📌 አስገድደው ሊድሩኝ ነው ምን ላድርግ?
#ተንቢሀት_ካውንስሊንግ (002)
🏒 ውድ ተንቢሀቶች፤ ሰሞኑን ለአንድ እህት የተሰጠውን ምክር እንብቤ ነበር። የቤተሰቦቿን ምክር ቸል እንዳትል መክራችኃል። በጋብቻ ሊያስገድዱኝ እየሞከሩ ስለሆነ ከወላጆቼ ጋር እየተጋጨው ነው። ልጁን አልወደድኩትም። የወላጆቼን ሀቅ ማጓደል ያስፈራኛል። ቢሆንም የማልወደውን ህይወት መጀመር አልፈልግም።
👉🏻 ጋብቻውን ባልቀበል ተጠያቂነት ይኖርብኛልን? ተጨንቄያለውና ምክራችሁን ለግሱኝ።
::::::::::::::::::
ምላሽ፦ ባለፈው በሰጠነው ምላሽ ላይ የቤተሰብን ምክር እና ተሞክሮ በትኩረት አድምጦ ውሳኔ ላይ ከመድረስ በፊት እንደ ደጋፊ ሀሳብ መመልከት ተገቢ መሆኑን ጠቁመናል። ይህ ማለት ግን የአንቺ ውሳኔ በነሱ ስሌትና ምርጫ ብቻ የተገደበ ነው ማለት አይደለም። ምርጫውና የመጨረሻ ውሳኔው ያንቺ ብቻ ነው። ሆኖም ግን የቤተሰብ ምርጫም መልካም ሊሆን ይችላልና መለስ ብለሽ የጠላሽው በምን ምክኒያት እንደሆነ አስተውይ። በወላጅ በኩል ወደ ትዳር መሄድ ኃላ ቀርነት ነው ከሚል መነሻ ብቻ ከሆነ ተሳስተሻል። ካለሽበት እድሜና ካለሽ የህይወት ተሞክሮ አንፃር ያዩብሽ የብስለት ማነስ መጥፎ ሰው ላይ እንዳይጥልሽ ከመስጋት ሊሆን ይችላል። መልካም ሰው በመምረጥ ልጅን ወደ ትክክለኛ ምርጫ ማመላከት ከተከበሩ የጨዋ ማህበረሰብ እሴቶች የሚቆጠር ነው። በወላጆችሽ በኩል የቀረበልሽን ሰው የጠላሽው በዲናዊ እንከኖቹ ምክኒያት ከሆነ ግን፤ ዲን የዲን መሰረት ነውና ለአፍታም እንዳታመነቺ። ሸሪዓን እስካልተፃረረ ድረስ ሌሎች መስፈርቶችንም ማስቀመጥ አትከለከይም።
☞ ወላጆች ልጃቸውን አስገድደው መዳራቸው ሀራም ነው። የኢስላም ሊቃውንት እንዳብራሩት ተከታዩ ሀዲስ ለዚህ መረጃ ነው።
(لَا تُنْكَحُ الْبِكْرُ حَتَّى تُسْتَأْذَنَ) رواه البخاري ومسلم
«ልጃገረድ ፍቃድ ሳትጠየቅ አትዳርም!» ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል
ማስገደድ የሚቻል ቢሆን ፍቃድ መጠየቋ ምንም ትርጉም አይኖረውም ነበር። ይህ ላላገባችዋ ልጃገረድ ከሆነ አግብታ የፈታችውን – ባለ ተሞክሮ ሴት– ነፃ ምርጫ እንዳላት ኡለማዎች ያሰምሩበተል። እንደዚሁ ወላጆች ወንድ ልጃቸውንም ማስገደድ አይፈቀድም።
አል ኢማም አል–ቡኻሪ ይህንን ሀዲስ በኪታባቸው ሲያሰፍሩ የሰጡት ርእስ [አባትም ይሁን ሌላ (ወሊይ) ልጃገረድንም ይሁን አግብታ የፈታችን ሴት በፍላጎቷ ካልሆነ በቀር መዳር እንደማይችል የሚገልፅ ክፍል] የሚል ነው።
አላህ ሴት ልጅ የለገሰው አባት፤ ልጁ የወደደችው ባል አቻዋና መሰረታዊ መስፈርቶችን ያሟላ እስከሆነ ድረስ ጌታውን ሊፈራና ፍላጎቷን ሊሞላ ይገባዋል።
ያልወደደችውን ሰው መርጦላት እንድታገባ ቢያስገድዳት አላህ ዘንድ ያስጠይቀዋል። ወላጆቹ ካለፍላጎቱ ቢድሩት ምን አይነት ምላሽ ሊኖረው እንደሚችል እራሱን ሊጠይቅ ይገባል። እውን ምርጫቸውን ሳይወድ በግድ ተቀብሎ ትዳር ይመሰርት ነበርን??
አባት ልጁን የሚድረው ለራሷ ጥቅም ነው። ኑሮዋም የራሷ ነው። ስለዚህ ለማትፈልገው ሰው መዳሩ ህይወቷን ማበላሸት ይሆናል። አብዛኛውን ግዜ በግዴታ የተመሰረተ ትዳር ለውድቀት የቀረበ ነው።
ሸይኹል ኢስላም ኢብኑ ተይሚያህ እንዲህ ብለዋል፦ «አንዲትን ሴት ለምትጠላው ሰው መዳር ከሸሪዓ መሰረታዊ መርሆዎችን ከመፃረሩ ባሻገር ጤናማ አዕምሮም የሚቀበለው አይደለም።
በአላህ ይሁንብኝ፤ ካለፍቃዷ አንድን ነገር እንድታከራይም ይሁን እንድትሸጥ ሊያስገድዳት አይችልም። የማትወደውን እንድትመገብ፣ እንድትጠጣ ወይም እንድትለብስም ማስደድ አይችልም። ታዲያ ከማትወደው ሰው ጋር በትዳር እንድትጣመርና ዘወትር አብራው እንድትኖር እንዴት ያስገድዳታል?? አላህ በባለትዳሮች መካከል ፍቅር እና መተዛዘንን ደንግጓል። ነገር ግን ይህ ትዳር የተመሰረተው እየጠላችው፣ እየሸሸችው ከሆነ ምን አይነት ፍቅርና መተዛዘን ሊመሰረት ይችላል?» አል ፈታዋ 32/25
ከዚህ በመነሳት፤ አንድ ሰው የወላጆቹን ምርጫ ባይቀበል ወላጆቹን እንደበደለ አይቆጠርም። ፍላጎታቸውን ባለማሟላቱም ወቀሳ የለበትም።
ይህንን በማስመልከት ኢብኑ ተይሚያህ እንዳሉት፤
وليس للأبوين إلزام الولد بنكاح من لا يريد، فإن امتنع لا يكون عاقاً، كأكل ما لا يريد الاختيارات" (ص 344) .
«ወላጆች ልጃቸውን በጋብቻ የማስገደድ መብት የላቸውም። ጋብቻውን ባይቀበል ወንጀለኛ አይሆንም።» አል–ኢኽቲያራት ገፅ 344
ወላጆች ለልጆቻቸው አዛኝ እንዲሆኑ፣ ሰዎች ያልኩትን ሁሉ ሊታዘዙኝ ይገባል ከሚል ኩራት በአላህ እንዲጠበቁ ይመከራሉ። በቤተሰብ ውስጥ ይህን መሰል አለመግባባት ሲከሰት ለልጃቸው ሀሳብ ቦታ በመስጠት በሰከነ መንፈስ መመካከር ይገባል።
ውዷ እህታችን...
ለወላጆችሽ ለስላሳ ሁኚ። ሀሳብሽን በጥበብ ግለጪ። ድምፅሽን ከፍ ከማድረግም ይሁን ከኩርፊያ ተቆጠቢ። ሸይጣን ይህንን መነሻ በማድረግ በመካከላችሁ ያለውን ክፍተት ሊያሰፋ ያሴራልና ጆሮ እንዳትሰጭው። በእጅጉ ጠንቃቃ ሁኚ። ነገሩ ካቅምሽ በላይ ከሆነ ለቤተሰብ ቅርብ የሆኑ አስተዋይ ሰዎች ጣልቃ ገብተው ወላጆችሽን እንዲያሳምኑልሽ ጥረት አድርጊ።
ከዚህ ሁሉ ጥረት በኃላ አሻፈረኝ ካሉ የመታዘዝ ግዴታ የለብሽም። በደሉ ከነሱ በኩል ነውና አንቺን አይጎዳሽም። ነገር ግን ሀቃቸውን አለማጉደልን እና በመልካም መኗኗርን የዘውትር ልማድሽ አድርጊ። እንኳን በጋብቻ በእምነት የሚፃረሩን ወላጆች እንኳ በዚህ መልኩ እንድንንከባከብ ታዘናል።
አላህ እንዲህ ብሏል፦
(وَإِنْ جَاهَدَاكَ عَلى أَنْ تُشْرِكَ بِي مَا لَيْسَ لَكَ بِهِ عِلْمٌ فَلَا تُطِعْهُمَا وَصَاحِبْهُمَا فِي الدُّنْيَا مَعْرُوفًا) لقمان/15 .
«ለአንተ በእርሱ ዕውቀት የሌለህን ነገር በእኔ እንድታጋራ ቢታገሉህም አትታዘዛቸው፡፡ በቅርቢቱም ዓለም (በዱንያ) በመልካም ሥራ ተወዳጃቸው፡፡ ወደእኔም የተመለሰን ሰው መንገድ ተከተል፡፡ ከዚያም መመለሻችሁ ወደእኔ ነው፡፡
ትሠሩት የነበራችሁትንም ሁሉ እነግራችኋለሁ፡፡» ሉቅማን 15
አላህ መልካሙን ሁሉ ይግጠምሽ!!
© ተንቢሀት
http://www.facebook.com/