Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

በሸይኹል አልባኒ እና “መውሊድ ይፈቀዳል” በሚል ሰው መካከል የተደረገ ድንቅ ቃለ-ምልልስ


በሸይኹል አልባኒ እና “መውሊድ ይፈቀዳል” በሚል ሰው መካከል የተደረገ ድንቅ ቃለ-ምልልስ

ሸይኹል አልባኒ ረሒመሁላህ፡- የተከበሩትን ነብይ ልደት ማክበር ኸይር ነው ሸር?
ሰውየው፡- ኸይር ነው፡፡ 
ሸይኹል አልባኒ፡- መልካም፡፡ ይህንን ኸይር የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እና ሰሐቦቻቸው አያውቁትም ነበር? 
ሰውየው፡- አይ፡፡
ሸይኹል አልባኒ፡- “አይ” ማለትህ አይበቃኝም፡፡ “ይሄ ነገር ኸይር ከሆነ ከአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እና ከሰሐቦቻቸው ይሰወራል ተብሎ ፍፁም የማይታሰብ ነው” ልትል ይገባል፡፡ እኛ ኢስላምንም ኢማንንም በሙሐመድ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም መንገድ እንጂ በሌላ አላወቅነውም፡፡ እሳቸው የማያውቁትን ኸይር እንዴት ልናውቅ እንችላለን? ይሄ ፍፁም የማይሆን ነገር ነው!! 
ሰውየው፡- የነብዩን ልደት ማክበር እሳቸውን በማሰብ የሚፈፀም ነው፡፡ ይሄ ደግሞ እሳቸውን ማክበር ነው፡፡ 
ሸይኹል አልባኒ፡- ይቺ የምናውቃት ፍልስፍና ነች፡፡ ከብዙ ሰዎችም እንሰማታለን፡፡ ከኪታቦቻቸውም አንብበናታል፡፡ ግን ግን የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ሰዎችን ወደ ኢስላም ሲጣሩ ወደ ኢስላም በሙሉ ነው የተጣሩት ወይስ ወደ ተውሒድ? 
ሰውየው፡- ወደ ተውሒድ:: 
ሸይኹል አልባኒ፡- አዎ መጀመሪያ የተጣሩት ወደ ተውሒድ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ሰላቶች ተደነገጉ፡፡ ከዚያ ፆም፡፡ ከዚያ ሐጅ፡፡ በዚህ መሰረት ቀጠለ፡፡ አንተም በዚህ ሸሪዐዊ ሱና መሰረት እርምጃ በእርምጃ ተጓዝ፡፡ መልእክተኛው ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም የማያውቁት ኸይር በፍፁም እንደማይኖር ተስማምተናል፡፡ ኸይርን ሁሉ ያወቅነው በመልእክተኛው ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም መንገድ አማካኝነት ነው፡፡ ይሄ መቼም እጅግ ግልፅ ከመሆኑ የተነሳ ማንም አይወዛገብበትም፡፡ እኔ በዚህ ጉዳይ ላይ የሚጣራጠርን ሙስሊም አይደለም ብዬ ነው የማምነው፡፡ ይህን አባባል ከሚደግፉ የመልእክተኛው ሐዲሦች ውስጥ ((ወደ አላህ የሚያቃርባችሁ ሆኖ ሳላዛችሁ የቀረኝ ነገር የለም)) የሚለው ይጠቀሳል፡፡ እናም መውሊድ ኸይር ከሆነ ወደ አላህ የሚያቃርበንም ከሆነ የግድ መልእክተኛው ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ያመላከቱን ነው ማለት ነው፡፡ ነው ወይስ አይደለም? እኔ እያንዳንዱ የምናገረው ቃል ሳያሳምንህ እንድትስማማ አልፈልግም፡፡ “ይቺ ነጥብ አላረካችኝም” የማለት ሙሉ ነፃነት አለህ፡፡ 
ሰውየው፡- እየተረዳሁህ ነው፡፡ 
ሸይኹል አልባኒ፡- ጀዛከላሁ ኸይረን፡፡ እንግዲያው ነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ((ወደ አላህ የሚያቃርባችሁ ሆኖ ሳላዛችሁ የቀረኝ ነገር የለም)) እንዳሉ አሳልፈናል፡፡ ይህን መውሊድ ማክበር “ይፈቀዳል” ለሚል ሁሉ እንዲህ እንላለን፡- “ይሄ መውሊድ እንደናንተ እምነት ኸይር ነገር ነው፡፡ እንግዲያው ወይ የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም አመላክተውናል ወይ ደግሞ አላመላከቱንም ማለት ነው፡፡” “አመላክተውናል” ካላችሁ ((ማስረጃችሁን አምጡ እውነተኞች ከሆናችሁ)) እንላለን፡፡ ይህን ማድረግ ደግሞ መቼም አይቻላቸውም፡፡የመውሊድ ደጋፊዎች የሚፅፉትን አይተናል፡፡ “ጥሩ ቢድዐ ነው” ከማለት ባለፈ ማስረጃ አይጠቅሱም፡፡ የመውሊዱ ደጋፊዎችም ተቃዋሚዎችም በመልእክተኛው ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ዘመንም በክቡራን ሰሐቦች ዘመንም በታላላቅ መሪዎች ዘመንም እንዳልተከበረ ይስማማሉ፡፡ ነገር ግን የሚያከብሩት ሰዎች “መውሊድ ውስጥ ምን ችግር አለበት? ነብዩን ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ለማስታወስ ነው፣ በሳቸው ላይ ሰለዋት ለማውረድ” ወዘተ. ይላሉ፡፡ እኛ ግን “ኸይር ቢሆን ኖሮ ይቀድሙን ነበር” እንላለን፡፡ አንተ እራስህ ((ከሰዎች ሁሉ በላጩ የኔ ዘመን ትውልድ ነው፡፡ ከዚያም የሚከተሏቸው፤ ከዚያም የሚከተሏቸው) የሚለውን የመልእክተኛውን ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ሐዲሥ ታውቃለህ፡፡ ቡኻሪና ሙስሊም የዘገቡት ሰሒሕ ሐዲሥ ነው፡፡ የነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ዘመን ማለት እሳቸውና ሰሐቦቻቸው የኖሩበት ጊዜ ነው፡፡ ቀጥለው የመጡት ታቢዖች ናቸው፡፡ ከነሱ የቀጠሉት ደግሞ አትባዑት-ታቢዒን ናቸው፡፡ እዚህም ላይ ምንም ውዝግብ የለም፡፡ በእውቀትም በተግባርም እኛ ልንቀድማቸው የምንችለው ኸይር ሊኖር ይችላል ብለህ ታስባለህ? ሊሆን ይችላል? 
ሰውየው፡- ከእውቀት አንፃር የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም በዘመናቸው ላሉ ሰዎች “መሬት ትዞራለች” ብለው ቢናገሩ 
ሸይኹል አልባኒ፡- ይቅርታ! ባታስቀይስ ደስ ይለኛል፡፡ እኔ የጠየቅኩህ ሁለት ነገር ነው፣ እውቀትና ተግባር፡፡ ከማስቀየስህ በመነሳት አንድ ነገር ግልፅ ላድርግ፡፡ እኔ የማወራህ እውቀት ሸሪዐዊ እውቀትን እንጂ ለምሳሌ ህክምናን አይደለም፡፡ የዛሬ ዶክተር ከኢብኑ ሲና ይበልጣል፡፡ ምክኒያቱም ከረጅም ዘመናት እጅግ በርካታ ተሞክሮዎች በኋላ ስለመጣ ነው፡፡ ባይሆን ይህ እውቀቱ በራሱ አላህ ዘንድ አያስሞግሰውም፡፡ በምርጥነቱ ከተመሰከረለት ትውልድም አያስበልጠውም፡፡ የሚያስሞግሰው በሚያውቀው እውቀት ብቻ ነው፡፡ እኛ ግን እያወራን ያለነው ስለ ሸሪአዊ እውቀት ነው ባረከላሁ ፊክ፡፡ ይህን ልታጤን ይገባል፡፡ ስለዚህ “እኛ ከነሱ የበለጠ ልናውቅ እንችላለን ብለህ ታምናለህ?” ብየ ስጠይቅህ እያልኩ ያለሁት ሸሪዐዊ እውቀትን ነው እንጂ እንደ ጂኦግራፊ፣ ስነ-ፈለክ፣ ኬሚስትሪና ፊዚክስ ያሉ ተሞክሯዊ እውቀቶችን ማለቴ አይደለም፡፡ ምሳሌ ውሰድ በዚህ ዘመን ያለ አንድ በአላህና በመልእክተኛው ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም የማያምን ከሃዲ በነዚህ የእውቀት ዘርፎች ከማንም በላይ ሊያውቅ ይችላል፡፡ ታዲያ ይህ እውቀቱ ወደ አላህ መቃረቢያ (ዙልፋ) ይሆነዋልን? 
ሰውየው፡- አይሆነውም፡፡ 
ሸይኹል አልባኒ፡- ስለዚህ አሁን የምናወራው ስለዚህኛው የእውቀት ዘርፍ አይደለም፡፡ የምናወራው በራሱ ወደ አላህ ስለሚያቃርበን እውቀት ነው፡፡ ከአፍታ በፊት መውሊድን ስለማክበር እያወራን ነበር፡፡ ጥያቄውን እንመልሰው፡፡ ዳግም ሳታስቀይስ መልሱን በግልፅ እንደማገኝ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ እናም በተሰጠህ አእምሮና ግንዛቤ ስታስበው በመጨረሻው ዘመን ያለነው እኛ ከሰሐቦች፣ ከታቢዖችና ከሙጅተሂድ አኢማዎች የበለጠ ሸሪዐዊ እውቀት ሊኖረን ይችላል ብለህ ታምናለህን? ወደ መልካም ስራና ወደ አላህ በመቃረብስ ከነኚህ መልካም ቀደምቶች እንቀድማለን ብለህ ታስባለህ? 
ሰውየው፡- ሸሪዐዊ እውቀት ስትል የቁርኣን ተፍሲር ማለትህ ነው? 
ሸይኹል አልባኒ፡- በቁርኣኑ ተፍሲርም ከኛ የበለጠ አዋቂዎች ናቸው፡፡ በመልእክተኛው ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ሐዲሥ ማብራሪያም ከኛ የበለጠ አዋቂዎች ናቸው፡፡ ባጠቃላይ የሸሪዐ እውቀት እነሱ ከኛ የበለጠ አዋቂዎች ናቸው፡፡ 
ሰውየው፡- ቁርኣን ተፍሲርን በተመለከተ ምናልባት በመልእክተኛው ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ዘመን ከነበረው የዛሬው ሳይበልጥ አይቀርም፡፡ ለምሳሌ ((ተራሮችንም ስታይ የደመና አስተላለፍ የሚያልፉ ሆነው ሳለ የቆሙ ናቸው ብለህ ታስባለህ፡፡ የአላህ ጥበብ ነው! ሁሉን ነገር ያስዋበ ጌታ! እርሱ በምትሰሩት ሁሉ ውስጥ አዋቂ ነው)) (አን-ነምል፡ 88) የምትለዋን የቁርኣን አያ በተመለከተ የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም በዘመናቸው ለነበረ አንድ ሰው “መሬት ትዞራለች” ቢሉ አንድ የሚያምናቸው ይኖር ነበር? አንድም ሰው አያምናቸውም ነበር?!! 
ሸይኹል አልባኒ፡- ስለዚህ ቅር እንዳትሰኝና ሁለተኛ እያስቀየስክ እንደሆነ እንመዝግብልህ፡፡ ወንድሜ እኔ የምጠይቀው ጥቅል እንጂ ነጠላ ነገሮችን አይደለም፡፡ በጥቅሉ ስንጠይቅ፡- ኢስላምን በጥቅሉ ማነው የበለጠ የሚያውቀው? 
ሰውየው፡- እሱ ግልፅ ነው፡፡ የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እና ሰሐቦቻቸው ናቸው፡፡ 
ሸይኹል አልባኒ፡- ይህን ነው የፈለግነው ባረከላሁ ፊክ! ደግሞ የምታግደመድምበት ተፍሲር ከተግባር ጋር ምንም አይነት ቁርኝት የለውም፡፡ ቁርኝቱ ከእሳቤና ከግንዛቤ ጋር ነው፡፡ በዚያ ላይ የጠቀስካትን አያ በተመለከተ ለመሬት መዞር ማስረጃ የሚያደርጓት ሰዎች ስህተት ላይ እንደሆኑ ነግሬሃለሁ፡፡ ምክኒያቱም አያዋ የምትያያዘው ከቂያማ ቀን ጋር ነው፡፡ ((ምድር በሌላ ምድር የምትለወጥበት ቀን፡፡ ሰማያትም እንዲሁ፡፡ ፍጡራንም ሁሉ ለአንድየውና ለአሸናፊው አላህ የሚቀርቡበት ቀን!!)) አሁን ጉዳያችን ይሄ አይደለም፡፡ ዘግይተው ከመጡት ሰዎች ውስጥ ሳይንሳዊ ወይም ተፈጥሯዊ የሆኑ እውነታዎችን ከሰሐቦች፣ ከታቢዖች፣ ወዘተ በበለጠ የሚያውቅ ሊኖር ይችላል ብየ አምንልሃለሁ፣ ለክርክር ሲባል፡፡ ግን ይሄ ከመልካም ስራ ጋር ቁርኝት የለውም፡፡ ለምሳሌ በዘመናችን በስነ-ፈለክና በመሳሰሉ እውቀቶች ከሃዲዎች ከኛ የበለጠ ያውቃሉ፡፡ ግን ከዚህ እውቀታቸው ምን ይጠቀማሉ? ምንም!! እና ስለዚህ “ምንም”አሁን ጠልቀን መግባት አንፈልግም፡፡ ልናወራ የምንፈልገው ወደ አላህ በሚያቃርበን ሁሉ ላይ ነው፡፡ እናም የክቡሩን ነብይ መውሊድ ስለማክበር ልናወራ እንፈልጋለን፡፡ እንደተስማማነው ይሄ መውሊድ መልካም ቢሆን ኖሮ መልካም ቀደምቶቻችን በዋናነትም የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ከኛ የበለጠ ያውቁት ነበር፡፡ ከኛ ቀድመውም ይሰሩት ነበር፡፡ እዚህ ላይ ብዥታ አለ? 
ሰውየው፡- የለም፡፡ ምንም ብዥታ የለም፡፡ 
ሸይኹል አልባኒ፡- ይህን ጥለህ ወደ አላህ ከሚያቃርቡ መልካም ስራዎች ጋር ግንኙነት ወደሌላቸው ተሞክሯዊ እውቀቶች እንዳታስቀይስ፡፡ ስለዚህ ሁሉም እንደሚስማማው ይሄ መውሊድ በነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ዘመን አልነበረም፡፡ ስለዚህ ይሄ ኸይር በመልእክተኛው ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም፣ በሰሐቦች፣ በታቢዖችና በሙጅተሂድ አኢማዎች ዘመን አልነበረም ማለት ነው፡፡ እንዴት ይሄ ኸይር ተሰወረባቸው?! ከሁለት ምርጫ የግድ አንዱን ልንል ነው፡- ወይ ይህን ኸይር እኛ እንዳወቅነው ያውቁት ነበር- የበለጡ አዋቂዎች ናቸውና፡፡ ወይ አያውቁትም ነበር፡፡ ታዲያ እነሱ ሳያውቁት እኛ እንዴት አወቅነው?“ያውቁት ነበር” ካልን - የሚቀርበውም መውሊዱን ለሚያከብሩት በላጩም ይሄ ነው- ግን ለምን አልሰሩትም? እኛ ከነሱ የበለጠ ወደ አላህ የቀረብን ነን? እንዲያው ሳት ብሎት ከዚያ ሁሉ ሰሐባና ታቢዒይ ውስጥ ከዓሊሞቻቸውና ዓቢዶቻቸው ውስጥ ይህን ኸይር የሚሰራው አንድ እንኳን እንዴት ጠፋ?! ኸይር ቢሆን ኖሮ ከሚሊዮኖች ሰለፎች ውስጥ እንዳው አንድ እንኳን ጭራሽ ሳይሰራበት ይቀራል የሚል ውል ይልብሃል? እነሱ ከኛ የበለጡ አዋቂዎች፣ ከኛ የበለጡ ደጋጎች ከኛ የበለጡ ወደ አላህ ቅርቦች ሆነው ሳለ?!! (ሰሐቦቼን አትሳደቡ! የሙሐመድ ነፍስ በእጁ በሆነችው ይሁንብኝ አንዳችሁ የኡሑድ ተራራን የሚያክል ወርቅ ቢለግስ እንኳን የነሱን እፍኝ አያክልም ግማሹንም!!) የሚለውን የመልእክተኛውን ሐዲሥ ታውቀዋለህ ብየ እገምታለሁ፡፡ በኛና በነሱ መካከል ያለውን ልዩነት ርቀቱን አየኸው አይደል?! ምክኒያቱም እነሱ በአላህ መንገድ ከመልእክተኛው ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ጋር ታግለዋል፤ በእኛና በነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም መካከል ያለው አይነት ረጂም ሰንሰለት ሳያስፈልጋቸው ትኩስ(ፍሬሽ) የሆነ እውቀትን ከሳቸው ተቀብለዋል፡፡ ልክ ይህን የሚመስል ነገር መልእክተኛው ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዲህ ሲሉ እንደጠቆሙት፡- (ቁርኣንን ልክ አዲስ ሲወርድ እንደነበረው መቅራት የፈለገ በኢብኑ ኡሚ ዐብድ አቀራር ይቅራው) ዐብዱላህ ኢብኒ መስዑድን ማለታቸው ነው፡፡እነኚህ መልካም ቀደምቶች በዋናነትም ሰሐቦች ረዲየላሁ ዐንሁም የማያውቁት እኛ ግን የምናውቀው ወደ አላህ የሚያቃርብ ነገር ሊኖር ይችላል ብለን ልናስብ አይቻለንም፡፡ልክ እኛ እንዳወቅነው “እነሱም ያውቁት ነበር” ካልንም ይህን ኸይር ችላ ብለውታል ብለን ፈፅሞ ልናስብ አይገባም፡፡ የማጠነጥንባት ነጥብ ግልፅ ሆናልሃለች ብዬ እገምታለሁ ኢንሻአላህ፡፡ 
ሰውየው፡- አልሐምዱሊላህ፡፡ 
ሸይኹል አልባኒ፡- ጀዛከላሁ ኸይረን፡፡ ሌላም ጉዳይ አለ፡- ኢስላም እንደሞላ የሚያስረግጡ በርካታ አያዎችና ሐዲሦች አሉ፡፡ ይህን ጉዳይ እንደምታውቅም እንደምታምንበትም እገምታለሁ፡፡ ይህን እውነታ በማወቅ ረገድ ዓሊሙም፣ ተማሪውም፣ ተራውም ሰው ልዩነት የላቸውም፡፡ ኢስላም ሞልቶ እንደጨረሰ ማለቴ ነው፡፡ ኢስላም እንደ አይሁድና እንደ ክርስትና እምነት በየጊዜው የሚቀያየርና የሚለዋወጥ አይደለም፡፡ በዚህ የአላህ ቃል ላስታውስህማ ((ዛሬ ሀይማኖታችሁን ሞላሁላችሁ፡፡ ፀጋዬንም በናንተ ላይ ፈፀምኩ፡፡ ኢስላምንም በሃይማኖትነት ወደድኩላችሁ፡፡)) አሁን ደግሞ መውሊድ ኸይር እንዳልሆነ በሌላ አቅጣጫ ልንመለከት ነው፡፡ እሱም “ኸይር ቢሆን ኖሮ መልካም ቀደምቶቻችን በቀደሙን ነበር” የሚል ነው፡፡ ከኛ የበለጠ አዋቂም፣ አላህን አምላኪም ነበሩና፡፡ ስለዚህ ይሄ መውሊድ ኸይር ከሆነ የኢስላም አካል ነው ማለት ነው፡፡ መውሊድን ደጋፊውም ተቃዋሚውም በነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ዘመን እንዳልነበር ይስማማሉ ብለን አሳልፈናል፡፡ ይሄ መውሊድ “ኸይር ከሆነ የኢስላም አካል ነው፡፡ ካልሆነ ግን አይደለም” በሚለውስ ላይ እንስማማለን? ((ዛሬ ሀይማኖታችሁን ሞላሁላችሁ)) የምትለዋ አንቀፅ የወረደችለት የነብዩን መውሊድ ማክበር አልነበረም፡፡ ስለዚህ ዛሬ የዲን አካል ሊሆን ይችላል? ስታስበው? ግልፅ እንድትሆንልኝ እፈልጋለሁ፡፡ ተማሪዎቻቸውን ፀጥ እንደሚያስብሉ ሸይኾች እንዳታስበኝ፡፡ ኧረ እንዳውም ተራውንም ህዝብ “ዝም በል!! አንተ ምን ታውቃለህ!” ይላሉ፡፡ በጭራሽ! ከእኩያህ ጋር፣ ወይም በእድሜም በእውቀትም ከሚያንስህ ጋር እንደምታወራው ሙሉ ነፃነት ይኑርህ፡፡ ካላሳመነህ “አላሳመነኝም” በል፡፡እናም መውሊድ ኸይር ነገር ከሆነ የኢስላም አካል ነው፡፡ ኸይር ነገር ካልሆነ ግን ከኢስላም አይደለም፡፡ ያሳለፍናት አንቀፅ ስትወርድ ጊዜ መውሊድ እንዳልነበረ ከተስማማን መውሊድ ከኢስላም እንዳልሆ ሲበዛ ግልፅ ነው ማለት ነው፡፡ እስካሁን የተናገርኩትን በኢማሙ ማሊክ ንግግር ላጠናክር ነው፡፡ እንዲህ ይላሉ፡- “በኢስላም ውስጥ መልካም ናት ብሎ የሚያስባት አንዲት ቢድዐን የፈጠረ (አስተውል! አንዲት ቢድዐ ነው ያሉት!! እንጂ ብዙ ቢድዐዎችን አላሉም) ሙሐመድ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ተልእኳቸው ላይ ሸፍጥ ሰርተዋል ብሎ ሞግቷል፡፡” ይሄ እጅግ አደገኛ ነገር ነው!! ማስረጃው ምንድን ነው ኢማም ሆይ! ቀጠሉ ኢማሙ ማሊክ “ከፈለጋችሁ((ዛሬ ሀይማኖታችሁን ሞላሁላችሁ፡፡ ፀጋዬንም በናንተ ላይ ፈፀምኩ፡፡ ኢስላምንም በሃይማኖትነት ወደድኩላችሁ፡፡)) የሚለውን የሀያሉን አላህ ቃል አንብቡ፡፡ ያኔ ዲን ያልሆነ ነገር ዛሬ ዲን ሊሆን አይችልም”መቼ ነው ኢማሙ ማሊክ ይህን ያሉት በመልካምነታቸው ከተመሰከረላቸው አንዱ በሆነው ከሂጅሪ ሁለተኛው ክፍለ ዘመን ላይ፡፡ ዛሬስ በአስራ አራተኛው ክ/ዘመን ምን የሚሆን ይመስልሃል ይሄ በወርቅ ቀለም የሚፃፍ ንግግር ነው፡፡ ነገር ግን እኛ ከሀያሉ አላህ ቁርኣንም፣ ከመልእክተኛው ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ሐዲሥም ዘንግተናል፡፡ “እንከተላቸዋለን” እያልን በከንቱ ከምንሞግታቸው ኢማሞቻችን ንግግርም እንዲሁ የትና የት ርቀን ነው ያለነው፡፡ እነሱን አርአያ በማድረግ ረገድ በእኛና በነሱ መካከል የምስራቅና የምእራብ ያክል ነው የተራራቅነው፡፡ ይሄዋ የመዲናው ኢማም ግልፅ በሆነ ቋንቋ “ያኔ ዲን ያልሆነ ነገር ዛሬ ዲን ሊሆን አይችልም” እያሉ!!ዛሬ ግን የነብዩን መውሊድ ማክበር ዲን ሆኗል፡፡ ያ ባይሆንማ ሱናውን አጥብቀው በያዙት ዓሊሞችና ለቢድዐ በሚከላከሉት ዓሊሞች መሀል ፍጭት ባልኖረ ነበር፡፡ በመልእክተኛው ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም፣ በሰሐቦች፣ በታቢዖችና በአትባዑት-ታቢዒን ዘመን ሳይኖር እንዴት ብሎ ዛሬ ዲን ይሆናል! ኢማሙ ማሊክ ከአትባዑት-ታቢዒን ናቸው፡፡ ((ከሰዎች ሁሉ በላጩ የኔ ዘመን ትውልድ ነው፡፡ ከዚያም ከነሱ ቀጥለው የሚመጡት፤ ከዚያም ከነሱ ቀጥለው የሚመጡት)) የሚለው ሐዲሥ ከሚጠቀልላቸው ውስጥ ናቸው፡፡ ታዲያ “ያኔ ዲን ያልሆነ ነገር ዛሬ ዲን ሊሆን አይችልም” “የዚህ ህዝብ መጨረሻው ክፍል የመጀመሪያው በቀናበት ካልሆነ በቀር አይቀናም” ይላሉ፡፡ የመጀመሪያው በምን ቀና በሃይማኖት ውስጥ አዲስ ነገር በመፍጠር ነውን መልእክተኛው ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ወደ አላህ ባልተቃረቡበት ነገር በመቃረብ ነውን እሳቸው እንደሁ (ወደ አላህ የሚያቃርባችሁ ሆኖ ሳላዛችሁ የተውኩት ነገር የለም) እያሉ ነው፡፡ግን ለምን የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ልደታቸውን እንድናከብር አላዘዙንም መልሱ ከዚህ ካልተፈቀደው መውሊድ በተቃራኒ የታዘዘ ሌላ መውሊድ ስላለ ነው፡፡ ይህኛው የተፈቀደው የመውሊድ አይነት በመልእክተኛው ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ዘመን ነበር ከዚያኛው በተለየ፡፡ በሁለቱ መውሊዶች መሃል ሰፊ ልዩነት አለ፡፡  
1. የተፈቀደው ማክበር ሁሉም ሙስሊሞች የሚስማሙበት ዒባዳህ ነው፡፡ 
2. የተፈቀደው መውሊድ በየሳምንቱ ይመላለሳል፡፡ ያልተፈቀደው ግን በአመት አንዴ ነው፡፡ የሁለቱ መውሊዶች ልዩነት እንግዲህ ይሄ ነው፡፡ የመጀመሪያው ዒባዳ ነው በየሳምንቱም ይደጋገማል፡፡ በተቃራኒው ያልተፈቀደው ግን ዒባዳም አይደለም በየሳምንቱም አይደጋገምም፡፡ ማስረጃ የሌለው ነገር አይደለም እያወራሁ ያለሁት፡፡ ይልቅ ሰሒሕ ሙስሊም ላይ የሚገኝን ሐዲሥ ነው የማቀርብላችሁ፡፡ በዚህ ሐዲሥ ላይ ቀተዳህ አል-አንሳሪ እንዲህ ይላል፡- አንድ ሰው ወደ ነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም መጣና “የአላህ መልእክተኛ ሆይ ስለ ሰኞ ፆም ምን ትላለህ” ሲላቸው (እሱ የተወለድኩበት ቀን ነው፡፡ ቁርኣኑ የወረደበት እንዲሁ) አሉ፡፡” የዚህ ንግግር መልእክት ምንድን ነው ልክ “እንዴት ይህን ትጠይቀኛለህ በዚህ ቀን ወደ ህይወት ያመጣኝና ወሕይም ያወረደብኝ ሆኖ ሳለ” የሚሉት ይመስላል፡፡ “በዚህ ቀን እኔን በማስገኘቱና በሱም በኔ ላይ ወሕይን በማውረዱ ምክኒያት ሀያሉን አላህ በማመስገን እለተ-ሰኞን ልትፆሙ ይገባል ማለታቸው ነው፡፡ ይሄ ከየሁዶች የዓሹራ ፆም ጋር ተነፃፃሪነት አለው፡፡ የረመዳን ወር ፆም በሙስሊሞች ላይ ከመደንገጉ በፊት ዓሹራን መፆም ግዴታቸው እንደነበር የምታውቁ የይመስለኛል፡፡ በአንዳንድ ሐዲሦች እንደመጣው ነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ወደ መዲና ሲሰደዱ የሁዶች የዓሹራ ቀንን ሲፆሙ አገኟቸው፡፡ ምክኒያቱን ሲጠይቋቸው “ይሄማ አላህ ሙሳን ህዝቦቹን ከፊርዐውንና ከሰራዊቱ ያተረፈበት ቀን ነው፡፡ አላህን በማመስገን ነው የምንፆመው” አሉ፡፡ መልእክተኛው ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም የዚህን ጊዜ (በሙሳማ እኛ ከናንተ ይበልጥ የተገባን ነን) በማለት እሳቸውም ፆሙት፡፡ እንዲፆምም አዘዙ፡፡ ((የረመዳን ወር ያ ነው፡- በሱ ለሰዎች መመሪያና እንዲሁም ቅንነትንና መለያን የያዙ ግልፅ ማስረጃዎች የወረዱበት የሆነ፡፡ ከናንተም ወሩን የደረሰ ይፁመው)) የሚለው እስከሚወርድ ድረስም ግዴታ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ኋላ ግን ግዴታነቱ ተሽሮ ሱና ሆኗል፡፡ከዚህ የተፈለገው አላህ ሙሳን በዓሹራ ቀን ከፊርዐውን ማትረፉን በማሰብ የሁዶች እለቱን ለምስጋና መፆማቸውን መልእክተኛው ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንደተጋሯቸው ማሳየት ነው፡፡ ታዲያ አላህ ለኛም መልእክተኛው ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም የተወለዱበትንና በሳቸው ላይ ወሕይ የወረደበትን ቀን እለተ-ሰኞን በመፆም የምስጋና በር ከፍቶልናል፡፡ አሁን ጥያቔ ልጠይቅህ ነውበምንም መልኩ የኸይር መንገድ እንዳልሆነ ያየነውን መውሊድ ከሚያከብሩት ውስጥ ብዙ ሰኞና ሀሙስን የሚፆሙ እንዳሉ አውቃለሁ፡፡ ግን አብዛሀኛው ሙስሊም ነው ሰኞን የሚፆመው በጭራሽ! አብዛሃኞቹ ሰኞን አይፆሙም፡፡ ታዲያ ይሄ እውነታን መገልበጥ አይደለምን አላህ ስለየሁዶች ((ያን ዝቅተኛውን በዚያ በላጭ በሆነው ትለውጣላችሁን)) ያለው በነዚህ ላይ ይሰራል፡፡ መልካሙ ይሄ ነበር፡፡ሰኞን መፆም፡፡ ይሄ ሁሉም ሙስሊሞች ባንድ ድምፅ የሚስማሙበት ነው፡፡ ነገር ግን አብዛሃኞቹ ሙስሊሞች አይፆሙትም፡፡ ወደሚፆሙት እጅግ ጥቂቶች ስንመጣ ደግሞ የሚፆምበትን ሚስጥር ያውቁ ይሆን በፍፁም!! አያውቁትም፡፡ ታዲያ የት አሉ ለመውሊድ የሚሟገቱት ዓሊሞች ለምንድን ነው የተፈቀደው መውሊድ ሰኞ መፆም እንደሆነ ግልፅ አያደርጉም ላልተፈቀደው መውሊድ ከመሟገት ይልቅ ለምን ወደዚህኛው አይቀሰቅሷቸውም!! ((ያን ዝቅተኛውን በዚያ በላጭ በሆነው ትለውጣላችሁን)) የሚለው ጌታ በርግጥም እውነት ተናገረ፡፡ (ስንዝር በስንዝር፣ ክንድ በክንድ ከናንተ በፊት የነበሩ ሰዎችን ፈለጎች ትከተላላችሁ፡፡ የአርጃኖ ጎሬ እንኳን ቢገቡ ያለጥርጥር ትገቡታላችሁ) ያሉት ነብይ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ምንኛ እውነት ተናገሩ! በሌላ አደገኛ በሆነ ዘገባ ደግሞ (ከነሱ በግልፅ መንገድ ላይ እናቱን የሚገናኝ ከኖረ ከናንተም ይህን የሚሰራ ይኖራል!!) አዎ የየሁዶችን ፈለግ እየተከተልን ነው ያለነው፡፡ በሚበልጠው ፋንታ የወረደውን እየወሰድን ነው፡፡ ልክ በየሳምንቱ የሚመጣውን ሸሪአዊውን የሰኞ መውሊድ በዚህ ምንም መሰረት በሌለው ባመት አንድ ጊዜ የሚመጣ መውሊድ እንደለወጥነው ማለት ነው፡፡ የሰኞው ሲፆም ግን ሚስጥሩን ከግምት ማስገባት ያስፈልጋል፡፡ እሱም አላህ በዚህ ቀን መልእክተኛውን ስላስገኘ እና ወሕይም ስላወረደባቸው ነው፡፡ ንግግሬም የምቋጨው የሚከተለውን የነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ንግግር በማውሳት ነው፡-(አላህ የሙብተዲዕን ተውበት ለመቀበል እምቢ ብሏል!!) ከፍ ያለው ጌታም እንዲህ ይላል፡- ((አንተ መልእክተኛ ሆይ! ከጌታህ ባንተ ላይ የወረደውን አድርስ፡፡ ይህን ባታደርግ መልእክቱን አላደረስክም፡፡ አላህ ከሰዎች ይጠብቅሃል)) በሰሒሕ ሙስሊም ላይ እንደመጣው ከታቢዖች አንዱ እናታችን ዓኢሻህ ዘንድ በመምጣት 

ሰውየው፡- የነብዩን ሲራ(ታሪክ) ማንበብ እሳቸውን ማላቅ አይደለምን 
ሸይኹል አልባኒ፡- አዎ 
ሰውየው፡- ከአላህ ምንዳ አለው ማለት ነው 
ሸይኹል አልባኒ፡- በደንብ አድርጎ!! ግን ከዚህ ጥያቄ ምንድን ነው የምትጠቀመው እስኪ ልጠይቅህ ታሪካቸውን እንዳታነብ የከለከለህ አለ አንድን ሸሪዐዊ አምልኮ መልእክተኛው ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም የተገደበ ጊዜና የተገደበ ሁኔታ ሳያስቀምጡለት እኛ በጊዜና በሁኔታ ልንገድበው እንችላለን መልስ አለህ 
ሰውየው፡- አይ የለኝም፡፡ 
ሸይኹል አልባኒ፡- የላቀው አላህ እንዲህ ይላል ((ወይስ ከሃይማኖት አላህ ያልፈቀደበትን የደነገጉላቸው ተጋሪዎች አሏቸው)) እንዲሁም ((ሊቃውንታቸውንና መነኮሳታቸውን፣ የመርየምን ልጅ አልመሲሕንም ከአላህ ሌላ ጌቶች አድርገው ያዟቸው፡፡ ነገር ግን አንድን አምላክ እንዲያመልኩ እንጂ አልታዘዙም፤ ከርሱ በቀር አምላክ የለምና፡፡ ከሚያጋሩት ሁሉ እርሱ የጠራ ነው፡፡)) ዐዲይ ኢብኑ ሓቲም ረዲየላሁ ዐንሁ ይቺን አንቀፅ በሰማ ጊዜ (ቀድሞ ክርስቲያን ነበር) ግራ ገባውና “እኛኮ አናመልካቸውም” አለ፡፡ መልእክተኛው ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ታዲያ (አላህ የፈቀደውን ይከለክሉ የለምን ተከትላችሁም ክልክል ታደርጉት የለምን አላህ የከለከለውንስ ይፈቅዱ የለምን ተከትላችሁስ ፍቁድ ታደርጉት የለምን) ቢሉት “እንዴታ!” አላቸው፡፡ እሳቸውም (ይሄው ነዋ እነሱን ማምለክ ማለት!) አሉት፡፡ ይህ እንግዲህ በአላህ ዲን ውስጥ ቢድዐ መፍጠር ምን ያህል አደገኛ እንደሆነ በግልፅ ያሳያል፡፡ 
(ሲልሲለቱል ሁዳ ወን-ኑር ካሴት ቁ. 94/1)