Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

የበረዶ ዘመን ቃልኪዳኖች

By Hassen Mohammed

እወቅ! ቀጥለህ የምትዳስሰው ነጥብ ምናልባት ጥቂት መደናገርን ግን ደግሞ ዘልአለማዊ መድህንን አጣምሮ ስለሚያወርስህ በጥሞና ተከተለው:: ነብዩ صلى الله عليه وسلم በአንድ ወቅት አንድ ወጣት ክንድ ላይ የሆነች የተንጠለጠለች ነገር ያስተውላሉ:: ፈጠን ብለውም "ምንድን ናት" ሲሉ ይጠይቁታል:: ወጣቱም "መድሀኒት" ሲል ይመልሳል:: ይህን ግዜ ቆጣ አሉና የፋጢመት አባት "አውልቀህ ጣላት! በሽታን እንጂ አትጨምርህም! ይህችን (ብጣሽ) አንጠልጥለህ በሞትክ ኖሮ ዝንታለምህን (ከጀሀነም እሳት) ነጻ ባልወጣህ ነበር!" አሉት:: እንዲሁ በሌላ አጋጣሚም የተወሰኑ ሰዎች ነብዩ صلى الله عليه وسلم ዘንድ ቃል ኪዳን (ሙባየአህ) ሊፈጽሙ መጡ:: እርሳቸውም ከእንግዶቹ መሀል አንደኛውን ለይተው ቃል ኪዳኑን አልቀበልህም አሉት አሉ:: ምነው ቢሏቸው "በእጁ ላይ ለመድሀኒትነት ያንጠለጠላት ነገር አለችው" ብለው መለሱ:: ግለሰቡም ሌላኛውን እጁን ሰድዶ ቋጠሮይቱን በጠሳት፥ ነብዩም ቃል ኪዳኑን ተቀበሉት:: ቀጥለውም "(ይህችን መሰል ነገር) ያንጠለጠለ በእርግጥም በአላህ ላይ አጋርቷል" አሉ:: ዛሬ በሰፈርህ ከሚጫወቱት ህጻናት መካከል ለአብነት ያህል አንዱን ጥራውና እጆችህን በአንገቱ ስር ልከህ ያሉትን ቋጠሮዎች ቁጠር:: ሶስት? አራት? ከዛ በላይ? ምንም ካልከኝ ደግሞ ሰፈራችሁ በቀበሌው ኢ-ልማታዊ ሰፈር እየተባለ ይታማል በለኝ:: ለማንኛውም ቋጠሮዎቹን እንደጨበጥክ የህጻኑን ስም ስትጠይቀው የሚጠራልህ የሰሀባ ስም ነው፥ አባቱ ደግሞ መስጂዳችሁ ውስጥ አወል ሶፍ በስማቸው ቦታ የተኖረላቸው ደንበኛ መሆናቸውን ትረዳለህ:: የዚህን ግዜ ትንሽ ግር እያለህ "አብዛኞቻቸውም፤ እነሱ አጋሪዎች ኾነው እንጂ በአላህ አያምኑም፡፡" የሚለውን የቁርአን አያህ ታስታውሳለህ:: የሆነ ሆኖ በአንገት ላይ የሚንጠለጠል ህርዝ (እርዝ)፥ በክንድ ላይ የሚጠለቅ ጎማ፥ በጣቶች ውስጥ ለመድሀኒትነት ተብሎ የሚዶል ቀለበት፥ ከጌጥነት እርከን ያለፈ ጥቅም ያለው ሀብል፣ ሰንሰለት፣ አልቦ እና ሌሎች ብዙ ቁሳቁሶች በእኛና በክህደት መካከል የተሰመረውን መለኮታዊ መለያ ድንበር የጣሱ፥ አንድነታችንን የሚንዱ፥ የመልእክተኛውን አደራ የበሉ፥ የሙስሊሞች እንግልትን የሚያጎለብቱ ጉዳዮች ናቸውና ...... እናስ ምን ይደረግ? እናማ ይህንን ጽሁፍ አንብበህ ሳትጨርስ በጥሰህ ጣለው! እንዳው በትንሹ ቤትህ ውስጥ አለመኖራቸውን እርግጠኛ ሁን:: ከዛም ................. "ወሀቢይ" ይሉሀል:: የእኛ ህዝብ የቋንቋ ክፍተት አለበት:: በሱዳንኛ ዘፈን ዱአ ብታደርግለት "አንቱ መጀን" ይላል:: በብጣቂ ጨርቅ የቀብር አፈር ይዞ ይመጣና በጥብጦ ሲጠጣ ስታየው ድንግጥ ብለህ "እንዴ! አፈር እኮ ይጎዳል" ብለህ አብራርተህ ሳትጨርስ "የለም የለም ይሄ አፈር አይደለም 'ቱራብ' ነው" ይልሀል:: እሷን ይጉመጠመጥና ደግሞ በሰላቱ ውስጥ "አንተን ብቻ እንግገዛለን፤ አንተንም ብቻ እርዳታን እንለምናለን፡፡" የሚትለውን አያህ በአረብኛ ያነባታል፥ ያነበንባታል:: ሌላም ግዜ ሀድራ ሲሾፍር ታዲያ በዛችው አንደበቱ "ኹዝ ቢ የዲ ያ ረሱለላህ" ማለቱ አይቀርም:: ከቶ የኛው እስልምና ከወደየት የመጣ ነው ጎበዝ? እንዳልኩህ እኛ ማህበረሰብ ዘንድ በአላህ ላይ ማጋራት ማለት መጀመርያ ስምህ አማርኛ መሆን አለበት ነው፥ ከዛም የሙስሊም እርድ ያልሆነን ስጋ መመገብ ነው በቃ! እስቲ ቀጣዩን ክስተት በደንብ እንመልከት:: "ከእርሱ በቀር ሌላ አምላክ የሌለውን አንድን አምላክ ሊገዙ እንጂ ያልታዘዙ ሲኾኑ ሊቃውንቶቻቸውንና መነኮሳታቸውን፣ የመርየምን ልጅ አልመሲሕንም ከአላህ ሌላ አማልክት አድርገው ያዙ፡፡" የምትለው አያህ በወረደች ግዜ አንድ ሰሀባ ትንታኔዋን ከጅሎ ለመልዕክተኛው صلى الله عليه وسلم "እነርሱ እኮ ሊቃውንቶቻቸውንና መነኮሳታቸውን አማልክት አድርገው አልያዙም" ብሎ አላቸው:: እርሳቸውም: "እንዴታ!" አሉት፥ "ሀራሙን ሀላል ሀላሉን ሀራም አደረጉላቸው እነርሱም ተከተሏቸው፥ ይህ ነው እነርሱን ማምለክ ማለት!" ብለው ተነተኑት:: ልብ በል! ዛሬ ስንት ሰው ነው እሮብ ዕለት ከቤት እንዳትወጣ ተብሎ በአለቆቹ ማዕቀብ ተጥሎበት ንፍሮ እየቀቀለ የሚውለው፥ ቀይ ወይንም ነጭ አልያም ረከስ ያለችውን ዶሮ መርጦ መግዛት ታግዶ ገብስማ ፍለጋ ገበያ ለ ገበያ የሚማስነውስ፥ በገዛ ገንዘቡ ከሸመተው እህል ይሄን ብላ ይሄን ድፋ ተብሎ የታዘዘውስ ...... ሌሎችም ብዙ ብዙ ሀላሎች ሀራም የተደረጉባቸው፥ ሀራሞች ሀላል የተደረጉላቸው የምናውቃቸው ሰዎች አሉ:: መቼም ብስል ሰው ከሆንክ ልክ በዚች ቅጽበት በአዕምሮህ የቤተሰቦችህን ስራ እየገመገምክ ነው፥ አልያ ግን ተበልተሀል በቃ! ዋናው ጉዳይ ከአላህ ውጭ ያሉ አካላት ሀራም ያደረጉበትን ሀላል እንዲሁም ሀላል ያደረጉለትን ሀራም አቤት ያለ ሰው አላህ ከእርሱ ኢባዳ የተብቃቃ መሆኑ መልዕክቱ ይድረሰው:: ቢሰግድም ቢጾምም? አዎን ቢሰግድም ቢጾምም የተውበት ትሩፋት እስከሚያጥበው ድረስ:: እርግጠኛ ነኝ በህይወትህ አንድ ግዜም ቢሆን ቅልጥ ያለ ሰርግ ሳትበላ አልቀረህም፥ የቅርብ አጃቢ ከነበርክማ ሙሽሮቹ ሲገቡ ትንሽ ደም ቢጤ አፍስሳችሁ ተሻግራችሁ ገብታችኋል:: እሺ ወይ ደግሞ አዲስ ቤት ሲሰራ መሰረቱ ወጥቶ እንዳለቀ ለቀን ሰራተኞቹ አንድ በግ ማረዱ ደንብ መሆኑን ሰምተኸል:: አልያም ሰው አዳልጦት ከወደቀ በኋላ ለምናምኑ ተብሎ የወደቀበት አካባቢ እንቁላል አፍርጠው ሲጥሉ ተመልክተኸል:: ሌሎችም ብዙ ሳይንስ ጥቅማቸውን በውል ያማያውቀው "ፍቱን" ህክምናዎችን በግልህ ሳታውቅ አይቀርም:: ባህል እና እምነት ሀሳብ የሚዋዋሱበት ህብረተሰብ ላይ ተወለድን፥ ከዛም ልክ ጷግሜ 5 ወይ 6 ሲሆን በቀዝቃዛ ውሀ ሻወር ካልወሰድክ ትባላለህ፣ ጭቅጭቅ ካበዛህ ኢስላም ስለ ንጽህና የሰጠው አስተያየት ይተነተንልሀል:: ሲቀጥልም እንጀራ በፌጦ .... እምቢ ካልክ የሆድህን በሽታ መቀስቀስህ ነው በቃ:: በሌላ ግዜ ደግሞ ግንቦት ወር ላይ የአመቱን ሰላም ለመጎናጸፍ የዋህ እናቶች በቡና እና በኑግ ቂጣ ሜዳ ላይ ወጥተው ሲለማመኑ ያጋጥምኸል:: በነገራችን ላይ የግንቦት ወር አድባር አረብኛ "ቨርዥኑ" ሰፈር ወር ይባላል:: ከተመሰጥክ አይቀር ይሄን ልጨምርልህ፥ እስቲ አንድ ቀን ጉለሌ ቀብር ውረድ:: ነጭ ጀለቢያ የለበሱ፥ ሂጃባቸውን ያላዛነፉ የአረብኛ ስም ያላቸው ሰዎች አንዱ ቀብር ላይ ዘፍ ብለው ሲያርዱ ታገኛለህ:: ወይ ጉድ! "እነ ሸህ:- አስቴር 'በስማም በስማም' ብላ ዘፈን አወጣች እኮ፥ እንዴት ነው እናዳምጠው አናዳምጠው" ብሎ ፈትዋ ጠየቀ አሉ ያገሬ ሰው - እውነቴን ነው ምልህ ከየት እንደምትጀምር ግራ ያጋባሀል:: እንደ ቀልድ አንዲት በግ ገዝተህ ማረድህን አትይ ወዳጄ፥ ዝንብ አፍኖ ገድሎ ጀሀነም የተላከ አለና:: እንዲህ ነው ታሪኩ: "ሁለት ሰዎች በጣዖት አምላኪዎች ግዛት ያልፉና ሳትገብሩ አትንቀሳቀሱም ይባላሉ:: አንደኛው ግለሰብ እኔ ዘንድ ምንም ነገር የለም ይላቸዋል:: የዚህን ግዜ እንዳው ዝንብ እንኳ ብትሆን ይሉታል:: ሰውዬውም ምን አነታረከኝ ብሎ እፍን ያደርግና ያቀርብላቸዋል፥ መንገድ ተለቀቀለት ማለት ነው - እወቅ! የተለቀቀለት የጀሀነም መንገድ ነው:: ሌላኛው ግን በአንጻሩ ከአላህ ውጭ ምንንም ለማንም አካል አልገብርም ቢላቸው አንገቱን ብለው ጀነት ሰደዱት" አሉ መልእክተኛው صلى الله عليه وسلم:: አላህ ከእኛ እርድ ዱለቱ ወይ ጥብሱ አይሄድለትም አትድከም፣ ስጋው ቆዳው ቀንዱ ደሙ ፈርሱ እዚሁ አንተ ቤት ቀሪ ነው፥ ባይሆን ይህችን አያህ አንብብልኝ "አላህን ሥጋዎቿም ደሞቿም ፈጽሞ አይደርሰውም፡፡ ግን ከእናንተ የሆነው ፍራቻ ይደርሰዋል፡፡" እንዴታ! አለሞቼ እራቶቼ አለቆቼ ቁጥቦቹ ታረቁን ባኩኹን፥ ይኸው ተቀበሉን ..... ጀባ ብለናል ተብሎ ከታረደ ስጋ ለአላህ የሚደርሰው ክፍሉ የቱ ነው እስቲ ልጠይቅህ? ይሄ ይገርምሀል እንዴ? ትንሽ ቆይቶ እኮ ደግሞ አራጁ በሰላቱ ውስጥ እንዲህ ይል ይሆናል:- "(إِنَّا أَعْطَيْنَاكَ الْكَوْثَرَ ﴿١﴾ فَصَلِّ لِرَبِّكَ وَانْحَرْ ﴿٢" "ስለዚህ ለጌታህ ስገድ፤ (በስሙ) ሰዋም":: አበቃሁ