Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ከቀብር ጋር ተያያዥነት ያላቸው ክልክል ተግባሮች

✔ ከቀብር ጋር ተያያዥነት ያላቸው ክልክል ተግባሮች
የእስልምና የመጀመሪያዎቹ ዘመናት ላይ ቀብርን መጐብኘት ተከልከሎ ነበር፡፡ ምክንያቱም ከድንቁርና ህይወት በመላቀቅ እንግዳ ስለነበሩና የተውሂድን ወሰን ለመጠበቅ ሲባል ነበር:: ሰዎች እምነታቸውን ሲያሳምሩ ከፍተኛ ስፍራ ሲሰጡት፣ ማስረጃዎቹ ግልፅ ሆነው ልቦች ውስጥ ሲሰርፅና የሽርክ ውዥንብሮች ሲጋለፁ ቀብርን መጐብኘት ዓላማው ተገድቦ ተፈቀደ፡፡
ቡረይዳ ኢብን ሁሰይብ እንዳስተላለፉት የአላህ መልዕክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል
‹‹ከዚህ በፊት ቀብርን እንዳትጐበኙ ከልክያችሁ ነበር አሁን ግን ጎብኙ፡፡››
አቡሑረይራ እንዳስተላለፉት ነብዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል ‹‹ቀብርን ጐብኙ ሞትን ያስታውሳችኋል፡፡››
አቡ ሰዒድ አል ኹድሪይ እንዳስተላለፉትም የአላህ መልዕክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል ‹‹ቀብርን መጐብኘት ከልክያችሁ ነበር አሁን ግን ጐብኙ ትምህርት ይሰጣችኃል፡፡››
አነስ ኢብኑ ማሊክም እንዳስተላለፉት የአላህ መልዕክተኛ እንዲህ ብለዋል ‹‹ቀብርን መጐብኘት ከልክያችሁ ነበር አሁን ግን ጐብኙ ምክንያቱም ልብን ያርሳል፣ አይንን ያነባል፣ አኺራን ያስታውሳል፡፡ ነገር ግን የተከለከለን ቃል እንዳትጠቀሙ፡፡››
ቡረይዳህ እንዳስተላለፉት የአላህ መልዕክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ቀብር ሲጐበኝ እንዲህ እንዲባል አስተምረዋል፦
"السلام عليكم أهل الديار من المؤمنين والمسلمين وإنا إن شاء الله بكم لاحقون أسأل الله لنا ولكم العافية"
“አሰላሙ ዓለይኩም አሕለ ዲያር ሚነል ሙእሚኒነ ወልሙስሊሚን ወኢና ኢንሻ አላሁ ቢኩም ላሂቁን አስአሉ ላሐ ለና ወለኩሙል ዓፊያ”
ትርጉሙ፦ (የአካባቢው ምእመናንና ሙስሊም ህዝቦች ሆይ! ሰላም በእናንተ ላይ ይስፈን እኛም በአላህ ፈቃድ ተከታዮቻችሁ ነን፡፡ አላህ እኛንም እናንተንም እንዲጠብቅ እለምናለው፡፡”
እነዚህና መሰል ሀዲሶች እንደሚጠቁሙት ቀብርን መጐብኘት ክልከላው ተነስቶ ለሁለት ታላላቅ ዓላማዎች ሲባል እንደተፈቀደ ነው፡፡
አንደኛ፡- አኺራን፣ ሞትንና ማለቅን በማስታወስ ዱንያን ችላ ለማለት እንዲሁም በቀብር ሰዎች ትምህርት በመውሰድ እምነትን ለማጠናከርና ከአላህ ጋር ያለንን ግንኙነት በማሳመር ቸልተኝነትን ለማስወገድ፡፡፡
ሁለተኛ፡- ለሙታኖች አላህ በማዘን ኃጢኣታቸውን እንዲምርና ይቅር እንዲላቸው በመለመን መልካምን መዋል፡፡
ከላይ ያሳለፍናቸው ማስረጃዎች የሚጠቁሟቸው ሲሆኑ ከነዚህ ሌላ ከቀብር የሚገኝ ነገር እንዳለ የሚሞግት ማስረጃ ይጠበቅበታል፡፡
✔ ሙታንንና ቀብሮችን ማምለክ
ሙታን ለራሱም ምንም ማድረግ የማይችል በመሆኑ ቀብሩ ዘንድ ሄዶም ይሁን በሩቁ አንዳችን ነገር እንዲያሳካ መለመን መከጀል ወይም ጉዳት ያደርስብኛል ብሎ መስጋት በአላህ ላይ ማጋራት (ሽርክ) ነው፡፡
ነብዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ቀብርን ለማምለክ ከሚዳርጉ ነገሮች ሁሉ ከሩቁ አስጠንቅቀዋል፡፡ ቀብር ላይ ከመስገድ ወይም መስጂድ ከመገንባት እንዲህ በማለት ከልክለዋል፦
“ከናንተ በፊት የነበሩ ህዝቦች የነብያቸውን ቀብር መስገጃ አድርገዋል እናንተም ቀብሮችን መስገጃ እንዳታደርጉ አጥብቄ እከለክላለሁ”
አይሁዶች እና ክርስቲያኖችን የነቢያትን ቀብር መስገጃ ስፍራ በማድረጋቸው እንዲህ በማለት ረግመዋል፦“አይሁዶች እና ክርስቲያኖች አላህ ከእዝነቱ ያርቃቸው፤ እነሱ የነቢያቸውን ቀብር መስጂድ አድርገዋል”
የእሳቸው ቀብር እንዳይመለክ አላህን እንዲህ በማለት ለምነዋል፡- “ጌታዬ ሆይ! ቀብሬን የሚመለክ ጣዖት እንዳታደርግብኝ”
እነዚህና ሌሎችም ነቢያዊ ትምህርቶች ቀብር ላይ ድንበር እንዳይታለፍና እንዳይመለክ ከሩቁ የሚያስጠነቀቁ ናቸው፡፡
ነብዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንኳን ቀብር ሊመለክ ይቅርና ቀብር ዘንድም ለአላህ እንዲሰገድ አልፈቀዱም፦
“ወደ ቀብር አትስገዱ ላዩም አትቀመጡ"
✔ በሌላ በኩል ከቀብርና ከጉብኝቱ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ነገሮችን ሐዲስ ለተውሂድ ድንበር ጥበቃ ሲል ከልክሏል፡፡
እነዚህን ማንኛውም ሙስሊም ከጥመት ለመጠበቅ ሲል ሊያውቃቸው ይገባል፡፡ ከነዚህ ውሰጥ
1ኛ. ቀብርን ሲጐበኝ የተከለከለን ንግግር ከመናገር መቆጠብ
ከላይ እንዳሳለፍነው ነብዩ “የተከለከለን ንግግር እንዳትናገሩ” ብለዋል:: ይህ ማለት ሸሪዓው ያወገዘውን ቃላት ማለት ሲሆን በመጀመሪያ ደረጃ የሚከለከሉት የሽርክ ቃላቶች ናቸው:: ለምሳሌ ቀብሮችን ከጭንቅ እንዲገላግሉት፣ እድሜውን እንዲያረዝሙት፣ ጤንነት እንዲለግሱት መለመን፡፡ይህ ግልፅ የሆነ ማጋራትና ክህደት ነው፡፡ ይህን የሚያወግዙና ሰሪውን የሚረግሙ ግልፅ የሆኑ ሀዲሶች ከነብዩ ተዘግበዋል፡፡
ሙስሊም ጁንዱብ ኢብኑ አብደላህን ጠቅሰው እንደዘገቡት የአላህ መልዕክተኛ ከመሞታቸው ከአምስት ቀናት በፊት እንዲህ ሲሉ ሰምቻለው ብለዋል ‹‹ከእናንተ በፊት የነበሩ ህዝቦች የነቢያታቸውንና የደጋግ ባሮችን ቀብር መስገጃ ስፍራ አደረጉ፡፡ እናንተ ግን ቀብሮችን መስገጃ እንዳታደርጉ ከልክያችኃለው፡፡›› ሙታንን መለመን፣ ጉዳዮችን እንዲያሳኩ መጠየቅና አምልኮዎችን ለነርሱ ማዋል ትልቁ ሽርክ ሲሆን ቀብር ዘንድ በማክበር ተቀምጦ እዚያ ስፍራ ዱዓእ ተቀባይነት እንደሚኖረው በማሳብ መጠባበቅና ቀብር ያለበት መሰጂድ ውስጥ መስገድ ውጉዝ የሆነ ቢድዓ ነው፡፡
ቡኻሪና ሙስሊም ዓኢሻን ጠቅሰው እንደዘገቡት ነብዩ በጣረ ሞት እያሉ እንዲህ ብለዋል ‹‹አይሁዶችና ክርስታኖች የነቢያታቸውን ቀብር መስገጃ ስፍራ ስላደረጉት አላህ ከእዝነቱ አባሯቸዋል፡፡››
2ኛ. ቀብር ዘንድ ማረድ
ይህ የሚደረገው ጉዳይን እንዲያሳኩ በማሰብ ለቀብሮች ለመቃረብ ከሆነ ይህ ትልቁ ሽርክ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ለሆነ ዓላማ ከሆነ ደግሞ አደገኛ የሆነና ለሽርክ የሚዳርግ ቢድዓ ነው፡፡ ነብዩ ኢስላም ውስጥ “አቅር” የለም ብለዋል፡፡ አብድረዛቅ እንዳሉት “በጃሂሊያ ዘመን ቀብር ዘንድ ከብትና በግ ያርዱ ነበር”
3ኛ. ከወጣው አፈር ውጭ በመጨመር ከፍ ማድረግ
4ኛ. ጄሶ መለሰን
5ኛ. ላዩ ላይ መፃፍ
6ኛ. ከላዩ መገንባት
7ኛ. ቀብር ላይ መቀመጥ
እነዚህ ሁሉ ለአይሁዶችና ክርስቲያኖች መጥመም ምክንያት የሆኑ ቢድዓዎችና ከፍተኛ የሽርክ መዘዞች ናቸው፡፡
ጃቢር እንዲህ ብለዋል ‹‹የአላህ መልዕክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ቀብርን በጄሶ መመረግ፣ ላዩ ላይ መቀመጥ፣ ከላዩ መገንባት፣ ከአፈሩ ውጭ መጨመርና ቀብር ላይ መፃፍ ከልክለዋል፡፡››
8ኛ. ቀብር ዘንድ መስገድ
አቡ ሙርሢድ አልገነዊይ እንዳሉት የአላህ መልዕክተኛ እንዲህ ሲሉ ሰምቻለው ‹‹ወደ ቀብር አትስገዱ ላዩም አትቀመጡ››
አቡ ሰዒድ አልኹድሪይ እንዳስተላለፉት የአላህ መልዕክተኛ እንዲህ ብለዋል ‹‹መሬት ሁሉም መሰገጃ ነው ቀብርና ገላ መታጠቢያ ሲቀር ፡፡”
9ኛ. ቀብር ላይ መስጂድ መገንባት
ይህ አይሁድንና ክርስቲያናትን ያጠመመ ቢድዓ ነው፡፡ ከላይ እንዳሳለፍነው ከዓኢሻ የሚከተለው ሀዲስ ተስተላልፏል ‹‹አይሁዶችና ክርስቲያኖች የነቢያታቸውን ቀብር መስጂድ በማድረጋቸው አላህ ከእዝነቱ አባረሯቸው፡፡››
1ዐኛ. ቀብርን የበዓል ስፍራ ማድረግ
ይህ ቢድዓ አደጋው የከፋ በመሆኑ ግልፅ በሆነ መልኩ ተከልክሏል፡፡ ከአቡ ሑረይራ እንደተላለፈው የአላህ መልዕክተኛ እንዲህ ብለዋል ‹‹ቀብሬን የበዓል ስፍራ እንዳታደርጉ፡፡ ቤታችሁንም መቃብር አታድርጉ፣የትም ቦታ ብትሆኑ ሰላትን አውርዱብኝ ሰላታችሁ የትም ብትሆኑ ይደርሰኛል፡፡››
11ኛ. ጓዝ ጠቅልሎ ቀብርን ለመጐብኘት መጓዝ
ይህም ወደ ሽርክ የሚያደርስ መንገድ በመሆኑ ተከልክሏል፡፡ በአቡ ሑረይራ እንደተላለፈው ነብዩ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል ‹‹ወደ ሶስት መስጂዶች እንጂ ጓዝን ጠቅልሎ ለመጐብኘት መጓዝ አይፈቀድም መስጂደል ሀራም፣ የመልዕክተኛው (ሰ.ዐ.ወ) መስጂድና የአልአቅሳ መስጂድ፡፡
http://www.facebook.com/emnetihintebiq

Post a Comment

0 Comments