Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ታላቁ የሐዲሥ ፈርጥ ከአውሮፓዊቷ አልባኒያ ምድር


“በዚህ ዘመን ከሰማይ በታች እንደ ታላቁ ዓሊም ሙሐመድ ናሲሩዲን አል አልባኒ ሐዲሥን የተገነዘበ አላውቅም፡፡” የቀድሞው የሰዑዲያ ጠቅላይ ሙፍቲ ሸይኽ ዐብዱል ዐዚዝ ኢብኑ ባዝየዘመናቸው ምሁራን አላህ በየክፍለ ዘመኑ ዲኑን እንዲያድሱ ከሚልካቸው የለውጥ ሰዎች አንዱ እንደሆኑ ያምናሉ፡፡ በሐዲሡም በፊቅሁም መስክ የነጠረ እውቀት ያካበቱ ለመሆናቸው ሁለት ሚዛናዊ ሰዎች አይወዛገቡባቸውም- ሸይኽ ሙሐመድ ናሲሩዲን አል አልባኒ ረሒመሁላህ፡፡ሸይኽ አልባኒ በ1332 ዓመተ-ሂጅሪያ (1914 እ.ኢ.አ) በወቅቱ የአልባኒያ ዋና ከተማ በነበረችው አሽቆድራ ተወለዱ፡፡ ቤተሰባቸው ድሃ ግን ኢስላማዊ ድባብ ያከበረው ነበር፡፡ አባታቸው ሐጂ ኑሕ ከኢስታንቡል የሸሪዐ ተቋም የተመረቁ ሲሆኑ በአካባቢያቸው እውቅ የሐነፊያ መዝሀብ አስተማሪ ነበሩ፡፡በአልባኒ የልጅነት ዘመን ሀገራቸው አልባኒያ አሳዛኝ በሆነ ታሪካዊ ቀውስ ውስጥ ወደቀች፡፡ በጊዜው የሀገሪቱ መሪ የነበረው አህመድ ዘውጉ ሀገሪቱን መርዛማ ዝገት አለበሳት፡፡ ሀገሪቱ የምትከተለውን ሸሪዐዊ ስርዓት ወደኋላው አሽቀንጥሮ በመጣል ምእራብ-ወለዱን የክህደት ስርዓት/ሴኩላሪዝም የሀገሪቱ ስርዓት አድርጎ አወጀ፡፡ የዚህን ጊዜ ነበር የሸይኽ አልባኒ አባት ሐጂ ኑሕ ከነቤተሰባቸው ኩፍርን ሸሽተው ሂጅራ የደረጉት - እትብታቸው ከተቀበረበት አልባኒያ ወደ ደማስቆ ሶሪያ፡፡ ለአላህ ሲባል የተከፈለ ታላቅ መስዋእትነት! “እራሳችሁንም ቤተሰባችሁንም ከእሳት አድኑ” አይደል መለኮታዊ ትእዛዙ?! ሸይኽ አልባኒ ይሄንን ያባታቸውን ውለታ እንዲህ ሲሉ ደጋግመው ያነሱት ነበር፡፡ “ጌታየ በኔ ላይ የዋለውን ፀጋ ቆጥሬ አልዘለቀውም ምናልባትም ከዋለልኝ ፀጋዎች ሁሉ ትልልቆቹ የአባቴ ወደ ሻም መሰደድና የሰዓት ጥገና ሙያውንም ለኔ ማስተማሩ ነው፡፡ሸይኽ አልባኒ በደማስቆ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በከፍተኛ ውጤት ቢያጠናቅቁም መደበኛው ትምህርት የአባታቸው ፍላጎት አልነበረምና ሳይገፉበት ቀርተዋል፡፡ ይሁን እንጂ በቁርኣን፣ በተጅዊድ፣ በነሕው እና በሶርፍ እንዲሁም ፊቅህ በሐነፍያ መዝሀብ አጠናክረው ቀጠሉ፡፡ ቁርኣንን ካባታቸው ላይ ያፈዙት ሸይኽ አልባኒ የሰዓት ጥገና ሙያንም በሚገባ ከሳቸው ቀስመዋል፡፡ በሙያውም ታዋቂ ከመሆናቸውም በላይ በሀይል እየጨመረ ለመጣው ዲናዊ ትጋታቸው ጊዜ እንዲኖራቸው አስችሏቸዋል፡፡የሐነፊያን መዝሀብ አጥብቀው የሚከተሉትና ከሱ ውጭ ግራ ቀኝ ማየት የማይፈልጉት የሸይኽ አልባኒ አባት ልጃቸውም በዚሁ ፈለግ እንዲጓዝ ካላቸው ፍላጎት የተነሳ በሐዲሥ ጥናት ላይ እንዳይሰማሩ ጠንካራ ማስጠንቀቂያ ሰጥተው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የአንድን መዘሀብ ጭፍን ተከታይነት በፅኑ ለሚያወግዙት ሸይኽ አልባኒ -የመዝሀቦቹን መሪዎች ከማክበራቸውም ጋር- ይሄ ነገር ፈፅሞ የሚዋጥላቸው አልሆነም፡፡ ገና በሀያ ዐመታቸው አካባቢ ነበር የሐዲሥ ጥናታቸውን አፋፍመው የጀመሩት፡፡ ለዚህም በሸይኽ ሙሐመድ ረሺድ ሪዷ ይዘጋጅ የነበረው “አልመናር” መፅሄት ለጥናታቸው ፈር-ቀዳጅ እንደሆናቸው ይነገራል፡፡ ለጥናታቸው አጋዥ የሆኑ ኪታቦችን አቅማቸው በፈቀደ እየገዙ ከዚህ ባለፈም ደማስቆ ከሚገኘው “አዟሂሪያ” ቤተ-መጻህፍት እየተዋሱ ይጠቀሙ ነበር፡፡ በጥናታቸው በገፉ ቁጥር ሱቃቸውን እየዘጉ ሰፊ ጊዚያቸውን በቤተ-መጻህፍቱ ማሳለፉን ተያያዙት፡፡ ትጋታቸውን ያስተዋሉት የቤተ-መጻህፍቱ ሀላፊዎችም ባሰኛቸው ጊዜ መጠቀም ይችሉ ዘንድ አንድ ልዩ ክፍልና የቤተ-መጻህፍቱን ቁልፍ በማስረከብ የማይረሳ እገዛ አድርገውላቸዋል፡፡ የዚህን ጊዜ ሸይኽ አልባኒ ከሶላት ውጭ ከማለዳ እስከ ዒሻ በኋላ ቤተ-መጻህፍቱን ቤታቸው አደረጉት፡፡የተውሒድና የሱናን ባንዲራ ሶሪያ ምድር ላይ ለረጂም ጊዜ ያውለበለቡት ሸይኽ አልባኒ ከተቀናቃኞቻቸው ጋር በዐቂዳ፣ በኢቲባዕ (ረሱልን ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም በመከተል)፣ በመዝሀብ ጭፍን ተከታይነትና በቢድዐ ዙሪያ በርካታ ውይይቶችን አድርገዋል፡፡ በሂደቱም በመዝሀብ ጭፍን ተከታዮችና በሱፍያ ሸይኾች ቀስቃሽነት ብዙ ፈተና ደርሶባቸዋል፡፡ በተመሳሳይ ጊዜ ደማስቆ ውስጥ ከሚገኙ ስመ-ጥር ዓሊሞች በአቋማቸው እንዲገፉ ያላሰለሰ ማበረታቻ ከጎናቸው ነበር፡፡የኋላ ኋላ በርካታ ስራዎቻቸው ለህትመት ሲበቁ በዝነኛው የመዲና ኢስላማዊ ዩኒቨርሲቲ አስተማሪ ሆነው ተመርጠው ለሶስት ዓመታት አገልግለዋል፡፡ ከሶስት ዐመታት በኋላም ወደ ቀድሞው ስራቸው የተመለሱ ሲሆን ሱቃቸውን ለአንድ ወንድማቸው በመተው ሙሉ ለሙሉ ትኩረታቸውን ወደ ጥንታዊው የ“አዟሂሪያ” መክተባ አደረጉ፡፡ኢማሙል አልባኒ ምንም እንኳ ከፖለቲካ የራቁ ቢሆኑም በተለያዩ ጊዜያት መንግስት በዐይነ-ቁራኛ ይከታተላቸው ነበር፡፡ሁለት ጊዜም ለእስራት ተዳርገዋል፡፡ የመጀመሪያው የ 1967ቱ ዐረብ-“ኢስራኢል” ጦርነት ከመከፈቱ ቀደም ብሎ ሲሆን የታሰሩትም ደማስቆ ውስጥ ቀድሞ ኢብኑ ተይሚያ ረሒመሁላህ ከታሰሩበት ወህኒ ቤት ነው፡፡ በሁለተኛ እስራታቸው ከታላላቅ ዐሊሞች ጋር የተገናኙ ሲሆን በእስራት ላይ እያሉም የሙንዚሪን “ሙኽተሶር ሶሒሕ ሙስሊም ‘ተሕቂቅ' አድርገዋል፡፡ሙሐዲስ አልባኒ ለደዕዋ ስራ ወደተለያዩ ሀገራት የተዘዋወሩ ሲሆን ከነዚህም ኳታር፣ ግብጽ፣ ኩዌት፣ ዐረብ ኢማራት፣ አውስትራሊያ፣ እንግሊዝና ስፔን ተጠቃሽ ናቸው፡፡ለሐቅ ባላቸው ፅኑ አቋምና ለለውጥ ባላቸው የማይታጠፍ ተጋድሎ የሚታወቁት ሸይኹል አልባኒ ውጫዊ የአመለካከት ወራሪዎችን ብቻ ሳይሆን የኢስላምን ውበት ያደበዘዙ ውስጣዊ ወራሪዎችንም በመዋጋት ፋና-ወጊ ነበሩ፡፡ ሸይኽ አልባኒ ለ“ተስፊያ”ና “ተርቢያ” ማለትም ኢስላምን ከቢድዓ፣ ከሺርኪያት፣ ከደካማ ማስረጃዎችና ሰርጎ-ገብ አመለካከቶች ማፅዳት ከዚያም ትውልድን በሶሐቦች ጊዜ እንደነበረው በቁርኣንና በሶሒሕ ሱና ኮትኩቶ ማውጣት አካሄድ ልዩ ትልቅ ትኩረት ይሰጡ ነበር፡፡ ከግማሽ ክፍለ-ዘመን በላይ የተጓዙበትን ይህን አካሄዳቸውን በርካቶች እንዲያጤኑበትና እንዲሄዱበት ያላሰለሰ ጥረት አድርገዋል፡፡ ሸይኹ ህዝብን ለማስደሰት ሲባል አንዳንዶች የሚያደርጉትን ፊቅሃዊ የተልፊቅ(ያለጠንካራ ማስረጃ ከየመዝሀቡ ገር ገሩን የመምረጥ) ፖሊሲን በፅኑ ያወግዙ ነበር፡፡ በመልካም በማዘዝና ከመጥፎ በመከልከል ጉዳይ ጠንካሮች ዘንድ ጠንካራ ደካሞች ዘንድ “ለስላሳ” የመሆን እስስታዊ ባህሪ አልነበራቸውም፡፡ ለኡማው አንድነት እጅግ የሚጨነቁት አልባኒ ለአንድነት የሚደርገው ጥረት ፍሬ ያፈራ ዘንድ ከባዶ የ”አንድ እንሁን” ጩኸት ባለፈ የግድ ወደ ቁርኣንና ሱና መመለስ እንደሚያስፈልግ አበክረው አሳስበዋል፡፡ሸይኽ አልባኒ በጠንካራ የሰለፊያ አቋማቸው የተነሳ ብዙ ሰቃይና እንግልት ደርሶባቸዋል፡፡ ለኢስላም ሲባል ከአልባኒያ የተጀመረው ስደት ደማስቆን መጨረሻው አላደረገም፡፡ በተለያዩ ጫናዎች ምክኒያት ከሶሪያ ወደ ዮርዳኖስ፣ ከዮርዳኖስ ዳግም ወደ ሶሪያ፣ ከዚያም ወደ ሊባኖስ፣ ከዚያም ወደ ዐረብ ኢማራት፣ በመጨረሻም ወደ ዮርዳኖስ ዐማን ተንከራተዋል፡፡የነቢዩን ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ሐዲሶችን ደረጃ በማጣራትና በመልእክተኛው ስም የሚወሩ መሰረተ-ቢስና ደካማ “ሐዲሦችን” አበጥሮ በማውጣት ለኡማው ባደረጉት ታላቅ አስተዋፅኦ ኢስላምን ላቅ ባለ ሁኔታ ላገለገሉ ምሁራን የሚበረከተውን አለም አቀፉን የንጉስ ፈይሰል ሽልማት በ1419 ዓመተ-ሂጀራ (1999 እ.ኢ.አ) ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ ባጠቃላይ ሸይኹ በተለይም በሙስጦለሐል ሐዲሥ (የሐዲሥ ጥናት) ዘርፍ ሑጃ ናቸው፣ ማስረጃ፡፡ ሸይኽ አልባኒ በተለያዩ የእውቀት መስኮች እጅግ በርካታ ኪታቦችን እና በሺህ የሚቆጠሩ የደዕዋና የፈትዋ ካሴቶችን ለኡማው አበርክተዋል፡፡ በተለይም በሐዲሥ ጥናት ዘርፍ እጅግ ውድ ድርሳናትን ከማበርከታቸውም በተጨማሪ ለዘመናት የተዘነጋውን የሐዲሥ ጥናት እንዲነቃቃ ካደረጉት ቀዳሚ ሰዎች አንዱ ናቸው፡፡ ለዚህም ነበር ዐሊሞች “የነኢብኑ ሐጀር አልዐስቀላኒን፣ ኢብኑ ከሢርንና የሌሎችንም ሙሐዲሦች ዘመን እንደ አዲስ አመጣው” ሲሉ ያወደሷቸው፡፡ ከላይ ከተጠቀሱት ስራዎቻቸው በተጨማሪ በዐለም-አቀፍ ደረጃ ታዋቂ የሆኑ በርካታ ተማሪዎችን አፍርተዋል፡፡ በመጨረሻም ጁማደሣኒያ 1419 ዓመተ-ሂጅራ (እ.ኢ.አ. ኦክቶበር 1999) ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል-ረሒመሁላህ ረሕመተን ዋሲዓህ፡፡
ስለ ሸይኽ አልባኒ ታላላቅ ዐሊሞች ምን ብለዋል? ጥቂት እንጥቀስ1. ሸይኽ ዐብዱልዐዚዝ ኢብኑ ባዝ ረሒመሁላህ (የቀድሞው የሰዑዲያ ጠቅላይ ሙፍቲ)፡- “በዚህ ዘመን ከሰማይ በታች እንደታላቁ ዓሊም ሙሐመድ ናሲሩዲን አልአልባኒ ሐዲሥን የተገነዘበ አላውቅም” ብለዋል፡፡ በአንድ ወቅት ሸይኽ ኢብኑ ባዝ እንዲህ የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር፤ “ረሱል ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም በሐዲሣቸው በየመቶ ዐመቱ ለዚህ ኡማ አላህ ዲኑን የሚያድስለት እንደሚልክለት ተናግረዋል፡፡ በዘመናችን ይሄ ሙጀዲድ (የተሀድሶ አራማጅ) ማን ነው?” የሸይኹም መልስ “እንደኔ እይታ የዚህ ዘመን ሙጀዲድ ሸይኽ ሙሐመድ ናሲሩዲን አልአልባኒ ነው፣ ወላሁ አዕለም” የሚል ነበር፡፡2. ሸይኽ ሙሐመድ ኢብኑ ሷሊህ አልዑሠይሚን ረሒመሁላህ፡- “አልአልባኒ ከአህለሱና ነው ለሱና ዘብ የቆመ፡፡ በሐዲሥም ኢማም ነው፡፡ በዘመናችን ከሱ ጋር የሚነፃፀር አንድም አናውቅም፡፡” “የተገናኘነው ለጥቂት ጊዜ ቢሆንም በተገናኘንበት አጋጣሚ ያስተዋልኩት በዐቂዳም በተግባርም ሱናን ለመተግበርና ቢድዐን ለመዋጋት ወደ ኋላ የማይል እንደሆነ ነው፡፡ ሰውየው በዘገባም ይሁን በግንዛቤ እጅግ የገዘፈ ዕውቀት ባለቤት ሲሆን በዒልሙም በሚንሀጁም(የሰለፊያ አካሄዱ) ወደ ሐዲሥ ዒልም ሰዎችን በማዞርም አላሁ ተዓላ በርካቶችን ጠቅሞበታል፡፡ ይህ ለሙስሊሞች ትልቅ ስኬት ነው፡፡”3. ሸይኽ ሙቅቢል ኢብኑ ሃዲ አልዋዲዒ ረሒመሁላህ (የየመን ሀገር ሙሐዲሥ)፡- “ዛሬም በሸይኽ አልባኒ ኪታቦች ትግላችንን አጠናክረን ቀጥለናል፡፡” “ስለ ሸይኽ ሙሐመድ ናሲሩዲን አልአልባኒ አላህ ይጠብቀውና በተደጋጋሚ ተጠይቄያለሁ፡፡ በርካታ ሰለፎች ከነሱ ስለሚበልጥ ሰው ሲጠየቁ ይሉ የነበረውን ነው የምለው፡፡ ‘እኔ ሳልሆን ስለሱ የምጠየቀው፣ እሱ ነው ስለኔ የሚጠየቀው!' ችግሩ ያለንበት ዘመን በርካቶች ዐሊም እና ጠንቋይ ሙእሚንንና ከሀዲ ሶሻሊስትን ያማይለዩበት ዘመን ነው፡፡… አህለሱና ያልሆነ እንጂ በሸይኽ አልባኒ እውቀት ማንም አይጠራጠርም፡፡ እኔ የማምነው ሸይኽ ሙሐመድ ናሲሩዲን አልአልባኒ ‘አላህ በየመቶ ዓመቱ ለኡማው ዲኑን የሚያድስለት ይልካል' የሚለው ሐዲሥ ከሚያረጋግጣቸው ሙጀዲዶች እንደሆነ ነው”4. ሸይኽ ዐብዱልዐዚዝ ኣሊሸይኽ (የአሁኑ የሰዑዲያ ጠቅላይ ሙፍቲ)፡- “ሸይኽ አልባኒ ሐዲሥን በተግባር የሚወድ ለሐዲሥ ጥናት ጥበቃና እንክብካቤ የሚያደርግ ታማኝ የሸሪዐ ምንጭ የሆነ ቅርብ ወንድማችን ነው፡፡”