ከአገር መፍረስ ባሻገር
~
አገር
እንድትፈርስ የሚመኙ፣ አገር ለማፍረስ የሚጥሩ፣ ለአገር አፍራሾች ድጋፍ የሚሰጡ ብዙ ሰዎች አሉ። ወንድሜ ሆይ!
እውነት በሃገር መፍረስ የምታተርፍ መስሎህ ነው? ለመሆኑ አገር ሲፈርስ ምን ምን ሊከሰት እንደሚችል አሻግረህ
ተመልክተሃል? ወይስ በሆኑ አካላት ላይ ያለህ ጥላቻና ቁጭት በሩቅ እንዳትመለከት ሸፍኖብሃል? ወንድሜ አገር ዳቦ
አይደለም ፤ እንደዋዛ ቆራርሰህ በመካፈል አትገላገልም።
* ሃገር ሲፈርስ እልፍ አእላፍ ይፈናቀላሉ። እንኳን
አገር ፈርሶ በብሄር ግጭትና ጥቃት ብቻ የሚሊዮኖች ህይወት ተመሰቃቅሏል። ምናልባት አንተ ከሚፈናቀሉት ባትሆን እንኳ
ራስህን በነሱ ጫማ ላይ አድርገህ ተመልከት።
* ሃገር ሲፈርስ እልፍ አእላፍ ትዳር ይፈርሳል። ከሌላ ብሄር ጋር የተጋቡ ወገኖቻችን እጅግ ብዙ ናቸው። ይሄ ዘር እየለየ የሚገድል ትውልድ የሚተዋቸው እንዳይመስልህ። ስንት ቤተሰብ እንደሚበተን ተመልከት።
* ሃገር ሲፈርስ እልፍ አእላፍ ንብረት ይወረሳል። እንኳን አገር ፈርሶ ሰላም በመጥፋቱ ብቻ የስንቱ ምስኪን ንብረት በተለያዩ ክልሎች በጉልበተኛ ተነጥቋል!
*
ሃገር ሲፈርስ እዚያም እዚህም መቋጫ የሌለው የድንበር ግጭት ይነሳል። በአንድ መንግስት ስር ሆነን ነው በሶማሊና
በኦሮሞ የድንበር ግጭት ከሚሊየን በላይ ህዝብ የተፈናቀለው። በአንድ መንግስት ስር ሆነን ነው አፋርና ዒሳ በየጊዜው
የሚጋደለው። በአንድ መንግስት ስር ሆነን ነው ዘጠኝ መቶ ሺ አካባቢ የጌዲዎ ህዝብ የተፈናቀለው። በአንድ መንግስት
ስር ሆነን ነው የወሎ ኦሮሞና የሸዋ አማራ የሚጋጨው። በአንድ መንግስት ስር ሆነን ነው በደቡብ ክልል የተለያዩ
ህዝቦች መካከል ግጭት የሚቀሰቀሰው። በአንድ መንግስት ስር ሆነን ነው ወሎ ኦሮሞ ነው፣ ወልቃይት፣ ደራ፣ በረራ፣
መተከል አማራ ነው የሚል ጩኸት የምንሰማው፡፡ ሃገር ከፈረሰ እነዚህ ጩኸቶች ዛሬ ከምናየው በላይ ሚሊዮኖችን የሚበላ
እሳት ይቀሰቅሳሉ።
* ሃገር ሲፈርስ እልፍ አእላፍ ነፍስ ይጠፋል። ከላይ የተጠቀሱት በሙሉ መጨረሻቸው እልቂት ነው።
*
ምናልባት መልኩ ይቀየር ካልሆነ በስተቀር በሃገር መፍረስ ጭቆና የሚቀር፣ ለድሃ ቀን የሚወጣ እንዳይመስልህ።
ወላሂ! ዘር እየለየ፣ ሃይማኖት እየመረጠ በሚገድል ቡድን፣ ከርሱን በሚያስቀድም ፖለቲከኛ መቼም ፍትህና ነፃነት
አታገኝም።
የሚሻለው በጋራ ለሰላምና ለፍትህ መጣር ነው። መፍትሄው እንደ ህዝብ ከገጠመን የስነ ምግባር ዝቅጠት
ለመውጣት ተባብሮ መሥራት ነው። ችግራችን ስር የሰደደ ነው። ችግራችን በማህበረሰብ ደረጃ የተንሰራፋ ነው። ስለ
መንግስት ችግር ጧት ማታ ማውራቱን እንደ ንቃት ቆጥረን እራሳችንን እየሸወድን እንጂ እንደ ህዝብ መተዛዘን ሳስቶ
መጨካከን ነግሶብናልኮ። በየገበያው የሚያጭበረብረው፣ በየተቋሙ ህዝብ የሚያጉላላው፣ ... ሁሉ ምንም ስቅ ሳይለው
ስለ ፍትህ እየወሸከተ ነው። ለብዙዎች ከትምህርት ገበታ መራቅ ሰበብ የሚሆነው፣ ዘርና ሃይማኖት እየለየ ተማሪዎቹን
የሚያከላፍተው አስተማሪ ምንም ሳያፍር ስለ ፍትህና ርትእ እየጮኸ ነው። ታካሚዎቹን ፊቱን አጨፍግጎ የሚያስተናግደው፣
በግዴለሽነት የሰው ነፍስ ላይ የሚቀልደው፣ ለርካሽ ጥቅም ሲል የማይገናኝ ምርመራ እያዘዘ ደካማ ወገኑ ላይ ጭካኔ
የሚፈፅመው ሃኪም እኮ ነው ስለ ፍትህ የሚጮኸው! የተበላሸ ምግብ፣ ጊዜው ያለፈበት መድሃኒት፣ ፎርጂድ እቃ፣
የተጭበረበረ ምርት፣ ... የሚሸጠው ነጋዴ እኮ መስራት አቃተን እያለ የሚያለቅሰው። ፍትህ በገንዘብ የሚሸጠው፣
ከሌባ ጋር ተቀናጅቶ የሚሰራው፣ እምነትና ብሄር እየመረጠ ፍትህ የሚቀብረው ዳኛና ፖሊስ እኮ ነው ስለ ፍትህ
የሚዘፍነው። ሚሊዮኖች የወጡበትን የቤት ካርታ አሳልፎ ለሌላ የሚሰጠው ሰራተኛ፣ የሚሊዮኖችን ውሃና መብራት እየቆረጠ
ሺ ጊዜ ብር እየተቀበለ የሚቀጥለው ሌባ እኮ ነው ስለ ፍትህና ስለ ነፃነት የሚለፍፈው። መኪናና ሞተር ሳይክል
አዘጋጃቶ፣ አንድ ላምስት ተደራጅቶ የሚዘርፈው፣ ህፃናት እያፈነ የሚወስደውኮ ነው እኩል ስለ ፍትህ የሚያወራው?
የሁለት ቀን ጨቅላ፣ የ70 አመት አዛውንት፣ አቅመ ደካማ ሴቶችን ሳይቀር የሚገድለው እኮ ነው የነፃነት ታጋይ
የሚባለው። እስኪ በየትኛው ዘርፍ ነው የሚነሳ ጥሩ ነገር ያለን? ፖለቲከኞቹ የኛው ነፀብራቆች ናቸው። እኛኑ ነው
የሚመስሉት። ከኛው የወጡ እንጂ ከሌላ ፕላኔት የመጡ አይደሉም። ክፋታቸው ክፍታችን፣ ንቅዘታቸው ንቅዘታችን ነው።
እንደ
ህዝብ በዚህ ደረጃ መልካሞች የመነመኑ ከሆኑ እንዴት ነው ፍትህና እፎይታ የምናገኘው? በቅድሚያ በራሳችን ላይ ሰፊ
ስራ መስራት ይጠበቅብናል። ወደተነሳሁበት ስመለስ፣ ስግብግብ ስሜታችን እየጋረደን፣ ቁንፅል አመልካከታችን
እየሸወደን እንጂ በርግጠኝነት በሃገር መፍረስ እንደ ህዝብ ከሳሪዎች እንጂ አትራፊዎች አይደለንም። ስለዚህ ደግመን
ደጋግመን ልንመለከት፣ ከጥፋት ልንርቅ፣ ለአጥፊዎች ጉልበት ከመሆንም ልንጠነቀቅ ይገባል። ጥፋትን ማስቆም ባንችል
እንኳ ቢያንስ ተጋሪ ባለመሆን የራሳችንን ድርሻ ልንወጣ ይገባል።
በኢብኑ ሙነወር
0 Comments