Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

በደል ምንድን ነው ?


በደል ምንድን ነው

«الَّذِينَ آمَنُواْ وَلَمْ يَلْبِسُواْ إِيمَانَهُم بِظُلْمٍ أُوْلَـئِكَ لَهُمُ الأَمْنُ وَهُم مُّهْتَدُونَ »
[سورة الأنعام : 83 ]

«እነዚያ ያመኑና እምነታቸውን በበደል ያልቀላቀሉ እነዚያ እነርሱ ጸጥታ አላቸው። እነርሱ የተመሩ ናቸው»
[አል አንዓም: 82]

🔐የቃላት መፍቻ፦

፠፤« آمَنُواْ » «ያመኑ» ፦

ኢማን (እምነት)፦

በቋንቋ ደረጃ እርግጠኛ ከመሆን ጋር እውነት ብሎ መቀበል ማለት ሲሆን።

በሸሪዓ ደግሞ፦ በልብ የሚቋጠር ፣ በምላስ የሚነገር ፣ በአካል የሚተገበር ፣ አላህን በመታዘዝ የሚጨምርና አላህን በማመፅ (ሸይጧንን በመታዘዝ) የሚቀንስ ነው።

፠«يَلْبِسُواْ» ፦ ያልቀላቀሉ።

፠« إِيمَانَهُم »፦ ተውሂዳቸውን።

፠« بِظُلْمٍ » «በበደል»፦

"በደል" ማለት በዚህ አገባብ በሽርክ ማለት ነው። ማሰረጃውም፦

ታላቁ ሶሃብይ ዐብደላህ ኢብኑ መስዑድ እንዲህ ብሏል ይህች የቁርኣን አያ (አንቀፅ) በወረደች ጊዜ ሶሃባዎች (ሁሉንም የወንጀል አይነት የሚያጠቃልል መስሏቸው) በጣም ከበዳቸው ፦

የአላህ መልዕክተኛ ﷺ ሆይ!

«ነፍሱን የማይበድል ማነው? አልናቸው።

እርሳቸውም እንዲህ አሉ፦

(ነገሩ) እናንተ እንደምትሉት አይደለም ።

« እምነታቸውን በበደል ያልቀላቀሉ» በሽርክ ያልቀላቀሉ ማለት ነው ።

ሉቅማን (ያ መልካም ባሪያ) ለልጁ ያለውን ንግግር አልሰማችሁምን?

«ُ يَا بُنَيَّ لَا تُشْرِكْ بِاللَّهِ إِنَّ الشِّرْكَ لَظُلْمٌ عَظِيمٌ »
[ﺳﻮﺭﺓ ﻟﻘﻤﺎﻥ: 13]

«ልጄ ሆይ! በአላህ አታጋራ ማጋራት ታላቅ በደል ነውና።»
[ሉቅማን: 13]

📚[አል ቡኻሪይ (3636) ዘግበውታል]

(ዙልም) በደልን በሶስት ዓይነት ከፍለን መመልከት እንችላለን፦

1• ሽርክ① (አንድ ሰው ራሱን የሽርክ ወንጀልን በመስራት መበደል)

2• አንድ ሰው ራሱን መበደል (ከሽርክ ውጪ ያሉ ወንጀሎችን በመስራት)

3• አንድ ሰው ሌላን አካል መበደል

፠« لَهُمُ الأَمْنُ » «እነርሱ ጸጥታ አላቸው »

«አምን» በሚለው የተፈለገበት፦

አንድ ሰው ተውሂድን በአግባቡ ከማረጋገጥ ጋር ከሽርክ ውጪ ያሉ ከባባድ ወንጀሎች ላይ እስካልዘወተረ ድረስ እሳት ከመግባት ነፃ መውጣት።

እንዲሁም፦

ተውሂድን በአግባቡ ከማረጋገጥ ጋር ከሽርክ ውጪ ያሉ ከባባድ ወንጀሎችን በመስራት የዘወተረ ከሆነ ደግሞ ጀሀነም ውስጥ በዘውታሪነት (ዘለዓለም) ከመቀጣት ነፃ መውጣት ነው። በወንጀሉ ልክ ተቀጥቶ ጀነት ተመልሶ ይገባል።

፠« مُّهْتَدُونَ » «የተመሩ ናቸው»፦
(ማለትም)

እነርሱ በዚህች ቅርቢቱ ዓለም (ዱንያ) ሀቅ (እውነትን ) ያወቁና በእርሱም የሰሩ ናቸው።

፠፠፠ ፠፠፠ ፠፠፠ ፠፠፠ ፠፠፠ ፠፠፠
①[ጥብቅ እርምት ፦

ሰዎች ዘንድ በብዛት ተሰራጭቶ የሚገኝ የተሳሳተ ገለፃ አለ እርሱም የዙልም ዓይነቶችን ሲጠቅሱ አንደኛውን አይነት "ሽርክ" በሚለው ፋንታ "የሰው ልጅ ጌታውን መበደል" በማለት መግለፅ ነው።

ይህ የተሳሳተ አገላለፅ ነው። የሰው ልጅ ጌታውን ፈፅሞ ሊበድል አይችልም ታላቁን ወንጀል ሽርክ እንኳን ቢሰራ ነፍሱን እንጂ አላህን በደለ አይባልም። አላህ በፍጡራኖቹ ከመበደል የጠራና የላቀ አምላክ ነው። ስለሆነም "የሰው ልጅ ጌታውን መበደል" ሳይሆን "ሽርክ" በሚለው መታረም ይኖርበታል።]

📚 [ምንጭ ፦«አል ጀዲድ ፊ ሸርህ ኪታቡ ተውሂድ ገፅ 26 » ተጨማሪ ሀሳቦች ታክለውበት]

✒ ሀይደር ኸድር (አቡ ሀማድ)

ــــــ ❁ ❁❁ ❁ ــــــ

✍ ዳሩል ኢህሳን

https://telegram.me/DarulIhsan
https://www.facebook.com/darulihsaan