Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

የአላህ ባህሪዎችን በተመለከተ ለብዥታዎች መነሻ ከሆኑት ውስጥ በጥቂቱ

   ይህ የተውሂድ ክፍል ቀላልና ግልፅ ሆኖ ሳለ ነገር ግን ለቁርዓንና ለሀዲስ መረጃዎች እጅ ባለመስጠታቸዉና አጉል ፍልስፍናን በመጠቀማቸው ብዙ የሙስሊም ቡድኖች የተምታቱ ሀሳቦችን ሲያራምዱበትና ከትክክለኛው መንገድ ሲያፈነግጡበት ይስተዋላል፡፡
     ከፊሎቹ የአላህን ባህሪዎች የተመለከቱ መረጃዎች፤ አላህን ከፍጡራን ጋር ስለሚያመሳስሉ አንቀበላቸውም ይላሉ፤  የተለየ ትርጓሜ በመስጠትም  መልዕክታቸውን ያዛባሉ። መረጃዎቹን ተቀብሎ ማጽደቅም አላህን ከፍጡራን ጋር ማመሳሰል እንደሆነ ያስባሉ። ከዚህም አልፈው የሀቅ ባለቤቶችን በኩፍር ይፈርጃሉ።
    ሌሎች ደግሞ “አላህ በምናውቀው ቋንቋ ነውና የሚያናግረን በቁርዓንና በሀዲስ የአላህን ባህሪዎች የተመለከቱ መረጃዎችን የምንረዳው ፍጡራን ላይ ባወቅነው ትርጉም ብቻ ነው” በማለት የአላህ ባህሪዎች ልክ እንደ ፍጡራን ባህሪዎች እንደሆኑ ይገልጻሉ። መረጃዎችን ከማየታቸው በፊት አላህ ፍጡራኑን እንደማይመስል እና ከፍጡራኑም እርሱን የሚመስል እንደሌለ የሚያስረዱ መረጃዎችን ቢያጤኑ ኖሩ ለዚህ ስህተት ባልተዳረጉ ነበር።
የሚከተለው ምሳሌ በዚህ ጉዳይ ላይ የሰዎች ውዝግብ ምንን መነሻ እንዳደረገ የምናይበት ነው።
? የአላህን ከዓርሽ በላይ መሆን በተመለከተ፤ አላህ እንዲህ ብሏል፦
     الرحمن على العرش استوى -  طه: ٥
“አረህማን ከዐርሽ በላይ ከፍ አለ (ሆነ)” (ጣሃ 5)

     አንዳንድ ቡድኖች “አላህ ከዓርሽ በላይ ነው” የሚሉ ሰዎች ለአላህ የፍጡራንን ባህሪ ስለሰጡ “ካፊር ናቸው” በማለት ይናገራሉ። በእነርሱ አመለካከት አንድ ሰው “አላህ ከዓርሽ በላይ ነው” ካለ አንድ ፍጡር ከሌላ ፍጡር በላይ እንዲሆን የሚያስፈልጉት ነገሮች ሁሉ ያስፈልጋሉ። የአላህን ከዓርሽ በላይ መሆን “ኢስቲዋዕ” ፍጡራን ከነገሮች በላይ ከመሆናቸው ጋር መለየት አልቻሉም። ስለዚህም የፈጣሪን ኢስቲዋዕ የተቀበለና ያመነ ሁሉ እነርሱ ቀድመው በአዕምሯቸው የቀረጹትን ምስል እንደተቀበለ አድርገው በማቅረብ ‘ካፊር ነው’ ይላሉ። ከእነዚህ ሰዎች መካከል ከፊሎቹ ስሞችንና ባህሪዎችን የተመለከቱ መረጃዎችን ሁሉ በማጣመም ትርጉም አልባ አደረጓቸው። ስለዚህም ‘‘ሙዓጢላህ’’[1] ተባሉ። ከእነርሱ መካከል ከፊሎቹ ደግሞ እነዚህን መረጃዎች አይተረጎሙም፤ እንዲሁ ይታለፋሉ፤ በማለት በአዕምሯቸው ከሳሉት ጣዖት ለማምለጥ ሞከሩ። እነዚህ ደግሞ “ሙፈዊዳህ”[2] ተብለው ተሰየሙ። ከሙዓጢላዎች ጋር አንድ የሚያደርጋቸው መሰረታዊ ነጥብ “የመረጃዎቹን ግልጽ መልዕክት መቀበል አላህን ከፍጡራን ጋር ማመሳሰል ‘ተሽቢህ’ ነው” ብለው ማመናቸው ነው”። እነዚህ ቡድኖች ባህሪዎችን አያጸድቁም ነገር ግን አቋማቸውን ሲያስረዱ ከሰለፎች አቋም ጋር ለማመሳሰል ጥረት ስለሚያደርጉ ብዙ ሰዎችን ሊያምታቱ ይችላሉ።
      ሌሎች ደግሞ የአላህን ከዓርሽ በላይ መሆን ይቀበላሉ። ይሁንና የአላህን ከዓርሽ በላይ መሆን የሚረዱት ልክ ፍጡር ከፍጡር በላይ እንደሚሆነው ነው። ስለዚህም “አላህ ከዓርሽ በላይ ነው” ስንል ልክ “ሰው ዙፋን ላይ እንደሚቀመጠው ነው” በማለት ያብራራሉ። እነዚህ “ሙሸቢሀ” ወይም “ሙመሲላ”[3] ይባላሉ።
ሁለቱም ወገኖች ከባድ ጥመት ዉስጥ ገብተዋል። የሚገርመው የሁለቱም ብዥታና በሽታ መነሻው አንድ መሆኑ ነው። በሽታቸው ስለአላህ የተነገሩ ባህሪዎችን ፍጡራን ጋር ባላቸው ትርጓሜና ይዘት መረዳት” ነው። የመጀመሪያዎቹ በዚህ መልኩ አዕምሯቸውን ከተጠናወተው የማመሳሰል በሽታ ለመዳን መረጃዎችን አጣመሙ፣ መልዕክቶችን አዛቡ፣ አስተባበሉም። ሁለተኛዎቹ ደግሞ በሽታቸውን አላወቁትም፤ ተቀበሉት። አላህንም በግልጽ ከፍጡራን ጋር አመሳሰሉ።
አህሉሱናን ወልጀማዓህ፤ አላህ በሁለቱ ጥመቶች መካከል ቀጥተኛውን መንገድ መራቸው። ከጥፋትም ጠበቃቸው። የአላህን ከዓርሽ በላይ መሆን አጽድቀው ከፍጡራን ጋር ማመሳሰልን ተጠነቀቁ። አላህ ሰሚ፣ ተመልካች፣ አዋቂ እና አዛኝ ነው ሲሉ፤ የፍጡራንን መስማት፣ መመልከት፣አዋቂነትና እዝነትን የተመለከቱ የፍጡራን የባህሪ መገለጫዎችና መለያዎችን አያስቡም። ልክ እንደዚሁ አላህ ከዓርሽ በላይ ነው ሲሉ ከፍጡራን ጋር የተያያዙ መለያዎችና ማነጻጸሪያዎችን አያስቡም። ስሞችንና ባህሪዎችን የሚያመላክቱ በቁርዓን እና በሱና የመጡ መረጃዎች ግልጽ መልዕክት ያላቸው እንደሆኑ ያምናሉ። ምንም አይነት የትርጓሜ ማጣመም አያስፈልጋቸውም። ከላይ እንዳየነው በዚህ ጉዳይ ላይ አህሉሱናን የተጻረሩ ቡድኖች ሁሉ መነሻቸው የተሳሳተ ግንዛቤ ነው።ይህ ማነጻጸሪያ የሁለቱን ጠርዘኛ አመለካከቶችና ሚዛናዊዉን የአህሉሱና አመለካከት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።

 ----------
[1] የአላህን ስሞችና ባህሪዎች ትክክለኛ ትርጉም አልባ አድራጊዎች።

[2] የአላህ ስሞችና ባህሪዎች ትርጉም አይታወቅም ባዮች።

[3] ፈጣሪን ከፍጡራን ጋር አመሳሳዮች

Post a Comment

0 Comments