Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

‹‹ሴቶች ፤ አስገድዶ መደፈር እና ዝሙት›› የመጣው መከራ ምክንያቱ ምን ይሆን???

‹‹ሴቶች ፤ አስገድዶ መደፈር እና ዝሙት››
የመጣው መከራ ምክንያቱ ምን ይሆን??? 

የአላህ መልክተኛ ((ﷺ)) የሚከተለውን ይላሉ፡፡
عن أبي هريرة رضي الله عنه قال: قال رسول صلى الله عليه وسلم ,, لايحل لإمرأة تؤمن با الله واليوم الأخرة أن تسافر مسيرة يوم وليلة إلا ومعها حرمة،، وفي لفظ البخاري إلا ومعهاذي محرم

‹‹በአላህ እና በመጨረሻው ቀን ያመነች ሴት ልጅ፤ የአንድ ቀን እና ለሊት የሚፈጅ መንገድ ያለ ሙህሪም (አባት፤ ባለቤቷ፤ ወንድም፤ አጎት፤ ወንድ ልጇ) መሄድ አይፈቀድላትም (ሃራም ይሆንባታል)፡፡››

فعن ابن عباس رضى الله عنهما قال: سعمت رسول الله صلى الله عليه وسلم يقول: لا يخلون رجل بامرأة إلا ومعها ذو محرم ’ولا تسافر المرأة إلا مع ذى محرم فقام رجل فقال : يارسول ,إن امرأتى خرجت حاجة ,وإنى اكتتبت فى غزوة كذاوكذا’فقال انطلق فحج مع امرأتك (رواه البخاري ومسلم)

ከአብድላህ ኢብን አባስ (ረድየላሁ አንሁማ) የአላህ መልክተኛን …… ሰምቼያለሁ እንዲህ ሲሉ ‹‹አንድ ወንድ ከአንድ ሴት ጋር ሰው በሌለበት ቦታ (ገለል ወዳለ ቦታ) አብሯት እንዳይሆን (ተከልክሏል) አብሯት ሙህሪም (አባት፤ ባለቤቷ፤ ወንድም፤ አጎት፤ ወንድ ልጇ) ሳይኖር፡፡

ሴት ልጅ ጉዞ አታድርግ (ክልከላ ነው) ከቅርብ ዘመዶቿ በስተቀር፡፡ አንድ ሰው ተነሳና፤ (ያረሱለላህ) አንቱ የአላህ መላክተኛ ሆይ((ﷺ)) ሚስቴ ሃጅ ባላ ሄዳለች፡፡ እኔ ደግሞ በሆነ ዘመቻ ልሄድ ተመዝግቤያለሁ (ምን ላድርግ አላቸው)

(የአላህ መላክተኛም((ﷺ)) ) አሉ ሂድ ከሚስትህ ጋር ሃጅ አድርግ›› ቡኻሪ እና ሙስሊም

ሃዲሱ በግልፅ እንደሚያሳየው፤ ብቻዋን ሃጅ ብላ የሄደች ሚስቱን እንኳን ያውም አላህ ለማምለክ፤ የአላህ መላክተኛ ((ﷺ)) ሂድ ሚስትህ ጋር አሉት ጀሃድን የሚያክል ነገር ተትቶ፡፡

የአላህ መልክተኛን ((ﷺ)) ትዕዛዝ መጣስ በዱንያ ላይ ብዙ ያስከፍላል፡፡ ኢስላም አንድን ነገር ቀድሞ ሲከለክል ለፍጡራን የሚሆነውን እና የማይሆነውን አውቆ ነው፡፡ በአረብ አገራት ላይም ይሁን በምእራቡ አለም ላይ ሴቶች ተደፈሩ የሚባል ወሬ ይሰማል፡፡

መጀመሪያውኑ ወንዶች ሴት ልጅ ላይ ያላቸውን ባህሪ አውቆ ኢስላም ለሴት ልጅ ከለላ ለመስጠት ሲል ሴትን ልጅ ከሙህሪም ውጭ ከአካባቢዋ ለቃ በብቻዋ እንዳትጓዝ ከለከለ፡፡ የኢማንም መለኪያ እና ሚዛን ተደርጎ ‹‹በአላህ እና በመጨረሻው ቀን ያመነች ሴት ልጅ፤ የአንድ ቀን ወይንም የሁለት ቀን የሚፈጅ መንገድ ያለ ሙህሪም (አባት፤ ባለቤቷ፤ ወንድም፤ አጎት፤ ወንድ ልጇ) መሄድ አይፈቀድላትም፡፡›› ተብሎ ተገለፀ፡፡

ሴትን ልጅ አደለም ደፍሮ ብትስማማም ‹‹ዝሙትን›› የሰሩ አላህ ዘንድ ከባድ ወንጀል ሰርተዋል፡፡ ኢስላም ‹‹ዝሙትን›› ከታላላቅ ወንጀሎች ውስጥ መድቦታል፡፡

በጣም የሚገርመው አደለም በሰው አገር፤ በገዛ አገራችን ሴቶች ሁል ጊዜም በባለጌ ወንዶች ይደፈራሉ፡፡ የቤተሰብ ከለላ ይፈልጋሉ፡፡ ኢስላም ይህን ከለላ ሰጥቷል፡፡ ችግሩን ስለሚያውቅ መፍትሄውን አስቀምቷል፡፡

በጣም የሚያበሳጨው ደግሞ ሚስቱን ሰርቶ እንዲያበላ አላህ ግዴታ ያደረገበት ባል ላይ ሆኖ ሳለ፤ ሚስቱን አረብ አገር ልኮ፤ ሚስቱ ለፍታ የላከችውን ገንዘብ እሱ እዚህ ጫት የሚቅም ስንት በሚስቱ የማይቀና አለ፡፡ የአላህ መልክተኛ((ﷺ)) ‹‹ደዩስ (በሚስቱ፤ በሴት ልጁ፤ በእህቱ፤ በእናቱ፤ በአማኝ ሴት ልጆች የማይቀና) ጀነት አይገባም›› ብለዋል፡፡

ወደ አላህ መልክተኛ ((ﷺ)) ቀጥተኛ መንገድ ሁላችንም የምንመለስ ያድርገን፤ መፍትሄው እዛ ላይ ነው፡፡ ውሽትን ቀን ከለሊት የሚቸረችሩ፤ ትንሹን ነገር አጋነው ከሚያወሩ የዜና እና ሌሎች አውታሮችን እየሰሙ ወሬ ከማዳመቅ፤ አላህ ወዳለው ትክክለኛ መንገድ፤ ነብያችን((ﷺ)) ወዳሳዩት መንገድ እንመለስ እና ሃይማኖታችንም፤ ማህበራዊ ኑሮዋችንም ተስተካክሎ እናገኘዋለን፡፡ አላህም ቃል ገብቷል፤ የአላህም ቃል አይታጠፍም፡፡

የአላህ ሰላት እና ሰላም በአላህ ውድ ነብይ ላይ፤ በቤተሰቦቻቸው፤ በባልደረባዎቻቸው እና ፈለጋቸውን በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን፡፡ አላሁመ አሚን፡፡
by Sadat Kemal Abu Nuh