Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

የመልካም በር ከፋች ሁን

 
የመልካም በር ከፋች ሁን
.
•┈┈•┈┈•⊰✿?✿⊱•┈┈•┈┈•
.
በሸይኽ ዐብድረዛቅ ቢን ዐብድል ሙሕሲን አባድ አልበድር (አላህ ይጠብቃቸው) የተዘጋጀ።
.
ትርጉምና ተጨማሪ ሀሳብ፦
(ሐይደር ኸድር)
.
አነስ ኢብኑ ማሊክ (አላህ መልካም ስራውን ይውደድለትና) እንዳስተላለፈው የአላህ መልዕክተኛ (ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ ብለዋል፦
.
عن أنس بن مالك رضي الله عنه قال : قال رسول الله صلى الله عليه وسلم : ( إِنَّ مِنْ النَّاسِ مَفَاتِيحَ لِلْخَيْرِ مَغَالِيقَ لِلشَّرِّ ، وَإِنَّ مِنْ النَّاسِ مَفَاتِيحَ لِلشَّرِّ مَغَالِيقَ لِلْخَيْرِ ، فَطُوبَى لِمَنْ جَعَلَ اللَّهُ مَفَاتِيحَ الْخَيْرِ عَلَى يَدَيْهِ ، وَوَيْلٌ لِمَنْ جَعَلَ اللَّهُ مَفَاتِيحَ الشَّرِّ عَلَى يَدَيْهِ ) .
.
"ከሰዎች መካከል የመልካም በር ከፋች የሆኑና የመጥፎ በር ዘጊዎች የሆኑ አሉ ፤ እንዲሁም ከሰዎች መካከል የሸር (መጥፎ) በር ከፋች የሆኑና የመልካም በር ዘጊየሆኑ አሉ። አላህ የመልካም በር መክፈቻ ቁልፍ በእጁ ላደረገለት ጡባ አለለት ፤ አላህ የመጥፎ በር መክፈቻ ቁልፍ በእጁ ላደረገለት ወይል አለለት።"
.
[ኢብኑ ማጃህ (237) ዘግበውታል። ኢማሙ አልባኒ ሰሒሕ ኢብኑ ማጃህ (194) ላይ ሐዲሡን ሐሰን ብለውታል ።]
.
"ጡባ" ፦ የጀነት ሰው ለመሆኑ መገለጫ ወይም በጀነት ውስጥ ያለች ዛፍ ነችም ተብሏል።
.
"ወይል" ፦ የጀሀነም ሰው ለመሆኑ ምልክት ወይም ጀሀነም ውስጥ ያለ ሸለቆ ነው ተብሏል።
.
ነፍሱ የ"ጡባ" ባለቤት የመልካም በር ከፋች ፣ የመጥፎ በር ዘጊ እንድትሆንለት የፈለገ ሰው ።
.
በሚከተሉትን ወሳኝ ነጥቦች ላይ አደራ እላለሁ፦
.
1/ ኢኽላስ
.
ንግግርንም ሆነ ተግባርን በኢኽላስ ለአላህ ብቻ ጥርት ማድረግ። ምክንያትም እርሱ የመልካም ነገሮች ሁሉ መሰረትና ምሰሶ የልዕቅና ሁሉ ምንጭ ነው። ከእዩልኝና ይስሙልኝን ሊርቅ ይገባል።
.
በኢኽላስ ላይ ያልተመሰረተ ማንኛውም ተግባርና ጥረት ከንቱ ልፋት የእምቧይ ካብ ነው።
.
2/ ዱዓ
.
ይህን መልካም ነገር አላህ እንዲገጥመንና እንዲወፍቀን ሌት ተቀን በዘውታሪነት ልንለምን ይገባል። ምክንያቱም ዱዓ የመልካም ነገሮች ሁሉ መክፈቻ ቁልፍ ነውና። አላህ ባሪያው ለምኖት ልመናውን ከንቱ አድርጎ አያስቀርበትም ተመላሽ አያደርግበትም። ሙእሚን ለጌታው ተዋርዶና ተናንሶ በምስጢር ያደረገውን ዱዓ ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ አያልፍበትም።
.
ከሶስት በአንዱ መንገድ ለልመናው ምላሽ ይሰጠዋል!
.
ለልመናው አፋጣኝ ምላሽ ይሰጣል።
.
ወይም የመጣበትን በላ ይመልስለታል።
.
አልያ ደግሞ ለየውመል ቂያማ ያስቀምጥለታል።
.
አደራ! ለመንኩ ለመንኩ መልስ አልሰጠኝም ብለህ ተስፋ አትቁረጥ ነብዩ ኢብራሂም ለረጅም ዓመታት ጌታቸውን ሲማፀኑ ከርመው ከሰባ ዓመታቸው በኋላ ልጅ እንደሰጣቸው አትርሳ!
.
ኢብራሂም ያንን ሁሉ ጊዜያት ጌታቸውን ሲማጸኑ ቆይተው የዱዓቸው ፍሬ በስተርጅና ሲመጣ ከመማረር ይልቅ ይህን ነበር ያሉት፦
.
"ጌታዬ ልመናን ሰሚ ነው።" (ኢብራሂም: 39)
.
3/ ዒልም
.
ዕውቀት ለመፈለግና ለማግኘት መልፋት ፣ መትጋትና መጓጓት (እንዲሁም) ለመገብየትም መጣር ግድ ይላል። ዕውቀት ወደ ልዕቅና እና ክብር ሲጠራ (ሲያደርስ) ከመጥፎና ውዳቂ ነገሮች ሁሉ ይከለክላል።
.
ዕውቀት ብርሃን ሲሆን ጅህልና ጨለማ ነው።ድቅድቅ ያለ ጨለማ! ጃሂል የመልካም በረ ከፋች ከመሆን ይልቅ የሸር በሮችን ቁልፍ በጠቅላላ ሸክፎ ለመዞር የቀረበ ነው። ምክንያቱ ከመሰረቱ ኸይር ምን እንደሆነ ሸር ምን እንደሆነ ለይቶ በአግባቡ አያውቅምና።
.
4/ ዒባዳን መፈጸም
.
ዒባዳ (አምልኮ) ተግባራትን መፈጸም። በተለይም ደግሞ ግዴታ የሆኑ የአምልኮ ተግባራትን መተግበር። ከነዚህ ግዴታ ተግባራት ደግሞ ልዩ በሆነ መልኩ ለሶላት ትልቅ ትኩረት መስጠት (ያስፈልጋል)። ምክንያቱም ሶላት ከጸያፊና መጥፎ ከሆኑ ተግባራት (ሁሉ) ትከለክላለችና።
.
5/ መልካም ስነ ምግባር!
.
(ድምጽ አልባ ዳዕዋ!)
.
መልካም ስነ ምግባር መላበስ ፣ ላቅ ባሉና በመጠቁ ባህሪያት መዋብ ፣ መልካም ስነ ምግባርን ከሚያጎድፉ ከሚያቆሽሹ ተግባራት እና የመጥፎ ስነ ምግባር መገለጫ ከሆኑ አጸያፊና ውዳቂ ከሆኑ ባህሪያት መራቅ ።
.
መልካም ስነግባር ከተቅዋ ጋር ተደምረው አንድን ሙእሚን ጀነት ለመግባት እንደሚረዱት መልክተኛው አስተምረዋል። በምርጥ ባህሪው ምክንያትም ቀን የሚፆሙና ለሊት የሚቆሙ ዓቢዶች የሚያገኙትን ምንዳም እንደሚሸምትም ተናግረዋል። በቂያማ እለትም በስራ ሚዛን ላይ በከፍተኛ ደረጃ ሚዛን እንደሚያነሳ አውስተዋል። ሌላም ሌላም ለመልካም ባህሪ ባለቤቶች ታላላቅ የምስራቾችን አበስረዋል።
.
ሙስሊምም ይሁን ሙስሊም ካልሆኑ ሰዎች ጋር ባለን መስተጋብር ላይ ጥሩ ስነምግባር ልንላበስ ፣ በመልካም ልንኗኗራቸው ይገባናል።
.
በተለይም ሙስሊሞች መገለጫቸው ከነበረው መልካም ስነ ምግባር እየራቁ ባሉበት እና እንኳን የውጪውን የውስጡንም የሚያስወጣ አስቸጋሪ ባህሪን ተላብሰው ባሉበት ወቅት መልካም ባህሪን መጎናፀፍና ለሌሎች አርዓያ መሆን ታላቅ ጀብድ ነው።
.
በምናሳየውም ስነ ምግባር ተማርከው ስለኛ ጀርባ ለማጥናት እንዲነሳሱና የምናንፀባርቀውን የኢስላምና የሱንና ብርሃን ፈልገው አግኝተው እንዲቋደሱ ማድረግ ይቻላል።
.
6/ ጓደኛ ምረጥ
.
ከመልካም ሰዎች ጋር መጎዳኘት እና ከመልካም ሰዎች ጋር መቀማመጥ። ከእነርሱ ጋር መቀማመጥ መላኢኮች በክብር ክንፋቸውን ዝቅ እንዲያደርጉልን የአላህ እዝነት እንዲያካበን ያደርጋል።
.
(በተቃራኒው)
.
ከመጥፎና ክፉ ሰዎች ጋር ከመቀማመጥ ልንጠነቀቅ ይገባል ። ምክንያቱም (የእነርሱ መሰብሰቢያ) የሸይጧኖች መከማቻ ስፍራ ነውና።
.
"ከዘንድሮ ጓደኛ የድሮ ጠላት ይሻላል።" ይላሉ ሰዎች እጅግ ምርር ሲላቸው። ወዳጅ መሳኝ ሸረኛና ምቀኛ የበዛበት ዘመን ላይ ነው ያለነው። የጓደኛው መልካም ነገር መስራት ለመልካም ነገር መሯሯጥ በዲኑ ላይ መፅናት የሚያበግነው አይኑን የሚያቀላው ነፍ ነው ። ከመልካም ነገር ርቆ የሸይጧን ሰራዊት እንዲሆን የሚጎተጉትና በል በል የሚል ጓደኛ የትየለሌ ነውና ጓደኛን በጥንቃቄ መምረጥ ያሻል። ለአኼራህ የሚጠቅምህን የሚመክሩ ፣ ችግርህን የሚካፈሉ ፣ ስትሳሳትና ስታጠፋ በእዝነት የሚመክሩህ ፣ ወደ መልካም ነገር የሚገፋፉ ውድ ጓደኞችም አሉና እነርሱን መርጦ መጎዳኘት ያስፈልጋል።
.
7/ ነሲሓ
.
(ከመቆርቆር ጋር ምክር መስጠት መመካከር )
.
ለአላህ ባሮች በሚገናኛቸውና አብሮ በሚኗኗራቸው ጊዜ ነሲሓ መስጠት። በመልካም ነገር ላይ እንዲጠመዱ ማድረግ እና ከመጥፎ ነገሮች እንዲርቁ ማድረግ።
.
ያለንበት ጊዜ ሙስሊሞችን ከቀጥተኛው ጎዳና አስፈንጥሮ ለማውጣት ፣ እርስ በእርስ ለማባላትና ለማለያየት ፣ ከዲናቸውን ለማቆራረጥ እና ክብራቸውን ለማርከስ ከየአቅጣጫው እየተዘመተበት ያለበት ነው።
.
ስለሆነም ሙስሊሞች ከምግብና ከመጠጥ ኧረ እንደውም ከአየርም የበለጠ ትክክለኛ ነሲሓ ያስፈልጋቸዋል።
.
በመሆኑም በኢኽላስ በወንድማዊነትና በተቆርቋሪነት ስሜት በእዝነት ሊመክራቸው ግድ ይላል። የጥፋት ኃይሎች በየአቅጣጫቸው እየጎተቷቸው የጥፋት አዘቅት ውስጥ ሊዶሏቸው (ሊከቷቸው) እየተውተረተሩ ነውና ሊደርስላቸው ይገባል።
.
በተቃራኒው መናገር ላይ ብቻ ትኩረት አድርጎ ሰዎችን በእልህ ከሐቅ እንዲሸሹ በማድረግ ለጥፋት ሀይሎችና ለሸይጣንና ጋሻጃግሬዎቹ ቀንደኛ ረዳት ከመሆን ሊታቀብ ይገባል።
.
የመልካም በር ከፋች መሆን ቢያቅተን የመጥፎ በር ከፋች አንሁን።
.
8 አኼራን ማስታወስ
.
ሞቶ መቀስቀስ እንዳለና የዓለማቱ ጌታ ፊት ቆሞ መተሳሰብ መኖሩን ማስታወስ።
.
መልካም የሰራ በመልካም ስራው ልክ እንደሚመነዳና መጥፎ የሰራም በመጥፎ ስራው ልክ እንደሚቀጣ ማስታወስ።
.
"فَمَنْ يَعْمَلْ مِثْقَالَ ذَرَّةٍ خَيْرًا يَرَهُ (7) وَمَنْ يَعْمَلْ مِثْقَالَ ذَرَّةٍ شَرًّا يَرَهُ " [الزلزلة:7-8] .
.
"የብናኝ ክብደት ያክልም መልካም የሰራ ሰው ያገኘዋል። (7) የብናኝም ክብደት ያክል ክፉን የሰራ ሰው ያገኘዋል።" (አል ዘልዘላህ 7 -8)
.
አኼራ አለብኝ ብሎ የሚያስብ ሰው ስሜቱንና ፍላጎቱን እየተከተለ ሰዎችን ወደጥፋት አይነዳም የሸር በሮችን ለመከፋፈት አይታትርም አላህ ፊት መቆምን ይፈራል።
.
9 ቅን አሳቢ መሆን!
.
የነዚህ ሁሉ መሰረትና ምሰሶው ደግሞ አንድ ሰው ለኸይር ነገር ክጃሎት ያለውና የአላህ ባሮችን ለመጥቀም ፍላጎት ያለው መሆኑ ነው። በዚህ ክጃሎቱም ላይ ቀጥ ካለ፣ በሀሳቡም ላይ ከጸናና በጉዳዩም ላይ በአላህ ከታገዘ ፣ ትክክለኛውንም መንገድ ይዞ ከተጓዘ በአላህ ፍቃድ የመልካም በር ከፋች የመጥፎ በር ዘጊ ይሆናል።
.
አላህ ባሮቹን ለመልካም ነገር በመግጠም ይረዳቸዋል። በፈለገው ሰው በኩል ደግሞ በእውነት ይከፍታል።
.
አላህ የመልካም በር ከፋች የመጥፎ በር ዘጊ ያድርገን!
.
እሁድ ሙሐረም 6 /1/1440
መስከረም 6/1/2011

Post a Comment

1 Comments