Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

አላህን ከአምሳያና ከጉድለት ማጥራት ‘ተንዚህ’ በአህሉሱና እና በአህባሾች እይታ



አላህን ከአምሳያና ከጉድለት ማጥራት ‘ተንዚህ’ በአህሉሱና እና በአህባሾች እይታ---------------------------------------------------------------------አቡጁነይድ ሳላህ አህመድ
www.nesiha.org----------------------------------------------------------------------
አህሉሱና የአላህን ባህሪያት ከአምሳያና ከጉድለት ማጥራት “ተንዚህ”ን በተመለከተ ያላቸው አቋም በሁለት መሰረቶች ላይ የተገነባ ነው። አላህን ከአምሳያ ማጥራት (ነፍዩል ሙማሰላህ)፡- አላህን ከፍጥረታት ምንም ነገር በምንም አይነት ባህሪ አይመስለውም፤ አላህም ከፍጥረታቱ ምንንም አይመስልም። አላህን ከጉድለት ማጥራት (ነፍዩ-ነቃኢስ)፡- አላህ ጉድለትን ከሚያመላክቱ ባህሪያት ሁሉ የጠራ ነው። ማንገላጀት፣ እንቅልፍ፣ አቅም ማጣት እና አለማወቅን ከመሳሰሉ የጉድለት ባህሪዎች ሁሉ የጠራ ነው።
ይሁንና፤ አብዛኛዉን ጊዜ በቁርአን ላይ ‘አላህን ከጉድለትና ከመመሳሰል ማጥራት’ ጥቅል በሆነ መልኩ የሚቀርብ ሲሆን፤ የአላህን ባህሪያት ማጽደቅ ግን በዝርዝር ሲቀርብ እናገኛለን። ተከታዮቹ አንቀጽ ይህንን መርሆ በጉልህ ያሳያል፤
لَيْسَ كَمِثْلِهِ شَيْءٌ وَهُوَ السَّمِيعُ الْبَصِيرُ - الشورى: ١١
‹‹የሚመስለው ምንም ነገር የለም፡፡እርሱም ሰሚው ተመልካቹ ነው፡፡» (አል ሹራ 11)
ይህ አንቀፅ የሚያስረዳው በየትኛውም ሁኔታ በፍጡራንና በፈጣሪ መካከል መመሳሰል እንደሌለና አላህ ሰሚና ተመልካች መሆኑን ነው፡፡ መስሚያና መመልከቻ የብዙ ፍጡራን መገለጫዎች ቢሆኑም ነገር ግን የአላህ መስሚያና መመልከቻ ከፍጡራኑ ጋር አይመሳሰልም፡፡ በመስሚያና በመመልከቻ አምሳያ እንዳሌለው ሁሉ በሌሎችም ባህሪያቱ አምሳያ የለውም፡፡
አንቀጹ የጉድለት ባህሪዎችን ጥቅል በሆነ መልኩ ዉድቅ ሲያደርግ ምሉዕ ባህሪዎችን ግን በዝርዝር ያጸድቃል። ይህ አንቀጽ ሙስሊሞች ለአላህ የማይገቡ ባህሪያትን ከመረዳት አንጻር ሊኖራቸው ለሚገባው ትክክለኛ አካሄድ መርሆን ይቀርጻል። ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው ሌሎች አንቀጾችም ይገኛሉ።
= አላህ እንዲህ ብላል፦
فَلَا تَضْرِبُوا لِلَّهِ الْأَمْثَالَ إِنَّ اللَّهَ يَعْلَمُ وَأَنْتُمْ لَا تَعْلَمُونَ - النحل: ٧٤
“ለአላህም አምሳያዎችን አታድርጉ አላህ ያውቃል፤ እናንተ ግን አታውቁም” (አነህል 73) አል ኢማም አጦበሪይ ይህን አንቀፅ በማብራራት እንዲህ ብለዋል፤
" فلا تمثلوا لله الأمثال ولا تشبهوا له الأشباه فإنه لا مثل له ولا شبه "
“አምሳያም ቢጤም የለውምና ለአላህ አምሳያና ቢጤ አታድርጉ” ተፍሲሩ ጦበሪ 7/621
= አላህ እንዲህ ብላል፦
(وَلَمْ يَكُنْ لَهُ كُفُوًا أَحَدٌ) الإخلاص: ٤
«ለእርሱም አንድም ብጤ የለውም» (አል ኢኽላስ 4)
ታላቁ የቁርአን ተንታኝ አል ኢማም አጦበሪይ እንዲህ ብለዋል:
" ولم يكن له شبيه ولا عدل وليس كمثله شيء "
‹‹አምሳያም አቻም የለውም እንደ እርሱ አምሳያ ምንም የለም፡፡››
= አላህ እንዲህ ብላል፦
هَلْ تَعْلَمُ لَهُ سَمِيًّا - مريم: ٦٥
«ለእርሱ ሞክሼን ታውቃለህን» (መርየም 65)
ኢብኑ ዓባስ ይህን አንቀፅ ሲያብራሩ እንዲህ ይላሉ:
" هل تعلم للرب مثلًا أو شبيهًا "
“ለአላህ አምሳያ ወይም ቢጤን ታውቃለህን?”
አህሉሱና የአላህን ባህሪዎችን ሲቀበሉና ሲያጸድቁ ከፍጡራን ባህሪዎች ጋር ምንም እንደማይመሳሰሉ ቀድመው ያምናሉ። ከላይ በተመለከተው ቁርአናዊ አካሄድ መሰረት ለአላህ ባህሪያትን በዝርዝር ማጽደቅና ጉድለትና መመሳሰልን በጥቅሉ ውድቅ ማድረግ አህሉሱና ከጥንት ጀምሮ የተጓዙበት አቅጣጫ ነው። እንደ አህባሾች በዚህ ፍጥረተ ዓለም ዉስጥ የሚገኙ ፍጥረታትን እና ባህሪዎቻቸውን በዝርዝር በማውሳት “አላህ ሰማይንና ምድርን አይመስልም፣ ጸሀይንና ጨረቃንም አይመስልም፣ ሰዉንና መላኢካን አይመስልም… ወዘተ” በማለት ዝርዝር የማነጻጸር አካሄድን አይከተሉም። በእርግጥ ለተለያዩ ምክኒያቶች በቁርአንና በሀዲስ ለአላህ እንደማይገቡ የተነገሩና በዝርዝር ውድቅ የተደረጉ አንዳንድ ባህሪዎችን እናገኛለን። በቅድሚያ ጥቂቶቹን እንመልከት እና መረጃዎቹ ምን እንደሚያመላከቱ እንገልጻለን። መመሳሰልን እና የጉድለት ባህሪዎችን በዝርዝር ዉድቅ በማድረግ ለአላህ የተገቡ ምሉእ ባህሪዎችን ከሚያጸድቁ ቁርዓናዊና ሀዲሳዊ መረጃዎች መካከል፤
قوله تعالى: وَتَوَكَّلْ عَلَى الْحَيِّ الَّذِي لا يَمُوتُ - الفرقان: 58
«በዚያም በማይሞተው ‘ሕያው’ አምላክ ላይ ተመካ፡፡» አልፉርቃን 58
اللَّهُ لا إِلَهَ إِلَّا هُوَ الْحَيُّ الْقَيُّومُ لا تَأْخُذُهُ سِنَةٌ وَلا نَوْمٌ - البقرة : 255
«አላህ ከእርሱ በቀር በሀቅ የሚመለክ ሌላ አምላክ የለም፡፡ ሕያው ራሱን ቻይ ነው፡፡ ማንገላጀትም እንቅልፍም አትይዘውም፡፡» አልበቀራህ 255
لما رفع بعض الصحابة أصواتهم بالتكبير وهم معه في السّفر قال رسول الله ه: "أيها الناس ارْبعُوا عَلَى أَنْفُسِكُمْ فَإِنَّكُمْ مَا تَدْعُونَ أَصَمَّ وَلَا غَائِبًا إِنَّمَا تَدْعُونَ سَمِيعًا بَصِيرًا ..." رواه البخاري ومسلم
የአላህ መልዕክተኛ ه በጉዞ ላይ እያሉ አንዳንድ ባልደረቦቻቸው ድምጻቸውን በጣም ከፍ አድርገው ተክቢር ሲያደርጉ እንዲህ ብለዋቸዋል፦ «እናንተ ሰዎች ሆይ! ለነፍሳችሁ እዘኑላት፤ እናንተ የምትጣሩት የማይሰማን አምላክ አይደለም፤ እሩቅም አይደለም። የምትጣሩት፤ ሰሚና ተመልካች የሆነውን አምላክ ነው።» ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል
እነዚህ እና መሰል አንቀጾች፤ ከላይ የተመለከተዉን “በጥቅል ዉድቅ የማድረግ እና በዝርዝር የማጽደቅ” ቁርአናዊ አካሄድና መርሆ የሚጻረሩ አይደሉም። ምክኒያቱም፤ እነዚህን የጉድለት ባህሪዎች በዝርዝር ውድቅ የማድረግ አላማ የእነርሱን ተቃራኒ ምሉዕ ባህሪያት ለአላህ ማጽደቅ ነው። ለምሳሌ፤ አላህ እንቅልፍ እና ማንገላጀት እንደማይዘው መግለጹ፤ በውስጡ ያዘለው፤ የተሟላ ህያዉነት “ሀያት” እና ነገሮችን ሁሉ ማስተናበር “ቀዩሚያህ” አላህ የሚገለጽባቸው ባህሪያት መሆናቸውን ነው። አንድን ባህሪ ዉድቅ ስናደርግ የዚያን ባህሪ ተቃራኒ በተሟላ መልኩ ለአላህ እናጸድቃለን። አህሉሱና ዘንድ፤ ዉድቅ የሚደረጉ ባህሪዎች ሁሉ በተቀራኒ ምሉእነትን የሚያመላክቱና መልካም ባህሪዎችን ባማረ መልኩ የሚያጸድቁ መረጃዎች ናቸው። ስለዚህ፤ እነዚህ በዝርዝር ዉድቅ የተደረጉ የጉድለት ባህሪያት በተዘዋዋሪ መልካም ባህሪያትን በዝርዝር የማጽደቅ አካል ናቸው። በቁርአን እና በሀዲስ ውድቅ የተደረጉ የጉድለት ባህሪዎችን በተመለከተ ትክክለኛው የአህሉሱናም አቋም ይኸው ነው።
ስለዚህ፤ በቁርአን ላይ ወጥነት ባለው መልኩ ተቀርጾልን የምናገኘው አካሄድ እና መርሆ “አላህን ከአምሳያና ከጉድለት በጥቅሉ ማጥራት እና የአላህን ባህሪያት በዝርዝር ማጽደቅ” ነው።
የጃሂሊያ ሰዎች፤ “መላዕክት የአላህ ልጆች ናቸው” ሲሉ፤ አላህ ይህ አይነቱ ባህሪ ለእርሱ እንደማይገባው ገልጿል፤ በአየቱል ኩርሲይም ህያውነቱን በመግለጽ እንቅልፍ እና ማንገላጀት እንደማይዘው ገልጿል፤ ሰማያትና ምድርን በመፍጠሩ ድካም እንዳልነካው ተናግሯል። አህሉሱና ይህንን ተቀብለው ለአላህ እንደማይገቡ በማረጋገጥ እና በተቃራኒው ምሉእ የሆኑ መልካም ባህሪዎችን በማጽደቅ ብቻ ይቆጠባሉ። ልጅ እንደሌለው ስለተገለጸ፤ አባትም የለዉም፣ እናት የለዉም፣ ወንድም የለዉም...ወዘተ የሚል አካሄድ የላቸውም። አህባሾች ግን ለመስማት በሚቀፍ አገላለጽ ብዙ ፍጥረታትን እና ባህሪዎቻቸዉን በመደርደር “አላህ ይህንን አይመስልም ያንንም አይመስልም” ይላሉ። ለምሳሌ፤ አላህ መላእክትን አይመስልም፣ ጂንንም አይመስልም፣ሰው አይመስልም፣ አካል አይመስልም፣ ብርሀንን፣ድንጋይን፣ ዛፍን አይመስልም…ወዘተ በማለት ደጋግመው መናገራቸው የተለመደ ነው። ሸይኻቸው አብዱላህ አልሀረሪ “አሸርሁል ቀዊም” በሚለው መጽሀፉ ገጽ 107 / “አሲራጡልሙስተቂም ገጽ 28 እና በብዙ ጽሁፎቹ ይህን አይነት ዝርዝር አስቀምጧል። “አልዓቂደቱል ኢስላሚያህ” በሚል ርዕስ ባቀረበው ሙሀደራ እንዲህ ብሎ ነበር፤« በቁርአን እንደመጣው፤
ليس كَمِثْلِهِ شَيْءٌ وَهُوَ السَّمِيعُ الْبَصِير - الشورى: ١١
‹‹የሚመስለው ምንም ነገር የለም፡፡እርሱም ሰሚው ተመልካቹ ነው፡፡» (አል ሹራ 11)
የአንቀጹ ትርጉም፤ አላህን ከፍጥረታት ምንም የሚመስለው የለም፣ከባድ አካልም ይሁን ቀላል አካል አይመስለዉም፣አላህ ሰውን አይመስልም፣መላእክትንም፣ መንፈስንም፣አይመስልም፣ብርሀንንም ይሁን ጨለማን አይመስልም፣ ተጨባጭ ከሆኑ ግዑዝ አካላትም እንደ ድንጋይ እና ዛፍንም አይመስልም»
ይህ አካሄድ ከላይ ለመመልከት የሞከርነዉን ቁርአናዊ አካሄድ የሚጻረር የጥመት መንገድ መሆኑ የሚያጠራጥር አይደለም። ውድ አንባቢ፤ አንድ ሰው ሊያወድስህ እና ሊያሞካሽህ አስቦ፤ “አንተ እኮ ሌባ አይደለህም፣ ማጅራት መቺ ቀማኛም አይደለህም” ቢልህ ደስታን ይፈጥርልሀልን? በእርግጠኝነት መልስህ የሚሆነው “እንዲህ አይነቱ ሰው ተገቢዉን ክብር አልሰጠኝም የሚል ነው”። ሀቅን ከመረዳት ቢድዓና ፍልስፍናዎች አይምሮዉን ለበረዙት ሰው ካልሆነ በቀር ይህ ግልጽ ነገር ነው። የሰይፍን ስለታማነት ለማድነቅ ከዱላ ጋር ያነጻጸረ በተቃራኒው ዱልዱምነቱን እየገለጸ ለመሆኑ አያጠራጥርም። አላህ ከጥፋት እና ከመደናበር ይጠብቀን። ምስጋና ለሀያሉ አላህ የተገባ ነው።

Post a Comment

0 Comments