Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

በጫማ ላይ የማበስ ሸሪዓዊ ድንጋጌውና ማስረጃው




በሙሉ አህለሱና ወልጀምዓ ስምምነት በጫማ ላይ ማበስ የተፈቀደ ነው፡፡ በጫማ ላይ ማበስ አላህ ከባሮቹ ጣጣን ለማቅለል ሲል ያግራራው ሲሆን ለመፈቀዱም ማስረጃዎቹ ሀዲስና የኡለማዎች ስምምነት (ኢጅማዕ) ናቸው፡፡ነብዩ እንደተገበሩት እንዳዘዙትና በዚህ ጉዳይ እንዳግራሩ የሚጠቁሙ ሶሂህ ሀዲሶች በብዛት ተዘግበዋል፡፡ ኢማም አህመድ እንዲህ ብለዋል “ጫማ ላይ ማበስ ለመፈቀዱ ልቤ ውስጥ ትንሽም ጥርጣሬ የለም ይህን የሚያስረዱ ከአርባ በላይ ሀዲሶች አሉ፡፡” ሀሰነል በስሪይ እንዲህ ብለዋል “ነብዩበጫማቸው ላይ እንዳበሱ ሰባ ሰሃባዎች ነግረውኛል፡፡”
ከነዚህ ሀዲሶች፦ ጀሪር ኢብን አብድላህ እንዳስተላለፉት“የአላህ መልዕክተኛ ተፀዳዱና ውዱእ ሲያደርጉ በጫማቸው ላይ አበሱ፡፡”( ሙስሊም ዘግበውታል)አዕመሽ ኢብራሂምን ጠቅሰው እንደዘገቡት “ይህ ሀዲስ ያስደስታቸው ነበር ምክንያቱም ጀሪር የሰለመው የአልማኢዳው (ስለ ውዱእ የሚናገረው) አንቀፅ ከወረደ በኋላ ነበርና”አንድ ሰው ጉዞ ላይ ሲኾንና ሀገርም ሲኾን በማንኛውም ሁኔታ በጫማ ላይ ማበስ እንደሚችል ሁሉም አህሉ ሱና ወልጀመዓ ተስማምተዋል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ “በጀውረብ” ላይ ማበስም የተፈቀደ ነው፡፡ “ጀውረብ” ከቆዳ ያልሆነ ማለትም ከጨርቅ ወይም ከሌላ የሚሰራ የእግር ልብስ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ካልሲ ማለት ነው፡፡ ካልሲ ላይ ማበስ የተፈቀደው ልክ እንደጫማ ለእግር አስፈላጊ ስለሆነና የሚታበስበትም ምክንያት ተመሳሳይ ስለሆነ ነው፡፡ ስለዚህ እግርን የሚሸፍን እስከሆነ ድረስ ማበስ ይቻላል፡፡