Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

የሸይኽ ሙሐመድ ዐብዱልወሃብ አልወሷቢ ረሒመሁላህ የህይወት ታሪክ በአጭሩ

የሸይኽ ሙሐመድ ዐብዱልወሃብ አልወሷቢ ረሒመሁላህ የህይወት ታሪክ በአጭሩ
ስያሜና የዘር ግንድ
እሳቸው አቡ ኢብራሂም ሙሐመድ ኢብን ዐብዱልወሃብ ቢን ሙሐመድ አል ወሷቢ አልዐብደሊይ አልየሚኒ ናቸው። ረሒመሁላህ
የዘር ግንዳቸው የሚመዘዘው ወሳብ ከተባለ ምንጭ ሲሆን በኒ ዐብደላህ ከተሰኘ ጎሳ ይመደባል።
ውልደት
ሸይኹ ረሒመሁላህ የተወለዱት በ1376 ሰፈር 12 እለተ ማክሰኞ ልክ ፈጅር አዛን ሲል ነው።
እውቀት
ሸይኹ በልጅነታቸው መፃፍና ማንበብ ብሎም ቁርኣን የተማሩት አካባቢያቸው ላይ አባታቸው በሚያስተምርበት መድረሳ ከራሳቸው አባት ነበር። ሸይኹ በወጣትነታቸው መጀመሪያ ላይ ወደ ሐረመይን (ሱዑዲያ) በመጓዝ በዳሩል ሐዲሥ መዲና ከ1392 እስከ 1396 ዓመተ ሒጅሪያ ተምረዋል። ከዚያም ሐረም አልመኪ (መካህ) በመሄድ ከ1397 እስከ 1398 ድረስ እስከ እዛ የሚገኘው መዐሃድ ላይ ተምረዋል።
ዳዕዋ እና በድጋሚ እውቀት
ከዚያም በ1398 ዓመተ ሒጅሪያ ወደ ሐገራቸው የመን በመመለስ አካባቢያቸው እና ሐገራቸው ላይ ተውሒድና ሱናን ማስተማር ያዙ። ሽርክና ቢድዓንም አጥብቀው ኮነኑ። በ1408 ዓመተ ሒጅሪያም ወደ ታላቁ ዐሊም ሸይኽ ሙቅቢል ረሒመሁላህ ደማጅ በመጓዝ ከሸይኹ ዒልምን መቅሰም ጀመሩ። እዚያም ከታላቁ ዐሊም ሸይኽ ሙቅቢል ረሒመሁላህ ዒልምን እየተጎነጩ እስከ 1412 ዓመተ ሒጅሪያ ድረስ የቆዩ ሲሆን በክረምቱ ጊዜ ወደ አካባቢያቸው ሐዲዳህ በመጓዝ መስጂዳቸው ላይ ያስተምሩና ዳዕዋ ያደርጉ ነበር።
ስራዎች
ሸይኹ ረሒመሁላህ በህይወት በቆዩባቸው ዘመናት ጥቂት የማይባሉ ኩቱቦችን የፃፉ ሲሆን ከነርሱ ውስጥ ግን እጅግ በጣም የሚታወቀው «አልቀውሉል ሙፊድ ፊ ዐዲለቱ ተውሒድ» የተሰኘው ኪታባቸው ነው።
ሸይኽ ሙቅቢል የሸይኽ ሙሐመድ ዐብዱልወሃብ አልወሳቢን በርካታ ኩቱቦች መቅድም የፃፉላቸው ሲሆን እንዲሁም አብዛኛውን ኩቱቦቻቸውን አወድሰውላቸዋል።
ኩቱቦቻቸውም መካከል
አልቀውሉል ሙፊድ ፊ ዐዲለቱ ተውሒድ
አልጀውሃር ፊ ዐደዲ ደረጃቱል ሚንበር
አልተልኺስ አልሀቢር ፊ ሑክም ሪዳዑል ኪበር
ቱህፈቱል ዐርበዐ ቢማ ጃአ አልዐስ ሊልኸጢብ
አልቀውሉል መርዲይ ፊ ዑምረቱል መኪይ
አልቀውሉል ቀዪይ ፊ ተኽሪጅ ወተህቂቅ አልሐዲሥ አልቁኑት ሊልሐሰን ቢን ዐሊይ
አልቀውሉል ሰዋብ ፊ ሑክሙል ሚሕራብ
አልጠርዱል ው አልኢብዐድ ዐን ሐውድ ፊ የሙሚል መዓድ
ተሕቂቅ ሪሳለቱል ሱዩጢ «ኢዕላም አልረይብ ቢሑዱሥ ቢድዓቱል ሙሓሪብ»
አስተማሪዎቻቸው
ሸይኹ ረሒመሁላህ የተማሩባቸው አብዛኛዎቹ አስተማሪዎቻቸው ታላላቅ ደረጃን የተጎናፀፉና ዐለም በእውቀታቸው ጥልቀት ከመሰከረላቸው ኮከብ ዑለማዎች ነው። ከነርሱል አሽሸይኹል ዐላማ ዐብዱል ዐዚዝ ኢብኑ ባዝ፣ ሸይኹል አልባኒ ሙሐዲሥ ዐላመቱል አልባኒ፣ አሽሸይኹል ፈቒህ ኢብኑል ዑሠይሚን፣ የየመኑ አንበሳ ሸይኹል ዐላማ ሙቅቢል ቢን ዋዲዒ፣ አሽሸይኽ ሙሐዲሥ ሐማደል አንሳሪ፣ አሽሸይኽ በክር ቢን ዐብደላህ አቡ ዘይድ (ረሒመሁሙላህ ረሕመተን ዋሲዐ) እና ሌሎችም ናቸው።
ከተማሪዎቻቸውም መካከል
አሽሸይኽ ሙሐመድ ኢብን ሷሊሕ አስ ሶማሊ፣ አሽሸይኽ ሙሐመድ ዐሊ መቅቡል አልሙሐመዲ፣ አሽሸይኽ ዐሊ ቢን ሙሐመድ አልኹላሲ እና ሌሎቹም ሲገኙበት ዛሬ ላይ የተማረበትን የእውቀት አባት ልቅና ረስቶ የሚሰድባቸውና ከሱና ፈንግሎ የሚያስወጣቸው የህያ አልሐጁሪ አላህ ይምራውና የዚህ ታላቅ ሸይኽ ተማሪ ነበር። [የበላበትን ወጪት ሰባሪ፣ የጎረሰበትን እጅ ነካሽ]
እኚህን ሸይኽ ረሒመሁላህ ታላላቅ የእውቀት ተራራዎች ያወደሷቸውና ሙገሳን የቸሯቸው ሲሆን ከነርሱም ውስጥ
ሸይኽ ሙቅቢል ቢን ዋዲዒ
ሸይኽ ሙሐመድ አልወሷቢን የየመን ሙፍቲ ይሏቸው የነበር ሲሆን «እኔ የሞትኩ እንደሆን በሸይኽ ሙሐመድ ዐብዱልወሃብ አልወሷቢ አደራ እላችኋለሁ» ይሉም ነበር።
ታላቁ ዐሊም የህያ አንነጅሚ ረሒመሁላህ
«ቀውሉል ሙፊድ» በተሰኘው የሸይኹ ኪታብ መቅደም ሲፅፉላቸው ሸይኽ ሙሐመድ አልወሷቢን «አልዐሊሙል ጀሊል» [ልቅና ያለው ዐሊም] እያሏቸው ነበር የሚፅፉት።
ሸይኽ ረቢዕ ኢብኑ ሓዲ አልመድኸሊ ሐፊዘሁላህ
« የመን ውስጥ ዑለማ የለም» ብለው የስሜት ተከታዮች እንደሚያወሩ በተነገራቸው ጊዜ የመለሱት «አሽሸይኽ ሙሐመድ ዐብዱል ወሃብ አልወሳቢስ? እሳቸውስ ምንድን ናቸው?» ብለው ነበር የመለሱት።
ሸይኽ ዑበይድ ቢን ዐብዲላህ አልጃቢሪ ሐፊዘሁላህም ሸይኹን ሲያሞግሷቸው በርካታ ጊዜ ተሰምቷል።
የመን ሃገር ከሚገኙ ታላላቅ ዑለማዎች እንደነ ሸይኽ ሙሐመድ አልኢማም፣ ሸይኽ ዐብዱረሕማን አልዐደኒ፣ ሸይኽ ዐብዱላህ አልዐደኒ የመሳሰሉ የእውቀት ተራራዎችም ሸይኹን በርካታ ጊዜ አወድሰዋቸዋል።
የሸይኹ ባህሪ
ሸይኹ ረሒመሁላህ በጥሩ እንጂ በመጥፎ ሲወሱ ታይቶምተሰምቶም አይታወቅም። በዙህዳቸው፥ ለእውቀት ትልቅ ቦታ መስጠታቸው ሁሌም ያስወድሳቸው ነበር። ከአስተማሪያቸው በላይ ደግሞ እሳቸውን ሊገለፃቸው የሚችል ያለ አይመስለንም። ስለዚህ ሸይኻቸው ታላቁ ሸይኽ ሙቅቢል ረሒመሁላህ ስለርሳቸው ሲናገሩ ባህሪያቸውን እንዴት እንደሚገልፇቸው አይተን ፅሁፉን እንጨርሳለን።
ሱናን አጥብቀው የሚወዱ
ለዐቂዳ ትኩረት የሚሰጡ
ጠቃሚ የሆኑ ርእሰ ነጥቦችን በትክክለኛው መንገድ የመረዳት ክህሎት ያላቸው
ሙስሊሞችን ከፋፋይ ለሆነው ቡድንተኝነት የጠነከረ ጥላቻ ያላቸው
ሐቁ ከተገለጠላቸው ከጀርባዬ ሳይሉ ሐቁን የሚቀበሉ [ዐሊም እንደዚያ ነው መሆንም ያለበት]
ለሱና ባልተቤቶች ላቅ ያለ ፍቅር ያላቸውና የቢድዓ ባለቤቶችን ደግሞ በመጥላት ላይ ብርቱ የሆኑ
መተናነሳቸው፣ ልስላሴያቸው፣ ትእግስታቸው፣ ቻይነታቸው፣ ሁሉም ተማሪ እስኪወዳቸው ድረስ እነዚህ ባህሪያት አላህ አድሏቸዋል።
በሁሉም ነገር ቻይ የሆነው ጌታችን አላህ ሙስሊሞችን እና ኢስላምን የሚተቅሙ ያድርጋቸው።
[من مقدمة፥ القول المفيد] [ የቀውሉል ሙፊድ መቅድም በሸይኽ ሙቅቢል]
ሸይኹ ረሒመሁላህ በመጨረሻም በ7 /10ኛው ወር በ1436 ዓመተ ሂጅሪያ ወደ ፈጣሪያችን አላህ ተመለሱ።
እኛም የአላህ ነን ወደ መመለሻችንም ወደ እላህ ነው
አላህ የሸይኹን ቀብር ኑር ያልብስላቸው። የጀነት ጨፌም ያድርግላቸው። ጀነቱል ፊርደውስ ያለሒሳብ ከቢገቡት እንዲያደርጋቸው አላህን በመልካም ስምና ባህሪያቶቹ ሁሉ እንማፀነዋለን።
[ይህ የሸይኹ የህይወት ታሪክ የተፃፈበት ዋነኛ መንስዔ በአሁኑ ሰዓት እኚህን ታላቅ ዐሊም በመሳደብና ያላቸውን ደረጃ ዝቅ በማድረግ ላይ (በሃገራችንም ሆነ በሌላው ሃገራት) የሚገኙ ድንበር አላፊዎች በመኖራቸው የሸይኹን ማንነት ለማሳወቅ ያህል ቢሆንም የእኚህን ሸኽ ልቅና ማወቃችን ከሸይኹ እንድንጠቀምባቸው ብሎም ለእውቀት ከፍተኛ ደረጃ ሰጥተን እውቀት መፈለግ ላይ እንድንበራታ ሞራል እንዲሆነንም ጭምር ነው።]