Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ሙዓዊያ ማለት ባጭሩ ይሄ ነው፡፡


ዲራር፡ ዐልይን አላህ ይማረው! ወላሂ እሱ እኛ ዘንድ (በስልጣኑ ከፍ ማለትን የማይፈልግ) እንደማናችንም ነበር፡፡ ስንሄድበት ያቀርበናል፤ ስንጠይቀው ይመልስልናል፣ ስንጎበኘው ያቀርበናል፤ በሩ ከሱ አይዘጋብንም፤ በረኛ ከሱ አያግደንም፡፡ ወላሂ እኛ ከሱ ጋር ከመቀራረባችንም ጋር ለግርማ ሞገሱ አናናግረውም … ፈገግ ሲል በስርኣት የተሰካካ ሉል ይመስላል፡፡
ሙዓውያ፡ ጨምረኝ!
ዲራር፡ ዐልይን አላህ ይማረው! ወላሂ ንቃቱ የረዘመ፣ እንቅልፉ የቀለለ ነበር- ሌት ከቀን ቁርኣን የሚቀራ፡፡
ሙዓውያ አለቀሰ፡፡ ከዚያም እንዲህ አለ፡- በቃህ ዲራር! በአላህ ይሁንብኝ ልክ እንዳልከው ነበር ዐልይ፡፡ አቡል ሐሰንን (ዐልይን) አላህ ይማረው፡፡
ማስጠንቀቂያ፡- ልብ ያለው ልብ ይበል፡፡ በዐልይና በሙዓውያ መካከል የተከሰተውን ልዩነት መነሻ አድርገው እራሳቸውን ዳኛ አድርገው የሙዓውያን ኢማን ጥያቄ ውስጥ የሚከቱ ስንቶች ናቸው? ለነብዩ (ዐለይሂሰላም) እና ለቤተሰቦቻቸው ተቆርቋሪ ይመስላሉ፡፡ እውነታቸውን ከሆነ ለምን “ሰሐቦቼን አትሳደቡ” የሚለውን የነብዩን ትእዛዝ አያከብሩም? ረሒመላሁ ኢብኑል ሙባረክ የዐልይንና የሙዓውያን ጦርነት አስመልክቶ እንዲህ ብሏል፡- “ሰይፎቻችንን አላህ ከዚህ ፊትና ጠብቋል፡፡ ታዲያ እኛ ለምን ምላሶቻችንን አንጠብቅም?”
ስለሙዓውያ ምን አሉ?
1. ነብዩ (ዐለይሂሰላም)፡ (( ጌታዬ ሆይ (ሙዓውያን) ቅንና ወደ ቅኑ መንገድ የሚመራ አድርገው)) አልባኒ “ሶሒሕ” ብለውታል፡፡
2. “ሙዓውያን በመልካም እንጂ አታንሱት” ዑመር ኢብኑል ኸጧብ ረዲየላሁ ዐንሁ (አልቢዳያ ወኒሃያ፡ 8/125)
3. ኢብኑ ዐባስ (ረዲየላሁ ዐንሁ)፡ “እሱ (ሙዓውያ) አዋቂ ነው (ቡኻሪ፡3765)
4. ሙጃሂድ፡- “ሙዓውያን ብታዩ መህዲ ይሄ ነው ትሉ ነበር”
5. ኢብኑ ሙባረክ እንዲህ ተብለው ተጠየቁ፡ “ሙዓውያ ኢብኑ አቢሱፍያን ነው ወይስ ዑመር ኢብኑ ዐብዱልዐዚዝ የሚበልጠው?” ኢብኑ ሙባረክ እንዲህ ብለው መለሱ፡ “ወላሂ ሙዓውያ ከነብዩ ጋር ሆኖ ባፍንጫው የገባው አቧራ ከዑመር ሺህ ጊዜ ይበልጣል”፤ “ሙዓውያ እኛ ዘንድ ፈተና ነው፡፡ እሱን በመጥፎ ሲመለከት ያየነውን በሶሐቦች ጉዳይ አናምነውም”
6. ኢማሙ አሕመድ፡ “ከሙዓውያና ከዑመር ኢብኑ ዐብዱልዐዚዝ ማን ይበልጣል?” ሲባሉ፣ “ሙዓውያ ነው የሚበልጠው፡፡ የነብዩን ሶሐቦች ከማንም ጋር አናወዳድርም”
- አንድ ሰው ኢማሙ አሕመድን “አንድ ሙዓውያን የሚያንቋሽሽ አጎት አለኝ” ሲላቸው “ከሱ ጋር አብረህ እንዳትበላ!!!” አሉት፡፡
7. ሙዓፋ ኢብኑ ዒምራን “ዑመር ኢብኑ ዐብዱልዐዚዝ ከሙዓውያ እንዴት ነው ደረጃው?” ተብሎ ቢጠየቅ በጣም ከተቆጣ በኋላ እንዲህ አለ፡- “ማንም ቢሆን ከነብዩ (ዐለይሂሰላም) ሰሐቦች ጋር አይነፃፀርም፡፡ ሙዓውያ እኮ የመልእክተኛው ፀሀፊ፣ ሶሐባቸው፣ አማቻቸው፣ ከአላህ በሚመጣው ወሕይ ላይ ታማኛቸው ነው”
8. ረቢዕ ኢብኑ ናፊዕ፡ “ሙዓውያ ለሙሐመድ ሶሐቦች መጋረጃ ነው፡፡ መጋረጃውን የተዳፈረ ሰው ከመጋረጃው ጀርባ ያለውን ይዳፈራል”
9. ኢብኑ ተይሚያ፡ “ሙዓውያ ከዚህ ኡማ ንጉሶች ሁሉ በላጭ እንደሆነ ዓሊሞች ባንድ ድምፅ ተስማምተዋል፡፡ ከሱ በፊት የነበሩት አራቱ የነብዩ ምትኮች(ኸሊፋዎች) ናቸው፡፡ እሱ የመጀመሪያው ንጉስ ነው፡፡ ንግስናው እዝነት የተንፀባረቀበት ነበር”
10. ኢብኑ ከሲር፡- “(ሙዓውያ) ታጋሽ፣ የተከበረ፣ ሰዎች ዘንድ የከበረ መሪ፣ ቸር፣ ፍትሀዊ፣ ለጋስ ነበር”
11. ኢብኑ አቢል ዒዝ አልሐነፊ፡ “የሙስሊሞች የመጀመሪያው ንጉስ ሙዓውያ ነው፡፡ ከሙስሊሞች መሪዎች ሁሉ በላጭ ነው”
12. ሙሒቡዲን አልኸጢብ፡- “በሌሎች ላይ የምሰጠውን ሀሳብ በተመለከተ በኔ ላይ ጥሩ ግምት ካላቸው የሙስሊም ወጣቶች አንዱ ‹ስለሙዓውያ ምን ትላለህ› ሲል ጠየቀኝ፡፡ እንዲህ ስል መለስኩለት፡፡ “ከሙስሊም ታላላቅ ሰዎች ስለአንዱ ታላቅ ሰው፣ ከነብዩ ምርጥ ሶሐቦች ስለሆነው የምጠየቀው እኔ ማን ሆኜ ነው? እሱ ከኢስላም መብራቶች አንዱ መብራት ነው፡፡ ባይሆን ይሄ መብራት ብርሀናቸው አለምን ከሞላ አራት ፀሐዮች ጎን ስለበራ ነው ብርሀኑ የደበዘዘው”
ለማሳጠር በዚሁ ልቁም እንጂ ብዙ ማለት ይቻል ነበር፡፡ እንግዲህ ሙዓውያ ማለት ይሄ ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ ምስክርነት ባለፈ የነብዩ ሶሐባ መሆኑ ታላቅ ለመባል በቂው ነው፡፡ ሺዐ ዘመም ዘገባዎችን፣ ያልተጣሩ ወሬዎችን፣ የተጣመሙ ማብራሪዎችን ይዞ የነብዩን ሶሐቦች የሚዳፈር ለማንም ሳይሆን ለራሱ ይፍራ፡፡ የአላህ መልእክተኛ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዲህ ይላሉ፡- “ሶሐቦቼን የተሳደበ የአላህ፣ የመላእክትና የሰዎች ሁሉ እርግማን በሱ ላይ ይሁን፡፡” የነብዩ እርግማን የሚቀለው ካለ ይዳፈር፡፡ “ካላፈርክ ያሻህን ስራ” ይላሉ ነብዩ፤ እኛ ማን ሆነን ነው የነብዩን ሶሐባ የምንዳፈረው? ለነገሩ እንዲህ የሚያደርው ጅህልና ነው፡፡ ኢማሙዘህቢ እንዲህ ይላል፡- “ጃሂል የራሱን ልክ አያውቅም፡፡ ታዲያ እንዴት የሌሎችን ልክ ሊያውቅ ይችላል?”
ሙሐመድ ኢብኑ ዐብዱልወሃብን አላህ ይማረውና እንዲህ ይላል፡- “የራሱን ልክ አውቆ ከድንበሩ የቆመን አላህ ይማረው”