☞ሒጃብ ከመልበስ ምን ከለከለሽ?
ለታላቁ ንግስናውና ለልቅናው በሚገባው መልኩ አላህን አመሰግነዋለሁ።
ወደ አላህ ውዴታና ወደ ገነቱ መንገድን ያመላከቱ በሆኑት
ክቡር መልእክተኛው ላይ የአላህ ውዴታና ሰላም ይስፈን።
ይህ የኢስላም መንገድ የተቃና መንገድ ነው። ዙሪያዉን መልካም ፍሬዎች አካበውታል። በመልካም ስነምግባርም ያንፃል። በጥብቅነት በንፅህና እንዲሁም በተሸፈነ ጌጥ ያንፀባርቃል። ከሙስሊሙ ማህበረሰብ ከቀጥተኛው ጎዳና ያፈነገጡ ሴትና ወንድ አማኞችኝ መረጋጋትና ሀሴት ወደ ተሞላበት ዱንያዊና አኼራዊ ተድላ ይመራቸዋል።
ከዚህ እፁብ ድንቅ መንገዶቹ ውስጥ አምላካችን አላህ ለሴት ልጅ የንፅህናዋና ክብሯ መገለጫ ይሆን ዘንድ ሒጃብን በሷ ላይ ግዴታ ማድረጉ ነው። በተቃራኒው ከቀጥተኛው መንገድ ያፈነገጠ ማህበረሰብ ሁሉ ወደ ሀሴትና ጤናማነት የሚመራው እምነታዊ መድሀኒት የሚሻ በሽተኛ ማህበረሰብ መሆኑ የማይታበል ሀቅ ነው። አንድ ማህበረሰብ ከቀጥተኛው መንገድ ማፈንገጡ ከሚታወቅባቸው መሰረታዊ መገለጫዎችና የችግሩንም ጥልቀት ይፋ ከሚያደርጉ ጠንቆች መካከል በሙስሊም ሴቶች ውስጥ የተንሰራፋው መራቆትና መገላለጥ በዋናነት ይጠቀሳል። ይህ ጠንቅ በሚያስቆጭ መልኩ የሙስሊሙ ማህበረሰብ ሴቶች መገለጫ ከሆነ ሰነባብቷል። በዚህም ጠንቅ ትክክለኛው ኢስላማዊ አለባበስ እየደበዘዘ መጥቷል።
☞የዚህ ታላቅ አደጋ መንስኤዎች ምንድናቸው?
ይህን ጥያቄ ለመመለስ በተለያየ ደረጃዎች ውስጥ ያሉ ሴቶችን ጠይቀን በጥቅሉ አስር ዋና ዋና ምክንያቶችን ጨምቀን ለእናንተ አቅርበናል።
እነዚህ እንስቶች ከሂጃብ የሸሹባቸውን መሰረታዊ ምክንያቶች ስናጤን ሚዛን የማይደፉ ደካማ ምክንያቶች መሆናቸውን ተገንዝበናል። የእያንዳንዳቸውን ምክንያት ተራ በተራ አብረን በዝርዝር እንመለከታለን።
①የመጀመሪያው ምክንያት፦ የመጀመሪያዋ ሴትን ምክንያት እንስማ "እኔ እስከ አሁን ድረስ በሂጃብ ውስጤ አላመነም አስፈላጊነቱ አልታየኝም!" ትላለች።
☞ለዚህች እህት ሁለት ጥያቄዎችን እንጠይቃታለን።
⇨የመጀመሪያው፦ የእስልምና ሀይማኖት ትክክል መሆኑን ውስጥሽ ተቀብሎታል? ታምኚበታለሽ?⇢
መልሷ አዎን! በትክክል ይሆናል።
"ከአላህ በስተቀር በእውነት የሚመለክ አምላክ የለም" ማለቷ የዐቂዳዋ መስተካከልን ይጠቁማል። ሙሐመድም የአላህ መልእክተኛ ናቸው ማለቷ ኢስላማዊ ሸሪዓን መቀበሏን ያስገድዳል። ስለዚህ በነዚህ የምስክር ቃሎቿ መሰረት ኢስላምን የህይወት መስመሯ ማድረጓና የእምነቷ ብቸኛ ምንጭ መሆኑን ማፅደቋ ይታወቃል።
☞ሁለተኛው፦ ሒጃብ ከኢስላማዊ ድንጋጌዎችና ግዴታዎች አይደለም ወይ? ብለን እንጠይቃታለን።
☞ይህች እህታችን አውነትን ለማወቅ እንደሚጥር ሰው ብትመራመርና ከልቧ ጉዳዩን ብታጤነው መልሷ "አዎን ሒጃብ ከኢስላም ግዴታዎች ውስጥ ነው!" የሚል ይሆን ነበር።
በአምላክነቱ ያመነችበት አላህ ሒጃብን በመፅሀፉ ውስጥ ግዴታ አድርጓል። በመልእክተኛታቸው ያመነችባቸው የአላህ መልእክተኛም በሱናቸው ውስጥ ሒጃብን ለሴት አማኞች በአጠቃላይ አዘዋል። እስልምና ትክክለኛ እምነት ነው ብሎ ተቀብሎ በውስጥ የሚገኙ ትእዛዛቶችን የማይተገብር ግለሰብን ምን ብለን እንሰይመው? ይህ ግለሰብ በየትኛውም ሁኔታ ቢሆን አላህ ካወደሳቸው ሰዎች ተርታ አይመደብም እነዚህ ትእዛዙን በመፈፀም ውዳሴ የተገባቸው እውነተኛ አማኞችን አስመልክቶ አላህ እንዲህ ብሏል፦ "የምእመናን ቃል የነበረው ወደ አላህና ወደ መልእክተኛው በመካከላቸው ሊፈርድ በተጠሩ ግዜ ሰማንም ታዘዝንም ማለት ብቻ ነው። እነዚህም እነሱ የፈለጉትን የሚያገኙ ናቸው።" አን ኑር 51
ማጠቃለያ፦ ኢስላምን እምነቴ ነው ብላ ከተቀበለች እንዴት ትእዛዙን
አትቀበልም?
ሁለተኛው ምክንያት❕ ሁለተኛዋ እህት እንዲህ ትላለች ሸሪዓዊ ሂጃብ ግዴታ እንደሆነ አውቃለሁ ነገር ግን እናቴ ትከለክለኛለች እሷን ካልታዘዝኩ ደግሞ አላህ እሳት ያስገባኛል! "
ለዚህች እህት የሚሰጠው መልስ የአላህ መልእክተኛ ጥበብ በተሞላው ንግግራቸው የተናገሩትን ነው እሱም "ፈጣሪን በማመፅ ላይ ፍጡርን መታዘዝ የለም" ማለታቸውን ነው። በኢስላም የወላጆች ደረጃ በተለይ የእናት ደረጃ በጣም የላቀ ነው። እንደውም አምላካችን አላህ የተለያዩ ቦታዎች ላይ እሱን በብቸኝነት ማምለክን ለፍጡር የሚያዝበት አንቀፆቹን በማስከተል የወላጆችን ሐቅ አደራ ይላል:- “አላህን ተገዙ በእርሱም ምንንም አታጋሩ በወላጆችም መልካምን ስሩ ... "
አላህ በማመፅ ከመታዘዝ ውጪ ወላጆችን በሁሉም ነገር መታዘዝ ቅሮት የሌለው ጉዳይ ነው።
አላህ እንዲህ ይላል፦ "ለአንተ በእርሱ ዕውቀት የሌለህን ነገር በእኔ እንድታጋራ ቢታገሉህ አትታዘዛቸው።" ሉቅማን 15
እነሱን በወንጀል ላይ አለመታዘዝ ለእነሱ መልካም መዋልን የሚከለክል ጉዳይ አይደለም። አላህ እንዲህ ይላል " በቅርቢቱ አለም በመልካም ስራ ተወዳጃቸው።"
ማጠቃለያ፦ እናትሽንም አንቺንም የፈጠረውን አምላክ አምፀሽ እንዴት እናትሽን
ትታዘዢያለሽ?
ሶስተኛው ምክንያት❕ ሶስተኛዋ ደግሞ እንዲህ ትላለች "የኑሮ ደረጃዬ ሸሪዓዊ ሂጃብን ለመልበስ ይከለክለኛል አቅሙ የለኝም"
ይህን ምክንያት የሚያቀርቡ እህቶች ሁለት አይነት ናቸው።
የመጀመሪያዋ ምክንያቷ እውነተኛ የሆነ ሲሆን ሁለተኛዋ ደግሞ ዘመኑ ያፈራቸውን የተጣበቡና የተጋጌጡ ልብሶችን ለመለበስ ፍላጎት ያላት ሒጃብ ላለመልበስ የውሸት ምክንያት የምትደረድር ናት። ከእውነተኛዋ እህታችን እንጀምር እህቴ ሆይ በየትኛውም ሁኔታ ቢሆን አንዲት ሴት ሸሪዓዊ መስፈርቶች የተሟሉለት ሂጃብ ሳትለብስ መውጣት እንደማትችል አታውቂም? ይህ ጉዳይ ሁሉም ሙስሊም እንስቶች ማወቃቸው ግዴታ የሆነ ነገር ነው። የዱንያ ጉዳይን ጠንቀቅሽ እያወቅሽ እንዴት ከአላህ ቅጣትና ከእርግማኑ የሚያድንሽን መሰረታዊ እውቀት ትዘነጊያለሽ?
ስለዚህ እህቴ ሆይ የሒጃብን መስፈርቶች በሚገባ ተማሪና እወቂ። ከቤት መውጣትሽ ግዴታ ከሆነ ሸሪዓዊ ሂጃብሽን ሳትለብሺ እንዳትወጪ። ይህ ተግባርሽ የጌታሽን ውዴታ የሚያሰፍንብሽና ሸይጣንን የሚያዋርድልሽ ነው። የተገላለጠና የተጣበበ ልብስ ለብሰሽ በመውጣትሽ የሚመጣው ክፋትና መዘዝ ለወሳኝ ጉዳይ ወጥተሽ ከምታመጪው ጥቅም የከፋ ነው። ኒያሽ ቢስተካከል ወኔሽም ቢቃና ወደ አንቺ በሺዎች የሚቆጠሩ መልካም በሮች ይከፈቱልሽ ይሆናል።
ለሁለተኛዋ ለምትዋሸዋ እህት ደግሞ እንዲህ እንላለን አላህ ዘንድ ልቅና ክብር ግርማ ሞገስ የሚገኘው በተሽቆጠቆጡ በተጣበቡ በተራቆቱ ጨርቆች አይደለም። እሱ ዘንድ ክብርና ደረጃ የሚኖረን አላህና መልእክተኛውን በመታዘዝ ንፁህ የሆነውን የሸሪዓ መንገድ በመከተል ብቻ ነው። ከዚህም ውስጥ የሴት ልጅ ንፁህነትና ጥብቅነት መገለጫ የሆነው ሒጃብ በዋናነት ይጠቀሳል። “እናንተ ሰዎች ሆይ! እኛ ከወንድና ከሴት ፈጠርናቹ። እንድትተዋወቁም ጎሳዎችና ነገዶች አደረግናቹ።አላህ ዘንድ በላጫችሁ በጣም አላህን ፈሪያችሁ ነው። አላህ ግልጽን አዋቂ ውስጥንም አዋቂ ነው።” ሁጁራት 13
ማጠቃለያ ፦ የአላህ ውዴታንና ጀነቱን ለማግኘት በሚደረገው ትግልና ጥረት ከገንዘብም ከነፍስም ውድ የሆኑ ነገሮች ይሰዋሉ። በአላህ መንገድም ይተዋሉ።
አራተኛው ምክንያት❕ ፦ያለሁበት ሀገር አየር ንብረት ሞቃት ነው ሙቀቱን መቋቋም አልችልም። ሒጃብ ለብሼ ደግሞ እንዴት ልሆን ነው? ትላለች፡፡
የሀገርሽን ሙቀት እንዴት ከጀሀነም ግለትና ሙቀት ጋር ታወዳድሪያለሽ የተከበርሽው እህቴ ሆይ? ሸይጣን ደካማ በሆነው አንዱ ወጥመዱ አጥምዶሻል። በዱንያ ሙቀት አዘናግቶ ወደ ጀሀነም እሳት ሊከተሽ እየተዘጋጀ ነው። ከሸይጣን መረብ ነፍስሽን አድኚ። የፀሀይ ሙቀት ፀጋ እንጂ ቅጣት እንዳልሆነ ተገንዘቢ። የፀሀይ ሙቀትና ግለት ከባድ የሆነውን የጀሀነም እሳትና ግለት አስታውሶሽ ከሱ የምትድኚበትን መንገድ ሊያስታውስሽ ይገባል። ያን ግዜ ትንሿን የዱንያ ምቾትን ከአላህ እሳት ነፃ ለመሆን ስትይ መስእዋት አድርገሽ በሀሴት ወደ አምላክሽ አላህ እንድትመለሺ ያደርግሻል። የእሳት ሰዎችን አስመልክቶ አላህ እንዲህ ይላል፦ የገሃነም እሳት ተኳሳነቱ በጣም የበረታ ነው ነው በላቸው
ማጠቃለያ ጀነት ለነፍስ በሚከብዱ ነገሮች ተከባለች። እሳትም በነፍስ ዝንባሌዎችና ፍላጎቶች ተከባለች።
አምስተኛው ምክንያት፦❕ አምስተኛውን ምክንያት ስሚ ሒጃብን ከለበስኩ ቡኋላ እንዳልተወው እሰጋለሁ። ብዙ ሴቶችም ሂጃብን ከጀመሩ ቡኋላ ትተውታል። ስለዚህ እንደነሱ ከመሆን ሳልጀምረው ቢቀርብኝ ይሻላል! " ለዚህች እህት እንዲህ እንላታለን። ሰዎች ሁሉ እንዳንቺ ቢያስቡ ኖሮ
ዲናቸውን በጥቅልም በዝርዝርም እርግፍ አድርገው ይተው ነበር። የወደፊቱን ስለማያውቁ ሁሉምን ዒባዳ ለወደፊት ጀምረን እንዳንተወው ስለምንፈራ ቢቀርብን ይሻላል ይሉ ነበር። ተመልከቺ ሸይጣን ሌላኛው ወጥመዱ ውስጥ አድኖሽ እንዴት እንደሚጫወትብሽ ከቅናቻውም ጎዳና በተልካሻ ምክንያት እንደሚያርቅሽ! መልካም የሆኑ ትንሽም ሆነ ተወዳች ተግባራቶችን አምላካችን አላህ ዘውታሪ ሲሆኑ ይወዳል። ግዴታ የሆነ ተግባርን ደግሞ እንዴት ሊሆን? ይበልጥ ዘውታሪ ሊሆን ይገባዋል። የአላህ መልእክተኛም እንዲህ ብለዋል " አላህ ዘንድ ተወዳጅ ተግባር ትንሽም ቢሆን ዘውታሪ የሆነው።
ስለዚህ ሳትጀምሪው ከመተውሽ በፊት ለምን ሂጃብ ጀምረው የተው እህቶች ወደዚህ ደረጃ ያደረሳቸው ምክንያት ምን እንደሆነ ለማወቅና ከዛም ለመጠንቀቅ ጥረት አታደርጊም። የፅናትና የእውነትን መንገድ ፈልገሽ ቆራጥ አትሆኚም?! ከነዚህ የፅናት መንገዶች መካከል የአላህ መልእክተኛ ዘውትር ሲያደርጉ እንደነበረው አላህ በዲናችን ላይ ፅናት እንዲሰጠን ከመራን ቡኋላ ወደ ጥመት እንዳንመለስ ዱዓ ማብዛት ነው። በተጨማሪም አላህን መፍራት ከወንጀል መራቅ በሰላት ላይ መዘወተር ለፅናት መሰረታዊ ነጥቦች ናቸው። ሙሉ በሙሉ የሸሪዓ ድንጋጌዎችን መከተልና መያዝ የፅናት መንገድ ነው። ሒጃብ ደግሞ ለሴቶች በዋናነት የሚጠቀስ ሸሪዓዊ ትእዛዝ ነው። አላህ እንዲህ ይላል፦
”እነርሱም በእርሱ የሚገሰፁበትን ነገር በሰሩ ኖሮ ለነርሱ መልካምና (በእምነታቸው ላይ) ለመርጋትም በጣም የበረታ ይሆን ነበር” አን ኒሳእ 66
ማጠቃለያ የቅናቻን መንገድ ይዘሽ የኢማንን ጥፍጥና ብታጣጥሚ ቅናቻና
ከያዝሽ ቡኋላ በፍፁም ወደ ኋላ አትመለሺም ነበር።
ስድስተኛው ምክንያት ❕ "ሒጃብ ከለበስሽ ማንም የሚያገባሽ የለም! ተብያለሁ ስለዚህ ካገባሁ ቡኋላ እለብሳለሁ" ትላለች።
እህቴ ሆይ ተገላልጠሽና በስስ ቀሚስ ተጣብቀሽ ለትዳር የሚፈልግሽ ወንድ የእውነት ላንቺ የሚገባ አይደለም። ይህ ወንድ አላህ በከለለላቸው የፈሳድና የክፋት መንገዶች ላይ የማይቆረቆርና የማይቀና ነው። ባንቺ በገዛ ሚስቱ ላይም ቅናትና መቆርቆር የማይሰማው ደዩስ ነው። ከእሳት ነፃ ሆነሽ ወደ ዘልአለማዊቷ ሀገር ጀነት እንድትገቢ በፍፁም ሊያግዝሽ አይችልም። ስለዚህ አላህን በማመፅና በማስቆጣት ላይ መሰረቱ የተጣለ ትዳር ጅማሬውም ፍፃሜውም አያምርም። በዱንያም በአኼራም እድለ ቢስነት ሊፃፍበት የተገባ ነው። ልክ አምላካችን አላህ እንዳለው፦ "ከግሳፄዬም የዞረ ሰው በእርሱ ጠባብ ኑሮ አለው። በ ትንሳኤ ቀንም ዕውር ሆኖ እንቀሰቅሰዋለን” ጣሃ 124
በመቀጠል እህቴ ሆይ ትዳር አላህ ለፈለገው ሰው የሚለግሰው ፀጋ ነው። በርካታ ሒጃብን በሚገባ የለበሱ እህቶች የሚያስቀና ትዳርን እያጣጣሙ እንደሆነ እወቂ። ስንትና ስንት የተገላለጡ ከሒጃብ የራቁ እህቶች ትዳር ናፍቋቸው የተራ ወንድ መጫወቻ እንደሆኑ በሚገባ ታውቂያለሽ። ስለዚህ ሒጃብ የማለብሰው ለብልግና ሳይሆን ትዳር ፈልጌ እስከሆነ ድረስ ለመልካም አላማ
ነው ማለትሽ ትልቅ ስህተት ነው። ለምን መሰለሽ የተቀደሰና ንፁህ አላማ በቆሸሸ መንገድና ተግባር አይፈለግም። ቢፈለግም አይገኝም። ከተገኘም የቆሸሸው ብቻ ነው የሚገኘው። አላማው ቅዱስ ከሆነ መዳረሻውም ንፁህ መሆን አለበት።
ማጠቃለያ፦ በወንጀልና በአመፅ የተገባ ትዳር የአላህን ረድዔት የተነፈገ ነው።
ሰባተኛው ምክንያት ❕ ሒጃብ አላደርግም ምክንያቱም አላህ እንዲህ ብሎኛል "በጌታህም ፀጋ አውራ" ዱሓ 11
አላህ የሰጠኝን ፀጋዎች ለስላሳ ፀጉሬን ፈታኝ የሰውነት ቅርፄን ማራኪው ፊቴንና ገፅታዬን መደበቅ አልፈልግም!" ትላለች። ይህ ንግግሯ የአላህ ትእዛዛትና ክልከላዎችን በራሷ አረዳድና እንዲሁም ስሜቷንና ዝንባሌዋን መሰረት አድርጋ ብቻ እንደምትመለከት ያሳያል። ስሜቷን ያልገጠ ሲሆን ባሰማና ባላየ ታልፋቸዋለች። ይህ ካልሆነ ይህን የአላህ ቃል የት አድርጋው ነው? " "አንተ ነብዩ ሆይ ለሚስቶችህ ለሴት ልጆችህም ለምእመናን ሚስቶችም ከመከናነቢያዎቻቸው በላያቸው ላይ እንዲለቁ ንገራቸው። ይህ እንዲታወቁና (በባለጌዎች) እንዳይደፈሩ ለመኾን በጣም የቀረበ ነው። አላህም መሃሪ አዛኝ ነው።"አህዛብ 59
እህቴ ሆይ በዚህ ንግግርሽ አላህ የከለከለውን ያስጠነቀቀውን ለነፍስሽ የተፈቀደ እያደረግሽ መሆኑ ይግባሽ። ውበትሽን ለሚፈቀዱ ሰዎች ብቻ ማሳየትሽ ላልተፈቀዱልሽ አካላት እራስሽን ላለማዋረድና ለፈተና ላለመጋለጥ አምላክሽ ሒጃብን ላንቺ በእዝነቱ መደንገጉ ታላቅ ፀጋ መሆኑ ይግባሽ።
የንፅህናሽን የልብሽን ቅናቻ የሚጠቁም ነው። ነገር ግን ለወጣውም ለወረደውም ለባለጌዉም ለበሽተኛውም አካልሽን ማራቆትሽ ውርደትና ዝቃጭነት መሆኑ ይግባሽ። መጨረሻውም በሸይጣን ወጥመድ ገብተሽ ራስሽን ማርከስ መሆኑ አንቺም ታውቂዋለሽ።
ማጠቃለያ፦ ለሴት ልጅ ከቅናቻው መንገድና ከሒጃብ በላይ ፀጋ አለን?
ስምንተኛው ምክንያት ❕ "ሒጃብ ዋጂብ እንደሆነ አውቃለሁ ነገር ግን አላህ ሒዳያ ሲሰጠኝ እለብሳለሁ።" ትላለች
ይህቺን እህታችን እስከ አሁኗ ሰኣት ድረስ የሒዳያን መንገድ ለማግኘት
የሄደችበትን ርቀትና ያደረገችውን ጥረት እንጠይቃታለን።
ሁላችንም እንደምናውቀው አላህ በጥበቡ ለሁሉም ነገር ምክንያት አበጅቷል። ከዚህም ውስጥ በሽተኛ ይሻለው ዘንድ መድሀኒት ይወስዳል። መንገደኛም መዳረሻ ይሆነው ዘንድ መጓጓዣ ይፈልጋል። ምሳሌዎቹ ብዙ ናቸው።
ይህችስ እህታችን ቅኑን መንገድ ለማግኘት ከልቧ ጥራለች? ሰበቦቹንስ አድርሳለች?
ፈጣሪዋ እንዳዘዛት በንፁህ ልቧ የቅናቻን መንገድ እንዲሰጣትስ ተማፅናለች? " ቀጥተኛዋን መንገድ ምራን" ፋቲሓ 6
መልካም ሴቶች ጋር መቀማመጥ በቅናቻ ላይ ለመዘውተርና በዲን ላይ ለመፅናት በዋናነት የሚጠቀስ ምክንያት ነው።
ማጠቃለያ ይህቺ እህት እህታችን የቅናቻን መንገድ ሰበቦችን ለማግኘት ከልቧ ብትጥር ኖሮ ሂዳያን አላህ ይሰጣት ነበር።
ዘጠነኛው ምክንያት ❕ ሂጃብ የምለብስበት ግዜዬ ገና ነው። እኔ ገና ልጅ ነኝ ትልቅ ስሆንና ሐጅ ካደረግኩ ቡኋላ ሒጃብ እለብሳለሁ!" ትላለች። እህቴ ሆይ የሞት መልአክ ደጃፍሽ ዘንድ በተጠንቀቅ ቆሞ ድንገት በርሽን ባላሰብሽው ሰኣት ሊከፍተው የአላህን ትእዛዝ እየተጠባበቀ መሆኑን እወቂ። አላህ እንዲህ ይላል "ለህዝብም ሁሉ የተወሰን ጊዜ አላቸው ጊዜያቸውም በመጣ ወቅት አንዲት ሰዐት አይቆዩም።(ከጊዜውም) አይቀድሙምም" አልዐእራፍ 34
እህቴ ሆይ ሞት ህፃን አወቂ ብሎ አይለይም። ከሂጃብ ርቀሽ በተጣበቁ ቀሚሶች ተራቁተሽ ድንገት አስደንጋጩ ሞት ሊመጣብሽ ይችላል። እህቴ ሆይ የአላህን ትእዛዝ እሺ በማለት ከቀዳሚዎቹ እንስት አማኞች ጎራ አሁኑኑ ተሰለፊ። “ከጌታችሁ ወደ ሆነች ምህረት፣ ወርዷ እንደ ሰማይና ምድር ወደሆነችም ገነት ተሽቀዳደሙ ለእነዚያ በአላህና በመልክተኞቹ ላመኑት ተዘጋጅታለች” አልሀዲድ 21
እህቴ ሆይ! አላህን በመርሳትሽ በዱንያም በአኼራም እዘነቱን ገፎሽ ነፍስሽን የምትረሺ ሆነሽ የአላህ ሐቅ በመዘንጋት ለኪሳራ እንዳትዳረጊ። ዛሬን እንጂ ነገን ማወቅ አትችይም። ስለዚህ ዛሬውኑ ተለወጪ። ትእዛዙን አክብሪ።
አላህ እንዲህ ይላል "እንደነዚያንም አላህን እንደረሱትና ነፍሶቻቸወን
እንዳስረሳቸው(ሰዎች) አትሁኑ። እነዚያ እነርሱ አመጸኞቹ ናቸው"አልሐሽር 19
እህቴ ሆይ በዚህ ለጋ እድሜሽ ሂጃብን መተውና ሌሎች ወንጀሎችን ከመዳፈር መራቅ አለብሽ። አላህ ቅጣቱ የበረታ እንዲሁም በቂያማ እለት ህይወትሽን በተለይ የወጣትነት እድሜሽን በምን እንዳሳለፍሽው ይጠይቀሻል።
ማጠቃለያ፦ ምኞትሽን አታርዝሚ ነገን እኖራለሁ ብለሽ አትተማመኚ
አስረኛው ምክንያት ❕ በመጨረሻም አስረኛዋ እህት እንዲህ አለች "ሸሪዓዊ ሒጃብ ከለበስኩ የሆነ ቡድን አባል ነሽ እባላለሁ። እኔ ደሞ ቡድንተኛና ጎጠኛ መባል አልፈልግም"
የኢስላም እህቴ ሆይ! በኢስላም ውስጥ ሁለት አይነት ህዝቦች ናቸው ያሉት አምላካችን አላህ በተከበረው ቃሉ እንዲህ ሲል አስፍሮታል።
የመጀመሪያው ህዝብ፦ አላህን በመታዘዝና ወንጀልን በመራቅ የአላህን ውዴታ የተጎናፀፈ የአላህ ህዝብ ነው። ሁለተኛው ህዝብ ፦ አላህን የሚያምፅ ብልሽትን የሚያስፋፋ ድንጋጌዎቹን የሚጥስ ወሰን አላፊ የሆነ የሸይጣን ህዝብና መንጋ ነው። እህቴ ሆይ! ሒጃብና መሰል የፈጣሪሽን የእዝነት ድንጋጌዎቹን በተገበርሽ ቁጥር ከቅጣቱ ነፃ ከሚወጡት ውዴታውን ከሚጎናፀፉት ቅን ባሮቹ ውስጥ ትሆኚያለሽ። ከአላህ ህዝቦችም ትሆኚያለሽ። በተገላለጥሽና በተጣበበ ቀሚስ ሰውን መፈተንና እራስሽንም ማዋረድ ካማረሽ በሸይጣንና በወዳጆቹ ከሀዲያንና መናፍቃን መርከብ ላይ ተሳፍረሻል። ምን የከፋ ወዳጅነት ነው!!!
ተመለከትሽ ከአላህ መንገድና ከነፃነት ወደ ሸይጣን እስር ቤት እንዴት እንደገባሽ? ጥሩውን በመጥፎ ጣፋጩን በመራራ መልካሙን በቆሻሻ እንደለወጥሽ አስተውይ!
እህቴ ሆይ! ወደ አላህ ሽሺ!! ሸሪዓውንም ተግብሪ! " ወደ አላህም ሽሹ እኔ
ለእናንተ ግልጽ አስጠንቃቂ ነኝና " ዛሪያት 50
ማጠቃለያ ፦ በጌታሽ የውዴታ መንገድ የእዝነቱ በር የጀነቱ መግቢያ ላይ ትሆኚ ዘንድ የሰውና የጋኔን ሰይጣናትን ጥሪ ከራስሽ አርቀሽ ወርውሪ!!! የአላህን ሸሪዓ አጥብቀሽ ያዢ። በቀደምት ቅዱሳን አማኝ እናቶች መንገድ ላይ ተጓዢ። በሰሀቢያት አስደናቂ ጀብድና የእምነት ፍኖት ላይ ተጓዢ።
ማገባደጃ⇩ አካልሽ በሸይጣን ገበያ ላይ በርካሽ ቀርቧል፤ የሰዎችን ልቦና ይመርዛል፣ የፀጉርሽ ጫፎች ከግንባርሽ ላይ ተዝረክርኳል፤ ጠባቡ ቀሚስሽ የአካልሽን ቅርፅና መገጣጠሚያ በሚቀፍ መልኩ ቁልጭ አድርጎ አጋልጦታል፤ የተጋጌጠውና በሽቶ የታወደው ልብስሽ ጌታሽን አስቆጥቶ የሸይጣን ጭፍሮችን አስደስቷል። በዚህ ሁኔታ የምታሳልፊው እያንዳንዱ ቀን ከጌታሽ መራቅን ለሸይጣን ቅርበትን እየሸለመሽ ያልፋል። ተውበት አድርገሽ ወደ ጌታሽ እስክትመለሺ ድረስ የእርግማን በር ከሰማይ ተከፍቶብሻል። በየቀኑ ወደ ቀብር እየቀረብሽ ነው። የሞት መልአክም ነፍስሽን ሊረከብ ተዘጋጅቶ እየጠበቀ ነው። አልዒምራን " ነፍስ ሁሉ ሞትን ቀማሽ ናት። ምንዳዎቻችሁንም የምትሞሉት በ ትንሳኤ ቀን ብቻ ነው። ከ እሳትም የተራቀና ገንተትን የተገባ ሰው በርግጥ ምኞቱን አገኘ። ቅርቢቱም ህይወት የመታለያ መሳሪያ እንጂ ሌላ አይደለችም" አሊዒምራን 185
እህቴ ሆይ! የተውበት ባቡር ሳያመልጥሽ ፈጥነሽ ተሳፈሪ! እህቴ ሆይ! ከነግ በፊት ዛሬን አስቢና አስተውይ! እህቴ ሆይ! ግዜው ከማለፉ በፊት አሁን ተመለሺ!
ሁዳ መልቲሚዲያ / ሪሳላ ቁ.1
ያግኙን፦ 0944787980 / t.me/huda4eth
ይህን ጽሑፍ በ(PDF) ለማውረድ አውርድ የሚለውን ይጫኑት
1 Comments
አሠላምአልይኩም
ReplyDelete