Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

የአህሉ ሱና ዳዕዋ

የአህሉ ሱና ዳዕዋ
بسم الله الرحمن الرحيم الحمد لله رب العالمين وصل اللهم وسلم وبارك على نبينا محمد وعلى آله وصحبه ومن تبعهم بإحسان إلى يوم الدين
በመጀመሪያ አህሉ ሱና ማለት ነቢዩ ه ይዘውት የመጡትን ኢስላም እንዳመጣጡ ምንም ዓይነት አዲስ ፈጠራ ሳይቀላቅሉ የተከተሉ ጀመዓዎች ማለት ሲሆን በእስልምና ስም የተለያዩ መንገዶችን የሚፈጥሩ ቡድኖች እንደሚከሰቱና ከሁሉም ሰላም የሚሆነው የሳቸውን ፈለግ ተከታዩ ቡድን ብቻ እንደሚሆን ነቢያችን ه አስቀድመው የተነበዩት ጉዳይ ነው::
አህሉ ሱና መሆን ማለት በሁሉም ሀይማኖታዊ ጉዳዮች የነቢዩን ه ፈለግ ብቻ መከተል ሲሆን የሳቸውን መመሪያ እስካልተከተለ ማንም ይሁን ማንን አለመከተል ንግግሮችንና መመሪያዎችን ከነቢያችን ه ሱና ጋር በማስተያየት የሳቸውን ፍላጎት የሚስማማውን ብቻ መርጦ መጓዝ ማለት ነው::
አህሉ ሱና ከላይ እንደተገለፀው የነቢዩ ተከታዮች ማለት በመሆኑ እሳቸውን ከሚከተሉባቸው ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ዳዕዋ ነው::
ዳዕዋ ማለት በትክክለኛው መንገድ ወደ ኢስላም መጣራት ሲሆን የአህሉ ሱና ወልጀማዓ ዳዕዋ ኢስላም የሚፈልገው ትክክለኛው ጥሪ ነው::
የአህሉ ሱና ዳዕዋ:-
1- በሸሪዓዊ እውቀት የተመሰረተ ነው::
አላህ እንዲህ ይላል
قُلْ هَٰذِهِ سَبِيلِي أَدْعُو إِلَى اللَّهِ ۚ عَلَىٰ بَصِيرَةٍ أَنَا وَمَنِ اتَّبَعَنِي ۖ وَسُبْحَانَ اللَّهِ وَمَا أَنَا مِنَ الْمُشْرِكِينَ [١٢:١٠٨]
«ይህች መንገዴ ናት፡፡ ወደ አላህ እጠራለሁ፡፡ እኔም የተከተለኝም ሰው በግልጽ ማስረጃ ላይ ነን፡፡ ጥራትም ለአላህ ይገባው፡፡ እኔም ከአጋሪዎቹ አይደለሁም» በል፡፡
በመሆኑም ያለ እውቀት ዳዕዋ ለማድረግ መሞከር ወይም ስለማናውቀው የዲን ጉዳይ ማውራት ወይም መፃፍ ዳዕዋ መሆኑ ቀርቶ አላህና መልክተኛው ላይ መቅጠፍ ሊሆን ስለሚችል ከባድ ጥንቃቄ ይሻል::
2- ወሳኝ ለሆኑ የዲን ጉዳዮች በተለይ ለተውሂድ ልዩ ትኩረት ይሰጣል:: ምክንያቱም ተውሂድ የእስልምና ዋና መሰረት በመሆኑና ነቢዩም ከሌሎች ጉዳዮች በበለጠ መልኩ ከፍተኛ ቦታ ሰጥተውት በቅድሚያ ያስተማሩት ጉዳይ ነውና::
3- ነገሮችን ቁልጭ አድርጎ ያብራራል:: በተለይ ተውሂድ ላይ ሙስሊሞች ከአጋሪዎች የሚለዩበትን የተውሂድ አይነት ግልፅ አድርገው ያብራራሉ::
4- ሂክማ (ጥበብ) መልካም ግሳፄና ትህትና የተሞላቸው ንግግሮች መገለጫዎቹ ናቸው:: ይሁንና ሂክማ ትክክለኛውን ትምህርት በትክክለኛው መንገድ መስጠት እንጂ ዋና ዋና ወይም ዳዕዋ ለሚደረግላቸው አስፈላጊ የሆኑ ጉዳዮችን ወደ ጎን ትቶ ቅርንጫፋዊ ነጥቦችን ብቻ መምረጥ ማለት አይደለም:: ይህን አይነት ተግባር ዳዕዋን ያለ እውቀት የሚያስኬዱ ቡድኖች ጋር በስፋት የምናስተውለው ጉዳይ ሲሆን ነገሩ ግን ሂክማ መጠቀም ሳይሆን ህብረተሰቡን ማታለል ነው:: "من غشنا فليس منا"
5- የአህሉ ሱና ዳዕዋ ሁሉንም የዲን ጉዳዮች የሚዳስስ እንጂ አንዱን ብቻ የሚለይ አይደለም:: ምክንያቱም ነብዩ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ልዩ ትኩረት ይስጡ እንጂ ከኢስላም ተግባራት የሚፈልጉትን ብቻ መርጠው አልነበረም ያስተማሩት:: በመሆኑም አንዳንድ አህሉ ሱናዎች ዘንድም ሳይቀር እንደሚስተዋለው ሌት ተቀን አንድን ርዕስ ብቻ በመደጋገም ሌሎችን የእስልምና አስተምህሮዎች ችላ ማለት ሊታረም የሚገባው ስህተት ነው::
6- አህሉ ሱናዎች እስልምናን በተለይ ተውሂድን የማስተማር ጥማት እንጂ ሙስሊሙን ህብረተሰብ በኩፍር የመፈረጅ አንዳችም ጉጉት የላቸውም ይልቁንም ሙስሊምን ማክፈር ነቢዩ ه በሀይለኛው ያስጠነቀቁት ጉዳይ በመሆኑ መስፈርቶቹን በማሟላት ረገድ ከባድ ጥንቃቄ ይወስዳሉ::
7- አህሉ ሱና የተሳሳቱ ቡድኖች ላይ ሸሪዓው በሚፈቅደው መሰረት ምላሽ ይሰጣሉ:: ይሁንና ይህንን ሲያደርጉ ብዙ ወንድሞች ላይ እንደሚስተዋለው የመሰዳደቢያ ወይም የመበቃቀያ መንገድ አድርጎ መውሰድ ብልግና እንጂ ዳዕዋ ሊሆን አይችልም:: በተለይ ይህ ርዕስ ቦታ ጊዜና የሰዎችን ሁኔታ ከግምት ውስጥ የሚያስገባ እንጂ ልቅ ስላልሆነ ማንም ሰው በሚፈልገው መልኩ ሊጠቀመው አይገባም::
8- የአህሉ ሱና ዳዕዋ በሙስሊሞች መካከል አንድነት እንዲጎለብት ልዩነትና አጉል ንትርኮች እንዲወገዱ ጥረት የሚያደርግ ሲሆን የተሳሳቱ ቡድኖችን ማውገዝ ለአላህ ብሎ ኩፍርና ኩፋርን መጥላትና ቢድዓም የሱና ተቀናቃኝ በመሆኑ አጠንክሮ መቃወም ብዙ ሰዎች እንደሚያስቡት መከፋፈል ሳይሆን አንድነትን ከመጠበቂያ መንገዶች አንዱ ነው:: ስለዚህ አህሉ ሱና የሚለፉለት አንድነት አላህና ነቢዩ ه የሚፈልጉትን አይነት እንጂ አላዋቂዎች የሚያልሙትን አይነት አይደለም::
በጥቅሉ ዳዕዋ ማለት ለሰዎች አላህ የመረጠላቸውን እስልምና እንዲቀበሉ በመጓጓትና በመራራት በትህትና መጋበዝ ማለት ሲሆን ይህም የነቢያት በተለይም የአዛኙ ነቢያችን هሀላፊነት ነበር::
ዳዕዋ በማድረግ ምድር ላይ መልካም ነገሮችና የአላህ በረከት የሚበራከት ሲሆን ዳዕዋን በመተውም ሳቢያ ምድር ላይ ብልሽት ይንሰራፋል ከሰማይም መዓት ይዘንባል::
ዳዕዋን ነቢዩ ባልፈለጉት መንገድ ለማድረግ መሞከር ግን እስልምናን በተገቢው መንገድ ሊያሳይ ስለማይችልና አንዳንዴም ሊያጠለሸው ስለሚችል ለንግዳችን ኪሳራ ከምንሰጋው ይበልጥ ሰግተን ልንታቀብ ይገባል::
جعلني الله وإياكم ممن يستمعون القول فيتبعون أحسنه وآخر دعوانا أن الحمد لله رب العالمين