Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

“ይህ ነው እምነቴ” ሸይኽ ሙሐመድ ኢብኑ ዐብዱልወሃብ ዕምነትን ከአንደበታቸው



“ይህ ነው እምነቴ”

ሸይኽ ሙሐመድ ቢን ዐብዱልወሃብ
""""""""""""""""""""""""""""""""""""""
ሸይኽ ሙሐመድ ኢብኑ ዐብዱልወሃብ ዕምነትን ከአንደበታቸው
______

ባለፉት ዓመታት መስሊሞች ሃይማኖታቸውን በነፃነት መተግበር እንዳይችሉ በሰፊው ሲነዙ ከነበሩ ማስፈራሪያዎችና አግላይ ስያሜዎች መካከል “ወሃብያ” አንዱና ዋነኛው ነበር። ስያሜው ተውሒድ እና የመልዕክተኛውን ሱንና የሚከተሉ ሙስሊሞችን ለማሸማቀቅና ለማግለል የዋለ መሣሪያ ይሆን ብዙ ተብሏል። ከዚህም አልፎ በመንግስት ደረጃ በአክራሪነት የሚያስፈርጅ ወንጀል ይሆን ዘንድ በውጭ አካላት ይዘወር የነበረው መጅሊስ እና ከሊባኖስ የመጣው የአሕባሽ አንጃ ጀሌዎች ያደረጉት ግፊት ሙስሊሙን ማሕበረሰብ እጅግ አሳዛኝ የታሪክ ጠባሳ ጥሎበት አልፏል። የተውሒድ ተጣሪዎች ላይ ወሃብያ የሚለውን ስያሜ ለመለጠፍ መነሻ ያደረጉት የተውሒድ ተጣሪና የዑማው ባለ ውለታ የሆኑትን ሸይኽ ሙሐመድ ቢን ዐብዱልወሃብ ድርሳናት እና አስተምህሮዎች ትቀበላላችሁ የሚል ነው። ለኢስላም ብዙ ውለታ የዋሉ ታላላቅ ሊቃውንቶችን መተቸት እና በኩፍር መፈረጅ ለነሱ ቀላል መሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነው። በተለይም ባለፉት ዓመታት ስልጣናቸውን ተገን በማድረግ በመንግስት ሚዲያዎችን ሳይቀር ሸይኹን እና እምነታቸውን ለማጥላላት የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ማራመጃ አድርገዋቸው ከርመዋል። ከምዝበራና ብክነት የተረፈውን የሙስሊሙን ሀብት በመጠቀም በሊባኖስ ነውጥ ፈጣሪነታቸው የታወቁ የአሕባሽ አንጃ መሪዎችን በማምጣት የመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ጭምር ተጠቅመው ተከታታይ የስም ማጠልሸት አሉባልታዎችን ነዝተዋል። ለመሆኑ በሸይኹ ላይ ሲነዙ የነበሩ ትችቶችን በመገምገም እውነታ ነው ወይስ አሉባልታ የሚለውን ለመወሰን በጠላቶቻቸው የሚሰነዘሩባቸውን ክሶች መሰረት ከማድረግ ይልቅ የሸይኹን የራሳቸውን ንግግርና ድርሳናት ማመሳከር አጠያያቂ ያልሆነ መፍትሔ በመሆኑ ስለ ሸይኹ እምነት ከራሳቸው አንደበት ልናስነብባችሁ ወደናል፤ ፍርዱን ለአንባብያን እንተዋለን።

የአላህ እዝነት በእሳቸው ላይ ይሁንና የቀሲም ህብረተሰብ በአንድ ወቅት ስለ ሸይኹ እምነት እና አካሄድ ጠይቋቸው የሚከተለውን ደብዳቤ ፅፈዋል፡-
‹‹አላህና በኔ ዘንድ ያሉት መላዕክቶቹ መስካሪዎቼ ናቸው... እናንተም ምስክሮቼ ሁኑ፤ እኔ የማምነው፤ አህለ ሱና ወልጀመዓ፣ ፊርቀቱ ናጂያ በሚያምኑበት እምነት ብቻ ነው። በቅድሚያ፤ በአላህ ማመን፣ በመላዕክቶቹ፣ በኪታቦቹ (በመፃህፍቱ)፣ በመልዕክተኞቹ፣በትንሳዔው ቀን እንዲሁም በክፉውም በደጉም ቀደር ማመን ነው እምነቴ...

በአላህ ማመን ስል፤ አላህ ስለራሱ በቁርዓንና በመልዕክተኛው ﷺ አንደበት ስለአላህ ባህሪያት የገለፀውን ሁሉ ያለምንም ትርጉም ማዛባት(ተህሪፍ) እና ትርጉም ማሳጣት(ተእጢል) ማመን ሲሆን፤ እንደ አላህ ያለ ማንም እንደሌለና አምሳያ እንደሌለው፣ ሰሚና ተመልካች አምላክ መሆኑን አምናለሁ። አላህ እራሱን የገለፀበትን ባህሪ ውድቅ አላደርግም። ንግግሩን በሌላ አልቀይርም፣ መልዕክቶቹንም አላዛባም። ስሞቹንና አንቀጾቹን አላጣምም፣ ይህን ይመስላልም አልልም። የላቀዉን አላህ ባህሪዎች ከፍጡራን ባህሪ ጋር አላመሳስልም፣ምክኒያቱም የላቀው ጌታዬ አቻም ይሁን ቢጤ የለውምና በፍጡራኑ አይገመትም።

ጥራት የተገባው አምላካችን ስለራሱም ይሁን ስለሌላው ከፍጡራኑ ይበልጥ አዋቂ፣ ንግግሮቹም የእውነቶች ሁሉ ዕውነት እና ውብ ናቸውና፤ አላህን ከፍጡራን ጋር በማመሳሰል “ተምሲል” እና ስለባህሪያቱ ምንነት ግምታቸውን በመናገር “ተክዪፍ” የታወቁት፤ የሐቅ ተጻራሪ ቡድኖች ለእርሱ ከሰጧቸው መገለጫዎች ሁሉ አላህ እራሱን አጥርቷል። እንደዚሁ ባህሪዎቹን ተቃርነው አንቀበልም፣ አናጸድቅም ያሉት “ሙዓጢላዎች” እርሱን ከሚገምቱበት ነገር ሁሉ አላህ ራሱን አጥርቷል። አላህ እንዲህ ይላል፤
﴿سُبحَٰنَ رَبِّكَ رَبِّ ٱلعِزَّةِ عَمَّا يَصِفُونَ١٨٠ وَسَلَٰمٌ عَلَى ٱلمُرسَلِينَ١٨١ وَٱلحَمدُ لِلَّهِ رَبِّ ٱلعَٰلَمِينَ١٨٢﴾ [الصافات: 180-182]
«የማሸነፍ ጌታ የሆነው ጌታህ ከሚሉት ሁሉ ጠራ፤ በመልክተኞቹም ላይ ሰላም ይኹን፤ ምስጋናም ለዓለማት ጌታ ለአላህ ይሁን» አልሳፋት 180-182

የቀሲም ህብረተሰብ በአንድ ወቅት ስለ ሸይኹ እምነት እና አካሄድ ጠይቋቸው የሚከተለውን ደብዳቤ ፅፈዋል፡-
ቀጥተኛውን መንገድ የሚከተሉት የስኬት ቡድኖች “አል-ፊርቀቱ ናጂያ” በአቋማቸው፤ የአላህ ተግባርን በተመለከተ፤ «የሰው ልጅ ምንም ነገር የመፈጸም ፈቃድና ችሎታ የሌለው ለድርጊቶች የተገራ ነው» በሚሉት “ጀብሪያዎች” እና «የሰው ልጅ ማንኛውንም ነገር ለመተግበር ሙሉ ፈቃድና ችሎታ አለው» በሚሉት “ቀደሪያዎች” መካከል ናቸው።

የአላህን የተስፋ ቃል (ዋዕድን) በተመለከተ፤ አቋማቸው በአጉል ተስፈኛ (ሙርጂዓዎች) እና በተስፋ ቢሶቹ (ወዒዲያዎች)መካከል ነው።

ኢማንን እና ዲንን በተመለከተ «ኢማን ተግባርን አያካትትም፤ አይቀንስም አይጨምርም፤ ወንጀልም ኢማንን አይጎዳም» በሚሉት “ጀህሚያ እና ሙርጂዓ” እንዲሁም «ተግባር ከኢማን ስለሆነ ወንጀል የፈፀመ ሁሉ ኢማኑ ተገፏል ካፊር ነው» በሚሉት “ሀሩሪያ እና ሙዕተዚላ” መካከል ናቸው፣ ሰሀቦችን በተመለከተ፤ ጥቂት የነብዩ ﷺ ቤተሰብ የሆኑ ሰሀቦችን እስከማምለክ በደረሱት “ረዋፊድ (ሺዓዎች)” እና ሰሀቦችን ካፊር ናቸው በሚል እስከመዋጋት በደረሱት አማፂያን» “ኸዋሪጆች” መካከል ናቸው፡፡

 እኔ የማምነው፤ ቁርዓን ፍጡር ሳይሆን ከአላህ የመጣ እና ወደ እርሱ የሚመለስ የእርሱ ንግግር መሆኑን ነው። አላህ በግልጽ ተናግሮታል፤ በእርሱ እና በባሮቹ መካከል አምባሳደር ወደሆኑት ታማኙ ባሪያው እና መልዕክተኛው ሙሐመድ ﷺ አውርዶታል፡፡

 አላህ የፈለገውን ሁሉ አድራጊ መሆኑን አምናለሁ፡፡ ከአላህ ፍላጎት ውጪም ተፈፃሚ የሚሆን ነገር የለም፡፡ ከእርሱ የይሁንታ ፈቃድ ውጪ የሚከሰት ነገር የለም፡፡ ከአላህ ውሳኔ የሚወጣ ፈፅሞ የለም፡፡ እርሱ ካስተናበረው ውጪም የሚከሰት ነገር የለም፡፡ ከተገደበው የአላህ ውሳኔ እና ፈቃድ የሚወጣ አይኖርም፤ በጥብቁ ሰሌዳ (ለውሀል መህፉዝ) ላይ ከተፃፈለት ውጪ ማንም አይተላለፍም፡፡

 የአላህ መልዕክተኛ ﷺ ከሞት በኋላ ይከሰታል፣ ይኖራል ብለው የነገሩንን ሁሉ አምንበታለሁ፡፡ የቀብር ውስጥ ፀጋንም ይሁን ቅጣትን አምንበታለሁ፡፡ ህይወት ወደየ ግለሰቡ አካል እንደምትመለስ እና የሰው ልጅ ሳይጫማ እርቃኑን ያልተገረዘ ሆኖ በትንሳዔው እለት በመሰብሰቢያው ሜዳ ለጌታው እንደሚቆም አምናለሁ፡፡ በዕለቱ ፀሐይ በጣም ትቀርባቸዋለች፣ ሚዛኖች ለምዘና ይቀመጣሉ፣ የባሮችም ተግባራት ይመዘናሉ፣ መልካም ተግባራቸው ሚዛን የደፋላቸው የሚድኑ ናቸው። ሚዛኑ የቀለለባቸው ግን ነፍሳቸውን የከሰሩ ሲሆኑ በጀሀነምም ዘውታሪዎች ናቸው፡፡ የባሮች ተግባር የተፃፈባቸው ድርሳናት ይዘረጋሉ፡፡ ከፊሉ በቀኝ እጁ መፀሐፉን የሚወስድ ሲሆን ከፊሉ ደግሞ በግራው የሚቀበል መሆኑን አምናለሁ፡፡

በትንሳዔው ሜዳ ላይ ለነብያችን ለሙሐመድ ﷺ ሀውድ የተሰኘ ኩሬ እንዳለ እምነቴ ነው። ውሀው ከወተት የነጣ፣ ከማር የጣፈጠ፣ መጠጫዎቹ በሰማይ ከዋክብት ቁጥር ልክ የሆኑ፣ አንዴ የተጎነጨ ሰው ከዛ በኋላ በፍፁም የማይጠማው መሆኑ እምነቴ ነው፡፡ ሰዎች በተግባራቸው መጠን በጀሀነም አፋፍ ላይ በተዘረጋው የሲራጥ ድልድይ ላይ እንደሚያልፉ አምናለሁ፡፡

 በነብዩ ﷺ አማላጅነት “ሸፋዓ” አምናለሁ፤ የመጀመሪያው አማላጅ መሆናቸውን እና እንዲያማልዱም ከሁሉም በፊት እንደሚፈቀድላቸው አምናለሁ። የእርሳቸውን ምልጃ የሚፃረር የጥመት ባለቤት የቢድዓ አራማጅ እንጂ ሌላ አይደለም፤ ይሁንና አማላጅነት ከአላህ ፍቃድና ውዴታ በኋላ የሚሆን ነው፡፡

وَلَا يَشْفَعُونَ إِلَّا لِمَنِ ارْتَضَى - الأنبياء: 28
«ለወደደውም ሰው እንጅ ለሌላው አያማልዱም» አል አንቢያዕ 28

مَنْ ذَا الَّذِي يَشْفَعُ عِنْدَهُ إِلَّا بِإِذْنِهِ - البقرة: 255
«ያ እርሱ ዘንድ በፈቃዱ ቢኾን እንጅ የሚያማልድ ማነው?» አልበቀራ 255

وَكَمْ مِنْ مَلَكٍ فِي السَّمَاوَاتِ لَا تُغْنِي شَفَاعَتُهُمْ شَيْئًا إِلَّا مِنْ بَعْدِ أَنْ يَأْذَنَ اللَّهُ لِمَنْ يَشَاءُ وَيَرْضَى - النجم: 26
«በሰማያት ውስጥ ካሉ መላዕክትም ብዙዎች፤ አላህ ለሚሻውና ለሚወደው ሰው ከፈቀደ በኋላ ቢኾን እንጅ ምልጃቸው ምንም አትጠቅምም» አልነጅም 26

እርሱም ከተውሒድ ውጪ ምንም አይወድምና ለተውሒድ ባለቤቶች እንጂ ለማንም አይፈቀድም፡፡

 ሙሽሪኮች ከምልጃ ምንም ድርሻ አያገኙም፡፡ አላህም እንዳለው፡-
فَمَا تَنْفَعُهُمْ شَفَاعَةُ الشَّافِعِينَ - المدثر: 48
«የአማላጆችም ምልጃ አትጠቅማቸውም» ሱረቱል ሙደሲር 48
ጀነትና እሳት ፍጡራን መሆናቸውን፣በአሁኑ ሰዓትም እንዳሉ አምናለሁ።የሚጠፉና የሚወገዱ አይደሉም።

 የትንሳዔው ዕለት ባሮች በዓይናቸው ጌታቸውን እንደሚመለከቱ አምንበታለሁ፣ልክ ጨረቃ ፍንትው እና ድምቅ ባለችበት ምሽት ምንም ነገር ከእይታ እንደማይደበቅባቸው ሁሉ፤ እነርሱም በግልፅ ጌታቸውን ያያሉ፡፡

ነብያችን ሙሐመድ የነብያት እና የመልዕክተኞች መደምደሚያ መሆናቸው እምነቴ ነው፡፡ የትኛውም የአላህ ባሪያ በመልዕክታቸው ካላመነ ነብይነታቸውን ካልመሰከረ እምነቱ ትክክለኛ አይሆንም።

ከህዝባቸው መካከል በላጩ አቡበከር ሲዲቅ ናቸው፣ ከዚያም ዑመሩል ፋሩቅ፣ ከዚያም ዑስማን ዙኑረይን፣ ቀጥሎም ተወዳጁ ዐሊይ ናቸው። ከዚያም በጀነት ከተበሰሩት አስሩ ሰሀቦች የተቀሩት (ከአራቱ ኸሊፋዎች ውጪ ያሉት )፣ ከዚያም የበድር ዘማቾች፣ ቀጥሎም በይዐቱ ሪድዋን የተባለውን ቃልኪዳን በዛፍ ስር ለነብዩ የገቡት ባልደረቦች፣ ከዚያም ቀሪዎቹ ሶሀቦች ናቸው ፡፡ አላህ ሁሉንም ስራቸውን ይውደድላቸው።

 የመልዕክተኛውን ባልደረቦች እወዳቸዋለሁ፣ መልካም ዝናቸውንም አነሳለሁ፣ ተግባራቸውንም እወድላቸዋለሁ፣ ከጌታችንም ምህረትን እለምንላቸዋለሁ፤ የእነርሱን ነውር ከመጥቀስ እቆጠባለሁ፣ በመካከላቸው በተፈጠረው ጉዳይ ዙሪያም ዝምታን እመርጣለሁ፡፡ የአላህን ትዕዛዝ በመተግበር የተሰጣቸዉን ደረጃ አምኜ እቀበላለሁ። አላህ እንዲህ ይላል፤
وَالَّذِينَ جَاءُوا مِنْ بَعْدِهِمْ يَقُولُونَ رَبَّنَا اغْفِرْ لَنَا وَلِإِخْوَانِنَا الَّذِينَ سَبَقُونَا بِالْإِيمَانِ وَلَا تَجْعَلْ فِي قُلُوبِنَا غِلًّا لِلَّذِينَ آمَنُوا رَبَّنَا إِنَّكَ رَءُوفٌ رَحِيمٌ - الحشر: 10
«እነዚያም ከበኋላቸው የመጡት፤ «ጌታችን ሆይ! ለእኛም ለእነዚያም በእምነት ለቀደሙን ወንድሞቻችን ምሕረት አድርግ፣ በልቦቻችንም ውስጥ ለእነዚያ ለአመኑት (ሰዎች) ጥላቻን አታድርግ፤ ጌታችን ሆይ! አንተ ርኅሩህ አዛኝ ነህና» ይላሉ። ሱረቱል አል-ሐሽር 10

 የምዕመናን እናቶች (የነብዩ ባልተቤቶች) ከማንኛውም መጥፎ ነገር የፀዱ ንፁሀን መሆናቸውን አምናለሁ፤ እወዳቸዋለሁም።

 አውሊያዕ (የአላህ ወዳጆች) ከራማ እና ነገሮችን የሚለዩበት “ሙካሸፋት” እንዳላቸው እምነቴ ሲሆን፤ ይሁንና ከአላህ ሐቅ ምንም ድርሻ የላቸውም። ከአላህ በስተቀር ማንም የማይችለውን ጉዳይ ከእነርሱ አይከጀልም፡፡

 አላህና መልዕክተኛው ﷺ ከመሰክሩላቸውና ከመሰክሩባቸው ግለሰቦች ውጪ ለማንም “የጀነት ወይም የእሳት ነው” ብዬ አልመሰክርም፣ ይሁንና፤ መልካም ስራን ለሚተገብር ጀነትን ተስፋ አደርጋለሁ፤ ለጥፋተኛም እሰጋለሁ። ማንኛውንም ሙስሊም ወንጀል ስለፈፀመ ካፊር አልልም፤ ከእስልምና ኬላም አላስወጣውም፤

ነብዩ ﷺ ከተላኩበት ዘመን አንስቶ፤ የዚህ ኡማህ የመጨረሻ ትዉልድ ደጃልን እስከሚጋደሉበት ወቅት ድረስ ቀጣይነት ባለው መልኩ ጂሀድ ተደንግጓል። አስፈላጊ በሆነበት ወቅት ሸሪዓዊ ህግጋቱን ጠብቆ ይፈጸማል። ጂሀድን የአምባገነኖች አድሎም ይሁን የፍትሀዊያን ፍትህ ውድቅ አያደርገዉም። ከመጥፎም ይሁን ጥሩ የሙስሊም መሪ ጋር ጂሀድ እንደተደነገገ አምናለሁ። የጀመዓ ሰላት ከእነርሱ ኋላ ተከትሎ መስገድም ይቻላል፡፡

 የሙስሊም መሪዎችን መስማት እና መታዘዝ ግዴታ መሆኑን የምቀበለው ነው፣ ጥሩዎችም ይሁኑ ክፉዎች የአላህን ተእዛዝ እንድንጥስ እስካላዘዙን ድረስ የመታዘዝ ግዴታ እንዳለብን አምናለሁ፡፡ የሙስሊሞች መሪን ተክቶ ኸሊፋ በመሆን ስልጣን የያዘ እና ሙስሊሙ ህብረተሰብ ወዶ የተቀበለውን መሪ እንዲሁም በጦር አሸንፎ ስልጣን የያዘ እና መሪ የሆነን ሰው መታዘዙ በርሱም መተዳደሩ ግዴታ ነው፡፡ እርሱ ላይ አምፆ መውጣት የተከለከለ ነው። የቢድዓ (የፈጠራና ፍልስፍና) ሰዎችን ማኩረፍና ተውበት እስኪያደርጉም እነርሱን መራቅ ይገባል እላለሁ፤ ይፋ በሚያደርጉት አቋማቸው መሰረት ውሳኔዬን አሳልፍባቸዋለሁ፣ በልባቸው የደበቁትን ግን ለአምላኬ እተወዋለሁ፣ ማንኛውም ቢድዓ ፈጠራ መሆኑንም አምናለሁ፡፡

ኢማን ወይም እምነት ማለት፤ በአንደበት መናገር (መመስከር)፣ በሰዉነት በአካላት መተግበር፣ በልቦና ማመን መሆኑን እና በመልካም ተግባር የሚጨምር በኃጢያት ደግሞ የሚቀንስ መሆኑን አምናለሁ። ኢማን ከ70 በላይ እርከኖች አሉት፤ ከፍተኛው ከአላህ ውጪ ሌላ አምላክ አለመኖሩን መመስከር ሲሆን ዝቅተኛው ደረጃ ደግሞ ከመተላለፊያ ጎዳና ላይ አስቸጋሪ ነገርን ማስወገድ ነው።

መልካምን ማዘዝ እና ከመጥፎ መከልከል ጽዱ የሆነው የሙሐመድ ﷺ ድንጋጌ ግዴታ በሚያደርገው መሰረት ሊፈጸም እንደሚገባው አምናለሁ፡፡ ይህ የምሞረከዝበት የምታገልበት እምነቴ ነው፣ እኔ ዘንድ ያለውን ድርሳኔን መልዕክቴን እንድታጠኑ የማስብላችሁ የምጓጓላችሁ ብሎም የምጨነቅላችሁ ጉዳይ ነው፡፡ አላህም በምንናገረው ላይ ተቆጣጣሪ ነውና›› ሲሉ ባጠቃላይ ህብረተሰቡ ላይ ክፍተት የተገባበትን ጉዳይ እና የራሳቸውን አቋም ገሀድ አድርገዋል፡፡ ሸይኹል ኢስላም ሙሐመድ ኢብን ዐብዱልወሀብ በእያንዳንዱ ባነሱት ነጥብ ላይ የመጠቀ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ እያንዳንዱ ነጥብም አደናጋሪ የቢድዓ አራማጆች ሙስሊሙን ህብረተሰብ ያሳሳቱበት እና ከቅኑ መንገድ ያንሸራተቱበት ብዥታም ውስጥ የከተቱበት በፍልስፍና ያቀዣበሩበት ጉዳይ ነውና፡፡

[ሙአለፋት አሽሸይኽ ሙሐመድ ኢብኑ ዐብዱልወሀብ ቅጽ 15/ገጽ 11-12
]

አሕመድ ሙሐመድ አቡ ፈውዛን

๏| ነሲሓ መጽሔት ቅጽ Vol 2 ቁጥር 1 |๏

 

Post a Comment

0 Comments