Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

እውን ሰለፍዮች በደዕዋ ላይ ሺዳ (መጠንከር) አለባቸው?

****** እውን ሰለፍዮች በደዕዋ ላይ ሺዳ (መጠንከር) አለባቸው? ****
ጠያቂ፡- የተከበሩ ሸይኽ! እዚህ ላይ የደዕዋን ዘርፍ የሚመለከት ጥያቄ አለ፡፡ እንዲህ የሚል ነው፡ እንደሚታወቀው እዝነት፣ ገራገርነት፣ ለስላሳነት ከነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ከተረጋገጡ ሱናዎች ናቸው፡፡ በደዕዋ ላይ እዝነትን ማስገኘት እና መተግበሩ ግዴታ ነው ወይስ እንዲሁ የሚወደድ ብቻ ነው?
ሸይኹል አልባኒ፡- ግዴታ ነው፡፡
ጠያቂ፡- ጥያቄው ያነገበው አላማና ግብ አለው፡፡
ሸይኹል አልባኒ፡- እንዴታ! ከጀርባው የሆነ ነገር አለ፡፡
ጠያቂ፡- ሰለፍዮች በተለያየ መልካቸው ደዕዋን ሲያሰራጩ በሺዳህ (ጠንከር በማለት) እና በእዝነት መቅለል የታወቁ ናቸው ይባላል፡፡ ምናልባትም ልክ ሊሆን ይችላል!! ይሄ ልክ ይመስለዎታል? በኔ በኩል እንደዚያ አስባለሁ፡፡ እስኪ በዚህ ላይ ያለዎት አስተያየት ምንድን ነው?
ሸይኹል አልባኒ፡- በመጀመሪያ የተናገርከው ውስጥ ማስተካከያ የሚፈልግ ነገር አለ፡፡ እሱም “ምናልባትም ልክ ሊሆን ይችላል” ማለትህ ነው፡፡
ጠያቂ፡- “ይሄ ልክ ይመስለዎታል?” አልኩኝ እኮ!
ሸይኹል አልባኒ፡- መጀመሪያ ግን “ምናልባትም ልክ ሊሆን ይችላል” ብለሃል፡፡ ጥንካሬ ይጎላባቸዋል የሚባለውን በተመለከተ ማለት ነው፡፡
ጠያቂ፡- እሺ ይቅርታ፡፡
ሸይኹል አልባኒ፡- ብለሃል ግን አይደል?
ጠያቂ፡- አዎ፡፡ ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡
ሸይኹል አልባኒ፡- እዚህ ላይ እንዲህ አይነት አነጋገር የሚናገሩ ወንድሞቻችንን የምናስገነዝበው አንድ እርማት አለ፡፡ ይሄ የፖለቲከኞች መልስ ነው፡፡ አስበውበት ላይሆን ይችላል፡፡ ቢሆንም ግን “ንግግር ያለው ከልብ ውስጥ ነው፡፡ የምላስ ተግባር ከልብ ያለውን ማስተጋባት ነው” ይባላል፡፡ እናም አንድ ተናጋሪ በሆነ ጉዳይ ላይ “ሊሆን ይችላል” ሲል “ላይሆንም ይችላል” የሚልም ሊቀርብበት ይችላል፡፡ ጥያቄህን በተመለከተ ሁለት ነገር እናንሳና ከዚያም መልሱን እናስከትላለን፡፡ “ሰለፍዮች ጥንካሬ እንጂ ልስላሴ የላቸውም፡፡ ይህ ነው መታወቂያቸው ወይም መንገዳቸው” ባዩ ማን እንደሆነ እርግጠኛ ሆነህ ታውቃለህ? ልብ በል! ለዚህ ጥያቄ በሩን የከፈትክልኝ አንተ ነህ፡፡ ምክኒያቱም “ልክ ሊሆንም ይችላል” ብለሃልና!!
ጠያቂ፡- ያ ሸይኽ! “ምናልባትም ልክ ሊሆን ይችላል” ማለቴን እኮ ይቅርታ ብያለሁ፡፡
ሸይኹል አልባኒ፡- በቃ?
ጠያቂ፡- አዎ!
ሸይኹል አልባኒ፡- እንግዲያው ትክክለኛውን ንግግር ልስማ፡፡ ምን ነበር ያልከው
ጠያቂ፡- ልድገመው?
ሸይኹል አልባኒ፡- እንዳትደግመው፡፡ ምክኒያቱም ስህተት ነዋ! ያለበለዚያማ ከምኑ ነበር ይቅርታ የጠየቅከው? “ሊሆን ይችላል” የሚለውን አውጥተህ አስተካክለህ ድገመው፡፡ አባባሌ ግልፅ ነው?
ጠያቂ፡- አዎ፡፡ ሸይኹል አልባኒ፡- እሺ ቀጥል፡፡
ጠያቂ፡- ጥያቄውን ከመጀመሪያው ልድገመው?
ሸይኹል አልባኒ፡- ችግር የለም፡፡ ምርጫው ያንተው ነው፡፡
ጠያቂ፡- እርሶ እንደመለሱት እዝነት፣ ገራገር መሆንና መለስለስ በደዕዋ ላይ ግዴታ ነው፡፡ ታዲያ የኔ ጥያቄ ስለ ደዕዋ እንጂ ስለ ግል ወይም የህይወት ጉዳዮች አይደለም፡፡ እናም እንደጠቀስከው ደዕዋ ለሚጠሩ ሰዎች ማዘንና መለስለስ ይገባል፡፡ ሰለፍዮች ግን እንደኔ አስተያየት በደዕዋ ላይ መጠንከርና የእዝነት መቅለል ይጎላባቸዋል፡፡ ይሄ የኔ አስተያየት ነው፡፡ የእርሰዎስ አስተያየት ምንድን ነው?
ሸይኹል አልባኒ፡- አንተ ከነሱ ነህ (ከሰለፍዮቹ)?
ጠያቂ፡- ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
ሸይኹል አልባኒ፡- አንተ ከነሱ ነህ? አንተ ሰለፊ ነህ?
ጠያቂ፡- አዎ፡፡
ሸይኹል አልባኒ፡- ስለዚህ አንተም ከነዚህ አጥባቂ ሰለፍዮች ነህ ማለት ነው?
ጠያቂ፡- እራሴን አላጥራራም፡፡ ማለት የፈለግኩት የሰለፍዮች የጎላ ምልክት ነው ለማለት ነው፡፡
ሸይኹል አልባኒ፡- ጉዳዩ እኮ እራስን የማጥራት ጉዳይ አይደለም!! ጉዳዩ እውነታን የመግለፅ ጉዳይ ነው፡፡ ይህን ጥያቄ ያነሳሃው ለመመካከር ነው፡፡ ስለዚህ “አንተም ከነዚህ አጥባቂ ሰለፍዮች ነህ ማለት ነው?” ብየ ስጠይቅህ “እራሴን አላጥራራም” የሚል ርእስ አይነሳም፡፡ ምክኒያቱም ተጨባጩን እውነታ መግለፅ ነዋ የምትፈልገው! ለምሳሌ እኔን ይህን ጥያቄ ብትጠይቀኝ “እኔ እንደማስበው ሙተሸዲድ (አጥባቂ) አይደለሁም” ነው የምልህ፡፡ ይህን ስል ግን እራሴን እያጥራራሁ አይደለም፡፡ ይልቅ ያለኝን እውነታ ነው የምነግርህ፡፡ ስለዚህ ጥያቄውን በሚገባ አጢነው፡፡
ጠያቂ፡- አዎ ሸይኽ መልሴ ያንተው አይነት መልስ ነው፡፡
ሸይኹል አልባኒ፡- እንግዲያው ሰለፍዮችን በጅምላ ሙተሸዲዶች (አጥባቂዎች) ናቸው ልንል አይገባም፡፡ የሚባለው ከፊሉ አጥባቂዎች ናቸው ነው፡፡ እናም አንዳንዱ ሰለፊ የደዕዋ አቀራረቡ ላይ ማጥበቅ አለበት እንላለን ማለት ነው፡፡ ግን እስኪ ንገረኝ ይሄ ከፊሉ ላይ መንፀባረቅ ሰለፍዮች ላይ ብቻ ያለ ነው?
ጠያቂ፡- አይ አይደለም፡፡
ሸይኹል አልባኒ፡- እና የዚህ ጥያቄ ፋይዳውስ አላማውስ ምንድን ነው? ሁለተኛ ደግሞ ይሄ በደዕዋ ላይ መገኘቱ ግዴታ ነው ያልነው መለሳለስ ሁልጊዜ ነው እንዴ ግዴታ የሚሆነው?
ጠያቂ፡- አይ አይደለም!!
ሸይኹል አልባኒ፡- ስለዚህ አንደኛ ላንተም ለሌሎችም የሆኑ ክፍሎችን በሆነ ባህሪ በጅምላ ልትወርፋቸው አይፈቀድም፡፡ ሁለተኛ በየትኛውም ግለሰብ ላይ ሰለፊም ይሁን ኸለፊ -እንደ አገላለፃችን- በዚህ ባህሪ ልቅ አድርገህ ልትገልፀው አይገባህም፣ በተገደበ መልኩ ካልሆነ በስተቀር፡፡ ምክኒያቱም በደዐዋ ላይ መለሳለስ ሁልጊዜ የሚፈቀድ ነገር እንዳልሆነ ተስማምተናልና፡፡ ዛሬ አንድ ሰለፊ የሆነ ሙስሊም ቢጠቀመው ሰዎች በጥብቅ የሚኮንኑበት አይነት ጥንካሬን መልእክተኛውን ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ሲጠቀሙበት እናገኛለን፡፡ ለምሳሌ የአቡ አስሰናቢል ኢብኑ በዕከክን ታሪክ ታውቅ ይሆናል፡፡
ጠያቂ፡- አላውቅም፡፡
ሸይኹል አልባኒ፡- አንዲት ሴት ነፍሰ-ጡር ሆና ሳለች ባሏ ይሞታል፡፡ አልቆየችም ወለደች፡፡ ነፍሰ-ጡር የሆነች ሴት ባሏ ቢሞት ስትወልድ ጊዜ ዒዳዋ እንደሚያልቅ ከመልእክተኛው ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ደርሷታል፡፡ እናም በሶሒሕ አልቡኻሪ ላይ እንደተጠቀሰው ከወለደች በኋላ ለትዳር ታማትራለች፡፡ ተዋዋበች፣ ተኳኳለች፡፡ አቡ አስሰናቢል ትንሽ ቀደም ብሎ ጠይቋት እምቢ ብላዋለች፡፡ ዝግጅቷን ሲመለከት ጊዜ መደበኛውን የዒዳ ጊዜ አራት ወር ከአስር ቀን ሳትጨርስ ማግባት እንደማይፈቀድላት ይነግራታል፡፡ ከሁኔታዋ ሴትዮዋ ለዲኗ ትኩረት የምትሰጥ ናት፡፡ እና ወደ መልእክተኛው ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ፈጥና በማምራት አቡ አስሰናቢል የተናገረውን ነገረቻቸው፡፡ ይህኔ መልእክተኛው ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዲህ አሉ፡- “አቡ አስሰናቢል ዋሸ!” አሉ፡፡ አሁን ይሄ አባባላቸው ጠንካራ ነው ወይስ ለስላሳ አገላለፅ?
ጠያቂ፡- ጠንካራ ነው፡፡
ሸይኹል አልባኒ፡- ጥንካሬው (ሺዳው) ከማን ነው? ከልስላሴው አባት!! (አመለ-መጥፎ፣ ልበ-ደረቅም ብትሆን ኖሮ ከዙሪያህ በተበተኑ ነበር) ከተባሉት ነው፡፡ ስለዚህ “መለስለስ ያስፈልጋል” የሚለው መርህ ቅድም እንደጠቀስነው ከሱ የማይወጣበት ቋሚ የሆነ ህግ አይደለም፡፡ ይልቅ ሙስሊም የሆነ ሰው መለስለስንም ከቦታው መጠንከርንም ከቦታው ሊያደርግ ይገባዋል፡፡ ልክ እንዲሁ በሙስነድ አልኢማም አሕመድ እንደተዘገበው በአንድ ወቅት ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ኹጥባ ባደረጉ ጊዜ ከሶሐቦች አንዱ ተነስቶ “አላህ ከሻውና አንተ ከሻሀው የአላህ መልእክተኛ ሆይ!” አላቸው፡፡ የዚህን ጊዜም እሳቸው “ለአላህ ባላንጣ አደረግከኝን!!! አላህ ብቻ ቢሻ በል!” አሉት፡፡ አሁን ይሄ ጠንካራ ነው ወይስ ለስላሳ መልስ?
ጠያቂ፡- አይ ይሄ የነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም አቀራረብ ነው፡፡
ሸይኹል አልባኒ፡- ይቺን እኔ ሽወዳ ነው የምላት፡፡ ምክኒያቱም ቀደም ብለህ በመለስክልኝ መልኩ አልመለስክልኝምና፡፡ አቡ አስሰናቢልን አስመልክተው እሳቸው ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም “ኡቡ አስሰናቢል ዋሸ!” ማለታቸው መጠንከር ነው መለስለስ?
ጠያቂ፡- እሄ መለስለስ ነው፡፡ ሸይኹል አልባኒ፡- ሁለተኛውስ?
ጠያቂ፡- አይ እንዲሁ ግልፅ ብቻ ነው ያደረጉለት፡፡ “ለአላህ ባላንጣ አደረግከኝን” በማለት፡፡
ሸይኹል አልባኒ፡- ይቺ ሽወዳ ናት ባረከላሁ ፊክ፡፡ እኔ “ገልፀውለታል ወይስ አልገለፁለትም?” ብዬ አልጠየቅኩህም፡፡ የጠየቅኩህ አመላለሳቸው በጥንካሬ ነው ወይስ በመለስለስ? የሚል ነው፡፡ ምነው አሁን የአመላለስ ዘየህ ተቀየረ? ቀድመህ እኮ “አቡ አስሰናቢል ዋሸ!” ማለታቸው ላይ ምንም እንኳን ግልፅ ያደረጉ ከመሆናቸውም ጋር “ግልፅ አደረጉ” ብለህ አልነበረም የመለስክልኝ፡፡ ግን ይሄ አገላለፅ መርህ ነው ብለን እንደተስማማነው ልዝብ፣ ልስልስ ያለነው ወይስ ጥንካሬ ነበረት? በግልፅ ቋንቋ ጥንካሬ እንዳለበት ተናግረሃል፡፡ ስለሁለተኛውስ ጥያቄ እንዴት ነው መልስህ?
ጠያቂ፡- ሁለተኛው ጥያቄ ላይ “ዋሸ!” አላሉትም፡፡ “ለአላህ ባላንጣ አደረግከኝን?!” ነው ያሉት፡፡
ሸይኹል አልባኒ፡- አላሁ አክበር!! እንዳውም ይሄ ይበልጥ የሰላ ትችት ነው!!! ባረከላሁ ፊክ፡፡ ሌላም ሐዲሥ አለ፡ አንድ ኸጢብ ተነስቶ “አላህና መልእክተኛውን የታዘዘ በርግጥም ተቀና፡፡ እነሱን ያመፀ ግን በርግጥ ጠመመ” አለ፡፡ የአላህ መልእክተኛም ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም “ምንኛ ክፉ ኸጢብ ነህ አንተ?!” ብለውታል፡፡ ይህስ ጠንካራ ነው ወይስ ለስላሳ አቀራረብ?
ጠያቂ፡- ጠንካራ ነው፡፡
ሸይኹል አልባኒ፡- ዋናው ነገር -ባረከላሁ ፊክ- ለስላሳ አቀራረብም አለ፡፡ ጠንካራ አቀራረብም አለ፡፡ እናም እንደተስማማነው ሁሌም በቋሚነት የሚሰራ ከልካይ የሆነ ወጥ ህግ የለም፡፡ ስለዚህ ሁልጊዜ መለስለስ ወይም ሁልጊዜ መጠንከር የሚባል ነገር የለም፡፡ ይልቅ አንዳንዴ ይሄኛው ሌላ ጊዜ ያኛው ይሆናል ማለት ነው፡፡ ግን እነዚህ በጅምላ (ልስላሴ የሌላቸው) ጠንካሮች ብቻ እንደሆኑ የሚወነጀሉት ሰለፍዮች በንፅፅር ከሌሎች አንጃዎችና ቡድኖች በበለጠ ሸሪዐዊ ብይኖች ላይ እና ሰዎችን መጣራት ላይ የሚያተኩሩ አይመስልህምን?
ጠያቂ፡- እዚህ ላይ ምንም ጥርጥር የለም፡፡
ሸይኹል አልባኒ፡- ባረከላሁ ፊክ! በዚህ ከሌሎች በላቁበት ትኩረታቸው ምክኒያት ሌሎች ከልስላሴ ጋር ቢቆራኝ እንኳን በመልካም ማዘዝንና ከመጥፎ መከልከልን እንደ ሺዳ (መጠንከር) ነው የሚያስቡት፡፡ እንዳውም አንዳንዱ “ይሄ ጊዜው አይደለም” እስከማለት ደርሷል፡፡ አንዳንዱማ ጭራሽ “በተውሒድ ላይ የሚደረግ ጥናት አንድነትን ይበታትናል” እስከማለት ድንበር ዘሎ ተሻግሯል!!
ስለዚህ አላህ ይባርክህና ካንተ ጋር ልደርስበት የምፈልገው ነጥብ ጉዳዩ አንፃራዊ መሆኑ ላይ ነው፡፡ ለምሳሌ ለደዕዋ ብዙ ሞራሉ የሌለው አለ፡፡ በተለይ ደግሞ ቅርንጫፋዊ ነገሮች ላይ- እነሱ ገለባ ወይም በይደር የሚቆዩ የሚገባቸው ነገሮች ሲሉ ይሰይሟቸዋል፡፡ እንዲህ አይነቱ በለዘበ አቀራረብም ቢሆን እንኳን እነዚህ ርእሶች ከተነኩበት ቦታውን ያልጠበቀ ማጥበቅ (ሺዳህ) እንደሆነ ነው የሚቆጥረው፡፡ ስለዚህ እንደኛው ሰለፊ ሆነህ እያለህ ጥቂቶች ጋር እንኳን ቢሆን “ሰለፊዮች አጥባቂዎች ናቸው” እያልክ በሰው መሃል ልታናፍስ አይገባም፡፡ ምክኒያቱም ከፊሎች እንደሚያጠብቁ ተስማምተናልና፡፡ ይሄ ግን ሌላው ቀርቶ ከሶሐቦች እንኳን ሊገኝ የሚችል ነው፡፡ ከነሱም ውስጥ ተለሳላሽ ነበር፡፡ አጥባቂም ነበር፡፡ ምናልባት የዚያን በመስጂድ ውስጥ የሸናውን ዘላን ጉዳይ ታውቅ ይሆናል፡፡ ሶሐቦች ሊመቱት አሰበው ነበር፡፡ አሁን ይሄ መለሳለስ ነው ወይስ ማጥበቅ?
ጠያቂ፡- አይ ሺዳህ (ማጥበቅ) ነው፡፡
ሸይኹል አልባኒ፡- ነገር ግን መልእክተኛው “ተውት” አሏቸው፡፡ ስለዚህ ከመጠንከር (ሺዳህ) ምናልባት ጥቂት ሰው እንጂ አይተርፍም፡፡ ባይሆን ሐቁ በደዕዋ ላይ መሰረቱ በጥበብና በመልካም ግሳፄ ሊሆን ነው፡፡ ታዲ መለሳለስንም ከቦታው፣ መጠንከርንም ከቦታው ማድረግህ ከሒክማ (ከጥበብ) ነው፡፡ እንጂ ከኢስላማዊ አንጃዎች ሁሉ ምርጥ የሆነችዋን፣ ከሁሉም አንጃዎች ልቃ ወደ ቁርኣንና ሱና በመልካም ቀደምቶች ግንዛቤ በመጣራት ላይ የምትተጋዋን ቡድን ልቅ አድርጎ በማጠንከር (በሺዳህ) መወረፍ ይሄ በምንም መልኩ ሚዛናዊነት ነው ብየ አላስብም፡፡ እንዳውም ይሄ ድንበር ማለፍ ነው፡፡ “አይ በውስጣቸው አጥባቂ የሆነ አለ” ማለቱን ግን ማን ሊክደው ይችላል? ሌላው ቀርቶ ቦታውን ባልጠበቀ መልኩ ማጥበቅ ከሶሐቦች እንኳን ያጋጥም እንደነበር አይተናል፡፡ ነገሩ እንዲያ ከሆነ ዘግይቶ የመጣው የኛ አምሳያው ዘንድ አጥባቂ (ሙተሸዲድ) መገኘቱ ይበልጥ የሚጠበቅ ነው፡፡ደግሞ አንድን ግለሰብ ነጥለን እንውሰድ፡፡ እንበልና ልዝብ ልስልስ ያለ ነው፡፡ ቦታውን ካልጠበቀ ማጥበቅ (ሺዳህ)ሁሌ ሊተርፍ ይችላልን?
ጠያቂ፡- አይተርፍም፡፡ ኧረ በፍፁም!!
ሸይኹል አልባኒ፡- እናኮ አላህ ይባርክህ እና ጉዳዩ ያለቀለት ጉዳይ ነው ማለት ነው፡፡ ነገሩ እንዲህ ከሆነ በኛ ላይ ያለው ግዴታ መመካከር ብቻ ነው፡፡ አንድ ሰው ቦታውን ባልጠበቀ መልኩ በጥንካሬ ሲገስፅ፣ ሲመክርና ሲያስታውስ ካየነው እናስታውሰው፡፡ ምናልባትም የራሱ እይታ ሊኖረው ይችላል፡፡ አስታውሰነው ከተቀበለ አላህ መልካሙን ይቀበለው፡፡ የራሱ የሆነ እይታ ከኖረው እንሰማዋለን፡፡ ጉዳዩም በዚያው ላይ ያልቃል፡፡
[ዱሩሱን ሊሽሸይኺልአልባኒ ረሒመሁላህ፡ 45/2]