Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ከነብዩ (ﷺ) መላክ በፊት የነበረው የሴት ልጅ ሁኔታ!



አላሁ (ሱብሀነሁወተዐላ) ነብዩን (ﷺ) ከመላኩ በፊት የነበረው የሰው ልጆች ሁኔታ ከመኖራቸው ይልቅ አለመኖራቸው የሚመረጥበት የጨለመና የዘቀጠ ሁኔታ ነበር:: ያ ዘመን በተለየ መልኩ ደግሞ ለሴት ልጅ የነበረው ገጽታ ብእሮች ቢጨመቁ ቃላቶች ቢቀመሙ እንኴ ዘግናኝና አሳዛኝ ሁኔታውን መግለጽ ይሳናቸዋል፡፡ ሙሉ ለሙሉ የወንድ ልጅ ባሪያ የነበረች በገዛ ንብረቷ ቀርቶ በገዛ እሷነቱ ላይ እንኴ የመብት እንጥፍጣፊ የማያውቃት የበታችና ተረጋጭ ነበረች::ስብእናዋን ሳይቀር የሚጠራጠር ሰው ነች ወይስ? የሚል ሙት ማህበረሰብ ውስጥ ለተአምር የምትኖር ነበረች፡፡ የሰቀቀንና የሲኦል ጉዞዋ በዚህ አያበቃም:: ይልቁንም ይሄ አሰቃቂ ጉዞዋ ህይወት ተብሎ እንዳታጣጥመው እንኴን የእግር እሳት የሆነበት ያአመጸኛ ህብረተሰብ በእንስሳት ታሪክ እንኴን በውል ያልታወቀ የቅጣት ጅራፍን ከነህይወቷ በመቅበር አሳረፈባት ፡፡ከዚህ በኃላ ግን እዝነትና ፍትህ መገለጫ ባህሪው የሆነው ታላቁ አምላክ (ሱብሃነሁወተአላ) ይህን ህይወት ላለው አይደለም ለግኡዙ አካል እንኴ የማይበጀውን ከንቱ ትውልድ በዚህ የአረመኔነት ሜዳ እንዳሻው ሊቦርቅ አልፈቀደለትም ስለዚህም መሃይምነትን ሊያጠፋ እውቀትን ሊረጩ፣ጭካኔን ሊያባሩ እዝነት ሊዘሩ ፣ጭቆናን ሊዋጉ ፍትህን ሊያነግሱ ቁርአንን በማስያዝ መልክተኛውን (ﷺ) አስነሳቸው:: ታዲያ ሙስሊሟ ሴትይህን ጸጋ የቸራትን ነጻ ያወጣትን የተሟላና እንከን የለሽ ሃይማኖት የመረጠላትን ታላቁን ጌታዋን ከምንምና ከማንም በፊት አመስጋኝ አትሆንምን፡፡እስኪ አልሃምዱሊላህ በይ እህቴ!