Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

የሴቶችን ሰልፍ በተመለከተ ለአቡ ሁመይራ ሹብሃት የተሰጠ ምላሽ


Ibnu Munewor
 
የሴቶችን ሰልፍ በተመለከተ ለአቡ ሁመይራ ሹብሃት የተሰጠ ምላሽ
1. ((ያነገቡት ሀሳብ አሳማኝ እንዳልሆነ የሚያውቁ ሰዎች ብዥታ ለመፍጠር ሲሉ ሀሳባቸውን ከሌሎች ሀሳቦች ጋር ደባልቀው ያቀርባሉ፡፡ ያንተም ፅሁፍ ከዚህ አይለይም፡፡ የሴቶች መገላለጥና መሽሞንሞንን ደካማውን ሀሳብህን ለመደገፍ ተጠቅመህበታል፡፡ የሴቶች መገላለጥና በሜካፕ መጋጌጥ ለስላማዊ ተቃውሞ ስትወጣ ብቻ ሳይሆን በየትኛውም መልኩ የሚወገዝ ነው፡፡)) ብለሃል፡፡
መልስ፡- በመጀመሪያ የጠቀስኩት ነጥብ ይሄ ብቻ አይደለም፡፡ ከቻልክ አብረህ ብትመልሰው ጥሩ ነበር፡፡ ከዚያ ባለፈ ይሄን በየትኛውም መልኩ የሚወገዝ ተግባር ግን ይፋ የሚወጣበት ሁኔታ ማመቻቸት አያስፈልግም፡
2. ((ሰለማዊ ተቃውሞ ደግሞ ሸሪዐዊ መሰረት አለው)) ብለሃል፡፡
መልስ፡- ደሊል ጠየቅኩህ እኮ ወንድሜ፡፡ ካለህ ለምን አታሰፍረውም እስኪ ከቃላት ክሸና ባለፈ በጠየቅኩት መሰረት የማያሻማና ቀጥጠኛ የሆነ አንድ የጠቀስከውን ማስረጃ ንገረኝ
3. ((በርግጥ በዚህ ሹበሀ ውስጥ የሚገቡት አረብ ሀገር ያሉትና እንደ ገደል ማሚቱ በዋትስ አፕ የምትልኩላቸውን ይዘው የሚጮሁት ቁርዐን እንኳ አስተካክለው ያልቀሩት ሴቶች ናቸው)) ብለሃል፡፡
መልስ፡- ሱብሐነላህ!! ከናንተ ጋር ተሰልፈው የሚጮሁትስ ምሁራን ናቸው እንዴ? የት አል ያ የምታላዝኑበት ሒክማችሁ? እንደ ገደል ማሚቶ ጩኸታችሁን ሳያወራርዱ በአውሮፓ በአሜሪካ የሚያስተጋቡትንስ ምነው ረሳሃቸው?
4. ((ትግል ግብና ግቡን ማስፈፀሚያ (MEANS) አለው ፡፡በኢስላም የሚደረግ ትግል ግቡ ሁልጊዜም የአላህ ቃል የበላይ ለማድረግ መሆን አለበት ፡፡ ማስፈፀሚያ መንገዱ ግን እንደተጨባጩ ይለያያል… )) ብለሃል፡፡
መልስ፡- በመጀመሪያ ሸሪዐዊ ግብ ላይ ለመድረስ ሸሪአዊ መዳረሻዎችን መጠቀም እንደሚቻል ግልፅ ነው፡፡ ግና የተፈቀዱ መንገዶችን እንጂ ሐራም ነገሮችን አይደለም እንደመዳረሻ መጠቀም ያለብን፡፡ ሰልፍን እንደሚፈቀድ ማስፈፀሚያ ዘዴ ብንወስደው እንኳን መዳረሻ ዘዴዎችን በመጠቀም ረገድ የከፋ ወይም ካለው የማይተናነስ ጥፋት መድረስ የለበትም የሚል የታወቀ መስፈርት አለው፡፡ “ጥፋት ባምሳያው አይወገድም!!” “ጉዳቶችን መከላከል ጥቅሞችን ከማምጣት ይቀደማል” የሚሉት ሸሪዐዊ መርሆዎች በሰፊው የሚታወቁ ናቸው፡፡ እነኚህ መስፈርቶች መሟላት አለመሟላታቸውን ደግሞ ለሰልፍ የሚግተለተሉት የመሃይማን መንጋ ከስሜት ባለፈ መለካት የሚችል የግንዛቤ አቅም የለውም፡፡ እንዳውም በነዚህ ሸሪዐዊ መርሆዎች እንመዝነው ካልን ሰልፋችሁ ጥፋት እንጂ ልማት አላመጣም!! ለስንት ሰው መገደል፣ ለስንት መስጂዶች መነጠቅ፣ ለስንት ህዝብ ከጀመዐ ሰላት መከልከል፣ ለስንት ህዝብ እስር ቤት መታጎር፣ አካለ ጎደሎ መሆን፣ ወዘተ ሰበብ ሆኗል፡፡ አመክኗዊ የሚመስለው በቃላት የተከሸነ ትንታኔህ ቀድመው አቋም ይዘው ደሊል ፍለጋ የሚባዝኑትን ከማርካት ያለፈ ፋይዳ የለውም፡፡
5. ((በተጨማሪ የዛን ጊዜ ስርዐት ያለው ማዕከላዊ መንግስት ባለመኖሩ በዚህ መልኩ ሰላማዊ ትግል ማድረግ ትርጉም አይኖረውም ነበር )) ብለሃል፡፡
መልስ፡- በል እስኪ ሙሳ ከፊርዐውን ጋር ያደረጉትን ጦርነት ንገረን፡፡ ነው ያኔም ማእከላዊ መንግስት አልነበረም? እስካፍንጫው ከታጠቀ ሃይል ጋር በባዶ እጅ እያጨበጨቡ ወጥቶ አንድ ጥይት ወደ ሰማይ ሲተኮስ ሴቶችን እየረጋገጡ ነፍሴ አውጪኝ የሚበረገግበት ሰልፍ ነው የትግል ስልታችሁ? አንዋር መስጂድ ወይም ሌላ መስጂድ ሰልፍ ስታስቡ ጊዜ የኢማሙ አሕባሽ መሆን ሳያሳስባችሁ ከኋላው ተከትላችሁ ሰግዳችሁ ሰልፍ ብላችሁ አስቂኝ ድራማ ትሰራላችሁ፡፡ እሄው ስንት አመታችሁ በተነጠቁት መስጂዶች ውስጥ “አሕባሽ አንከተልም” በሚል ከመስጂዶች ርቃችኋል፡፡ ጁሙዐ የለ ጀማዓ የለ፡፡ እኔ “ተከተሉ አትከተሉ” ፈትዋ ልሰጥ አይደለም፡፡ ግን ምን ሲባል ነው በሰላት እቃቃ የምትጫወቱት? መከተሉ ካልተቻለ የሰልፍ ጊዜ ሰልፉ በሚደረግበት መስጂድ ያሉ ኢማሞችን ተከትላችሁ ለምን ትሰግዳላችሁ? ከአሕባሽ ኋላ የተሰገደ ሰላት ዋጋ ከሌለው ጁሙዐ ሳትሰግዱ እያዋላችሁ ነው ማለት ነው!! ተከትሎ መስገዱ ከተቻለ ይሄን ሁሉ ጊዜ ለስንት አመት የጀማዓ ሰላት አድማ የምታደርጉት በማን ፈትዋ ቡራኬ ነው?? እንዲህ አይነቱ ለሰላት ዋጋ የማይሰጥበት ትግል አፈር ድሜ ይብላ!! ደግሞ “ረሱል (ሰ.ዐ›ወ›) በቁረይሾች ሲደበደቡ አቡበከር ሲዲቅ ጌታዬ አላህ ነው በማለቱ ብቻ ልትገሉት ነው ብለው ማውገዛቸው በቂ ማስረጃ አይሆንም ?)” ብለሃል፡፡ ታዲያ አቡበክር ሲዲቅ ረዲየላሁ ዐንሁ ሰልፍ ነው እንዴ ያደረጉት? “አዎ” ከሆነ መልስህ ((የዛን ጊዜ ስርዐት ያለው ማዕከላዊ መንግስት ባለመኖሩ በዚህ መልኩ ሰላማዊ ትግል ማድረግ ትርጉም አይኖረውም ነበር ለማንስ ነበር አቤት የሚባለው?)) ያልከውን ዋጋ አያሳጣብህም? እናስ ታዲያ አቡበክር ለየትኛው መንግስት ነበር “አቤት” ያሉት?
6. ((በተጨማሪ የዛን ጊዜ ስርዐት ያለው ማዕከላዊ መንግስት ባለመኖሩ በዚህ መልኩ ሰላማዊ ትግል ማድረግ ትርጉም አይኖረውም ነበር ለማንስ ነበር አቤት የሚባለው ? ዛሬ ግን ማዕከላዊ መንግስት አለ፡፡ አለም አቀፍ ተቋማት አሉ ፡፡ ሚዲያ አለ ፡፡)) ብለሃል፡፡
መልስ፡- እስኪ የትኛው ማዕከላዊ መንግስት፣ ዐለም አቀፍ ተቋም፣ የትኛው ሚዲያ ነው የፈረንሳይን ፀረ-ሒጃብ ህግ ያስቀየረው? እስኪ የስንት ጊዜ ሰልፋችሁ ነው ፍሬ ያፈራው? እንዳውም መሬት ላይ ያለውን ጥላችሁ በስሜት ስለምትፈርዱ እንጂ ሰልፋችሁ እምቧይ ነው እያፈራ ያለው!!!
7. ((ጨቋኝ መሪ ፊት እውነትን መናገር ከጂሃድ ሁሉ በላጭ ነው)) የሚለውን ሐዲሡን አውርደሃል፡፡
መልስ፡- በመጀመሪያ ጥያቄው ስለሰልፍ ብቻ ነው፡፡ ለምን አራምባና ቆቦ እንደምትረግጥ አላውቅም፡፡ ነው ወይስ እኔን እንዳልከኝ ያነገቡት ሀሳብ አሳማኝ እንዳልሆነ የሚያውቁ ሰዎች ብዥታ ለመፍጠር ሲሉ ሀሳባቸውን ከሌሎች ሀሳቦች ጋር ደባልቀው ያቀርባሉ ልበልህ? ደግሞም ተናገር እስኪ ከአምባገነኖች ፊት መናገሩን ለሰልፍ ማስረጃ ካደረግከው ምነውሳ ታዲያ ሙስሊሞች በተታሮች ሲጨፈጨፉ ሰልፍ አልወጡም? ምነውሳ ቁርኣን ፍጡር ነው የሚለው የኩፍር ስርኣት በህዝቡ ላይ ሲጫን እነ ኢማሙ አሕመድ ሰልፍ አልቀሰቀሱም? ምነውሳ ትክክለኛውን የአህሉሱና ዐቂዳ ለማክሰም ባንድ ላይ ባሴሩ ሱፍዮችና የቢድዐ አጋሮቻቸው ሴራ ኢብኑ ተይሚያና ተማሪዎቻቸው ያ ሁሉ ግፍ ሲፈፀምባቸው ሰልፍ አልቀሰቀሱም? ነው ያኔም ማእከላዊ መንግስት ስላልነበረ ነው?
8. ((በረሱል (ሰ›ዐ›ወ.)ጊዜ ሴቶች ባሎቻችን እየመቱን ነው ሲሉ ተሰብስበው ሰሞታቸውን አሰምተዋል፡፡ ለመሪ ተበድለናል ማለት ከዚህ የተለየ አይመስለኝም፡፡)) ብለሃል፡፡
መልስ፡- ይሄ አባባልህ ማስረጃ መሆን መቻሉን ከማንም በፊት አንተ እራስህ እርግጠኛ አይደለህም!! “ከዚህ የተለየ አይመስለኝም” ማለትህን አስተውል!! እሺ ያኔ ሴቶች ያደረጉትን የተቃውሞ ሰልፍ እንደሆነ የሚገልፅ አንድ የሱና ዐሊም ጥቀስ፡፡ እንደማታመጣ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ግን እንዲያው ሰልፍ ነበር እንኳን ብንል እነሱ “አቤት” ያሉት ለነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ነው፡፡ አንተና የምትቀሰቅሳቸው ሴቶች “አቤት” የምትሉትስ ለማነው? አሁን ይሄ አይን ያወጣ መቀላቀል አይደለም?! ይሄ መቀላቀል ካልሆነ የመቀላቀል ትርጉሙ ምንድን ነው?
9. ((ስለ መቀላቀል እስኪ አንተኑ ልጠይቅህ የረሱል (ሰ.ዐ›ወ.)መስጂድ ውስጥ ሴቶችና ወንዶች እንዴት ነበር የሚሰግዱት ? እንዳሁኑ አጥር ተለይቶ አልነበረም ፡፡ፊትና ኃላ ነበሩ ፡፡ …)) ብለሃል፡፡
መልስ፡- በመጀመሪያ ዑለማዎች ሴቶችና ወንዶች ተለያይተው እንዲሰግዱ ማድረጋቸውን በግልፅ እየተቃወምክ ነው፡፡ ጎሽ የኛ ምሁር! ከዓሊሞቹ በላይ ዓሊም ለመሆን መጣርህ የሚደንቅ ነው!! የሚገርመው ከጎንህ ያሉት ያጨበጭቡልሃል እንጂ አያርሙህም፡፡ ከዚያ ባለፈ አይደለም ዛሬ ተኩላ በበዛበት ዘመን ቀርቶ እናታችን ዓኢሻ ረዲየላሁ ዐንሃ እንኳ ከነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ሞት ኋላ ከሴቶች በኩል የታዩ ለውጦችን ተመልክታ ይህን ሁኔታ ነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ቢያዩ ኖሮ ከመስጂድ ያግዷቸው ነበር ነው ያለችሁ፡፡ ለመሆኑ ትችትህ ወደሷም ይዞር ይሆን ታዲያ ያለውን ስጋት ተመልክተው ጥንቃቄዎችን መውሰዱ ሆነ የሚያስተቸው?
10. ((የረሱል ሚስት ሰፍያን ጀግንነት አልሰማህም እንዴ?)) ብለሃል፡፡
መልስ፡- አልሰማሁም!! የረሱል ሚስት ሰፍያ ከዚህ ጋር የሚያያዝ ማስረጃ ሊሆንህ የሚችል ምን አረገች? ማስረጃው ካለህ አትጠቅሰውም? የሰፍያ ቢንቲ ዐብዲልሙጠሊብን ረዲየላሁ ዐንሃ ልትጠቅስ ከሆነ በመጀመሪያ የሚቀላቅለው አንተ እንጂ እኔ እንዳልሆንኩ እመን፡፡ ደግሞ ያም ቢሆን ለሴቶች ሰልፍ ደሊል ሊሆንህ አይችልም፡፡ ሶፍያ “ሰልፍ ነው የወጣችው” የምትል ከሆነ ንገረኝ፡፡ “ጂሃድ ነው የወጣችው ስለዚህ ሴቶች ጂሃድ መውጣት ይችላሉ” የሚል ኢስላማዊ ብይን ልትሰጥ ከሆነ ((ሴቶች ውጊያ እንጂ ትግል አለተከለከሉም)) ያልከውን እያፈረስከው ነው፡፡
11. ((ውጊያ ላይ ተገኝተው በግጥም ያበረታቱ ነበር ፡፡ የቆሰሉትን ያክሙ ነበር ፡፡ የረሱል ሚስት ሰፍያን ጀግንነት አልሰማህም እንዴ ? )) ብለሃል፡፡
መልስ፡- ሰውየ ርእሳችን እኮ ሰልፍ እንጂ ሌላ አይደለም፡፡ እነሱ “ሰልፍ ነው ያደረጉት” ልትል ከሆነ ሹብሃ መንዛትህን ተውና በግልፅ ተናገረው፡፡ ደግሞ የመዲና ሴቶች ተግተልትለለው ሰልፍ ቀርቶ ጂሃድ አልዘመቱም!! ከሙስሊሙ ጦር ጋር የተገኙ ሰሐብያት ገድል ጂሃድ መዝመት እንደሚችሉ እማኝ ልታደርገው ከሆነ ((ሴቶች ውጊያ እንጂ ትግል አለተከለከሉም)) ያልከው ስህተት እንደሆነ እመን፡፡ ከዚያም ጂሃድ ሴቶችን እንደማይመለከት የሚያስረዱ ማስረጃዎችን ምን እንደምታደርጋቸው አስረዳን፡፡
12. ((ረሱልና (ሰ.ዐ.ወ.) ሰሀቦች ከተቡክ ዘመቻ ሲመለሱ “ጠለዐል በድሩ አለይና ..”እያሉ ሲቀበሏቸው መዲና በግንብ ተከፍላ ወንዶች በዛ ሴቶች በዚህ ሁነው ነበር እንዴ?)) ብለሃል፡፡
መልስ፡- በመጀመሪያ ለወንዶችና ለሴቶች መቀላቀል ደንታ እንደሌለህ አሳይተሃል፡፡ ለጋጠወጦችም ሹብሃ እያስታጠቅክ ነው፡፡ ከዚያ ባለፈ “ጠለዐል በድሩ አለይና ..” ይሉ ከነበሩት ውስጥ ወንዶች ለመኖራቸው ማስረጃ ማቅረብ ይጠበቅብሃል፡፡ ከተቡክ ዘመቻ የቀሩት አቅመ ደካሞች፣ ሴቶችና ሙናፊቆች ነበሩ፡፡ ሙእሚን ሆነው የቀሩት በጣት የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ እነሱም እንዲህ ባደባባይ ሊነሽዱ ቀርቶ ከጦርነቱ በመቅረታቸው ተሸማቀው ነው የተቀመጡት፡፡ ስለዚህ የገነባሃው ግንብ ከመሰረቱ ይናዳል፡፡ ቀድመህ አቋም ይዘህ ስለሆነ ደሊል ፍለጋ የምትባዝነው እንዲህ ዐይነት ትርምስ ውስጥ ትወድቃለህ፡፡ ምናልባት ድፍረትህ ሴቶች ሰሐብያት ከሙናፊቅ ጋር ተሰልፈው ሲነሽዱ ነበር እስከማለት እንደማይደርስ እጠብቃለሁ፡፡
13. ((በነገርህ ላይ ሴት ከቤቷ መውጣት የለባትም የሚል ጭብጥ ያለውን ሀሳብህን ላይክ እያረጉልህ ያሉት ያለ መህረም ከቤት ሳይሆን ከሀገር ወጥተው አረብ አገር ባዕዳን ጋር እየሰሩ ያሉ ናቸው ፡፡በነካ እጅህ እሰኪ ኑ ወደ ቤታችሁ ተመለሱ በላቸው ፡፡)) ብለሃል
መልስ፡- አንደኛ አትዋሽ!! እነሱ ብቻ አይደሉም!! በዐረብ ሀገር ስለኖሩ የኔን ፅሁፍ “ላይክ” በማድረግ ምን የሚያገኙት ዱንያዊ ጥቅም አለ? ሁለተኛ የናንተን ሀሳብ የሚጋሩም ያለ መህረም ወጥተው ባዕዳን ጋር እየሰሩ ያሉ ብዙ አሉ በዐረቡም በካፊሩም ዓለም፡፡ ለምን ዐረብ ሀገር ያሉት ላይ እንዳነጣጠርክ አላውቅም!! ነው ወይስ በሌላ ሀገር ያሉት የናንተን ሀሳብ ስለሚጋሩ ገንዘብ ለመሰብሰብ እንጂ ጥፋትን ለማስጠንቀቅ ሲሆን ከነመኖራቸውም ትዝ አይሏችሁም፡፡ የናንተን ሀሳብ ስላልተጋራ ብቻ ሙስሊምን በዚህ መልኩ ማብጠልጠል እውነት መቆርቆር ነው? እስኪ እኔም ልጠይቅህ በነካ እጅህ አልከሶ አብሬት ለሺርክ መመላለሱ ክልክል እንደሆነ እስኪ ቢያንስ ለሰልፍ የምትቀሰቅሱትን ያክል ቀስቅሱ፡፡ በአሜሪካ፣ በአውሮፓ፣ በዐረብ ሀገር ገንዘብ ለመሰብሰብ የምትወተውቱትን ያክል እንኳን እስኪ ስለተውሒድ አስተምሯቸው፡፡ አብረዋችሁ የሚወጡ ሴቶችንም ፖሊስ ሲመጣ እየረጋገጣችሁ ለማለፍ መቀስቀሳችሁን እምቢ ብትሉ እንኳን እስኪ ቢያንስ አለባበሳቸውንም እንዲያስተካክሉ ንገሯቸው፡፡ ደግሞም ያንተንም ፅፍ “ላይክ” ካደረጉት ውስጥ በግልፅ ለሺርክ የሚሟገቱ አሉ፡፡ ለሰልፍ ከመጮሃችሁ በፊት እነሱን ዘላለማዊ ክስረትን ከሚያላብሰው ሺርክ መልሷቸው፡፡ እግረ መንገዴን በዐረብ ሀገራት የናንተን ተንኮል የነቁ ሴቶች መኖራቸውን ስለነገርከኝ አመሰግናለሁ፡፡
14. በጥቅሉ ካንተም ከሌሎችም ስለጂሃድ የሚያትቱ ማስረጃዎችን ለሰልፍ እያጣቀሳችሁ ሌሎችን ጂሃድ እንደተቃወሙ እያቀረባችሁ ነው፡፡
እስኪ ነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ከሰሐቦቻቸው ጋር ወደ መዲና ከመሰደዳቸው በፊት የተደረገ አንድ ጦርነት ካለ ጠቁመን፡፡ ወደ መዲና ከተሰደዱም በኋላ መስፈርቱን ያሟላ እውነተኛ ጂሃድ እንጂ በቆመጥ የሚበተን ሰልፍ አይደለም ያደረጉት፡፡ ለመሆኑ ስለ ጂሃድ የሚያትቱ አያዎችን ለሰልፍ ማስረጃ በመደርደር ከሰልፍ የሚቀሩ ሰዎችን ከጂሃድ እንደሚቀሩ በመውቀስ የቀደማችሁ አንድ የሱና ዐሊም ይኖር ይሆን? በል እስኪ ሙሳ ከፊርዐውን ጋር ያደረጉትን ጦርነት ንገረን፡፡ እስካፍንጫው ከታጠቀ ሃይል ጋር በባዶ እጅ እያጨበጨቡ መውጣት ነው ጂሃዱ? የጂሃድ ስልቱ ከጊዜ ጊዜ ስለሚቀያየር ሰልፍን እንደመረጣችሁ እየነገርከን ነው፡፡ መልካም፡፡ እስኪ ከሂጅራ በፊት የነበረው ትግል ምን ነበር? ከደዕዋና ከሰብር ያለፈ ነገር ልትጠቅስ ትችላለህ? በፊርዐውንስ ላይ የተነሳው የትግል ስልት ምን ነበር? ያንንስ የነብያት ስልት ዛሬ መጠቀሙ ለጠላት እንደ ማበር የሚቆጠረው በምን ሂሳብ ነው?
15. ዐልይ ኢብኑ አቢ ጣሊብ “በትክክለኛ የኢስላም ጎዳና ላይ ማን እንዳለ ማወቅ ከፈለግክ የጠላቶች ቀስት ወደሚወረወርበት አቅጣጫ ተመልከት” ብሏል በማለት ያላችሁበትን አቋም ትክክለኛነት ለማሳመን ጠቅሰሃል፡፡
መልስ፡- ስለዚህ አንተ ሐቅ ላይ እንዳለህ ለማሳየት በጠቀስከው አባባል እንመዝን፡፡ ዛሬ ሱፍዩም፣ ሺዐውም፣ አሽዐሪውም፣ ተክፊሩም፣ ኢኽዋኑም፣ ተብሊጉም … በመካከላቸው ያለውን ልዩነት ችላ ብለው ከማንም በላይ የሚያጠቁት የሰለፍያ ደዕዋን ነው፡፡ ስለዚህ ባሰፈርከው መስፈሪያ መሰረት ማነው ሐቅ ላይ ያለው? ማስረጃዎችን እየጠመዘዙ ለከንቱ አላማ ማዋል የስሜት ተከታዮች ልዩ መገለጫ ነው፡፡ ለዚህም እኮ ነው ዐልይ ኢብኑ አቢ ጣሊብ “ፍርድ ለአላህ ብቻ ነው” በሚል ቁርኣናዊ መልእክት እሱንና ባልደረቦቹን ያከፈሩ ኸዋሪጆችን “ለባጢል ታስቦ የተነገረ እውነተኛ አባባል ነው” የሚል ወርቅ ንግሩን ጥሎ ያለፈው፡፡ የጠላት ጥቃት የተደራረበበት ሁሉ ሐቅ ላይ ከሆነ “አልቃኢዳህ” ላይ ምእራቡ ባጠቃላይ ዘምቶበታል፡፡ ስለዚህ ሐቅ ላይ ነው እንበል? “አዎ” ካልክ ምነውሳ ባዶ እጅህን እያወዛወዝክ በቆመጥ ከምትበተን እንደነሱ አታፈነዳም?!!!
16. ((ይህ ጭፍን ጥላቻችሁ የትሊደርስ ይሆን በኢስላም አስተምሮ ሴት የሚለው ስያሜ የድክመት ምልክት መሆኑን…)) እያለ አንዱ ለቅልቋል፡፡
መልስ፡- እስኪ ማነው በኢስላም አስተምሮ ሴት የሚለው ስያሜ የድክመት ምልክት ነው ያለው? አሁን ይሄ ከደሊል ይልቅ ሴቶችን በስሜት ለማሰለፍ እንደምታቆበቁቡ አያሳይም?!! የሴት ሰሐብያትን ገድል እያጣቀሱ ለሰልፍ ከቀሰቀሱ በኋላ ቆመጥ ሽሽት ሴቶችን እየረጋገጡ ማለፍ ነው ለሴቶች ዋጋ መስጠቱ? “ብርጭቆዎች ናቸው በጥንቃቄ ይያዙ” ያሉት እኩ መልእክተኛው ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንጂ እኛ አይደለንም? እንዲህ አይነቱ ቅስቀሳ ሴቶችን በእጅ አዙር በዲናቸው እንዲያዝኑ ከማድረግ ያለፈ ፋይዳ የለውም፡፡