Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

የፌስቡክ ዳዕዋ መለኪያ???


የፌስቡክ ዳዕዋ መለኪያ???
================

ወደ አላህ መጣራት አንድ ባርያ ወደ አላህ የሚቃረብበት እንጂ የሰውን ቲፎዞ የሚያበዛበት አይደለም፡፡ በጥበብ መጣራትም እያንዳንዱ ተጣሪ ላይ ግድ ይለዋል፡፡ በጥበብ ማለት ግን ሰውን ላለማስከፋት ወይንም ቁጥር እንዳይቀንስ ተብሎ ሽርክ እና ቢድዐ ያለበትን ‹‹አኽላቅ፤ ሰላት እና ሌሎች አርስቶቸን›› ማስተማር አይደለም፡፡

የማንኛውም ስራ ሂሳብ ከፋዬ አላህ ብቻ እና ብቻ መሆኑ ሊታወቅ ይገባዋል፡፡ ነብያት በጠቅላላ ከጌታቸው የተላኩበትን ድርሻ ተወጥተው ተውሂድን አድርሱ ሲባሉ አድርሰዋል፡፡ ህዝባቸው አልቀበላቸው ያላቸውም ነበሩ፡፡ነገር ግን አርስቱን መቀየርም ይሁን፤ በሌላ አርስት ከያዝኳቸው በኋላ ወደ ተውሂድ እመለሳለሁ ያለ አንድም ነብይ የለም፡፡

ፌስቡክ ለዳዕዋ መድረክነት በጣም ታላቅ ኢንፎርሜሽን ማሰራጫ ነው፡፡ ይህንን ኒዕማ ብዙ ሙስሊሞች እየተጠቀሙበት ስለሆን ኪታብ የድምፅ ፋፌልን፤ ፅሁፎችን እና ሌሎችን በዚህ ሚድያ መጠቀም ስለሚቻል እና አገራችን ላይ የተለያየ ክፍለ ሃገራት ላይ ያሉ ወንድም እና እህቶች ይህን ሚድያ ስለሚጠቀሙት፤ ነብያት ሽርክ ባለበት ሁኔታ ጥርያቸውን ከተውሂድ ስለጀመሩ ወደ አላህ መንገድ የሚጣሩ አላህ ያዘነላቸውም የነብያትን ፈለግ በመከተል ከተውሂድ የጀመሩ አሉ፡፡

ሌላው አሁን አሁን ዳዕዋ ሲደረግ የዳኢው ማንነት ታይቶ ‹‹አርስት እንገድብበት፤ እዚህ ውስጥ እናዳትገባ፤ ስለ መውሊድ እንዳያነሳ፤ ስለ መንዙማ እንዳያነሳ›› የሚባል ፈሊጥ ስለመጣ ይህን ነፃ ማንም ከልካይ የሌለበትን መድረክ ተጠቅሞ አላህ እና መልክተኛው ይጀመር ያሉትን አርስት ማስተማር ተችሏል፡፡ አልሃምዱሊላህ፤ አላህ የእሱን ፌት ፈልገው ከሚሰሩት ያድርገን፡፡

ይህ በሚሆንበት ግዜ facebook has Like (ያንን ፅሁፍ መውደድን መግለጫ), Share (ለሌሎች ማዳረስ), Comment (ሃሳብን ደግፎም ነቅፎም መስጫ) አለው፡፡

ታድያ አንዳንዶች የሰውን ዳዕዋ የሚለኩት ወቅቱን እና ሰዓቱን የደገፈ ነገር ተፅፏል ወይንስ አልተፃፈም ሳይሆን ብዙ Like፤ Share ተደርጎ ጭቅጭቅ ኮሜንት ከሌለ ‹‹ጥሩ›› ብለው ያልፉታል፡፡ በተገላቢጦሹ ኮሜንት ላይ ጭቅጭቅ ከበዛ ‹‹ይህ ዳዕዋ ችግር አለበት›› የሚል ሁናቴ ውስጥ የሚወድቁ ብዙ አሉ፡፡ አላህ ለነሱም ለእኛም ይዘንልን እና ሃቁን ይምራን፡፡

ማስታወሻዎች
================

1) ዳዕዋን እኮ ሂሳብ የሚከፍለው አላህ እንጂ የፌስቡክ Like ብዛት አይደለም፡፡ ይህ ከሆነ ሚዛኑ እዚሁ ፌስቡክ ላይ የዘፋኝ ፒጅ ተከፍቶ 45000 ላይክ አግኝቷል ያውም ሙስሊሞች ላይክ ካደረጉት ውስጥ አሉበት፡፡ ታድያ ላይክ የሃቅ መለኪያ ነውን??? የዘፋኙን ላይክ ካደረጉት ውስጥ እዚህ ስለ ተውሂድ እና ሱና ትምህርት ሲሰጥ ሽርክ እና ቢድዐ ሲጋለጥ የሚጨቃጨቁ አሉ፡፡ ሌላው የሴት ፎቶ ፌስቡክ ላይ ተለጥፎ ከ200 በላይ ላይክ እና 150 ማሻአላህ ተብሏል፡፡ እና ይሄ ሚዛን ነውን???

2) ነብዩ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ‹‹አንድ ነብይ ብቻውን ይመጣል›› አሉ፤ አላህ ደግሞ ነብየላህ ኑህ አለይሂ ሰላም 950 ዳእዋ አድርጎ ያመኑለት ጥቂቶች እንደሆኑ ተነናገረ፡፡ ታድያ ሂሳብ ከፋዬ አላህ ኑህን ማድረሱን እንጂ የሚያየው ህዝቦቹ እንዲያውም የውመል ቂያማ አላደረሰልንም ብለው ይክዱታል፡፡ ታድያ ኑህ አርስት ቀየረ???

3) ፌስቡክ ላይም ይሁን የት ሃቁ ከወጣ ሃቁ የሚሰሩትን መጥፎ የሚያጋልጥባቸው ሰዎች መጨቃጨቃቸው፤ ስም ማጥፋታቸው አይቀርም፡፡ የነሱ ምላስ ተፈርቶ ሃቅ ከመናገር ወደ ኋላ አይባልም፡፡ ሂሳብ ከፋዬ አላህ ብቻ ነውና፡፡

4) ፌስቡክ ላይ ከአንድ በላይ አካውንት ያላቸው ሰዎች አሉ፡፡ በአንዱ አካውንቱ ፅፎ በአንዱ ላይክ ቢያደርግ ይሄ ላይክ ቁጥር መብዛቱ ዳዕዋውን ሃቅ አያሰኝለትም፡፡ ልክ እንደዛው በተለያየ አካውን ገብቶ ቢጨቃጨቅም አርስቱ ትክክል እስከሆነ ድረስ የዚህ ሰው እና መሰሎቹ መቃወም ምንም አይፈይድም፡፡ አላህ ውስጥ አዋቂ እውቀተ ረቂቅ ነውና፡፡

ሊረሳ የማይገባው ነብዩ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለምም) ከነብይነታቸው በፊት ‹‹ታማኙ ሙሃመድ›› ነበር ስማቸው፤ ልክ ተውሂድ ሲሉ ‹‹ድግምተኛ፤ እብድ፤ ገጣሚ....ሌሎችን›› ተባሉ፡፡ ቆም ብለን እናስብ ስራችንን የአላህን ፊት ብቻ ፈልገው ከሚሰሩት ያድርገን፡፡

የሃቅ ደጋፊዋ፤ አጋዧ፤ ረዳቷ አላህ ነው፡፡ ሃቅ በቁጥር አይለካም፤ ሰዎች በሃቅ ይለካሉ እንጂ፡፡

አላህ ሃቁን ይምራን፡፡ አላህ ሆይ! ሃቅን በሃቅነቱ አሳየን የምንቀበለውም አድርገን፤ ባጢልን በባጢልነቱ አሳየን የምንርቀውም አድርገን፡፡ የአላህ ሰላት እና ሰላም በነብያት ሁሉ መደምደሚያ፤ በቤተሰቦቻቸው፤ በባልደረቦቻቸው፤ ሃቅን በተከተለ ላይ ሁሉ ይሁን፡፡