Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ኢትዬጵያ ላይ ሽርክ እየተስፋፋ ነው፡፡


by Sadat Kemal Abu Nuh
ለተውሂድ ቅድሚያ አለመስጠትን ምን አመጣው? ከሽርክ የበለጠ አስከፊ ነገር ሊመጣ ይችላልን??? አላህ ወደ ተውሂድ ተጣሪ ያድርገን ሰሞኑን እየሰማነው ያለነው በጣም አስደንጋጭ ሁኔታዎች ውስጥ የሽርክ መስፋፋት ነው፡፡ ብዙዎች ለምን ጆሮ ዳባ ልበስ እንደሚሉት ባይገባኝም፤ ነብያት በጠቅላላ፤ በተለይ የአላህ መላክተኛን ((ﷺ)) በጣም ያሳስባቸው እና እንቅልፍ ይነሳቸው ነበር፡፡ ሰሞኑን በቅርብ ቀን የሚከበረው ሰዎች ዘንድ ‹‹ዋናውን ሃጅ ከማድረግ በፊት የኑርሁሴን ይቀደማል›› የሚሉለት ‹‹አሩሲ አናጂና›› ሊከበር ነው፡፡ ይህም እንዴት ዝም ይባላል??? አህመደ ነጃሺ ላይ ከጎንደር ለሚመጡ ዘያሪዎች ሰፋ ያለ ቤት ለመስራት መሬት ለመጠየቅ እና ገንዘብ ለማሰባሰብ እየተሞከረ ነው፡፡ እንደሚታወቀው አህመደ ነጃሺ ላይ ሰዎች ለቀብሩ በቀጥታ ከአላህ ውጭ ሱጁድ የሚያደርጉበት ቦታ ነው፡፡ ታድያ እንዴት ይሆን ሰዎች ለሽርክ ገንዘባቸውን የሚተባበሩት??? የአካባቢው ነዋሪዎች ወደ ነጃሺም፤ ወደ አሊ ጎንደር ቀብር፤ ወደ አብድልባሲጥ፤ አባድር፤ ቡሬ እና የመሳሰሉት ቦታዎች እየሄዱ ይገኛል፡፡ የዘንድሮ ‹‹አብሬት መውሊድም›› በታሪኩ ታይቶ የማይታወቅ ነው፡፡ አውቶብስ ተራ አካባቢ ‹‹አብሬት አብሬት›› ሲሉ የነበሩ ‹‹የሚኒባስ እና ቅጥቅጥ›› መኪናዎች ብዛት ሽርክ ምን ያህል እየተስፋፋ እንደሆነ ያሳያል፡፡ Facebook ላይም ‹‹የሸህ ሁሴን ጂብሪል ትንቢት›› እያለ ፖስት የሚያደርግም አልጠፋም፡፡ የነገን የሚያውቀው አላህ ብቻ ሆኖ ሳለ፤ ነብያችንም ((ﷺ))‹‹የነገን አውቃለሁ ያለ ጋር የሄደ የ40 ቀን እና ለሌት ሰላቱ ውድቅ ነው፤ ካመነበት በእኔ ላይ በተወረደው ክዷል፡፡›› ብለዋል ነሺዳ እና መንዙማ እየተባለ ከአላህ ውጭ ነብያችን ((ﷺ)) ላይም ይሁን ሌሎች ፍጡራን ላይ ከባባድ ድንበር ማለፍ እየታየ ነው፡፡ ዘንድሮ ከወጡ መንዙማዎች ውስጥ ይህ ከባድ ሽርክ ይገኝበታል፡፡ <<ያ ቀመረል መካ አሰላሙ አለይካ ልቤ ባንቱ በእርሶ ተመካ>> ብሎ የአላህን መብት ሙሉ ለሙሉ አሳልፎ ለነብያንች ((ﷺ))ይሰጣል፡፡ ኢብራሂ (አለይሂ ሰላም) እሳት ላይ ሲወረወሩ፤ ነብያችን ((ﷺ))በጠላት ሲከበቡ ‹‹በአላህ ላይ ተመክቼያለሁ፤ ይንኛ ያማረ መጠጊያ›› ነበር ያሉት፡፡ ዛሬ ዛሬ ያውም ቀኑን ሙሉ ሰዎች ተርበው ውለው፤ ቁርዓንን እንዳይሰሙ በእንደዚህ አይነት ሽርክ ሰዉን ከመንገድ ያስቱታል፡፡ ወደ አላህ መንገድ እንጣራለን የሚሉት አብዛኛዎቹ አላህ ካዘነላቸው ጥቂቶች ውጪ፤ ተውሂድን አይደለም የዳእዋቸው መጀመሪያ ሊያደርጉት የዳእዋቸው መጨረሻም አላደረጉትም፡፡ ሁሉም የአላህ መልክተኞች ጥሪያቸውን በተውሂድ ነበር የጀመሩት፤ በተለይ ነብያችን ((ﷺ)) በተውሂድ ጀመሩ፤ በእርሱም ላይ ዘወተሩ፤ ሊሞቱ ሲሉም ስለ ሽርክ አስከፊነት እያስጠነቀቁ ሞቱ፡፡ ከነብያችን ((ﷺ)) ለምን ይመስላችኋል ሙአዝን (ረድየላሁ አንሁ) ወደ የመን ሲልኩት ‹‹መጀመሪያ ጥሪህ ተውሂድ እና የኔን መልክተኝነት ማስመስከር ይሁን ይህን እሺ ካሉህ በቀን እና በለሊት 5 ወቅት ሰላት ግዴታ ተደርጎባቸዋል…….›› ያሉት??? ምክንያቱም ግልፅ ነው፤ ማንኛውም ስራ ተውሂድ ካልተስተካከለ እና የነብያችንን ((ﷺ)) ሱና ካልገጠመ አላህ ዘንድ ተቀባይነት የለውም፡፡ ተውሂድን ሳያውቁ ሰዎች ወደ ሰላት እንኳን አይጠሩም፤ አብዛኞቹ ዳኢዎች ቢያውቁ ኖሮ፡፡ (አላህ ካዘነላቸው ጥቂቶች ውጪ) አብዛኖቹ ዳኢዎች ግዴታቸውን ቢወጡ ኖሮ፤ ነብያት ፍሬ እንዳፈሩት እነርሱም ፉሬ ባፈሩ ነበር፡፡ ነገር ግን ተውሂድን ችላ አሉት፤ ሁሉም የዘራውን እያጨደ ይገኛል፡፡ አላህ የነብያት ተልኮ ከሚረዱት እና ቅድሚያ ሰጥተው ከሚተገብሩት ያድርገን፡፡ አገራችን ላይ ሽርክን አላህ ያጥፋልን፡፡ ስሞታችንን ለአላህ ብቻ እና ብቻ እናሰማለን፤ አላህም እርሱ ላይ የሚመኩትን መልስ ይሰጣቸዋል፡፡ አላህ ሆይ! እርዳን፡፡