Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ስለ የኢስላም ነብይ ሙሐመድ (ሰለላሁ ዓይሂ ወሰለም) ምን ያህል ያውቃሉ?

 



ስለ የኢስላም ነብይ ሙሐመድ (ሰለላሁ ዓይሂ ወሰለም) ምን ያህል ያውቃሉ?


በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩህሩህ  በጣም አዛኝ በሆነው።

 ምስጋና ለአለማቱ ጌታ አላህ የተገባ ነው:: የአላህ ሰላትና ሰላም በመልዕክተኛው በቤተሰቦቻቸውና በባልደረቦቻቸው እንዲሁም የእነርሱን ጎዳና በተከተሉ ላይ ይሁን::

በዚህ ፅሁፍ ከላይ በተጠቀሰው ርዕስ ዙሪያ በፕሮፌሰር ሸይኽ ሷሊህ ሲንዲይ (በመዲና ዩኒቨርሲቲ (የዓቂዳ) ኡሱሉ-አዲን ትምህርት ክፍል መምህር) በምስል የተዘጋጀውን አጭር መልዕክት ወደ አማርኛ ቋንቋ በመመለስ ለማቅርብ እሞክራለሁ:: ይህም ሙስሊሙን ጨምሮ አብዛኛው የዓለማችን ማህበረሰብ የመልዕክተኛውን (ሰለላሁ ዓይሂ ወሰለም) ማንነት እና ስብዕናን በተመለከት የሚፈፀሟቸውን ስህተቶች ከማረም አንፃር ሲሆን ሆን ብለው የእርሳቸውን ክብር ለማጉደፍ ለተነሱ ጎራዎች ደግሞ የማይሳካላችው መሆኑን ለመንገርም ጭምር ነው::

ፕሮፌሰር ሸይኽ ሷሊህ ሲንዲይ መልዕክታቸውን እንዲህ በማለት ይጀምራሉ፡-


አላህ(ሱ.ወ) ፍጡራንን ያለ አላማ አልፈጠርቸውም በከንቱም አልተዋቸውም:: ይልቅ እርሱን በምን መልክ እንደሚያመልኩ የሚያብራሩ የህይወት መንገድን ገልፀው የሚያሳዩ ለምድራዊም ይሁን ለወዲያኛው ዓለም ስኬት የሚያበቋቸውን መልዕክተኞችን ልኮላቸዋል::

መልዕክተኞች በቁጥር ብዙ ሲሆኑ ከነርሱም መካከል ኑህ ኢብራሂም ኢስሃቅ ያዕቁብ ሙሳ ዳውድ ሱለይማን እንዲሁም ዒሳ በሁሉም ላይ የአላህ ሰላትና ሰላም ይሁን እንደ ምሳሌ የሚጠቀሱ ናቸው::

አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ ከዒሳ ዓለይሂ አሰላም  በኋላ ሙሀመድን ሰለላሁ ዓይሂ ወሰለም የነብያት ማሳረጊያ፣ መልዕክታቸውን የመጨረሻ መልዕክትና መፅሀፋቸውን (ቁርአንን) የሰማያዊ መፀሀፍት መደምደሚያ አድርጎ ላካቸው።

ስለዚህም መልዕክታቸው ሁሉን ያካተተ፣ የተሟላ፣ የሰው ልጆችን ብቻ ሳይሆን አጋንንትን ጭምር የሚያጠቃልልና ለሁሉም ዘመናት እና ቦታዎች የሚስማማ ሆኗል ።

 መልእክታቸው መልካም ሆኖ ወደ እርሱ ሳያመላክት እኩይ ሆኖ ከእርሱ ሳያስጠነቅቅ ያለፈው ነገር የለም።

 ከተላኩበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ዓለም ፍፃሜም እሳቸው ይዘውት ከመጡት እምነት (ዲን) ውጪ አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ ሌላን አይቀበልም።

 ለጥቂት ደቂቃዎች ከእኝህ የተከበሩ ነብይ የህይወት ታሪክ ጋር ቆይታ ልናደርግ እወዳለሁ። 

ይህም ከመልካም ስነ-ምግባራቸው እና የመጠቀ ስብዕናቸው የተወሰነውን እንድንተዋውቅ ነው።

ስማቸው ሙሐመድ ኢብኑ ዓብዲላህ ኢብኑ ዓብዲልሙጠሊብ አል-ሀሺሚይ አል-ቁረሺይ ሲባሉ የዘር ሐረጋቸውም በጣም የተከበር እና ምርጥ የዘር ሐርግ ነው።

እኝህ የተከበሩ ነብይ በ571 (አመት ልደት) በመካ ከተማ የተውለዱ ሲሆን ከመወለዳቸው በፊት አባታቸው በመሞቱ የቲም (ለአካለ መጠን ከመድረሱ በፊት አባቱን በሞት ያጣ) ልጅ ሆነው አድገዋል።

የማይፅፉ እና የማያነቡ የነበሩ ሲሆን (በህይወት ዘምናቸው) አንድም መስመር አንብበውም ይሁን ፅፈው አያውቁም። በፍፁምም ስንኝን ተሰኝተው የማያውቁ ጨዋ እና የተከብሩ ነበሩ።

ወገናቸው በእውነተኝነት፣ በታማኝነት እና በመልካም ስነ-ምግባራቸው የሚያውቃቸው ስለነበረም ከነብይነት በፊት “ታማኙ” በሚል ቅፅል ስም ይጠራቸው ነበር።

እድሜያቸው አርባ ዓመት ሲሞላ አላህ መልዕክተኛው አድርጎ የላካቸው ሲሆን በስልሳ ሶስት ዓመታቸው የዚህን ዓለም በሞት ተለይተዋል።

ምንም እንኳ በዚህ አጭር መልዕክት ስለ መልካም ስነ-ምግባራቸው እና ስለመጠቀው ስብዕናቸው ሁሉ መተንተን የሚከብድ ቢሆንም ነገር ግን የተወሰነውን ቀንጭበን ለማቅረብ እንሞክራለን።

ዝርዝር የህወት ታሪካቸውን ለማወቅ ለሚፈልጉ ስለ እሳቸው ገድል የሚተርኩ መፃህፍትን እንዲያነቡ እንመክራለን።

የህይወት ታሪካቸውን የሰው ልጆች ሁሉ ሊያጤኑት እና ሊያስተነትኑት የሚገባ ነው። እንዴታ!! እኝህ የአላህ መልዕክተኛ የማይፅፉ እና የማያነቡ ሆነው ባስተላለፉት መልዕክት የመላው ሰብዓዊ ፍጡር ታሪክ ተቀይሮ ሲያበቃ። ከክፍለ ዘመን ባነሰ ጊዜ ውስጥም መልዕክቱን የተቀበሉ ሀገራት በምዕራቡ በኩል ከሳዑዲ (ሂጃዝ) አንስቶ እስከ አፍሪካ ጫፍ በምስራቁ አቅጣጫም እስከ ቻይና ድንበር የደረሱ ሲሆን!!

በእርግጥም የአላህ መልዕክተኛ ከሰው ዘር በሙሉ የላቀ ስነ-ምግባርና ስነ-ስርዓት ባለቤት ነበሩ። አላህም በጥሩ ስነ-ስርዓት አንፆ ለዚህ ማዕረግ አብቅቷቸዋል።

ከሰው ልጆች ሁሉ ታጋሽ፣ ፍትሀዊ፣ ጨዋ፣ ለጋስ፣ ትሁት እና እጅግ በጣም የሚተናንሱ፣ ያገለገለ ጫማቸውን በእጃቸው የሚጠግኑ፣ የተቀደደ ልብሳቸውን የሚጥፉ እንዲሁም በቤት ውስጥ ስራ ቤተሰባቸውን የሚረዱ ነበሩ።

እጅግ አይናፋር የአንድን ግለሰብ አተኩረው ፊት ለፊት የማይመለከቱ፣ ከማንኛውም ሰው ግብዣ ቢቀርብላቸው ግብዣውን የሚቀበሉ፣ ምንም ትንሽ እንኳ ቢሆን ስጦታን የማይንቁ፣ ውለታን የሚመልሱ፣ የጌታቸው ክብር እና ድንበር ሲነካ የሚቆጡ፣ በግል ጉዳያቸው ሰዎች ድንበር ሲያልፉባቸው ይቅር የሚሉ፣ ህሙማንን የሚጠይቁ፣ ሙታንን የሚቀብሩ፣ ያለ አጃቢ እና ጠባቂ የሚንቀሳቀሱ፣ ያገኙትን የሚለብሱ፣ ከመጓጓዣ በተገኘው የሚጓጓዙ ነበሩ። የቀረበውን የሚመገቡ፣ በፍፁም ምግብን የማያነውሩ፣ ከድሆች ጋር የሚቀመጡ፣ ከሚስኪኖች ጋር የሚበሉ፣ ትላልቆችን የሚያከብሩ፣ ዝምድናን የሚቀጥሉ፣ ከልበ ደርቆች (ንግግር እና ተግባር) የሚታጋሱ፣ ለይቅርታ ጠያቂዎችም ይሁን ለስህተተኞች ይቅር ባይ ናቸው። ይቀልዳሉ ነገር ግን እውነትን እንጂ አይናገሩም።  ይስቃሉ ነገር ግን አያስካኩም ነበር።  

ድሀን ስለድህነቱ የሚንቁ ንጉስን ስለ ንግስናው የሚፈሩ አልነበሩም። ይልቁን ሁለቱንም በእኩልነት ወደ እምነት (ዲን) ይጠሩ ነበር። ልበ ደንዳናና ደረቅ እንዲሁም በየገበያው የሚጮሁም አልነበሩም። ማነኛውም ሰው ወደ እሳቸው ጉዳዩን ይዞ ቢመጣ ቢያስፈፅሙለት እንጂ ችላ የማይሉ፣ ማግራትን የሚወዱ፣ ማክበድን የሚጠሉ፣ ያገኙትን በሰላምታና በመጨበጥ የሚቀድሙ እንዲሁም የጨበጣቸውን ሰው እጅ እርሱ እስኪለቃቸው ድረስ የማይለቁ ነበሩ።

 ሰዎች በተሰባሰቡባቸው ቦታዎች ከደረሱበት የሚቀመጡ፣ ከባልደረቦቻቸውም የተለይ መቀመጫ ያልነበራቸው ናቸው። ወደ ቤታቸው የሚመጣን እንግዳ መቀመጫ ትራሳቸውን በመስጠት ከራሳቸው እሱን በማስበለጥ የሚያከብሩ፣ የሚያውቃቸው ሁሉ እርሳቸው ዘንድ ከሰዎች ሁሉ ተወዳጅ እርሱ መሆኑን እስኪያስብ ሲያናግሩት ፊት የማይነሱ፣ ጆሮአቸውን የሚያውሱ እንዲሁም ፈገግታን የተላበሱ ነበሩ። 

ባልደረቦቻቸውን በማክበርና በማቅረብ‐ ሕፃናትን ሳይቀር ‐ በጥሩ ቅጽል ስማቸው የሚጠሩ እንዲሁም ሕፃናትን ለማላመድ የሚያጫውቱ ነበሩ። በጥቅሉ ከሰው ልጆች በአጠቃላይ ለሰብዓዊ ፍጡራን ሁሉ ሩህሩህ፣ ቅን እና ጠቃሚ ነበሩ ማለት እችላልሁ።

ይህን የመልዕክተኛውን እጅግ ማራኪ ስብዕና ልዳስስ የሞከርኩበትን አጭር ንግግሬን “የዚህን ሙስሊም ያልሆን ነገር ግን (በርሳቸው ማንነት ላይ) ሚዛናዊ የነበረውን ግለሰብ ንግግር እናድምጥ” በማለት አጠናቃለሁ።

እሱም ታዋቂው እንግሊዛዊ ፈላስፋ ቶማስ ካርሊያል(1795-1881 እ.ኤ.አ) እማኝነት ነው “አል-አብጣል” On Heroes And Hero Worship And the Heroice በሚል ርዕስ በፃፈው መፅሀፍ ላይ ስለ መልዕክተኛው ሙሀመድ በሰፊው የገለፀ ሲሆን ናሙና ሊሆን የሚችለውን ንግግሩን እንደሚከተለው እጠቅሳለሁ። ንግግሩን ለክርስቲያን ወገኖቹ እንዲህ በማለት ነበር የጀመረው:—

“እጅግ አሳፋሪ ከሆኑ ነገሮች አንዱ በዚህ ክፍለ ዘመን ካሉ ሰዎች መካከል “የእስልምና ሀይማኖት ውሸት ነው ሙሀመድም አታላይ እና አስመሳይ ነው” ብሎ የሚናገርን ሰው ማድመጥ ነው። እንዲህ ዓይነት በየቦታው እየትሰራጩ ያሉ የማይረቡ እና አሳፋሪ ንግግሮችን ልንዋጋቸው ሀላፊነት አለብን። ይህ መልዕክተኛ ያስተላለፈው መልዕክት ለአስራ ሁለት ክፍለ ዘመናት ከሁለት መቶ ሚሊዮን (ተጨባጩ ከ1.8 ቢሊዮን) በላይ ለሆኑ የሰው ልጆች አንፀባራቂ ብርሀን ከመሆን አልተወገደም። ታዲያ እንዴት ይህን ያህል ለቁጥር የሚያዳግት ብዛት ያላቸው ሰዎች የኖሩበት እና የሞቱበት መልዕክት ሀሰት እና ሽንገላ ነው ተብሎ ይታሰባል?!! እኔ ግን ይህን አይነት አመለካከት ልይዝ ፈፅሞ አይቻለኝም።” ንግግሩ እዚህ ላይ አብቅቶል

ከዚህ በላይ ያሳለፍናቸው ጥቂት ገለፃዎች ከመልዕክተኛው ድንቅ ባህሪያት አንፃር ባህርን በጭልፋ እንደሚባለው ቢሆንም እርሳቸውን ከመውደድ እውነተኝነታቸውን ከመመስከር ብሎም እርሳቸውን ከመታዘዝ እና በርሱ ላይ ሳይጨምሩ ፈለጋቸውን ከመከተል አንፃር ከሙስሊሞች የሚጠበቀው ሀላፊነት ከፍተኛ ነው።

በርሳቸው መልዕክተኝነት ያላመነ የርሳቸውን ፈለግ እና ታሪክ ላልተከተለው ማህበረሰብ የማስተላልፈው መልዕክት እንደሚከተለው ይሆናል። ይህ ከዚህ በላይ በጥቂቱ የዳሰስነው የኝህን ታላቅ ሰው ታሪክ ነው። ትኩረትህን ልትቸረው ልታጤነው ይገባል። በእውነት እና ከልብ ከመነጨ ርህራሄ የምጠይቅህ ከኝህ የአላህ መልዕክተኛ አንፃር ያለህን አቋም እንድትመረምረው ነው። ምንም ያህል ብትለፍ እና ብትደክም ከሰው ልጆች መካከል ከሳቸው ሌላ በዚህ አይነት መልኩ የተሟላ ስብዕና ያለው ሰው አታገኝም ይህ በራሱ በእርግጥ የሳቸውን የአላህ መልዕክተኝነት የሚያረጋግጥ ግልፅ መረጃ ነው።


✍️ ትርጉም ጣሀ አህመድ (1431ሂ)


Post a Comment

0 Comments