Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

የእኛ ህይወት እና ኢኽላስ


ስራን ለአላህ ማጥራት ኢኽላስ ማለት እኛ ህይወታችንን በሙሉ የምንሰራውን ስራ የሚመዘንበት የመጀመሪያው መስፈርት ነው፡፡ የነብያችንም((ﷺ)) ሱና ኢኽላስን በመከተል ሁለተኛው መስፈርት ነው፡፡
የአላህ ባርያ ሆይ! ነፍሴን ጨምሮ እሲቲ የኢኽላስ ጉዳይ ክብደቱ ይገባን ዘንድ ትንሽ ምሳሌዎችን እንውሰድ፡፡ ስራን መስራት ሳይሆን ዋናው አሳሳቢ ነገር፤ የተሰራው ስራ ኢኽላስ እና ሱናን ገጥሟል ወይ ነው፡፡
የሽርክ አስቸጋሪነት እና ከባድነቱ ሌሎች ስራዎችን ሁሉ አንድ ሽርክ ሲቀላቀልባቸው በዜሮ ማባዛቱ ነው፡፡
አለም ላይ የሌሎች ሃይማኖት ተከታዬች፤ ምፅዋትን ይለግሳሉ፤ ከለሊቱ 8 ሰዓት እግራቸው ተቆራርጦ እያለቀሱ ይለምናሉ፤ ይፆማሉ፤ ስራ ተብለው የሚወሰዱትን ጠቅላላ ይሰራሉ:: ግን የውመል ቂያማ ያፍራሉ፤ ይሸማቀቃሉ፤ ምክንያቱም የሰሩት ስራ ለአላህ ተብሎ ያልተሰራ ስለሆነ፤ ለአላህ ተብሎ የተሰራ ስላልሆነ እና የአላህ መላክተኛን ((ﷺ)) ሱና ስላልገጠም፡፡ አላህ እነሱን አስመልክቶ እንዲህ ይላል
وُجُوهٌ يَوْمَئِذٍ خَٰشِعَةٌ
ፊቶች በዚያ ቀን ተዋራጆች ናቸው፡፡
عَامِلَةٌ نَّاصِبَةٌ
(አልሰሩም እንዳይባል ሰርተው ለፍተው ነበር) ሠሪዎች ለፊዎች ናቸው፡፡
تَصْلَىٰ نَارًا حَامِيَةً
(ያቺን አሳማሚ ጀሃነም ይገቧታል) ተኳሳን እሳት ይገባሉ፡፡
ይህ እንግዲህ የአላህ ባርያዎች ሆይ! ጠንቅቀው ልናውቀው እና በማንኛውም ሰዓት ስራችንን ልንመዝንበት የሚገባው ነው፡፡

1) ፌስቡክ ላይ ስንፅፍ ምን ፈልገን ነው፡፡ የ ላይክ ብዛት ለመቁጠር ከሆነ አላህ ይጠብቀን መክሰራችንን አውቀን ዛሬውኑ ስራችንን እናስተካክል፡፡

2) ዳዕዋ ስናደርግ፤ ‹‹ብቃት አለው›› መባል ፈልገን ነው ወይንስ የአላህን ፊት ፈልገንበት??? ኢኽላሳችን ችግር ካለው አሁንም ቢሆን ሳይረፍድ ዛሬውኑ፤ አሁኑኑ ለአንድ አላህ ብቻ ስራችንን እናጥራ፡፡

3) ለቤተሰባችንም ይሁን ለሌሎች መልካም ስንውል ምን ፈልገንበት ነው???

4) አላህ እንደው በጠቅላላው ‹‹ሰላቴም፤ እርዴም፤ ህይወቴም፤ ሞቴም ለአለማቱ ጌታ ነው በል›› ይላል፡፡ የአላህ ባርያዎች ሆይ! እስቲ ቁጭ ብለን እስከዛሬ የሰራናቸውን ስራዎች እንደርድራቸው፤ በብዛት አላህ ከሚጠብቅብን አኳያ አብዛኛውን እድሜ በጥሩ ሁኔታ ያላሳለፍን ብዙ ልንሆን እንችላለን፤ ከዚህም በመቀጠል አለ የሚባለውን የሰራነውን ስራ ደግሞ በኢኽላስ እና በሱና እንመዝነው፡፡ ያኔ ቀን እና ለሌት የሚያስለቅሰን ነገር ይኖራል፡፡ የአላህ ባርያዎች ሆይ! ሁላችንም ተሳቻቾች ነን፤ ከተሳቻቾች ሁሉ በላጩ ወደ አላህ በንሰሃ የሚመለሰው ነው ብለዋል ነብዩና ((ﷺ)) ታድያ ሁሌ ለምን ይሆን ከንሰሃ ወደ ኋላ የምንለው???

ታላቅ ምሳሌዎችን እንይ የተውሂድ እና የነብያት አባት ኢብራሂም እና ልጁ ኢስማኢል (አለይሂሙሰላም) ካእባን ገንብተው ሲያበቁ አላህን እንዲህ ሲሉ ለመኑት ‹‹ጌታችን ሆይ! ከእኛ ተቀበል፤ አንተም ሰሚም አዋቂም ነህ እና፡፡ እኛንም ማረን (በንሰሃ ተመለስብን፤ ተውበታችንን ተቀበለን) አንተም ወዳንተ የሚመለሱትን መሃሪ እና አዛኝ ነህ›› ነበር ያሉት፡፡

ይህ ለእኛ ታላቅ ምሳሌ እና አርአያ ነው፡፡ ስራችንን በኢኽላስ ሰርተንም አላህን ዘወትር እንዲቀበለን እናም ላጠፋነው እና ላጓደልነው እንዲምረን እንለምነው፡፡ የአላህ ባርያዎች ሆይ! ኢኽላስ እና ሱና ትልቅ ነገር እንደሆነ የገባን ቀን ስራውን ለመስራት ከምንቻኮለው እና ስራን ለማብዛት ከምንቻኮለው በላይ ኢኽላስ እና ሱና ላይ በጣም ትኩረት እንሰጣለን፡፡

አላህ ሆይ! የኢኽላስ እና ሱና ባለቤቶች አድርገን፡፡ አላህ ሆይ! ላንተ ምንም አይደበቅህም፤ የእኛን ደካማነት ታውቃለህ፤ አስተካክለን፤ ምራን፤ አንተ ካልመራሀው በቀር ሁሉም ጠማማ ነው፡፡ አላህ ሆይ! በስም እና በባህሪያትህ እለምንሃለሁ ኢኽላስን እና ሱናን ግጠመን፤ በሰራነው ከመገረም እና ከመደነቅ አንተው ጠብቀን፤ ላንተ እጅ እግራቸውን ከሰጡ ባሪያዎችህ አድርገን፤ ካንተ ውጭ ሃይልም ጥበብም የለም፡፡