Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ቀለማትና ኪታቦች


"ወዲኒ ነቢ"፣ "ነብያችንን"፣ "ቁርአን ልምታልህ?"፣ "ቁርአንን"፣ "የቁርዐን በረካ ይድፋኝ"፣ "አባቴ ይሙት"፣ "ከእናቴ ስጋ ይነጥለኝ"፣ "የእናቴን ቀን ያሳየኝ" ...... ኡፍፍፍ ሲዘገንን ያ አላህ! እነዚህ ሁሉ የልጅነት ማሀላዎቻችን ነበሩ:: የሆነን ነገር ፈልገህ ሰው ስትለምን ደግሞ "በ 30 ጁዝ ቁርዐን"፣ "በነብያችን"፣ "በእናትህ"፣ "በእከሌ" ምናምን ትለውና ግግም ሲል "በሁሉም ይዤሀለው" ብለህ ጥፍር አድርገህ ታስረዋለህ:: የት አባቱ ይሄዳል? "በሁሉም" ተይዞ! እንዲህ ነው እንጂ:: ዛሬ አድገናል እንበል (አርጅተናል ማለት ደብሮኝ ነው)፥ ማሀላችንም በቁጥርም በአይነትም አድጓል:: ትላንት በ"ሁሉም" ብለን በደፈናው የማልንባቸው አካሎች ዛሬ "ስፔሺያላይዝ" ስናደርግ ለብቻ ለብቻ ነጣጥለን እንደ ጉዳዩ ክብደት አስፈላጊውን አካል ጥቅም ላይ ማዋል ጀምረናል:: "ጌታው ሸህ አሊን እንዲህ አላልኩም"፣ "አብዶዬን እኔ አይደለሁም"፣ "አባቴ ይድፉኝ እንዲህ አልወጣኝም" ....ዋ ኢስላማ!.... እንዴ በአገሩ "ወላሂ" ብሎ የሚምል የለም ማለት ነው? ተው ተው! አለ አትቸኩል! ግባ መርካቶ፥ ዱባይ ተራ ቦምብ ተራ፥ እዛ ደግሞ መሀላ የአረፍተነገር መባቻ ሆኖ እስክትጠግብ ድረስ ሰምተህ ትመለሳለህ:: ሰዉም እኮ ተላምዶት ልክ እንደ ዝንብ ከወሬዎችህ መሀል "ወላሂ ወላሂ" የምትለውን "እሽ እሽ" እያለ ነው የሚያዳምጥህ:: ለማንኛውም መሀላ ቁምነገሩ "Made in China" የሚለውን ጽሁፍ ማስለቀቅ አልነበረም:: በጭራሽ! ባይሆን ለምትምልበት አካል ያለህን ፍራቻና ክብር ይገልጻል:: አድማጭ ሆነህ ከተማለልህ ደግሞ በተማለበት አካል ያለህን እምነት ያህል ተናጋሪውን ታምነዋለህ ማለት ነበር:: አስር ግዜ "ወላሂ" አስብለኸው "እስቲ እጄን ምታልኝ" የምትለው አንተ የትኛው አጣሪ ኮሚቴ ነህ? እንተማመን እንጂ ጎበዝ! አውቃለሁ ልማድ ሆኖብኝ ነው እንደምትለኝ:: ወደ ቤትህ ግባ ደግሞ:: ከዛ አንድ በእድሜ ተለቅ ያለ ሰው "ሸኾቼን፣ ቆሌዬን፣ ጨለዬን" እያለ ሲያሳምን ትሰማለህ:: አንተም ቀብበል ታደርግና "እንዴ ይሄ ነገር እኮ ሽርክ ነው አባዬ!" ማለትህ አይቀርም:: ወሬ አዳማቂውም ሳትቀድመው "ኤዲያ እሄ ነጭ ኪታብ አያመጣው የለ!" ይልና ርእሱን ወደ ቀለማት ምርጫ ይቀለብሰዋል:: ከመቀጽበትም የአንተ አፍ ሳይከት የእነርሱ ጆሮዎች ይዘጋሉ:: ከእቤት ስትወጣ "ወሀቢይ" ይሉሀል፥ እቤት ስትሆን ደግሞ "ኪታብህ ነጭ ነው" ነው ሙግቱ:: ወይ አበሳ ... እውነት ግን ኪታብህ ቀለሙ ምንድነው? አሁን ድረስ የሚያናደኝ ደግሞ ምን መሰለህ .... ቆይ አንተ: "ትልቅ" ሰው ናቸው "ጉልበታቸውን" ሳም ተብለህ አታውቅም? እርግጠኛ ነኝ አጋጥሞሀል:: ከዛ ያቺ ሚጢጢ ጉንጬን በአንድ እጃቸው ጨምድደው ይይዟትና አፋቸው ውስጥ ያለውን የ"ጫት" መረቅ ፊቴ ላይ ይነሰንሱብኛል:: ትምህርት እንዲገባኝ፥ ሹመት እንዳገኝ፥ ሀብታም እንድሆን እኮ ነው አሪፍ አይደል! ለአኼራውማ ጡሌዬን ይዘህ ተከተለኝ ብለውኛል:: ..... እንዲህ እየተባልን ከስንቱ "በረካ" ዛቅን መሰለህ:: ሌላ ደግሞ በመስጂድ ማይክራፎን ከሚነገር ታሪክ አንዱን ላውጋህ:: ዝናብ ጠፋ አሉ የሆነ አገር እና ሰዉ በጣም ተጨነቀ:: ከዛ መላ ሲያስፈልጉ ከቆዪ በኋላ ወደ አንድ ታዋቂ ወደሆነ ቀብር ዘንድ ሄዱ እና ጉዳያቸውን አጫወቱት:: ሟችም ግራ ቀኙን በጥሞና ካጤነ በኋላ: "ጋቢያችሁን ዘርጉና ንግግሬን እፈሱ፥ ከዛም መልሳችሁ ቋጥሩት፥ አገራችሁ ሳትደርሱም እንዳትፈቱት" ብሎ ይነግራቸዋል:: ሰዎቹም እንደተባሉት አገራቸው ሲደርሱ ጋቢያቸውን ክፍት ቢያደርጉት ወዲያውን አገሩ ዝናብ በዝናብ ተጥለቀለቀ ይባላል:: (ሙሉውን ታሪክ "ለማ በገበያው" የሚለው የ4ኛ ክፍል አማርኛ መጽሀፍ ላይ ይፈልጉት):: አላህ ያሳያችሁ እስቲ ይሄ ተረት ተረት መስጂድ ውስጥ ይነገራል? ዛሬ ሰዎች "በረካ"ን ፍለጋ ድንበር ለቀው ከንፈዋል:: ከዛፉ፣ ከሙዳይ፣ ከድንጋይ፣ ከገደላት፣ ከቀብር ቦታዎች፣ ከቀናቶች እንኳ ሳይቀር ማለቴ ነው:: ሌሎች ደግሞ የህብረተሰቡን ድክመት አይተው በየሀድራው እንደ የጀባታው መጠን "በረካ" የሚቸረችሩም አሉ:: ሰዉም አይኑ ተይዞበት ኖሮ በየቂምሀው መሀል "በርክ" ሲል ያጋጥምሀል:: እኔ እኮ ማይገባኝ ለኛ "በረካ" ላምታቺዎቹ "ፈረንካ" ይሁን ያለው ማን ነው? ቀድሞውንስ "በረካ"ውን ሽጠኸው "ፈረንካው" ምኑ ይረባሀል? ባይሆን አንድ ክስተት ትውስ አለኝ:: እየውልህ በአንድ አጋጣሚ ላይ መልእክተኛውን صلى الله عليه وسلم አዳዲስ ሰለምቴዎች ይመጧቸውና እንደ ሙሽሪኮቹ ሁሉ ለእኛም "በረካ መጎናጸፊያ" ዛፍ ያብጁልን ይሏቸዋል:: ያን ግዜ የነበረውን የነብዩን ቁጣ ይሄን ያህል ነው አልልህም፥ ግን ምን አሉ መሰለህ "....... !الله أكبر" :: የከባድ ቁጣ ማሳይያ ቃል:: አዎን እጅጉን ተቆጡ ሙስጠፋ صلى الله عليه وسلم :: ጉዳዪ መርዝ ነውና:: እኔ አሁንም እቤትህን ፈትሽ ነው ምክሬ:: ወላጆችህ ዘንድ ዝለቅና "አንታለል"፥ "ጉዳዪ ከባድ ነው"፥ "ከእስልምና ያስወጣል"፥ "በረካውም ቢሆን በአላህ እጅ ነው" በላቸውማ .... የእነርሱ መልስ እንደሚከተለው ይሆናል:: በፊት በብላክ ቴሌቪዥን ዘመን ከጎረቤት ልጆች ጋር ተጋፍተን ኳስ ጨዋታ ድጋፍ ስንሰጥ ገሚሳችን የ"ነጭ" ለባሽ ገሚሳችን ደግሞ የ"ጥቁር" እንሆን ነበር:: ምንም አይነት ቀለም ያለው ምስል ቢመጣ እኛ ጋር ነጭ ወይንም ጥቁር ሆኖ ነበር የሚታየን:: ሌላ አይነት ቀለም የምናየው ምናልባት "ስዕል" ደብተራችን ላይ ብቻ ነው:: ከዛልህ የእድል ነገር ሆኖ ከለር ቲቪ በየሰፈሩ ነገሰ፥ በመሆኑም የኳስ ተጨዋቾቹ ቁምጣና ካልሲ እንደሚለያይ ተደረሰበት፥ ህጻናቱ ሁላ ቀለም ይጽፉ፣ ቀለም ይገባቸው፣ ቀለም ይታያቸው ጀመር፥ ወላጆቹ ግን አሁንም ድረስ "ነጩ ኪታብ" ማለት አላቆሙም:: አላህ ይዘንላቸው ማጠቃለያ ተከትለኸኝ እንደሁ በሁለት የተለያዩ ርእሶች ስር አንድ አምስት ነጥቦችን ባልተገራ አማርኛ አወጋዉህ ከሆነ ከአጥር ጀርባ ከተወረወረ መጽሀፍ ኮርጄ ማለት ነው:: ባለቤቱ ግን ከስድሳ በላይ ቁምነገሮችን በአንድ ታዋቂ ርእስ ስር አካቷቸዋል:: የሆነው ሆኖ ኋላ ላይ ማንነቱን እጠቁምሀለው:: ያለንበትን ግዜ በአንጻሩም ቢሆን የ"በረዶ ዘመን" እለዋለሁ:: ሙስሊሞች የሚወያዩበትን አንድ መስኮት ብትከፍት አልያም ስለ ሙስሊሞች ዜና ታትሞ ብታነብ ብሶት እንጂ አያጋጥምህም:: መቀሌ፥ ጎንደር፥ ሀረርጌ፥ አወልያ፥ በኒ፥ ሶሪያ፥ የመን፥ ኢራቅ፥ ፈረንሳይ፥ ፓኪስታን .... አያሌ በርካታ ቦታዎች:: በልሊታዎች ሁሉ ዙሪያችንን ከበው ካማራቸው ቦታ ይቦጫጭቁናል:: ሲፈልግ በ"ወሀብያ" ሹካ እንደ ፓስታ ይጠቀልለናል፥ ካልሆነም እንደ ቁርጥ ስጋ በ"አሸባሪ" ቢላ ጎረድ ጎረድ ያጫውተናል:: እንዳው ካማራቸው ቦታ አልኩህ እኮ:: ለማንኛውም ከዚህ የላቀ የ"በረዶ ዘመን" እፊታችን ቆሟል:: ለዛን ግዜ ከበጀህ ብዬ ነው ስለ በረዶ ዘመን ቃልኪዳኖቹ ማውራቴ:: ነገሮች ሁሉ እንዲህ ምስቅልቅል ባሉብን ሰአት ማምለጫ አቋራጩ ራስን ዞር ብሎ መፈተሽ ብቻ ነው ባይ ነኝ:: ከአላህ ተጣልቶ "መፍትሄ አፋልጉኝ!" ማለት መታወር ይመስለኛል:: ነገ ደግሞ እኮ አላህ ፊት መቆም አለ፥ ስለ ቃልኪዳኖቹ መጥጠየቅም አለ፥ ስራዎችን ማስመዘንም አለ፥ ነፍሱንም በሽርክ የበደለ ሰው በደለኛ የሚሆንበት ፍርድም አለ እኮ ዘመዶቼ:: አንዳንድ ግዜ ግፍ እንዲህ መብዛቱን ሳስተውል "ምናለ አሁኑኑ ቂያማ ቆም ቢልባቸው!" ብዬ እመኝና ደግሞ የነፍሴ በደሎች ትዝ ይሉኛል:: ዳሩ በማናችን በደል ቀድሞ እንደሚፈረድ ከቶ ማን አወቀው? የእኔ በደል በነፍሴ ላይ ወይንስ የጠላቶቼ በእኔ ላይ? አላህ ይሁነን ብቻ:: መልካም! "በዚህ ፍጥነት ቢመጡን እንኳ?" ነው የሁላችን ጥርጣሬ: አይደል? አዎን ጠላት የከነፈውን ያህል ቢከንፍ ከአላህ ጋር የተውሂድ ፍቅር ለመመስረት እንቅፋት አይሁነን:: ያለ ጠላትም እኮ መሰቃየት፣ መንገላታት አለ፥ መታመም፣ መሞት፣ መቀበርም አለ፥ ያለ ተውሂድ ግን ሁለቱም አገር ላይ ቅንጣት ህይወት የለም:: "ለእርሱ ገሀነም አለችው፡፡ በውስጧም አይሞትም ሕያውም አይኾን" ይላል መመሪያችን:: እናም ዛሬ ለተገፋው ሰውነታችን ነገ ማረፍያ የሚሆን ቦታ እናብጅለት ወገን:: በአጠቃላይ የሰጠሁህ አምስት ቃልኪዳኖች ላይ ሀምሳ ምናምን ስትጨምርበት አንድ ዝነኛ መጽሀፍ ታዘጋጃለህ ማለት ነው:: አባዝተህ፥ ተርጉመህ፥ አብራርተህ አስረዳቸው ቤተሰቦችህን፥ ከቻልክም አሰራጨው:: ሰዎችንም አንብቡት ከምትላቸው ብታነብላቸው ይቀላቸዋል --- እንዳይሰሙ እንዳያዩ ሆነው የታሪክ ማእቀብ ተጥሎባቸዋልና:: በነገርህ ላይ ስለ ርእሱ ብዙ አትጨነቅ፥ ዋናው መልእክቱን አድርስ እንጂ የፈለግከውን ሰይመው:: ካላገኘህም እኔው ልጠቁምህ:- ....................."كتاب التوحيد لشيخ الإسلام محمد ابن عبد الوهاب"....................... ልትለው ይመችሀል:: ጨርሻለሁ:: جعلني الله وإياكم ممن ذُكِّر فنفعته الذكرى وصلى الله على محمد وعلى آله وصحبه وسلم