Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

አጠር ያሉ ዘካተል ፊጥርን የሚመለከቱ ህግጋቶች፣ ለሁሉም ሙስሊሞች


[አጠር ያሉ ዘካተል ፊጥርን የሚመለከቱ ህግጋቶች፣ ለሁሉም ሙስሊሞች]
"""""""""""""""""''
የፊጥር ሶደቃ (ዘካተል ፊጥር) ግዴታነትን የሚጠቁሙ ሶሂህ ሀዲሶች…
---------------------
ከዐብደላህ ኢብኑ ዑመር (ረዲየላሁ ዐንሁማ) ተይዞ «የአላህ መልእክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ሶደቀተል ፊጥርን ወይም የረመዷን ፊጥርን በወንድም በሴትም፣ በጨዋም በባሪያም፣ ከተምር አንድ ቁና ወይም ከገብስ አንድ ቁና (መስጠትን) ግዴታ አድርገዋል አለ። #ሰዎች ለትንሹም ለትልቁም (ለአዋቂም ለህፃንም) ከስንዴ ግማሽ ቁና መስጠት ያብቃቃል ብለዋል። አለ» ቡኻሪ 1511 ሙስሊም 984 ላይ ዘግበውታል።

ቡኻሪ 1503 ላይ በዘገበው ሌላ ዘገባ ነቢዩ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) «ሰዎች ወደ (ዒድ) ሶላት ቦታ ከመውጣታቸው በፊት እንዲሰጡ» አዘዋል የሚል ዘገባ አለ።

ከላይ "#ሰዎች" ያለው፣ ሙዓዊያን (ረዲየላሁ ዐንሁ) ፈልጎበት ነው፣ ሙዓዊያ ስልጣን ላይ ሲተካ ግማሽ ቁና ስንዴ መስጠት አንድ ቁና ገብስና መሰል ነገሮችን ከመስጠት እኩል ነው ብሎ ነበር፣ በቀጣዩ ሀዲስ እንደምናየው ደግሞ ሌሎች ሶሃቦች በነቢዩ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ጊዜ እንሰጥ እንደነበረው ስንዴውንም ቢሆን ሙሉ ቁና ነው ምንሰጠው ብለዋል።

ከአቢ ሰዒድ አል_ኹድሪይ (ረዲየላሁ ዐንሁ) ተይዞ፣ እንዲህ አለ:– «በነቢዩ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ዘመን ከምግብ አንድ ቁና እንሰጥ ነበር፣ ወይም ከገብስ አንድ ቁና፣ ወይም ከአይብ አንድ ቁና፣ አለያም ከዘቢብ አንድ ቁና (እንሰጥ ነበር)፣ ሙዓዊያ (ረዲየላሁ ዐንሁ) ስልጣን ላይ በተተካ ጊዜ ግን ስንዴ እየበዛ መጣ፣ ይህን ጊዜ (ሙዓዊያ) ከስንዴ አንድ እፍኝ የዚህን (የገብብስ መሰል ከላይ የተጠቀሱ ነገሮችን ማለቱ ነው) ሁለት እፍኝ ይተካል፣ አለ። ሀዲሱን ያስተላለፈልን ሶሃቢይ አቢ ሰዒድ:– እኔማ በነቢዩ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ጊዜ የማወጣው የነበረውን ያህል (አንድ ቁና) ከማውጣት አልወገድም። አለ» ቡኻሪ 1508 በዚሁ ቃል ዘግበውታል፣ ሙስሊም፣ አቡዳውድ ነሳኢይ፣ ትርሚዚይ፣ ኢብን ማጃና ኢማሙ አህመድ ዘግውታል።
አንድ ቁና በኪሎ ግራም ሲሰላ ከ2.5 እስከ 3 ኪሎ ነው ተብሏል።

ታላላቅ የኢስላም ሊቃውንቶች ከዚህ ጋር በተያያዘ ተጠይቀው የሰጡት ብይን (ፈትዋ) አጠር ባለ መልኩ የሚከተለው ነው…
----------------------

1, ዘካተል ፊጥር ፍርዱ ምንድነው?
:black_small_square: ኢብኑ ባዝ (አላህ ይዘንላቸውና) እንዲህ ይላሉ:–
“የፊጥር ዘካህ በሁሉም ሙስሊም በትልቁም በትንሹም፣ በሴቱም በወንዱም፣ በጫዋውም ሰው ሆነ በባሪያው፣ ግዴታ ነው።” [አልፈታዋ 14/197]

2, ዘካተል ፊጥር የሚሰጠው በምንድነው?
:black_small_square: ኢብኑ ባዝ (አላህ ይዘንላቸውና) እንዲህ ይላሉ:–
“ከምግም፣ ከተምር፣ ከገብስ፣ ከስንዴ፣ ከዘቢብ፣ አልያም በአመዛኙ የዑለማዎች ንግግር ከሌሎች ይህን ከመሳሰሉ፣ ሰዎች እንደ ሀገራቸው ከሚመገቡት ነገር (ለአንድ ሰው) አንድ ቁና ትሰጣለች።”

3, የዘካተል ፊጥር መስጫው (ማውጪያ) ጊዜው መቼ ነው ሊሆን የሚችለው?
:black_small_square: ኢብኑ ባዝ (አላህ ይዘንላቸውና) እንዲህ ይላሉ:–
“የማውጫ (የመስጫ) ጊዜዋ ከረመዷን በ28ኛው፣ በ29ኛው፣ በ30ኛው፣ ቀንና በዒዱ ንጋት ከሶላት በፊት ነው።” [አልፈታዋ 32/14–33]

4, የዘካተል ፊጥር ማውጫ ምክንያት ምንድነው?
:black_small_square: ሸይኽ ኢብን ዑሰይሚን (አላህ ይዘንላቸውና) እንዲህ ብለዋል:–
“ባሪያው አላህ በሰላም ስላስፈጠረውና ሙሉ ፆሙን (በህይወት እያለ) ስላስጨረሰው ምስጋናውን ይፋ ማድረጊያ ነው።” [አልፈታዋ 18/257]

5, ዘካተል ፊጥር ግዴታ የማትሆንበት ምን አይነት ሰው ነው?
:black_small_square: ሸይኽ ኢብን ዑሰይሚን (አላህ ይዘንላቸውና) እንዲህ ብለዋል:–
“ከአንድ አካል በስተቀር ግዴታ የማትሆንበት የለም!፣ እነርሱም ምንም የሌላቸው ድሆች ናቸው።” [አልፈታዋ 18/259]

6, ልጅን ዘካተል ፊጥር እንዲሰጥ ውክልና መስጠት ፍርዱ (ብይኑ) ምንድነው?
:black_small_square: ሸይኽ ኢብን ዑሰይሚን (አላህ ይዘንላቸውና) እንዲህ ብለዋል:–
“ማንኛውም ሰው ለልጆቹ በጊዜው እንዲከፍሉለት ውክልና መስጠት ይፈቀድለታል። በጊዜው በስራና በመሳሰሉ ጉዳዮች ከሚኖርበት ሀገር ውጪ ሆኖ ውጥረት ውስጥ ቢሆን (በጊዜዋ እንዲሰጥለት ውክልና መስጠት ይችላል)።” [አልፈታዋ 18/262]

7, ድሃና ዘካተል ፊጥር መቀበል የሚገባው ሰው፣ ዘካተል ፊጥርን እንዲቀበልለት ለሌላ ሰው ውክልና መስጠት ይችላልን?
:black_small_square: ሸይኽ ኢብን ዑሰይሚን (አላህ ይዘንላቸውና) እንዲህ ብለዋል:–
“ይህ ይፈቀድለታል” [18/268]

8, ዘካተል ፊጥር በሚሰጥ ጊዜ የተለየ የሚባል ዱዓ አለን?
:black_small_square: “ዘካተል ፊጥር በሚሰጥበት ጊዜ የሚባል የተለየ ዱዓ አናውቅም።” [ቋሚ የፈትዋ ኮሚቴ 9/387]

9, የዛከተል ፊጥርን ዋጋ በገንዘብ ማውጣት ይፈቀዳልን?
:black_small_square: ኢብኑ ባዝ (አላህ ይዘንላቸውና) እንዲህ ይላሉ:–
“በአብዘሃኛው የእውቀት ባለቤቶች ንግግር የዘካተል ፊጥርን ዋጋ በብር ቀይሮ ማውጣት አይፈቀድም። ምክንያቱም ነቢዩ صلى الله عليه وسلم እና ሶሀባዎች ከሚሰጡት ከነበረው ተቃራኒ ስለሆነ ነው።” [አልፈታዋ 14/32]
:black_small_square: ሸይኽ ኢብን ዑሰይሚን (አላህ ይዘንላቸውና) እንዲህ ብለዋል:–
“ከምግብ እህል (ምግብ ነክ) ነገር ካልሆነ ነገር ማውጣቱ አያብቃቃውም። ምክንያቱም ግዴታ የሆነችው ከምግብ ነውና።” [አልፈታዋ 18/265]

10, ዘካተል ፊጥር ለመስጠት እንደሌላው ዘካ፣ ግዴታ የሚሆንበት መጠን አለውን?
:black_small_square: ኢብኑ ባዝ (አላህ ይዘንላቸውና) እንዲህ ይላሉ:–
“ይህን ያህል ካልደረስ ግዴታ አይሆንበትም የሚባል ገደብ የለውም። ይልቅ ሙስሊም በሆነ ላይ ሁሉ ለራሱ፣ ለቤተሰቦቹ፣ ለሚስቱና ለልጆቹ እንዲሁም በሱ ሀላፍትና ስር ላሉት፣ አንድ ቀን ለሊቱን ጨምሮ ከሚመገበውና ከሚመገቡት ምግብ ከተረፈ፣ ማውጣቱ ግዴታ ይሆንበታል።” [አልፈታዋ 14/197]

11, ዘካተል ፊጥር የሚሰጠው መጠን ስንት ነው?
:black_small_square: ኢብኑ ባዝ (አላህ ይዘንላቸውና) እንዲህ ይላሉ:–
“ግዴታው ሰዎች ሀገራቸው ላይ ለምግብነት ከሚጠቀሙት ነገር አንድ ቁና ነው። በኪሎ በአማካኝ 3ኪሎ ነው።” [አልፈታዋ 14/203]

12, ዘካተል ፊጥርን፣ ዘካተል ፊጥር የሚሰጠው ሰው ከሚኖርበት ሀገር ውጪ ለሌላ ሀገር መስጠት ይፈቀዳልን?
:black_small_square: ኢብኑ ባዝ (አላህ ይዘንላቸውና) እንዲህ ይላሉ:–
“ሱንናው ዘካተል ፊጥር የሚሰጠው ሰው በሚኖርበት ሀገር ውስጥ ለሚገኙ ድሆች ዘካውን መስጠትና ወደሌላ ሀገር አለመውሰዱ ነው።” [አልፈታዋ 14/213]

13, ዘካተል ፊጥር ማህፀን ውስጥ ላለ (ላልተወለደ) ልጅ ማውጣቱ ግዴታ ይሆናልን?
:black_small_square: ሸይኽ ኢብን ዑሰይሚን (አላህ ይዘንላቸውና) እንዲህ ብለዋል:–
“ዘካተል ፊጥር መህፀን ውስጥ ላለ ልጅ በግዴታነት አይሰጥም፣ ነገር ግን በተወዳጅነት መንገድ መስጠት ይቻላል (ተወዳጅ ነው)።” [አልፈታዋ 18/263]

14, ዘካተል ፊጥር ሙስሊም ላልሆኑ ሰራተኞች መስጠት ይፈቀዳልን?
:black_small_square: ሸይኽ ኢብን ዑሰይሚን (አላህ ይዘንላቸውና) እንዲህ ብለዋል:–
“ዘካተል ፊጥርን ሙስሊም ለሆኑ ድሆች ካልሆነ በስተቀር ለሌላ መስጠት አይፈቀድም።” [አልፈታዋ 18/285]

15, የአንድ ሰው ዘካተል ፊጥር ለአንድ ሰው ብቻ ነው የምትሰጠው ወይስ ለተለያዩ ሰዎች ትከፋፈላለች?

:black_small_square: “የብዙ ሰዎችን ዘካተል ፊጥር ለአንድ ሰው ብቻ መስጠት ይፈቀዳል፣ ልክ ለተለያዩ ሰዎች በታትኖ መስጠት እንደሚቻለው።” [ቋሚ የፈትዋ ኮሚቴ: 9/377]

16, ዘካተል ፊጥርን ተቀብሎ የሚሸጥ ሰው ፍርዱ (ብይኑ) ምንድነው?

:black_small_square: “የወሰደው ሰው ለመውሰድ ተገቢ ከሆነ ከወሰደ በኋላ መሸጡም ይፈቀድለታል።” [ቋሚ የፈትዋ ኮሚቴ: 9/380]

17, ዘካተል ፊጥርን ያለ ምክንያት የዒድ ሶላት ተሰግዶ እስኪያበቃ ድረስ ማዘግየት ፍርዱ (ብይኑ) ምንድነው?
:black_small_square: ሸይኽ ኢብን ዑሰይሚን (አላህ ይዘንላቸውና) እንዲህ ብለዋል:–
“የዒድ ሶላት ተሰግዶ እስኪያበቃ ድረስ ማዘግየቱ ክልክል (ሀራም) ነው። ከዘካተል ፊጥርም አታብቃቃውም።” [አልፈታዋ 18/266]
ወላሁ አዕለም!!
✍🏻ኢብን ሽፋ ረመዷን 24/1441 ዓ. ሂ

Post a Comment

0 Comments