Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ሀቅ አንድ እና አንድ ብቻ ናት፡፡ ከሃቅ በኋላ ጥመት እንጂ ምን አለ? የሃቅን መንገድ ማወቅ

ሀቅ አንድ እና አንድ ብቻ ናት፡፡ ከሃቅ በኋላ ጥመት እንጂ ምን አለ?
የሃቅን መንገድ ማወቅ
አብደላህ ኢብን መስዑድ (ረድየላሁ አንሁም) እንዲህ ይላሉ
ነብዩ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) መስመርን ሳሉልን እና እንዲህ አሉን
‹‹ይህ የአላህ ቀጥተኛው መንገድ ነው››
ከዛም
በቀኝ እና በግራ ሌሎች መስመሮችን ስለው እንዲህም አሉ
‹‹እነዚህ ሌሎች መንገዶች ናቸው፡፡ እያንዳንዳቸው ላይ ሸይጧን ተጣሪ ያለባቸው››
ከዛም የሚከተለውን አንቀፅ አነበቡ
وَأَنَّ هَٰذَا صِرَٰطِى مُسْتَقِيمًا فَٱتَّبِعُوهُ ۖ وَلَا تَتَّبِعُوا۟ ٱلسُّبُلَ فَتَفَرَّقَ بِكُمْ عَن سَبِيلِهِۦ ۚ ذَٰلِكُمْ وَصَّىٰكُم بِهِۦ لَعَلَّكُمْ تَتَّقُونَ
«ይህም ቀጥተኛ ሲኾን መንገዴ ነው፤ ተከተሉትም፡፡ (የጥመት) መንገዶችንም አትከተሉ፡፡ ከ(ቀጥተኛው) መንገዱ እናንተን ይለያዩዋችኋልና፡፡እነሆ ትጠነቀቁ ዘንድ በርሱ አዘዛችሁ፡፡» ሀሰን፡ ኢማሙ አህመድ (1/435)፣ ነሳዒ (7/49) እና ሌሎችም ዘግበውታል፡፡
ለሙስሊሞች በጣም አስፈላጊው የሆነው ይህችን ብቸኛ እና ብቸኛ የሆነችውን የሃቅ መንገድ ማወቅ በእምነትም ይሁን በመንሃጅ (በአካሄድ) የሰለፎችን ይህችን የሃቅ መንገድ መከተል እና እሷን የሚቃረኗት የሆኑትን የጥፋት መንገድም ለጥንቃቄ ሲባል ማወቅ እና መራቅ ነው፡፡
የተሳሳተ የሆነውን መንገድም ለመጠንቀቅ ሲባል ማወቅ እንደሚያስፈልግ የምንይዘው ከታላቁ ሰሃባ ሁዘይፋ (ረድየላሁ አንሁም) ንግግር ነው፡፡ እንዲህም ይላል
‹‹ሰዎች የአላህ መላክተኛን (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ስለ ጥሩው ነበር የሚጠይቋቸው፤ እኔ ደግሞ መጥፎውን እጠይቃቸው ነበር እንዳልወድቅበት በመፍራት›› ቡኻሪ (6/615) ሙስሊም (12/235)
የሚከተለውን ግጥም ባለቤት አላህ ይዘንለት
‹‹መጥፎን ነገር አወቅኩት፤ ለራሱ ሲባል ሳይሆን እርቀው ዘንድ፤
መጥፎን ከጥሩ ለይቶ ያላወቀ (መጥፎ ላይ) ይወድቅበታል››
የአላህ መላክተኛ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ለሰሃባዎቻቸው ይህ ኡመት 73 ቦታ እንደሚከፋፈል እና 1 ብቸ ነፃ እንደሚወጣ ሲነግሯቸው የሰሃባዎች ጥያቄ የነበረው
‹‹የትወኛዋ ናት ያቼ መንገድ›› ነበር፡፡
የአላህ መላክተኛም (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ‹‹እኔ እና ሰሃበዎቼ ዛሬ ያለንበትን መንገድ የተከተሉ ናቸው›› አሉ፡፡
የአላህ ባርያ ሆይ! ለነፍስህ እዘንላት፡፡ሰሃባዎች የትኛዋ ናት ነፃ የምትወጣው ብለው እንደጠየቁት እኔም/አንተም/አንቺም ነፃ የምትወጣዋን መንገድ ብቻ እና ብቻ አጥብቀን ልንይዝ ይገባናል፡፡
አላህ ቀጥተኛዋን መንገድ ይምራን፡፡ ጨለማዎች ከሆኑት የጥመት መንገዶች አላህ ይጠብቀን፡፡
የአላህ ሰላት እና ሰላም በነብያት መደምደሚያ፤ በቤተሰቦቻቸው፤ በባልደረቦቻቸው፤ ሃቅን በተከተለ ላይ ሁሉ ይሁን፡፡