጣ ድረስ “ተቀየረ” አይባልም። በጥቅሉ አንድን ድርጊት ስለፈፀመ ብቻ ድርጊቱ እንደ “መቀየር” አይታሰብም፤ በዚህ ቃልም አይገለፅም!
[ለተጨማሪ ማብራሪያ “ደርኡ ተዓሩዲ’ል-ዐቅሊ ወን-ነቅል” ጥራዝ 4 ገፅ 72-75 እንዲሁም “መጅሙዑ’ል-ፈታዋ” ቅፅ 6 ገፅ 249-250 ይመልከቱ።]
በዚህ መሰረት “አላህ አይቀያየርም!” ሲባል የህልውናው የበላይነት መቼም የማይለወጥ፣ የባህሪያቱ ምጥቀት መቼም የማይከስም፣ ዘልአለማዊነቱ የማይቋረጥ፣ እንደፍጡራን የጉድለት ክስተቶችን የማያስተናግድ ፍፁም መሆኑን ለማሳየት ከሆነ ትክክለኛ መልዕክት ይሆናል።
እነዚያ ሙግተኞች ይህን የሚሉት ግን ይህን ጉልህ መልዕክት ወጥነው አይደለም! አዎን! “ፈጣሪ አይቀያየርም!” ሲሉ የሰማ የዋህ ለጌትነቱ ከማይገቡ ጉድለቶችና ጠንቆች እያላቁት ይመስለው ይሆናል! እውነታው ግን የ“መቀየር”ን የታወቀ መልዕክት በመቀየር አላህ ስለራሱ ያፀደቃቸውን እውነታዎች እየቀየሩ፣ አድራጊነቱንም እየገደቡ መሆናቸው ነው! አዎን! በአሻሚ ገለፃዎች ተከልለው በቁርኣን የተረጋገጡ መገለጫዎቹን ይንዳሉ!
ሙስሊሞች እንደ ንግግር፣ መፍጠር፣ ለፍርዱ መምጣት፣ ከዐርሹ ላይ መሆን ያሉ መሰል አድራጎታዊ የጌታ መገለጫዎችን እንደ መቀየር እንደማያስቡ ግልፅ ነው።
የፍጡር አድራጎት እንኳ መቀየር ካልሆነ የአላህ አድራጎት ሁኔታ ጭራሽ በአእምሮ የማይደረስበትና ከፍጡራን ሁኔታ እጅግ የተለየና የላቀ መሆኑ እየታወቀ እንዴት በ“መቀየር” ይገለፃል?!
እንደሚታወቀው ፍጥረታት ከመፈጠራቸው በፊትና ከተፈጠሩ በኋላ ያለው ልዩነት በቀጥታ የሚመለከተው ፈጣሪን ሳይሆን ፍጡራንን ራሳቸውን ነው! የፍጡራን ህልውና ካለመኖር ወደ መኖር በመሸጋገሩ የአዲስነት ክስተትን አስተናግዷል። አላህ ግን ሁሌም ፈጣሪ፣ ሁሌም የሻውን አድራጊ ከመሆን አልተወገደም! ያኔ ብቻውን የነበረ መሆኑ፣ አሁን ደግሞ ፍጡራን በመኖራቸው ከነርሱ በላይ መሆኑ የማንነት ለውጥ ነውን?
ከላይ እንዳየነው የህልውናው የበላይነት (ዑሉው) ከማንነቱ የማይነጠል የዝንተ አለም መገለጫው ነው! ዐርሹን ከፈጠረ በኋላ በርሱ ላይ መሆኑ (ኢስቲዋእ) ደግሞ ይህንን የሚያጎላ አድራጎታዊ መገለጫ እንጂ መቀየር አይደለም!
ስለሆነም የአላህ ከዐርሹ በላይ መሆን ከመቀየር ጋር በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሚዛመድበት መንገድ የለምና በባዶ ማስፈራሪያ ፅኑ መለኮታዊ እውነታን መፃረር አይቻልም!
ደግሞም፦
#ሐ- አላህ የሻውን ሁሉ ማድረጉ የምሉእነቱ መገለጫ እንጂ ጉድለት ሊሆን አይችልም! እንዲያውም አድራጊ የሆኑ ነገሮች አድራጊ ባልሆኑት ላይ መሰረታዊ ብልጫ እንዳላቸው የማንም አእምሮ አይክድም! ስለሆነም ይህንን ፅኑ እውነታ በአሻሚ ቃላት መናድ አይቻልም!
› ታዋቂው የኢስላም ሊቅ አል-ፉደይል ኢብኑ ዒያድ (187 ዓ.ሂ) እንዲህ ይላሉ፦
«إِذَا قَالَ لَكَ جَهْمِيٌّ: أَنَا أَكْفُرُ بِرَبٍّ يَزُولُ عَنْ مَكَانِهِ، فَقُلْ: أَنَا أُؤْمِنُ بِرَبٍّ يَفْعَلُ مَا يَشَاءُ»
«አንድ ጀህሚይ “እኔ ከቦታው በሚወገድ ጌታ እክዳለሁ!” ካለህ “እኔ ደግሞ የሻውን በሚሰራ ጌታ አምናለሁ!” በል!»
[አል-ቡኻሪይ - “ኸልቁ አፍዓሊ’ል-ዒባድ” ጥራዝ 2 ገፅ 36 ቁጥር 61፣ ኢብኑ በጥ-ጠህ - “አል-ኢባናህ” (ሶስተኛው ክፍል) ጥራዝ 3 ገፅ 204፣ አል-ላለካኢይ - “ሸርሑ ኡሱሊ’ዕቲቃዲ አህሊ’ስ-ሱን-ናህ” ጥራዝ 2 ቅፅ 3 ገፅ 452]
እንዲሁም አል-ኢማም ኢስሓቅ ኢብኑ ራሀወይህ (238 ዓ.ሂ) እና አል-ኢማም የሕያ ኢብኑ መዒን (233 ዓ.ሂ) ተመሳሳይ ንግግር አስፍረዋል።
[ኢብኑ በጥ-ጠህ - “አል-ኢባናህ” (ሶስተኛው ክፍል) ጥራዝ 3 ገፅ 206፣ አል-ላለካኢይ - “ሸርሑ ኡሱሊ’ዕቲቃዲ አህሊ’ስ-ሱን-ናህ” ጥራዝ 2 ቅፅ 3 ገፅ 453፣ አል-በይሀቂይ - “አል-አስማኡ ወ’ስ-ሲፋት” ጥራዝ 2 ገፅ 375-376፣ አዝ-ዘሀቢይ - “ሲየሩ አዕላሚ’ን-ኑበላእ” ጥራዝ 11 ገፅ 376]
ስለዚህ በመሰል ስልቶች ቁርኣናዊ እውነታን መጋፋት መረጃዎችን ከማጣመም በቀር የሚፈይደው ትርፍ የለም!
---
(2-4) «..አላህ አሁንም ያለ ቦታ ነው!» የሚለው ገለፃ ደግሞ በሚከተሉት ነጥቦች ይብራራል፦
“ቦታ” የሚለው ቃል ሁለት አይነት ግንዛቤን ሊያስጨብጥ የሚችል በመሆኑ የተፈለገበትን መልዕክት ሳናጣራ በደፈናው ማፅደቅ ወይም ማፋረስ ተገቢ አይሆንም። ስለዚህም፦
1- “ቦታ” በፍጥረታት ክልል የተገደበ ግኝ ስፍራ ከታሰበበት በርግጥ አላህ ከፍጥረተ አለሙ ውጭ ነውና በእንዲህ ያለ “ቦታ” አይደለም!
ዐርሽ የፍጥረት ክልል ማብቂያ የመጨረሻው ጣሪያ ነውና! አላህ ከዐርሹ በላይ መሆኑን መናገር ደግሞ ይህንን አያስገነዝብም! በተለያዩ ቁርኣናዊና ነብያዊ ማስረጃዎች ላይ “በሰማይ” መሆኑ መነገሩ ደግሞ ስርወቃሉ በዐረብኛ ቋንቋ ጥቅል ከፍታን የሚጠቁም በመሆኑ እንጂ አላህ እንደ መላእክት በሰማያት ውስጥ የተገደበ እንደሆነ የሚያስብ አንድም ሙስሊም የለም!
2- ከቦታዎች ወሰን ውጭና ከፍጥረታት ክልል በላይ ያለው በአንፃራዊ ይዘቱ እንደ “ቦታ” ከታሰበ ደግሞ ቃሉን ፈርተን ብቻ ስፍር ቁጥር በሌላቸው መረጃዎች የተረጋገጠውን የበላይነቱን አናስተባብልም።
በየትኛውም የአላህ፣ የመልዕክተኛውና የቀደምት ምርጥ ትውልዶች ንግግር ላይ ጭራሽ ባልተወሳው “አላሁ መውጁዱን ቢላ መካን!” (አላህ ያለ ቦታ ያለ ነው!) በሚለው የኑፋቄ መፈክር ተሸብረን እንዲህ ቁልጭ ያለ ሸሪዓዊና አእምሯዊ እውነታን አንጋፋም!
- እንዲያውም ስለ አላህ ከሁሉም ፍጡር ይበልጥ አዋቂ የሆኑት መልዕክተኛ የባሪያዪቱን አማኝነት ለማረጋገጥ “አላህ የት ነው?” ማለታቸው ይህን እውነታ አጉልቶ ያሳያል! [ሰሒሑ ሙስሊም ቁጥር (537) ይመልከቱ!]
በዚሁ አጋጣሚ “አላህ ያለ ቦታ ነው!” የሚለው መፈክር ከሙዕተዚላዎች የተወረሰ መሆኑን ለማረጋገጥ ከፈለጉ “መቃላቱ’ል-ኢስላሚይ-ዪን” የተሰኘውን የአቡ’ል-ሐሰን አል-አሽዐሪይ መፅሐፍ ጥራዝ 1 ገፅ 286 ይመልከቱ!
- «አላህ በሁለተኛው መልእክት ላይ በተብራራው "ቦታ" ላይም አይደለም!» ካሉ ደግሞ ህልውናውን እያፋረሱ ነው!
የሚከተለው ነጥብ ይህን ይበልጥ ያጎላል፦
--
(2-5) ህልውና ወይስ ህሊናዊ?!
ልብ ይበሉ! የጥያቄው ውጤት የሚያመራው የፈጣሪን የበላይነት ወደ ማረጋገጥ እንጂ ወደ ማስተባበል ሊሆን አይችልም!
› ለዚህም አል-ኢማም አሕመድ (241 ዓ.ሂ) በፅሁፋቸው ያሰፈሩትን የሚከተለውን አእምሯዊ እውነታ እናስተውል፦
قال الإمام أحمد ابن حنبل: وإذا أردت أن تعلم أن الجهميّ كاذبٌ على الله حين زعم أن الله في كل مكان، ولا يكون في مكان دون مكان، فقل له: أليس الله كان ولا شيء؟ فسيقول: نعم. فقل له: حين خلَقَ الشيءَ خلقَه في نفسه أو خارجًا من نفسه؟ فإنه يصير إلى ثلاثة أقاويل، لابد له من واحد منها:
إن زعم أن الله خَلَق الخلْق في نفسه فقد كفر، حين زعم أنه خلق الجن والشياطين وإبليس في نفسه.
إن قال: خلقهم خارجًا من نفسه ثم دخل فيهم، كان هذا كفرًا أيضًا حين زعم أنه دخل في كل مكان وحشٍ قذِر رديء.
وإن قال: خلقهم خارجًا عن نفسه، ثم لم يدخل فيهم، رجع عن قوله كلِّه أجمع، وهو قول أهل السنة.
=› «ጀህሚዩ አላህ በሁሉ ቦታ እንዳለና በአንድ ቦታ ሳይኖር በሌላ እንደማይሆን ሲሞግት በአላህ ላይ እየዋሸ መሆኑን ለማወቅ “አላህ ምንም ነገር ሳይኖር የነበረ አይደለምን?” በለው! እርሱም “ነበረ!” ይላል። “ነገሮችን በፈጠረ ጊዜ በራሱ ውስጥ ፈጠራቸው ወይስ ከራሱ ውጭ?” በለው። ያኔ ወደ ሶስት መልሶች ያመራል፤ ከነርሱ አንዱን ከመምረጥ ውጭ አማራጭ የለውም፦
1- አላህ ፍጡራንን በራሱ ውስጥ እንደፈጠራቸው ከሞገተ በርግጥ ይከፍራል፤ አጋንንትን፣ ሰይጣናትንና ኢብሊስን በውስጡ እንደፈጠረ ሞግቷልና!
2- “ከራሱ ውጭ ፈጥሯቸው ከዚያም በውስጣቸው ገብቷል!” ካለም ክህደት ነው፤ በአፀያፊ፣ በቆሻሻና በተልካሻ ቦታ ሁሉ እንደገባ ሞግቷልና!
3- “ከራሱ ውጭ ፈጥሯቸው ሲያበቃ በውስጣቸው አልገባም!” ካለ ደግሞ ከመጀመሪያው ንግግሩ መሉ በሙሉ ተመልሷል! ይኸኛውም የአህሉ’ስ-ሱና አቋም ነው!»
[አሕመድ ኢብኑ ሐንበል - “አር-ረድ-ዱ ዐለ’ዝ-ዘናዲቀቲ ወ’ል-ጀህሚይ-ያህ” ገፅ 300-301]
ልብ ይበሉ! “አላህ አሁን ያለው ያኔ እንደነበረው ነው!” በሚለው ብንስማማ በላይኛው የኢማሙ ማብራሪያ መሰረት ከፍጥረተ አለሙ የቦታ ገደብ ውጭ መሆኑን አረጋገጥን ማለት ነው፤ አላህ ፍጡራኑን ያስገኘው ከራሱ ውጭ እንደሆነ ግልፅ ነውና! ከውጭ ከሆነ ደግሞ ከበላያቸው እንጂ ከበታች አይሆንም! እነዚያ ሙግተኞች ግን ከፍጥረተ አለሙ ውጭ መሆኑን ራሱ አይቀበሉም! የኢማሙ ጥያቄ እጅግ ቀላል ስሌት ሆኖ ሳለ የዘንድሮ ጀህሚያዎች የመረጡት የሽሽት መልስ ግን እንደ ሚስጥረ ስላሴ የተቋጠረ ነው! «በፍጥረተ አለሙ ውስጥ አይደለም፤ ከዚያ ውጭም አይደለም! ከላይም አይደለም፤ ከታችም አይደለም!..» ይሉናል።
- ለመሆኑ የአላህ ህልውና ህሊናዊ ብቻ ነው ወይስ እውን?
የቀድሞው የአሽዐሪይ-ያህ መንገድ እውነተኛ ጠንሳሽ የሆነው ኢብኑ ኩል-ላብ (243 ዓ.ሂ) እንኳ ያኔ እንዲህ ብሎ ነበር፦
وأَخْرَجُ من النظر والخبر قولُ من قال: لا هو في العالم ولا خارجٌ منه! فنفاه نفيًا مستويًا؛ لأنه لو قيل له: صفه بالعدم، ما قدر أن يقولَ فيه أكثرَ منه
«ከአእምሯዊ ምልከታም ከነጋሪት ማስረጃዎችም (ቁርኣንና ሐዲሥ) ይበልጥ ያፈነገጠው ደግሞ “በፍጥረተ-ዓለሙ ውስጥም አይደለም፤ ውጭም አይደለም!” በማለት (ሁለቱንም) እኩል የሚያፈርሰው ተናጋሪ ንግግር ነው! ምክንያቱም “(አላህን) ጭራሽ የማይገኝ በሆነ ኢምንትነት መገለጫ ግለፀው!” ቢባል ከዚህ የበለጠ ንግግር ሊናገር አይችልምና!»
[“በያኑ ተልቢሲ’ል-ጀህሚይ-ያህ” ጥራዝ 1ገፅ 44፣ “ደርኡ ተዓሩዲ’ል-ዐቅሊ ወን-ነቅል” ጥራዝ 6/119) (-ከኢብኑ ፉረክ እንዳተላለፉት)]
- አዎን! ይህ አፍራሽ ሀተታ «አላህ የለም!» ከሚለው መልዕክት የሚለይበትን ይዘት የሚያብራሩበት አንደበት የላቸውም! እንዲሁ ብቻ «አላሁ መውጁዱን ቢላ ከይፍ!» ማለትም፦ «አላህ ያለ ሁኔታ የሚገኝ ነው!» ወደሚል መፈክር ይጣደፋሉ! ያ የማይፈታ ትንግርታቸው የሚያሳድረውን አሉታዊ እንድምታ ለማለዘብ የመረጡት መሸሻ ይህ ነው። ይህን ንግግር አስመልክቶ ሶስት ነጥቦችን ለማንሳት እወዳለሁ፦
#አንደኛ፦ ማንኛውም ነገር የራሱ የሆነ ሁኔታ ሳይኖረው ገሀዳዊ ግኝት ሊኖረው አይችልም፤ ሊታሰብ ይችል ይሆናል፤ እውን ግን አይሆንም!
ለዚህም ነው ከጥንት ጀምሮ የኢስላም ሊቃውንት ስለ አላህና መገለጫዎቹ ሁኔታ “እንዴት” (ከይፍ) እያሉ መጠየቅን ያወገዙት ስለ ጉዳዩ ስላልተነገረንና አእምሯችንም ስለማይደርስበት እንጂ “አላህ ያለ ሁኔታ ያለ ነው!” በሚል መነሻ አይደለም!
› ለምሳሌ አል-ኢማም ዐብዱ’ል-ዐዚዝ አል-ማጀሹን (164 ዓ.ሂ) የአላህን ባህሪያት ስለሚያስተባብሉት ጀህሚያዎች በሰጡት ምላሽ ላይ የተናገሩትን እንደምሳሌ እንይ፦
وَإِنَّمَا يُقَالُ: كَيْفَ كَانَ؟، لِمَنْ لَمْ يَكُنْ مَرَّةً ثُمَّ كَانَ، فَأَمَّا الَّذِي لَا يَحُولُ، وَلَا يَزُولُ، وَلَمْ يَزَلْ، وَلَيْسَ لَهُ مِثْلٌ، فَإِنَّهُ لَا يَعْلَمُ كَيْفَ هُوَ إِلَّا هُوَ
=› « “እንዴት ሆነ?” የሚባለው እኮ አንድ ጊዜ ያልነበረ ሆኖ ከዚያ ስለሆነ ነገር ነው! ጭራሽ የማይለወጠው፣ የማይወገደው፣ ሁሌም የነበረውና አምሳያ የሌለው ግን እርሱ እንዴት እንዳለ ከርሱ በቀር የሚያውቅ የለም!»
[ኢብኑ በጥ-ጠህ - “አል-ኢባነህ” (ሶስተኛው ክፍል) ጥራዝ 3 ገፅ 64፣ አዝ-ዘሀቢይ “አል-ዑሉዉ ሊል-ዐሊይ-ዪ’ል-ገፍ-ፋር” ገፅ 141 ቁጥር 386]
- “አላህ ሁኔታ የለውም” ሳይሆን “እንዴት እንዳለ ከርሱ በቀር የሚያውቅ የለም!” ማለታቸው ይሰመርበት።
#ሁለተኛ፦ በቁርኣንና በሐዲሥ የተረጋገጡ የጌታ ባህሪያትን በጥቅሉ ማፅደቅ ሁኔታቸውን ከመግለፅ አይመደብም፤ ያ ሌላ ይሄ ሌላ! ያስተውሉ! ስለባህሪያቱ ዝርዝር ይዘትና ሁኔታ መናገርን ያወገዙት የአበው ሊቃውንት ራሳቸው እነዚያን ባህሪያት ያፀድቁ እንደነበር፤ ብሎም የማያፀድቁትን ሁሉ አጥብቀው ይኮንኑ እንደነበር የጥንቶቹ መዛግብት በሙሉ ይመሰክራሉ!
#ሶስተኛ፦ አል-ኢማም ኢብኑ ዐብዲ’ል-በር (463 ዓ.ሂ) ለመሰል ውዥንብር መልስ ሲሰጡ እንዲህ ይላሉ፦
فإِنْ قَالَ: إِنَّهُ لَا يَكُونُ مُسْتَوِيًا عَلَى مَكَانٍ إِلَّا مَقْرُونًا بِالتَّكْيِيفِ، قِيلَ: قَدْ يَكُونُ الِاسْتِوَاءُ وَاجِبًا وَالتَّكْيِيفُ مُرْتَفِعٌ، وَلَيْسَ رَفْعُ التَّكْيِيفِ يُوجِبُ رَفْعَ الِاسْتِوَاءِ، وَلَوْ لَزِمَ هَذَا لَزِمَ التَّكْيِيفُ فِي الْأَزَلِ؛ لِأَنَّهُ لَا يَكُونُ كَائِنٌ فِي لَا مَكَانٍ إِلَّا مَقْرُونًا بِالتَّكْيِيفِ، وَقَدْ عَقلْنَا وَأَدْرَكْنَا بِحَوَاسِّنَا أَنَّ لَنَا أَرْوَاحًا فِي أَبْدَانِنَا وَلَا نَعْلَمُ كَيْفِيَّةَ ذَلِكَ، وَلَيْسَ جَهْلُنَا بِكَيْفِيَّةِ الْأَرْوَاحِ يُوجِبُ أَنْ لَيْسَ لَنَا أَرْوَاحٌ! وَكَذَلِكَ لَيْسَ جَهْلُنَا بِكَيْفِيَّة "عَلَى عَرْشِهِ" يُوجِبُ أَنَّهُ لَيْسَ عَلَى عَرْشِهِ
=› «“(አላህ) ሁኔታው አብሮ ሳይገለፅ በ‘ቦታ’ ላይ መሆን አይችልም!” ካለ እንዲህ ይባላል፦
“ስለሁኔታው ጭራሽ የማይወሳ ሆኖ እያለ ‘ኢስቲዋእ’ (በዐርሹ ላይ መሆኑ) የፀና ይሆናል! ስለሁኔታው አለመወሳቱ የ‘ኢስቲዋእ’ መሻርን አያስከትልም! ይህ የግድ ቢሆን ኖሮ ዝንተ አለሙን (ፍጡራን ገና ሳይኖሩ በፊት) ስለ ነበረበት ሁኔታ ማውሳትን ያስከትል ነበር! ምክንያቱም ማንኛውም ነገር ሁኔታ ሳይኖረው ያለ ቦታም ሊኖር አይችልምና! መቼም በሰውነታችን ሩሕ (ነፍስ) እንዳለን ተገንዝበናል፤ በህዋሳችንም ደርሰንበታል! ስለ ሁኔታዋ ግን አናውቅም! ስለ ሩሓችን ሁኔታ አለማወቃችን ግን ሩሕ እንደሌለን አያመለክትም! ልክ እንዲሁ (አላህ) በዐርሹ ላይ የሆነበትን ሁኔታ አለማወቃችን በዐርሹ ላይ አለመሆኑን አያመለክትም!”»
[ኢብኑ ዐብዲ’ል-በር - “አት-ተምሂድ” ጥራዝ 7 ገፅ 137]
===
በመጨረሻም ከላይኛው ጥያቄ ጋር ተያይዞ የሚነሳ አንድ የተለመደ መፈክር አለ፦ «አላህ ዐርሽ ወይም ሌላ ቦታ አያስፈልገውም!»
ይህን አስመልክቶ ሁለት መልሶችን ብቻ እንጥቀስ፦
#1ኛ፦ አላህ ከዐርሹ በላይ የሆነው ቦታ ስለሚያስፈልገው እንደሆነ የሞገተ አንድም ሙስሊም ሳይኖር ይህንን ክርክር ማንሳት ከንቱ ነው፤ ከርዕሱ የወጣም ዛዛታ ነው!
አላህ ከማንኛውም ፍጡር ምንም አይነት እርዳታ የማይፈልግ ተብቃቂ ጌታ ነው! ዐርሽን፣ ሰማያትንና ምድርን እንዲሁም መላ ፍጡራንን በወሰን-የለሽ ችሎታው የሚቆጣጠረውና የሚያስተናብረው ማን ሆነና?! ያለ እርሱ እርዳታ የትኛውም ፍጡር ሊኖርም ሆነ ሊቆም መች ይችልና?! ሃያሉ አምላካችን ልቅናና ጥራት የተገባው ነው!
إِنَّ ٱللَّهَ يُمۡسِكُ ٱلسَّمَٰوَٰتِ وَٱلۡأَرۡضَ أَن تَزُولَاۚ وَلَئِن زَالَتَآ إِنۡ أَمۡسَكَهُمَا مِنۡ أَحَدٖ مِّنۢ بَعۡدِهِۦٓۚ إِنَّهُۥ كَانَ حَلِيمًا غَفُورٗا
= «አላህ ሰማያትንና ምድርን እንዳይወገዱ ይይዛቸዋል፤ ቢወገዱ ከርሱ ሌላ አንድም የሚይዛቸው የለም! እነሆ እርሱ ሁሌም ታጋሽ መሀሪ ነውና።» [ፋጢር 41]
ግን ይህ የሚያሳየው ጀህሚያዎችና ተከታዮቻቸው በቁርኣንና በሱን-ናህ የተረጋገጡትን የጌታ ባህሪያት መልዕክት እንዲቆለምሙ ያደረጋቸው ቀድሞውኑ የመረጃዎቹን መልዕክት የተረዱት የፍጡራን ባህሪያትን በሚረዱበት ይዘት መሆኑን ነው!
ለምሳሌ፦ አላህ በዐርሹ ላይ መሆኑን የሚያረጋግጡ ማስረጃዎችን ሲሰሙ የሚገነዘቡት መልዕክት አንድ ፍጡር በሌላ ነገር ላይ መሆኑን በሚገነዘቡበት ይዘት ስለሆነ “አላህ ከዐርሽ በላይ ከሆነ ለርሱ ዐርሽ ያስፈልገዋል ማለት ነው! ዐርሽ ይሸከመዋል ማለት ነው! ..ወዘተ” በሚል ፈሊጥ የበላይነት መገለጫውን ወደማፋረስ አቀኑ! አዎን! እነርሱ ናቸው አመሳሳዮቹ! ቀድሞውኑ ይህን የፍጡር መገለጫ ከማስረጃዎቹ የሚረዳው ህሊናው በማመሳሰል አባዜ የተበከለ ብቻ ነውና!
ይህንና ሌሎች ትክክለኛ መገለጫዎቹን ያለ ምንም አጉል ፈሊጥ ለጌታ ማንነት በሚገባው መልኩ የሚያፀድቁት ሌሎች ሙስሊሞች ግን አላህ ከእንደዚህ አይነት ጉድለት የጠራ መሆኑን አስቀድመው ስለሚያምኑ መረጃዎቹን ማጣመም አላስፈለጋቸውም!
#2ኛ- አላህ በጥበቡ የሚፈፅማቸውን አድራጎቶች በእንዲህ ያለ ሰንካላ መነሻ መጋፈጥ አያስኬድም!
አላህ ማንኛውንም ነገር በአንድ ቃል በቅፅበት ማከናወን የሚችል ሃያል ጌታ ከመሆኑ ጋር በጥበቡ ሰማያትንና ምድርን በስድስት ቀናት ፈጥሯል። ታዲያ እርሱ ምንም የሚሳነው ባለመሆኑ ብቻ የስድስት ቀናቱን እውነታ እናስተባብላለን?!
እንዲሁም አላህ የማንም እገዛ ሳያስፈልገው ሁሉን ማከናወን የሚችል ከመሆኑ ጋር የተለያዩ የፍጥረተ አለም ክንውኖችን በርሱ ፈቃድ የሚያስተናብሩ መላእክትን ፈጥሯል። ታዲያ እርሱ እገዛ የሚያስፈልገው ባለመሆኑ የመላኢካን ህልውና እንክዳለን?!
ለእንዲህ አይነት ጥያቄ በር ከተከፈተ በአንፃሩ ደግሞ ማብቂያ የሌላቸው ምሳሌዎችም ይዥጎደጎዳሉ!
====
ያሳለፍናቸውን ነጥቦች በአጭሩ እንከልሳቸው፦
*ጥቅል ምላሾቹ አምስት ሲሆኑ እነርሱም እንደሚከተለው ይቀርባሉ፦
1- የአላህ ከበላይነት በፅኑ ማስረጃዎች የተረጋገጠ በመሆኑ ጥያቄን አያስተናግድም!
2- በአንፃሩ ደግሞ ይህ ሙግት በየትኛውም መረጃ ላይ አይገኝም!
3- መሰል ጥያቄዎችን ማንሳት የተወገዘ ፈጠራ ነው!
4- ተውሒድ በንፅፅራዊ አመክንዮ አይለካም!
5- ያላወቅነው እውነታ ያወቅነውን አይሽርም!
*ዝርዝር ምላሾቹ ደግሞ ባጭሩ የሚከተሉት ነበሩ፦
1- «ቅድሚያ የት ነበር?!» የሚለው ቃና ራሱ ስህተት ነው! ምንም ባልነበረበት ከምን በላይ ነበር ይባላል?!
2- «ዐርሽም ሆነ ሌላ ቦታ ሳይፈጠር የነበረ ጌታ ነው!..» የሚለው ደግሞ ከዐርሹ በላይ ከመሆኑ ጋር በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ አይጋጭም!
3- «..የማይቀያየር ጌታ ስለሆነ..» የሚለው ደግሞ የማሸማቀቂያ ስልት እንደሆነና ከዐርሹ በላይ መሆኑ በየትኛውም ቋንቋ "መቀየር" ተብሎ እንደማይጠራ፣ ያንንም የሚያስገነዝብ እንዳልሆነ ተብራርቷል።
4- «አሁንም እንደያኔው ያለ ቦታ ነው..» የሚለው አሻሚ ቃል ደግሞ "ቦታ" የፍጡራን ክልል ውስጥ ያለ ግኝ ስፍራ ከታሰበበት ያስማማናል፤ ከቦታዎች ክልል ውጭ ያለው በአንፃራዊ ገለፃ "ቦታ" ከተሰኘ ደግሞ ቃሉን ፈርተን የበላይነቱን አናስተባብልም!
5- የአላህ ህልውና እውን መሆኑን ካመኑ ፍጡራኑን ያስገኘው ከራሱ ውጭ ነውና ሁሌም ከበላያቸው እንጂ ከበታች እንደማይሆን ሊያረጋግጡ የግድ ይላል!
*በመጨረሻም "አላህ ቦታ አያስፈልገውም!" የሚለው ነጥብ ውዝግብ የሌለበት መሆኑንና በዐርሹ ላይ መሆኑ መገለፁም ይህንን ጉድለት የሚያስገነዝብ እንዳልሆነ በምሳሌዎች ቃኝተናል!
ለጊዜው ጨርሻለሁ!
Ilyas Ahmed