አፄዎቹ እና አባገዳ - ቅድሚያ ለተውሒድ

በቅርብ የተለጠፉ

Post Top Ad

Thursday, October 4, 2018

አፄዎቹ እና አባገዳ


አፄዎቹ እና አባገዳ
.
.
ከቅርብ አመታት ወዲህ ይበልጥ እየጦዘ የመጣው የብሔር ፓለቲካ ብዙ ነገሮችን ለውድድር እያቀረበ ሰዎችን ማፎካከር ተያይዟል።
.
ለዘመናት የአፄው ስርአት ቂመኛ የነበሩ ሰዎች የዘር ፓለቲካው ትርክት በሚጎትተው 'የማን አባት ገደል ገባ' ፉክክር ተነሳስተው በሚጠሏቸው አፄዎች መኮፈስ ጀምረዋል።
.
ሌላው ደግሞ ምንም ስሜት የማይሰጠው በነበረው እንዳውም ጭራሹንም የማያውቀውን የገዳ ስርአት እያሞገሰ ራሱን 'የገዳ ልጅ' ብሎ መኩራራት ይዟል።
.
ተፎካካሪዎቹ በረድ ይልላቸው ዘንድ ከዘረኝነት ባለፈም በሌሎች ጥፋቶች ዲናቸው ጋር እንዳይጋጩ ለማቀብ እውነታውን ማስታወስ ያስፈልጋል።
.
በዚህ ፅሁፍ የሁለቱም ስርአቶች በጎ እና መጥፎ ጎን ማወዳደር ዓላማዬ አይደለም። ይልቁን አመሰራረታቸውንና ተቋማዊ ገፅታቸው ከሸሪዓችን እንዴት እንደሚጋጭ እንዲሁም ለሙስሊሞች የነበራቸው እይታና ተፅእኖ ምን እንደሚመስል በጥቅሉ ለማሳየት እሞክራለሁ።
.
.
#አፄዎቹ (ሰለሞናዊ ስርወ መንግስት)...
.
ከአፄዎቹ ስርአት ስንጀምር፤ ስርአቱ ራሱን የተመረጠ የይሁዳ ዘር አድርጎ በሚያስብ፣ ዘሩን እንደምንም ከነብዩ ሱለይማን (ዐ.ሰ) ለማድረስ በሚደክም፣ በኦርቶዶክስ ክርስትና ተከታዮች የተመሰረተ ፊውዳላዊ ስርአት ነበር።
.
ስርአቱ ከመፅሀፍ ቅዱስ እንደተውጣጣ በሚሞግተው ሰው ሰራሽ ህግ (ፍትሀነገስት) የሚፈርድ ነበር። በርግጥ ፍትሀነገስትን ለመሸንገያነት እንጂ ለትክክለኛ መፍረጃነት የሚያውለው አልነበረም።
.
የስርአቱ አድናቂዎች 'ሰለሞናዊው ስርወ መንግስት' ኢትዮጵያን በስልጣኔ ማማ እንዳስቀመጠ፣ የራሷን ቋንቋና ፊደል እንዳበረከተ፣ ህልውናዋን ጠብቃ እንድትቆይ እንዳደረገ የመሳሰሉ የግነት ትረካዎችን ያነሱለታል። ይህ ግን መስሊሙን መስዋእት በማድረግ ለክርስቲያኑ ወገን የተበረከት እንጂ የጋራ የሚያኮራ ታሪክ አልነበረም።
.
እንዲያውም ስርአቱ በክርስትና ቀኖና ላይ የተመሰረተ እንደመሆኑ ለእስልምና እና ሙስሊሞች ቦታ የሚነፍግ እንዲሁም የሙስሊሙን ህልውና የሚገፍ ፀረ-ሙስሊም ስርአት ነበር።
.
የሀገሪቱን አንድ ሶስተኛ ሀብት ለቤተክርስቲያን የሰጠ፣ ገበሬውን ከርስቱ እያፈናቀለ መሬቱን ለአድባራትና ገዳማት ያበረከተ፣ ባላገሩን ለካህናትና ቀሳውስት ግብር እንዲያስገባ ያስገደደ ስርአትም ነበር።
.
አፄዎቹ በግዛታቸው ስር ያሉ ሙስሊሞች በሰላም ሀይማኖታቸውን እንዳይተገብሩ፣ ንብረትና ሐብት እዳያፈሩ፣ በነፃነት እንዳይንቀሳቀሱ ማፈን የአገዛዝ ታሪካቸው ነበር። ከዚህም አልፈው ራሳቸውን ችለው በሌላ ቦታ መንግስት መስርተው የሚተዳደሩ ሙስሊሞችን መተናኮል፣ መረበሽ፣ መውረር፣ መዝረፍና ማፈናቀል የዘመናት ስራቸው ነበር።
.
እንዲሁም ስርአቱ ያመጣው የክርስቲያንና እስላም አድልዎ፣ የወታደር እና ባላገር ክፍፍል፣ የባላባትና ጭሰኛ መደብ፣ የባሪያ እና አሳዳሪ ዜግነት የመሳሰለው ህዝባችንን ለዘመናት የግፍ በትር እንዲያርፍበት አድርጓል። በዚህም አፄዎቹን ልንወዳቸው ቀርቶ አምርረን እንድንጠላቸው ምክንያት ሁኗል!
.
እናም ስርአቱን አድናቂዎቹ ከሚሞግቱለት እጅግ በራቀ መልኩ መጥፎ ካባ ለብሶ በክፋት እንዲታወስ ሁኗል። ይህ እንግዲህ ተቋማዊ ገፅታው ፀረ ሙስሊም ከመሆኑ ባሻገር ነው።
.
.
#አባገዳ (Sirna Gadaa)
.
የገዳ ስርአት በዋቄፈና ዘልማዳዊ እምነት ላይ የተመሰረተ ፓለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ሐይማኖታዊ መዋቅር ያለው ስርአት ነው።
.
ስርአቱ በዋቄፈና እምነት እንደ ህገደንብ በሚታየው ሳፉ/Safuu/ መሰረት የሚያስተዳድር ሲሆን በውስጡ ማህበራዊ፣ ሐይማኖታዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን የሚያሳልጡ ተቋማትን ያቀፈ ነው።
.
ብዙ ግዜ ስለገዳ-ስርአት ዴሞክራሲያዊነት፣ ፍትሃዊነት እንዲሁም አካታችነት ሲሰበክ እንሰማለን። ምናልባት ይህን የሚሉት ሰዎች የገዳ ስርአትን በአካባቢው ከነበሩት ሌሎች የአገዛዝ ስርአቶች ጋር በማወዳደር ሊሆን ይችላል።
.
ይህ ግን ለኛ ሙስሊሞች ስሜት የሚሰጥ አይደለም፤ ሙስሊሞች በዲሞክራሲ አናምንምና። እስልምና የተሟላ የህይወት መመሪያ እንደመሆኑ የህዝብ አስተዳደር በሸሪዓዊ መርሆ ላይ ይመሰርታል። በዚህም ህግጋትን ከቁረአንና ሐዲስ እየመዘዘ የሚመራ ይሆናል።
.
በአንፃሩ ዲሞክራሲ የአላህን ህግ የማውጣት ስልጣን ነጥቆ በህዝብ (ተወካዮች) ድምፅ የሚቀይር፤ ትክክል ሆነም አልሆነ አብዛኛው ሰው በመረጠው መንገድ የሚመራ፣ በነፃነት ስም እስልምና እርም ያደረጋቸውን ነውረኛ ተግባራት ሳይቀር እንዲተገበሩ የሚፈቅድ በመሆኑ ከሽርክ አንስቶ ለብዙ ጥፋቶች የሚዳርግ እንደሆነ ዓሊሞች ይናገራሉ።
.
በተጨማሪም አፈቀላጤዎች አላዋቂዎችን አሞኝተው ስልጣን የሚቆናጠጡበት፣ ባለሀብቶች ፓርቲዎችን በመደገፍ ስም በእጅ አዙር የሚገዙበት፣ በሎቢይስቶች (lobyist) አማካኝነት ሀብታሞችና ሌሎች አካላት የሚመቻቸውን ህግ እያወጡ ህዝቡን የሚበዘብዙበት ስርአት በመሆኑም እንደ ፍፁማዊ ተደርጎ ለመመዘኛነት የሚቀርብ አይደለም። ስለሆነም የገዳ ስርአትን በዲሞክራሲ መመዘኛ ማንቆለጳጰስ ጤፍን በቀዳዳ ጣሳ እንደመስፈር ነው።
.
ሌላው ለገዳ ስርአት እንደ መልካም ጎንነት የሚጠቀሰው ደግሞ ፍትሀዊነት ነው። ፍትህ Subjective ነው። ፍትህ እንደ ስርአቱና እምነቱ የተለያየ ምልከታ አለው። እኛ ሙስሊሞች ትክክለኛ ብለን የምናምነው ፍትህ ለዲሞክራቶች ግፍ ይመስላቸዋል (እይታቸው የተንሸዋረረ ነውና)። በአንፃሩ እነርሱ ፍትህ የሚሉት ደግሞ በሸሪዓችን ታላቅ በደል ይሆናል። እናስ ገዳ በየትኛው ተመዝኖ ነው ፍትሀዊ የሚባለው?
.
ስለገዳ አካታችነት የሚጠቀሰው ግን ዝርዝር ጥያቄ ያስነሳል። የገዳ ስርአት በዋቄፈና እምነት ላይ እንደመመስረቱ የስርአቱ አካል ለመሆን በዋቄፈና ማመንን ይጠይቃል ወይም በእምነቱ መሰረት የሚፈፀሙ ስርአቶችን መተግበር ይጠብቃል። ያን ያላሟላ ግን አይካተትም!
.
ተያይዞም የ'ቃሉ' ጎሳ አባላትን በዋቄፈና እምነት ካህንነት ብቻ ገድቦ ከሽግግር አመቻችነት እና የመንፈስ አባትነት በዘለለ ከፓለቲካው ተሳትፎ ማራቁ የአካታችነት ሙገሳውን ይቀንሳል። (በነገራችን ላይ 'ቃሉ' የሚባል ጎሳ በኦሮሞ፣ ሶማሌና አፋር ብሄሮች ውስጥ በተለያየ መልኩ ሲገኝ ለዋቄፈና የማይገዙት ሙስሊም ተወላጆቹ እስልምናን በማስተማር በይበልጥ ይታወቃሉ)
.
ሌላው በገዳ ስርአት አባቱ ያልተሳተፈን ሰው ስርአቱ አያካትትም። እንዲሁም በወረራ እና ግጭት የተያዙ አካባቢ ነዋሪዎችን ወይም ጎሳዎችን ከስርአቱ የሚያገልም ነው። ለኔ ስሜት ባይሰጠኝም ሴቶችን በ'ሲንቄ' መማክርት ብቻ መገደቡንም ተቺዎች ከአግላይነት ይጠቀሱበታል።
.
እነዚህ እንደስርአት በአንፃራዊነት ገዳን በአካታችነት ለሚያሞግሱት ማስታወሻ ይሆን ዘንድ የሚቀርቡ ትችቶች እንጂ ሸሪዓዊ ምልከታን የተመሰረቱ እንዳልሆነ ልብ ይሏል። ምክንያቱም ስርአቱ በጥቅሉ ሰው ሰራሽ እና በኩፍር (ዋቄፈና) ላይ እንደመመስረቱ ይህ ጎደለ ይህ ሞላ የምንልበት አይሆንም።
.
የገዳ ስርአት ጥንታዊነት እንደአፄዎቹ የሚዘከርበት የውሸትም ቢሆን የተፃፈ ታሪክ የለውም። ሆኖም በ16ኛው ክፍለ ዘመን የገዳ ስርአት የእድገት ጣሪያውን የነካበት እንደነበር ታሪክ ያወሳል።
.
በወቅቱ የክርስቲያኑ ሰለሞናዊ ስርወ መንግስት እና የሙስሊሙ የአዳል ሱልጣኔት ባደረጉት ረጅምና አውዳሚ ጦርነት መዳከማቸው ተከታታይ የገዳ ሉባ ጦረኞች ለመስፋፋት እጅግ ምቹ ሁኔታ ፈጥሮላቸዋል።
.
እናም የሰለሞናዊው ስርወ መንግስት ወደ ሰሜን ሸሽቶ ጎንደር ሲከትም የአዳል ሱልጣኔት በገዳ ጦረኞች ክፉኛ ተጎድቶ በአውሳ ሱልጣኔት እና በሀረር ኢሜሬት ለሁለት ተከፍሏል። በመሆኑም ገናናው የሙስሊም ስልጣኔ በሀረር ግንቦችና በአፋር በረሀ እንዲቀበር ገዳ ምክንያት ሁኗል።
.
የአፄው ስርአት ከ13ኛው ክፍለዘመን አንስቶ ያልተሳካለተን የሙስሊሙን መንግስት የማክሰም ህልም የገዳ ጦር በሚከተለው የደፈጣ ጦርነት ስልት በጥቂት አስርት አመታት አሳክቶታል።
.
የኅላ ኋላ የገዳ ስርአትም ቢሆን መቶ አመት ባልሞላ ጊዜ የተቆጣጠረውን እጅግ ሰፊ ግዛት ማስተዳደር አልቻለም። አብዛኞቹ ተዋጊዎች በየደረሱበት ሰፍረው እስልምናን እየተቀበሉ ከገዳ ስርአት ሲያፈነግጡና ተስፋፊዎቹ የየራሳቸውን የስርአተ መንግስት መዋቅር ሲያወጡ ገዳ ቀስ በቀስ እየተዳከመ ሄዶ በቦረና ብቻ ተገድቦ ሳለ በመጨረሻም በአፄዎቹ የሀገር ምስረታ ወቅት አክትሞለት ነበር።
.
.
#ስንጠቀልለው
.
ከላይ ያወሳናቸው ሁለቱም ስርአቶች በአሁኑ ወቅት አንድም ሙተዋል ወይም ጥርስ አልባ አንበሳ ሁነዋል። የአፄዎቹ ስርአት ሙሉ በሙሉ አክትሞለታል። ገዳም ቢሆን በማዕከላዊ ዕዙ መዳከም፣ በተከታዮቹ ማፈንገጥና በአፄዎቹ ጥቃት ተመናምኖ ጠፍቷል። ምንም እንኳ ዛሬ ምልክታዊ (Symbolic) በሆነ መልኩ ይዘውት የሚንገዳገዱ ቢኖሩም።
.
ሁለቱም ስርአቶች በሰው ሰራሽ ህግ የሚመሩ በኩፍር እምነቶች ላይ የተገነቡ ናቸው። በመሆኑም ለአንድ ሙስሊም በስርአት ደረጃ አንዱን ካንዱ የሚያስበልጥበት መሰረት አይኖረውም።
.
እርግጥ ነው ባሳለፉት የአገዛዝ ወቅት በተፈፀሙ ጥፋቶች ላይወዳደሩ ይችላሉ። ይሁንና የፅሁፋችን መሰረታዊ ማጠንጠኛ እሱ አይደለምና እርሱን ለመመዘኛነት አናቀርብም። ይልቁን ስርአቶቹ ለእስልምና እና ለሙስሊሞች አግላይና ጠቃሚ ያልሆኑ በመሆናቸው እንስማማለን።
.
እንዳውም እስልምና እና ሙስሊሞች ላይ ምንም እንኳ ደረጃው ቢለያይም ሁለቱም ጉዳት አድርሰዋል። እናም እንደሙስሊም የምንርቃቸውና የምንተቻቸው እንጂ የምናሞግሳቸውና የምንኮራባቸው አይደሉም። አዎን እነሱ ለኛ ምናችንም አይደሉም፤ በዳይ እንጂ!
.
ስለሆነም የአፄዎቹን ስርአት ከጎሳ ወይም ብሔር ሳናዛምድ እንደምንጠላና እንደምናወግዘው ሁሉ የገዳንም ስርአት እንደዚሁ በመንግስታዊ ቁመናውና አግላይ በዳይ አካሄዱ ልንጠላውና ልንቃወመው ይገባል።
.
ማንም ሙስሊም ራሱን ከእስልምና ጠላት አፄዎች ጋር እንደማያጠጋጋው ሁሉ በኩፍር ከተመሰረተው የገዳ ስርአት ጋርም ራሱን ሊያቀራርብ ወይም ሊይገናኝም አይገባም።
.
አላህ በቁርአኑ እንዲህ ይለናል ...
.
.( إِنِ الْحُكْمُ إِلَّا لِلَّهِ ۖ يَقُصُّ الْحَقَّ ۖ وَهُوَ خَيْرُ الْفَاصِلِينَ ) الأنعام/57
.
"ፍርዱ ለአላህ ብቻ ነው፡፡ እውነትን ይፈርዳል፡፡ እርሱም ከፈራጆች ሁሉ በላጭ ነው» በላቸው" አልማኢዳ 57
.
.
فَالْحُكْمُ لِلَّهِ الْعَلِيِّ الْكَبِيرِ (غافر 12)
.
"ስለዚህ ፍርዱ፣ ከፍተኛ ታላቅ ለሆነው አላህ ብቻ ነው" ጋፊር 12
.
.
أَلَيْسَ اللَّهُ بِأَحْكَمِ الْحَاكِمِينَ (التين 8)
.
"አላህ ከፈራጆች ሁሉ ይበልጥ ፈራጅ አይደለምን? (ነው)" አ'ቲን 8
.
.
وَلَا يُشْرِكُ فِي حُكْمِهِ أَحَدًا (الكهف 26)
.
"በፍርዱም አንድንም አያጋራም" አል-ከህፍ 26
.
.
( أَفَحُكْمَ الْجَاهِلِيَّةِ يَبْغُونَ وَمَنْ أَحْسَنُ مِنَ اللَّهِ حُكْماً لِقَوْمٍ يُوقِنُونَ ) المائدة/50
.
"የመሀይምነትን ፍርድ ይፈልጋሉን? ለሚያረጋግጡ ሰዎች ከአላህ ይበልጥ ፍርዱ ያማረ ማነው?" አልማኢዳ 50
.
.
( أَمْ لَهُمْ شُرَكَاءُ شَرَعُوا لَهُمْ مِنَ الدِّينِ مَا لَمْ يَأْذَنْ بِهِ اللَّهُ وَلَوْلا كَلِمَةُ الْفَصْلِ لَقُضِيَ بَيْنَهُمْ وَإِنَّ الظَّالِمِينَ لَهُمْ عَذَابٌ أَلِيمٌ ) الشورى/21
.
"ከሃይማኖት አላህ በርሱ ያልፈቀደውን ለነርሱ የደነገጉ ተጋሪዎች ለነርሱ አልሏቸውን? የፍርዱ ቃል ባልነበረ ኖሮ በመካከላቸው (አሁን) በተፈረደ ነበር፤ በደለኞችም ለርሱ አሳማሚ ቅጣት በእርግጥ አልላቸው" ሹራ 21
.
.
مَا تَعْبُدُونَ مِن دُونِهِ إِلَّا أَسْمَاءً سَمَّيْتُمُوهَا أَنتُمْ وَآبَاؤُكُم مَّا أَنزَلَ اللَّهُ بِهَا مِن سُلْطَانٍ ۚ إِنِ الْحُكْمُ إِلَّا لِلَّهِ ۚ أَمَرَ أَلَّا تَعْبُدُوا إِلَّا إِيَّاهُ ۚ ذَٰلِكَ الدِّينُ الْقَيِّمُ وَلَٰكِنَّ أَكْثَرَ النَّاسِ لَا يَعْلَمُونَ ( يوسف 40)
.
"ከርሱ ሌላ እናንተና አባቶቻችሁ የሰየማችኋቸውን ስሞች እንጅ አትገዙም፤ አላህ በርሷ ላይ ምንም አስረጅ አላወረደም። ፍርዱ የአላህ እንጅ የሌላ አይደለም እርሱን እንጅ ሌላን እንዳትግገዙ አዟል፤ ይህ ትክክለኛው ሃይማኖት ነው፤ ግን አብዛኞቹ ሰዎች አያውቁም" ዩሱፍ 40
.
.
በመጨረሻም ነብያችን (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) በአባትና በአያት ስራ መጀነን እንደማይገባ፣ ይህም ተግባር የጃሒሊያ/መሀይምነት ጉዳይ እንደሆነ ሲናገሩ "በዘር መመፃደቅ እና በዘር መሰዳደብ" የሳቸው ኡማ የማይተወው ነውር የድንቁርና/ጃሂሊያ ተግባር መሆኑን አውስተው ነበር። (ሙስሊም ዘግበውታል)
.
እንዲሁም ነብያችን (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ... "ስራው ወደኋላ ያስቀረው ዘሩ ወደፊት አያስቀድመውም" ብለው ነበር።
.
.
በሽርክ እና በቢድዓ የተዋጠ ማህበረሰብ ይዘን በዘረኝነት ተነሳስተን ከአላህ ህግ ውጭ በሆነ በሚፈርዱ ያውም ለሙስሊሞች ቀበኛ በሆኑ ስርአቶች መኩራራት ጤነኝነት አይደለምና እንመከር!
.
.
አላህ ወደ ዓቅላችን ይመልሰን!

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages