Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

የትእግስት መሰላል ከድል ደጃፍ ያደርሳል!


የትእግስት መሰላል ከድል ደጃፍ ያደርሳል!
ፈተና የአላህ ሱና ነው። መልኩ ቢለያይም ደረጃው ቢፈራረቅም ማንም የማያመልጥበት የሆነ ወጥመድ። ጌታችን አላህ "ሰዎች አመንን ስላሉ ብቻ ሳይፈተኑ ሊተው ያስባሉን?" ሲል እስትንፋሳችን ዱንያን እስከምትሰናበት ድረስ ከፈተና እንደማናመልጥ እቅጫችንን ነግሮናል። ኧረ እንዳውም “ከፍርሃትና ከረሃብም በሆነ ነገር፤ ከገንዘቦች፣ ከነፍሶችና ከፍሬዎች በመቀነስም በእርግጥም እንፈትናችኋለን” ሲል አስረግጦ ነግሮናል፡፡ ታዲያ ብልጦቹ ይታገሳሉ፡፡ ሽልማታቸውንም ያፍሳሉ፡፡ ቂሎቹ ደግሞ ይወራጫሉ፣ ምንም ጠብ ላያደርጉ የትእግስትን እድል በማሳለፍ ከሁለት ያጣ ይሆናሉ፡፡
በርግጥ የዋሆች ባያስተውሉትም ፈተና ማለት ቅስማችንን የሚሰብረን ነገር ብቻ አይደለም፡፡ ፈተና ስቃይ እንግልቱ፣ መከራው መአቱ ብቻ ሳይሆን ድሎት ምቾቱም፣ ሁሉም የአላህ ፈተና ነው። ታዲያስ "ከዚያም ከ(ተዋለላችሁ) ፀጋዎች ሁሉ በርግጥም ትጠየቃላችሁ" ማለቱ ምንድን ነው የሚያመላክተን? እንዳውም ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ከማጣት ይልቅ የማገኘትን ፈተና ሰግተውልናል። ጌታችን በክፉ ከተፈተነው ትእግስትን፤ በበጎ ከተፈተነው ምስጋናን ይጠብቃል። የኛ ነገር ግን ሲበዛ ግራ ነው። ብናገኝ ጥጋባችን መከራ። ብናጣ ምሬታችን ፈተና። ቢደላን ምስጋናውን አናውቅበት፡፡ ቢከፋን ትእግስቱን አንችልበት።
በህይወታችን ላይ የሚያጋጥመን እያንዳንዱ ነገር ቢከፋም ቢለማም ሁሉም ከአላህ ነው። ይሄ ከስድስቱ የኢማን ምሰሶዎች የአንዱ መሰረታዊ መልእክት ነው፣ ቀደር። በቀደር ማመን በመርህ ደረጃ ከማስተጋባት ባለፈ በተጨባጭ በህይወታችን ላይ ልናስገኘው የሚገባ አንኳር የሙእሚን መለያ ነው። በቀደር ማመን አማኞችን ጀግና ያደርጋል። አላህ ከወሰነው ውጭ ምንም አይደርስብኝም ብሎ የቂን ብሎ የሚያምን አካል የፍጡራን ሴራ አያሸብረውም። ሞራሉንም አይሰብረውም፡፡ የዘወትር መፈክሩ "አላህ ለኛ የፃፈብን እንጂ ፈፅሞ አያገኘንም" የሚለው መለኮታዊ ቃል ነው። በቀደር ስታምን ሰው ጂኑ ከጥንት እስከ ዛሬ ባንድ አብረው ቢዘምቱ አላህ ከፃፈብህ ውጭ ቅንጣት ታክል ምንም እንደማያደርሱብህ ስለምታምን በፍጡር አትሸበርም፣ ከፍጡር አትከጅልም። በቀደር ስታምን አንዴ በተከሰተ ነገር በከንቱ አትብከነከንም፣ በባዶ አትቆዝምም። የሆነውን ላትቀይር ነገር "እንዲህ አድርጌ ቢሆን ኖሮ" እያልክ የቂል ፀፀት ውስጥ አትገባም። ለምን ቢባል "ቢሆን ኖሮ" ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዳሉት “የሸይጧንን ስራ ትከፍታለችና፡፡” አላህ አለምን ከመፍጠሩ ከሃምሳ ሺ አመት በፊት የወሰነውን ውሳኔ በቢሆን ኖሮ አትቀይረውምና ለአላህ እጅ ስጥ። “አላህ ቀደረው፣ የሻውንም ፈፀመ” በል። የሙእሚን መታወቂያው ይሄው ነው፡፡ “የሙእሚን ነገሩ አስገራሚ ነው፡፡ ነገሩ ሁሉ ለሱ መልካም ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ለአማኝ እንጂ ለማንም አይደለም፡፡ (ሙእሚን) አስደሳች ነገር ቢያገኘው ያመሰግናል ይህ ለሱ መልካም ነገር ነው፡፡ ጎጂ ነገርም ቢያገኘው ይታገሳል ይህም ለሱ መልካም ነገር ነው” ይላሉ ውዱ ነብይ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም፡፡ [ሙስሊም]
ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም የሚወዱትን ነገር ሲመለከቱ "ምስጋና ለአላህ ይሁን በፀጋው በጎ ነገሮች ይፈፀማሉ" ሲሉ "የሚጠሉትን ሲመለከቱ ደግሞ "በማንኛውም ሁኔታ ምስጋና ለአላህ ይሁን" ይሉ ነበር። እኛ በሚደርሱብን ነገሮች ከትእግስት ይልቅ ብስጭትን፣ ተስፋ መቁረጥን፣ ቀንን መራገምን ምርጫችን የምናደርገው ቀላል አይደለንም፡፡ በሚደንቅ ሁኔታ አላህን እስከማማረር አልፎም እስከመሳደብ የሚደርሱም አሉ፡፡ ሱብሓነላህ! የምትጮኸው ለዲን ከሆነ የዲኑን ባለቤት አዛ ስታደርግ ዋሾነትህን በራስህ ጊዜ አጋልጠሃል፡፡ የተፈተንከው በዱንያህ ከሆነ ለርካሽ ዱንያ ስትል ክቡር ጌታህን ተዳፍረህ ቀላልነትህን አሳይተሃል፡፡ የሰው ልጅ ሆይ! አንተ የቱ ጋር ነህ?
ወንድሜ ሆይ ምንም ቢደርስ ታገስ! እርግጠኛ ሁን በትእግስት ምንም የምታጣው ነገር የለም፡፡ እንዳውም ትእግስቱን ከቻልክበት ካሰብከው ትደርሳለህ፡፡ ያለምከውን ታሳካለህ፡፡ ድል ትፈልጋለህ? እንግዲያውስ ታገስ፡፡ “እወቅ ድል ከትእግስት ጋር ነው” ብለውሃል ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም፡፡ እርዳታ ትፈልጋለህ? እንግዲያውስ ታገስና ወደ ጌታህ ተመለስ፡፡ “በትእግስትና በሶላት ታገዙ” እያለ ነው ጌታህ፡፡ ካለህበት ጭንቅ መውጣት ትፈልጋለህ? እንግዲያውስ ታገስ፡፡ ይበልጥ በተጨነቅክ ቁጥር ይበልጥ ፍጡርን እየተወክ ይበልጥ በጌታህ ላይ ተስፋህን እየጣልክ ትመጣለህ፡፡ ያኔ እፎይታን ታገኛለህ፡፡ “እፎይታ ወይም ግልግል ከጭንቅ ጋር ነው” ይላሉ መልእክተኛው ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም፡፡ ታገስ በትእግስት የጠላት ውስብስብ ሴራዎች ይበጣጠሳሉ፡፡ ታገስ በትእግስት እብሪተኛ አንባገነኖች ይፈራርሳሉ፡፡ ታገስ በትእግስት ደካሞች ድሎትን ይጎናፀፋሉ፡፡ “ዝም ብለን ልንቀመጥ ነው ወይ?” አትበለኝ፡፡ ወንድሜ ሆይ! ለመሆኑ የሶብር ትርጉሙ ዝም ብሎ መቀመጥ የሆነው ከመቼ ጀምሮ ነው? በየትኛውስ መዝገበ-ቃላት ላይ ነው እንዲህ አይነት ፍቺ የሚገኘው? እኛ እኮ በፈተና የመጀመሪያዎች አይደለንም፡፡ ቀደምቶች በዲናቸው ሳቢያ በመጋዝ ለሁለት ተሰንጥቀዋል፡፡ ቀደምቶች በዲናቸው ሳቢያ አይናቸው እያየ ከሚንቀለቀል እሳት ውስጥ ተማግደዋል፡፡ ቀደምቶች በዲናቸው ሳቢያ ከፈላ ዘይት ውስጥ ተነክረዋል፡፡ ቀደምቶች ነፍሳቸው እያለ በስለት ተዘልዝለዋል ተመትረዋል፡፡ ቆስለዋል ደምተዋል፡፡ ይሄ ወደፊትም የማይቋረጥ የጌታችን ሱና ነው፡፡ ጌታችን አላህ እንዲህ ይላል፡- “በገንዘቦቻችሁ እና በነፍሶቻችሁ በርግጥ ትፈተናላችሁ፡፡ ከነዚያም ከናንተ በፊት መፅሀፍን ከተሰጡትና ከነዚያ ከሚያጋሩትም ብዙን ማሰቃየት ትሰማላችሁ፡፡” አዎ የሚደርስብን የደረሰባቸው ነው፡፡ ካለንበት ለመውጣት የታዘዝንበት ብልሃትም የታዘዙበት ነው፡፡ “ብትታገሱና ብትጠነቀቁ ይህ ከጥብቅ ነገሮች ነው” ብሎናል፡፡ [አሊ ዒምራን፡ 186] ፈተናው ሊከብድ ስቃዩ ሊጨምር ይችላል፡፡ ግና መለኮታዊ አዋጁን እንስማ፡ “በእውነቱ የእነዚያ ከበፊታችሁ ያለፉት (ምእመናን መከራ) ብጤ ሳይመጣችሁ ጀነትን ልትገቡ ታስባላችሁን? መልእክተኛውና እነዚያ ከርሱ ጋር ያመኑት “የአላህ እርዳታ መቼ ነው?” እስከሚሉ ድረስ መከራና ጉዳት ነካቻቸው፣ ተርበደበዱም፡፡ ንቁ! የአላህ እርዳታ በእርግጥ ቅርብ ነው (ተባሉም፡፡)” [አልበቀራ፡ 214]
አዎ የአላህ እርዳታ ቅርብ ነው፡፡ ግና የአላህን ትእዛዝ ማክበር ይጠይቃል፡፡ ፈረጃውን ለማፋጠን፣ ድሉን ለማቅረብ የሻ የአላህን ህግጋት ይጠብቅ፡፡ ጌታችን “አላህን ብትረዱ ይረዳችኋል” ይላል፡፡ ዲኑን መርዳት ትእዛዙን በመጠበቅ፣ ክልከላውን በመራቅ፣ ሸሪዐውን በማይጥስ መልኩ ለዲናችን ዋጋን በመክፈል ይገለፃል፡፡ ለውጥ ከፈለግን እራሳችንን እንለውጥ፡፡ “በርግጥም አላህ በህዝቦች ዘንድ ያለውን (ገፅታ) በነፍሶቻቸው ያለውን (ሁኔታ) እስከሚቀይሩ ድረስ አይለውጥም፡፡) [አርረዕድ፡ 11]
“እስከመቼ” አትበለኝ፡፡ “የአላህ ውሳኔ እስከሚመጣ ድረስ” እልሃለሁ፡፡ ለመሆኑ ሙሳ ዐለይሂስሰላም እስከመቼ ነው ፊርዐውንን የታገሱት? ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እስከመቼ ነው ደናቁራን አጋሪዎችን የታገሱት? ረጋ ብለህ አስተውል፡፡ የያኔው ምክንያት የዛሬው ምክንያት ነው፡፡ የያኔው ሰቀቀን ከዛሬ እጥፍ ድርብ የከፋ ሰቀቀን ነው፡፡ የያኔው መፍተሄ የዛሬም መፍተሄ ነው፡፡ ይልቅ እወቅ! “አላህን ጠብቅ ይጠብቅሃል፡፡ አላህን ጠብቅ ፊት ለፊትህን ታገኘዋለህ፡፡ ስትለምን አላህን ለምን፡፡ ስትታገዝ በአላህ ታገዝ፡፡ እወቅ! ህዝቦች በሙሉ በሆነ ነገር ሊጠቅሙህ ቢሰባሰቡ አላህ ላንተ በፃፈልህ እንጂ አይጠቅሙህም፡፡ በሆነ ነገር ሊጎዱህ ቢሰባሰቡም አላህ ባንተ ላይ በፃፈው እንጂ አይጎዱህም፡፡ ብእሮቹ ተነስተዋል! መዝገቦቹም ደርቀዋል፡፡” “እወቅ! የሳተህ ነገር የሚያገኝህ አልነበረም፡፡ ያገኘህም ነገር የሚስትህ አልነበረም፡፡ እወቅ!!! ድል ከትእግስት ጋር ነው፡፡ ግልግል ከጭንቅ ጋር ነው፡፡ ከከባድም ነገር ጋር ገር ነገር አለ፡፡” ወሶለላሁ ዐላ ነቢይና ሙሐመዲን ወዐላ ኣሊሂ ወሶሕቢህ ወሰለም፡፡
(ኢብኑ ሙነወር፣ ሐምሌ 28/2007)

Post a Comment

1 Comments

  1. ወላሂ በቀን 2ጊዜ ደግሜ የማነብበት ስአት አለኝ የማይጠገብ ምክር ጀዛኩሙአላህ

    ReplyDelete