Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

በሬ ሆይ ሳሩን አየህና ገደሉን ሳታየው‬


ለአላህ ብዬ በምወደው ወንድሜ የተፃፈ
አንድነት ሀይል ነው፡፡ ልዩነት ብርታትን ይነሳል፡፡ ወኔን ያኮስሳል፡፡ ስኬትን ይቀንሳል፡፡ ወንድማማችነትን ያሳሳል፡፡ ለውጭ አጥቂ በር ይከፍታል…፡፡ አንድነታችን ሀይላችን በተለያዩ አረሞች ይጠቃል፡፡ ከነኝህ ፀረ አንድነት አረሞች ውስጥ ቀዳሚው ደግሞ ቢድዐ ነው፡፡ የቢድዓን አፍራሽ ሚና የተረዱት ግን እጅግ ጥቂቶች ናቸው፡፡ አላህ ያዘነላቸው ሲቀሩ በርካቶች ለተለያዩ የቢድዓ አንጃዎችና ቁንጮዎቻቸው ጥብቅና በመቆም የቢድዓን መሰረቶች ያፀናሉ፡፡ ለቢድዓና ለሙብተዲዖች የሚያደርጉትን መከላከልም ለኢስላማዊ ህብረት ለአንድነት ጥብቅና መቆም አድርገው ይስሉታል፡፡
ግን…
ግን ወንድሞችና እህቶች አንድ የምንሆነው ለመበታተናችን ሰበብ የሆነውን ቢድዐን በማለፍ በመተላለፍ ነው እንዴ? ቀድሞ ነገር በምን ተለያይተን? ከጥንት ከጧቱ ጀምረን ብንከታተል ሙስሊሙን የበታተነው ቢድዐ እንጂ ሌላ ምንድን ነውና?! እስኪ የትኛው ፈር የለቀቀ አንጃ ነው በሱና ላይ የተመሰረተው? አንድም አናገኝም!! ኸዋሪጅ፣ ሺዐ፣ ቀደርያህ፣ ሙርጂአህ፣ ሙዕተዚላ፣ ጀህምያ፣ አሽዐርያህ… ወዘተ ሁሉም ከሱና ያፈነገጠ አዲስ ቢድዐ በማምጣታቸው ነው ራሳቸውን የቻሉ አንጃዎች ሆነው ኡማውን የከፋፈሉት፡፡በኢስላም ታሪክ የተነሱ ኡማውን የከፋፈሉ አንጃዎች በሙሉ መነሻቸው ቢድዐ ነው:: ታዲያ በምን ስሌት ነው እየለያየን ያለንን ቢድዐ ብንተላለፍ አንድ እንሆናለን ብለን የምናስበው?! እንዳው ሁኔታችንን ሳስተውል “በሬ ሆይ ሳሩን አየህና ገደሉን ሳታየው” የሚለው ሀገርኛ ብሂል በደንብ የሚገልፀን ይመስለኛል፡፡ በሬው ከገደሉ አፋፍ ላይ ያለው ሳር ሙሉ ትኩረቱን ስቦት ገደሉን ከነመኖሩም ዘነጋው፡፡ እርግጥ ነው ሳሩን ቢያገኘው ይጠቅመዋል፡፡ ለዚያም ነው የቋመጠው፡፡ግን ያላስተዋለው አደጋ የጎመጀለትን ሳር ብቻ ሳይሆን ህይወቱንም አስከፈለው፡፡ መጨረሻውም በአሰቃቂ ሁኔታ ገደል መግባት ሆነ፡፡ የኛም ሁኔታ እንደዚያው ይመሰላል፡፡ ህብረታችን ያጓጓናል፡፡ በርግጥም የሚያጓጓ ነገር ነው፡፡ ግን እሱን ለማሳካት ስንል አስፈሪ የቢድዐ ገደሎችን ከነመኖራቸውም ዘነጋናቸው፡፡ እያየንም እንዳላየን አለፍናቸው፡፡ ታዲያ የምንጓጓለትን ህብረት ብቻ ሳይሆን ብዙ ነገሮቻችንን ይዘው እንጦረንጦስ እያምዘገዘጉን ነው፡፡ እኛ ግን ሙሉ ትኩረታችን ሳሩ (ህብረታችን) ላይ በመሆኑ ገደሉ (የቢድዐ አደጋዎች) ሊታየን አልቻለም፡፡ እያየን እንዳላየን የምንተላለፈው ከባባድ ቢድዐ የምናልመውን አንድነታችንን ብቻ ሳይሆን ብዙ ነገር ነው የሚያስከፍለን፡፡ እስኪ ጥቂት የቢድዐ አደጋዎችን ከአንዳንድ ማስረጃዎች ጋር እንመልከት
1. ቢድዐ አንድነትን ያናጋል፡፡ የዒርባድ ኢብኑ ሳሪያህን ሐዲስ ያስታውሱ፡፡
ኢብኑ ተይምያን አላህ ይማረውና እንዲህ ይላል፡- “ቢድዐ ከመለያየት ጋር የተቆራኘች ናት፡፡ ሱና ደግሞ ከመቀራረብ ጋር የተቆራኘች ናት፡፡ ልክ የሱናና የጀማዓ ባለቤቶች እንደሚባለው የቢድዓና የልዩነት ባለቤቶች ይባላል” (አልኢስቲቃማህ፡ 1/42)
2. ቢድዐ ከባድ እርግማን ላይ ይጥላል፡፡ ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም “አዲስ ፈሊጥ ያመጣ ወይም ሙብተዲዕን ያስጠጋ የአላህ የመላእክትና የሰዎች ሁሉ እርግማን በሱ ላይ ይሁን” ይላሉ፡፡ አልባኒ ሶሒሕ ብለውታል፡፡
3. ቢድዐ የነብዩን ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ሐውድ ያስከለክላል:: ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዲህ ይላሉ፡- “እኔ በሐውድ ላይ ቀዳሚያችሁ ነኝ፡፡ በኔ ዘንድ ያለፈ ከሐውዱ ይጠጣል፡፡ ከሱ የጠጣ ዘላለም ጥም አይነካውም፡፡ ወደኔ የማውቃቸው የሚያውቁኝ ሰዎች ይመጣሉ፡፡ ከዚያም እኔና እነሱ እንዳንገናኝ ይደረጋል፡፡ እኔም ‘እነሱ እኮ ከኔ ናቸው’ ስል ‘ካንተ በኋላ ያመጡትን አዲስ ፈሊጥ አታውቅም!’ የሚል መልስ ይሰጠኛል፡፡ እኔም ‘ከኔ በኋላ ለቀየረ በሩቅ በሩቅ!’ እላለሁ” አልባኒ ሶሒሕ ብለውታል፡፡
4. ቢድዐ የተውበትን እድል ያጠባል፡፡ ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም “አላህ ከሙብተዲዕ ሁሉ ቢድዐውን እስከሚተው ድረስ ተውበትን ጋርዷል” አልባኒ ሶሒሕ ብለውታል፡፡
5. ቢድዐ ስራን ውድቅ ያደርጋል፡፡ ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም “የኛ ትእዛዝ የሌለበትን (ዒባዳዊ) ስራ የሰራ ስራው ውድቅ ነው” ይላሉ፡፡ ቡኻሪና ሙስሊም የዘገቡት
6. ቢድዐን ለሌሎች ያስተላለፈ ሰው ከሱ አይተው በሚሰሩ ሁሉ ወንጀሉ ይመዘገብበታል፡፡ ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም “… በኢስላም መጥፎን ፈለግ የቀየሰ በራሱም እሱን ተከትለው እስከቂያማ ድረስ በሚሰሩትም ወንጀሉ አለበት” አልባኒ ሶሒሕ ብለውታል፡፡
ቢድዐ በጥቂቱ እነዚህ አደጋዎች አሉበት፡፡ እንግዲህ ይሄ ሁሉ ጉድ እያለ ነው የቢድዐ ጉዳይ እየተሸፋፈነ እየተላለፈ የሚታለፈው፡፡ አላህ ጤነኛ በሆነ መልኩ ለዲናችን የምንቆረቆር ያድርገን፡፡


ኢብኑ ሙነወር ( Ibnu Munewor )