Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ሒጃብ ፊት መሸፈንን ያካትታል አያካትትም❓

📃 ሒጃብ ፊት መሸፈንን ያካትታል  አያካትትም
ፊት ስላለመሸፈን የተነገሩ ሃዲሶች ሰነዳቸው ላይ ድክመት አሉባቸው። አንዳንድ ደግሞ ትክክለኞችም አሉ፡፡
 ከደካማዎቹ መካከል ቀጣዩ ከዓኢሻ ረዲየላሁ ዐንሃ ተወራ የተባለው ሀዲስ አንዱ ነው:-
ይህም
አስማዕ ቢንት አቢበክር (ረዲየላሁ ዐንሀ) ወደነብዩ (ﷺ) ያሉበት ቤት መጥታ ገባች፡፡ በወቅቱ በላይዋ ላይ ያለው ስስ ልብስ ነበር ነብዩም (ﷺ) ከእርሷ ዞሩና እንዲህ አሉ፡-
📓« አስማዕ ሆይ ሴት ልጅ ለአካለ መጠን ከደረሰች እርሷን ማየት አይቻልም። ይህና ይህ ሲቀር። » ኣሉ። ከዚያም ወደ ፊታቸውና እጃቸው አመለከቱ።
ይህ ሀዲስ ደካማ ባይሆን ኖሮ
" ይህና ይህ " ብለው ነጥለው ያመላከቱት የማይሸፈነው የሰውነት ክፍል ፊት እና መዳፎች ናቸው።
ነገር ግን ደካማ ሀዲስ ነውና በቂ መረጃ አይሆንም።
ትክክለኛ ዘገባ የሆነው ደግሞ ኢብን አባስ (ረዲየላሁ አንሁ) ያወራው ሃዲስ ነው ።
እሱም እንዲህ ይላል :-
” أَرْدَفَ رَسُولُ اللَّهِ ‏‏صَلَّى اللَّهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ ‏الْفَضْلَ بْنَ عَبَّاسٍ ‏‏يَوْمَ النَّحْرِ خَلْفَهُ عَلَى عَجُزِ رَاحِلَتِهِ وَكَانَ ‏ ‏الْفَضْلُ ‏رَجُلًا وَضِيئًا فَوَقَفَ النَّبِيُّ ‏صَلَّى اللَّهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ ‏ ‏لِلنَّاسِ يُفْتِيهِمْ وَأَقْبَلَتْ امْرَأَةٌ مِنْ ‏‏خَثْعَمَ ‏‏وَضِيئَةٌ تَسْتَفْتِي رَسُولَ اللَّهِ ‏‏صَلَّى اللَّهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ ‏‏فَطَفِقَ ‏‏الْفَضْلُ ‏‏يَنْظُرُ إِلَيْهَا وَأَعْجَبَهُ حُسْنُهَا فَالْتَفَتَ النَّبِيُّ ‏‏صَلَّى اللَّهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ ‏‏وَالْفَضْلُ ‏‏يَنْظُرُ إِلَيْهَا فَأَخْلَفَ بِيَدِهِ فَأَخَذَ بِذَقَنِ ‏الْفَضْلِ ‏فَعَدَلَ وَجْهَهُ عَنْ النَّظَرِ إِلَيْهَا فَقَالَتْ: ‏‏يَا رَسُولَ اللَّهِ إِنَّ فَرِيضَةَ اللَّهِ فِي الْحَجِّ عَلَى عِبَادِهِ أَدْرَكَتْ أَبِي شَيْخًا كَبِيرًا لَا يَسْتَطِيعُ أَنْ يَسْتَوِيَ عَلَى الرَّاحِلَةِ فَهَلْ يَقْضِي عَنْهُ أَنْ أَحُجَّ عَنْهُ قَالَ:نَعَمْ “
የእርዱ እለት (በሐጅ አስረኛው ቀን) የአላህ መልእክተኛ ﷺ ፈድል ቢን አባስን በመጓጓዣቸው ላይ ከኋላ አፈናጥውት ይጓዛሉ። ፈድል ቆንጅዬ የሆነ ልጅ ነበር።
ነቢዩ ﷺ ቆመው ለሰዎች ለጥያቄዎቻቸው ምላሽ እየሰጡ እያለ ፣ አንዲት ቆንጆ የከስዐም ጎሳ (የመን የሚገኙ) የሆነች እንስት መጣችና የአላህ መልእክተኛን ﷺ ጥያቄ ትጠይቃለች።
ፈድል ደግሞ በውበቷ ተገርሞ ያያታል። ነቢዩ ﷺ ፈድልን ሲመለከቱት እሱ ልጅትን እያየ ነበርና እጃቸውን ወደኋላ ሰንዝረው የፈድልን አገጭ ያዙና እንዳያያት ፊቱን ኣዞሩት።
( እሷም የመጣችለትን ጥያቄዋን አቀረበችላቸው)
« የአላህ መልእክተኛ ሆይ ! አላህ በባሮቹ ላይ የደነገገው የሀጅ ግዴታ ያረጀ ሽማግሌ በሆነው አባቴ ላይ ደርሷልና እሱ ደግሞ በመጓጓዣው ላይ እንኳ ተስተካክሎ መቀመጥ አይችልም።
ስለዚህ እኔ ሀጅ ባደርግለት ግዴታው ይካካስለታልን ? (ስትላቸው)፤ አዎን አሏት። » .
📇[ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል]
ታላቁ የሀዲስ ሊቅ ሸይኽ አብዱል ሙህሲን አል ዓባድ (አላህ ይጠብቃቸውና) ይህንን ሃዲስ ፊትን ስለመግለጥ ማስረጃ ማድረግን በተመለከተ ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል:-
« ሴት ፊቷን ስለመግለጥ ይህን ሀዲስ ማስረጃ የሚያደርጉ ሰዎች ሊገነዘቡት የሚገባው ነገር: ይህ አጠቃላይ ሳይሆን ውስን ሁኔታን አመልካች መሆኑን ነው::
ስለዚህ ይህ ሀዲስ በጣም በርካታ የቁርአንና የሀዲስ ማስረጃዎችን ፈጽሞ መቃወም አይችልም። ሌላው ጉዳይ ደግሞ ይህች ሴት ኢህራም ላይ ነበረች። ስለዚህ ፊቷን የገለጠችው ለኢህራሙ ሊሆን ይችላል ፡፡ምክንያቱም በሀዲስ ውስጥ ይህ እንዳለ አሳልፈናልና::
ቡኻሪ በዘገቡትና ዓብደላህ ኢብን ኡመር እንዳወራው የአላህ መልእክተኛ (ﷺ) ይህን ተናግረዋል:-
📓«ኢህራም ውስጥ ያለች ሴት ለፊቷ መሸፈኛ የተዘጋጀውን (ኒቃብ)ና ጔንት አትለብስም» ብለዋል።
አሊያም ፊቷን መገለፇ ለሌላ ጉዳይም ሊሆን ይችላል። ምሳሌ ነብዩ (ﷺ) አይተዋት እንዲያገቧት ፈልጋም ሊሆን ይችላል::
ስለዚህም ይህ ሀዲስ ብቻውን ፊትን ላለመሸፈን ደጋፊ ማስረጃ ሊሆን አይችልም።
📚[ሀፊዝ ኢብኑ ሀጀር ይህንን በፈትሁል ባሪ (4/68) የአቢ ያዕላ ሙስነድ ላይ ይህንን የሚያመለክት የጠነከረ ሰነድ እንዳለም ጠቅሰዋል፡፡] በማለት ሸይክ አብዱልሙህሲን አልአባድ አስረድተዋል።
እንግዲህ ለአንዲት በንጽህናና በጨዋነት ህይወት መድመቅና መፍካት ለምትሻ ሙእሚን ሴት ይህ ከበቂዋ በላይ ነው::
እርግጥ አንዳንድ ዑለማእ ይህንን በመንተራስ ፊት መግለጥ እንደሚቻል ይገልጻሉ::
ሆኖም በዚህ ሰአት እኛ ግዴታ የሚሆንብን ማስረጃዎች ይበልጥ የሚደግፉትን አቋም መያዝ ነው::
ይህንን የኡለማእ ፈትዋ ተንተርሰው ፊታቸውን የማይሸፍኑ እህቶች ላይ ሊኖረን የሚገባው አቌም ደግሞ ሌሎች ማስረጃዎችን አቅርበንላቸው በጥበብ ማስረዳትና ማሳወቅ እንጂ በዚህ ሰበብ ሆድና ጀርባ ልንሆን በፍጹም አይገባም::
🔑ፊቷን ካልሸፈነች በሚልም የእህትነት መብቷን ልትነፍጊያት አይንሽን ላፈር ልትያት አይገባም::
ይልቁንም አንቺን ለመሸፈንና እንደ አልማዝ እንቁ ለመሆን ያበቃሽ ጌታ እርሷንም እንዲያበቃትና ያሉባትን ችግሮች አስወግዶ እንዲያመቻችላት ልትለምኚላት ይገባል፡፡
በእውነቱ ኒቃብን በመልበስ የሚገኘውን ሰላም፣ እርካታ፣ ደስታና እርጋታ አምናበት ተግብራ ያየች ብቻ ናት የምታውቀው።
አንዳንድ እህቶች ስለ ፊት መሸፈን ሲነገራቸው እኛ ልባችን ንጹህ ነው ሌላ ነገር አያስብም እና ሌላም ሌላም ሲሉ ይደመጣሉ።
በርግጥ የተገለጡ ሁሉ ብልግናን ፈላጊዎች ናቸው አልተባለም። አይደሉምም።
ነገር ግን የአላህን ሱብሃነሁ ወተአላ ትእዛዝ በተቃረኑ ቁጥር ቀልብ እየተበላሸና እየዛገ መሄዱ ሳይታለም የተፈታ እውነታ ነው::
ሃያ አራት ሰአት ከወንዶች ጋር እየተደባለቁ አንዱ ከንፈርሽ ድንቅ ነው እያላት ፣ አንዱ ኮብላላው አይንሽ እያላት፣ ባየው ሲያሞካሻት ልቡና ልቧ ላይ ምንም ሳይፈጠር በጤንነት እዘልቀዋለሁ ማለት ራስን መሸንገል ነው፡፡
በግልፅ የመተያየት ጣጣም ነው ከሰው እይታ በመገለል ለማውራት፣ ለመጨባበጥና ለሌላውም ቅርርቦሽ የሚያበቃው።
ነቢዩ ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም እንደጠቆሙን
አንድ ወንድ ከአንዲት ሴት ጋር በተገለለ ቁጥር ሶስተኛቸው ሸይጣን ነውና ወደ ገደሉ ሊከታቸው ይመቸዋል።
እንዲሁም መጨባበጡም ከባድ አደጋ የሚያመጣ በመሆኑ አስቀያሚና ዘግናኝ ውጤት ማስከተሉን ሲገልፁ
« አንድ ሰው ያልተፈቀደለትን ሴት ከሚጨብጥ ከብረት በሆነ ወስፌ ጭንቅላቱን ቢወጋ ይሻላዋል» ብለዋል።
ለዚህ ሁሉ መኣት የሚያበቃን መተያየቱ ነው።
ይህ ደግሞ ተጨባጭ የሆነ ነገር ነው። የማያያትን ሴት ለመቃለድ፣ ለመሳሳቅ፣ ለመጨዋወት፣ ከሰው እይታ ተገልሎ ለማውጋት እንዲሁም ለማቀፍም ሆነ ለመጨበጥም ደፍሮ የሚቀርብ ወንድ ማግኘት ከባድ ነው።
ምክንያቱም በምን አይቷት፣ በምን አውቋት፣ በምንስ ተመኝቷት
እንደሚታወቀው በመልክ የሚያውቋት የቅርብ ቤተሰቦቿ ከቀሪው ህዝብ አንፃር ጥቂት ናቸው።
ስለዚህ ከአብዛኛው በላእ በዚህ መጠበቂያ ዳነች ማለት ነውና አደራ ሂጃብሽን።
📅Jumaad Al-Awel 02/1436
📆Juma'a MARCH 23/2015