ሙአዚኑ ለሰላተል ፈጅር አዛን እያለ መብላት ወይም መጠጣት በሸሪዓ ሑክሙ (ፍርዱ) ምንድን ነው?
ፆመኛ ከእውነተኛው ጎህ መቀደድ አንስቶ ፀሀይ እስክትጠልቅ ድረስ ፆምን ከሚያበላሹ ነገሮች መቆጠብ ግዴታ ነው። ይህ ማለት ጎህ ሲቀድ እንጂ “አዛን” አይደለም። ሀያሉ አምላካችን አላህ እንዲህ ብሏል፡-
"የንጋት ነጭ ክር (ብርሃን) ከጥቁር ክር (ከሌሊት ጨለማ) የተለየ እስኪገለጽላችሁ ድረስ ብሉ ጠጡም።" (አል-በቀራህ 2፡187)
ስለሆነም አንድ ሰው እውነተኛው ጎህ እንደመጣ ሲያውቅ መብላትና መጠጣት ማቆም አለበት, በአፉ ውስጥ ምግብ ካለ መትፋት አለበት; ያንን ካላደረገ ጾሙን አበላሽቷል።
ሆኖም አንድ ሰው ፈጅር መውጣቱን (ጎህ እንደ ወጣ) እርግጠኛ ካልሆነ እስኪያረጋግጥ ድረስ መብላት መጠጣት ይፈቀድለታል። ጊዜው ከመድረሱ በፊት ሙአዚኑ አዛን እንደሚል ካረጋገጠ ወይም አዛኑን በሰዓቱ ወይም በጊዜው ማለቱን እርግጠኛ ካልሆነ፡ እርግጠኛ እስኪሆን ድረስ መብላት ይችላል። ይሁንንና አዛኑን እንደሰማ ከመብላትና ከመጠጣት ቢታቀብ ተመራጭ ተግባር ነው።
አንዳንድ ሰዎች ቀጣዩን ሐዲስ እንደማስረጃ በማቅረብ አዛን እያለ የሚበሉና የሚጠጡ ሰዎች አሉ።
አቡ ሁረይራ (ረዲየላሁ ዐንሁማ) እንዲህ ብለዋል፡- የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “ከእናንተ አንዳችሁ ዕቃው(ኩባያው፣ምግቡ) በእጁ ላይ እንዳለ፣አዛን ቢሰማ እስኪጨርስ አያስቀምጠው።” (አህመድ 10251) (አቡ ዳውድ 2350 )አልባኒ በሶሂህ አቢ ዳውድ ሰሂህ ብለውታል።
⛔️ይሁንና ይህን ሐዲስ በተመለከተ ዑለማዎች ጎህ ሳይቀድ የሰላት ጥሪ የሚያደርግ ሙአዚንን የሚመለከት ነው ብለው ተርጉመውታል።
ሸይኽ ዐብዱል ዐዚዝ ኢብኑ ባዝ (ረሒመሁላህ) የፈጅርን አዛን ሰምቶ እየበላና እየጠጣ የቀጠለ ሰው የፆሙ ፍርዱ ምንድን ነው? ተብለው ተጠየቀው ቀጣዩን ምላሽ ሰጥተዋል።
" ሙእሚን ማድረግ ያለበት ፆምን ከሚያበላሹ፣ ከመብላትና ከመጠጣት ወዘተ ነገሮች መከልከል ይኖርበታል። ግዴታ ፆም ከሆሆነ ለምሳ፦ እንደ ረመዷን እና “ነዝር”ስለትን ለመሙላት የሚፆምህ መውጣቱ ካረጋገጠ ከምግብና ከመጠጥ እንዲሁም ፆምን ከሚያበላሹ ነገሮች መታቀብ አለበት።
ምክንያቱም አላህ በቁርኣኑ (ትርጉሙ ሲተረጉም) እንዲህ ይላል፡-
"የንጋት ነጭ ክር (ብርሃን) ከጥቁር ክር (ከሌሊት ጨለማ) የተለየ እስኪገለጽላችሁ ድረስ ብሉ ጠጡም።" (አል-በቀራህ 2፡187)
የፈጅር ሰላት ጥሪ መሆኑን ካወቀ መብላቱን ማቆም አለበት። ሙአዚኑ ጎህ ሳይቀድ አዛን የሚል መሆኑ ከታወቀ መብላቱን ማቆም የለበትም። ጎህ መውጣቱ እስኪገለጥለት ድረስ መብላትና መጠጣት ይፈቀድለታል።
ሙአዚኑ የሶላትን ጥሪ ከፈጅር በፊትም ሆነ በኋላ እንደሚል ካላወቀ አዛኑን ሲሰማ፤ መብላቱን ቢያቆም የተሻለ እና ደህንነቱ የተጠበቀ ነው።( ከተጠያቂነት የሚያድነውን ተግባር ፈፅሟል)። ነገር ግን በአዛን ጊዜ ቢጠጣ ወይም ቢበላ ምንም ችግር የለውም። ምክንያቱም ፈጅር እንደወጣ አያውቅምና።
እንደሚታወቀው የኤሌክትሪክ መብራት ባለባቸው ከተሞች ነዋሪዎቹ ፈጅር መውጣቱን ማወቅ ባይችሉም የአዛን ሰአትና ደቂቃን የታተመ የጊዜ ሰሌዳን መከተል እንደሚችሉ ይታወቃል።
ነቢዩ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ቃል፡- “የሚጠራጠርህን ነገር ትተህ የማያጠራጥርህ ተግብር።” በሌላ ሀዲሳቸውም (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹አጠራጣሪ ጉዳዮችን የራቀ ሰው ሃይማኖቱን ክብሩን ጠብቋል።” አላህም የብርታት ምንጭ ነው!
📘(ፈትዋ ረመዳንያ፣ በአሽራፍ አብዱልመቅሱድ የተጠናቀረ፣ ገጽ 201)
ከላይ ለቀረበው ጥያቄ ምላሹ ሲጠቃለል እነሆ ፦ አንድ ሰው እውነተኛው ጎህ እንደመጣ ሲያውቅ መብላትና መጠጣት ማቆም አለበት, እና በአፉ ውስጥ ምግብ ካለ መትፋት አለበት; ያንን ካላደረገ ጾሙን አበላሽቷል።
✍️ አቡሁዘይፋ ሱለጧን ኸድር
⏰ ቅዳሜ ረመዷን 03/ 1444 አ/ሂ
ወላሁ አዕለም!
https://t.me/sultan_54
0 Comments