Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

የኒካህ ኸይሩ ቀላሉ ነው


ግፊት አለ፣ ስኳር አለ፣ ስንት ነገር አለ!
እንዴት ነው ነገሩ... ቁጥር አይፈራም እንዴ? ቢያንስ ቁጭ አድርጎ አረጋግቶ ምናምን እንጂ ባንዴ ጫን ሲያደርጉበት እዛው ፌንት ቢበላስ?
ሆ! ለሰርግ ሄዶ ሆስፒታል ሊያድር? የለም የለም ጥሩ አይደለም! እንተዛዘን እንጂ! ማግባት ያሸልማል እንጂ ያስቀጣል እንዴ? ያውም ባንዴ ትቢያ የሚያበላ ቅጣት!
ልጃችሁን ስጡን ማለት ለትዳር፣ ለወግ ለማእረግ እንጂ ለክፉ አይደል? ብትዳር ብትኳል፣ ከሀራም ብትጠበቅ ለሷ ሰላም ለቤተሰቧ ኩራት ነው።
ማንም አባት የትኛዋም እናት ልጇ ስትንዘላዘል ማየት መስማት አትሻም። ብትዘወጅ፣ ከጥሩ ተጣማሪ በሀላል ብትቆራኝ የአእምሮ እረፍት የመንፈስ ሰላም ይሰጣል።
ታዲያ 'ልጃችሁን ስጡኝ እና ከጭንቀት ልገላግላችሁ' ያለን እንዲህ ባፍጢም የሚደፋ መህር መጠየቅ ምን ይሉታል? በግዜ መዳሯ ግዜዋ አለመባከኑ ለሷም ለቤተሰቧም ክብር ሆኖ ሳለ የመጣን ጠያቂ እንደገቢዎች ግብር ናላ በሚያዞር ቁጥር ማባረር ተገቢ አይደለም።
10,000
20,000
ባለፈው የሰማሁት ደሞ ጉድ ነው ...
60,000 ....
ኧረ ጎበዝ እየተሳሰብን?
ግፊት አለ፣ ስኳር አለ፣ ስንት ነገር አለ! ልጁ እዛው ፍግም ቢልስ? ለደስታ መጥተን እናልቅስ እንዴ?
'ሲያንሳት ነው፣ ቤተሰቧን ትታ እኮ ራሷን እየሰጠችው ነው' የሚል ይኖራል። እንዴ እሱስ ቤተሰቡን ትቶ እራሱን እየሰጣት አይደለም እንዴ። እንዴት ያለ ሒሳብ ነው? እንደውም የሱ አይብስም ብላችሁ ነው?!
ደሞ እንደ ጀብድ 'የእገሌ ልጅ በዚህ ያክል የገሌ ደሞ በዚህ ያክል ተዳረች' እያሉ መጎረር። አጀብ! ድንቄም ጉራ! ሙሽራው ቆሽቱ አርሯል እነሱ 'በዚህ ያክል መህር' ብለው እልል ይላሉ።
ሊጎረርስ የሚገባው ቀለል ባለ ሁኔታ በተዳረችው ነበር። ነቢያችን (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ምን አሉ ...
"የኒካህ ኸይሩ ቀላሉ ነው" ኢብኑ ሂባን ዘግበውታል
ዳሩ የሚኮራበትና የሚታፈርበት ተደበላልቆብናል። ድንኳን ሳይጣል፣ ሰው ሳይተራመስ ምግቡ ሳይባክን ቀለል ባለ መህር ያገባችው ልትኮራ ሲገባት፤ በአባካኝነት መወቀስ ያለባቸው፣ ያላቅም በመደገስ መነወር የሚገባቸው፣ ሙዚቃና መንዙማ(ያው በለው) በማተራመስ ማፈር ያለባቸው በተቃራኒ ሲቆለሉ ማየት ያሸማቅቃል።
ከምሬ ነው! ዛሬ ጥሩው መጥፎ መጥፎው ጥሩ እየመሰለን ነው። የሱኒዩ ቤት ሙዚቃ የማይከፈትበት ዛሬ በነሺዳ ተብዬ ዘፈን ሲናወጥ መስማት ተለምዷል። የገሪባ መቦዘኛ የነበረው ዲቤ ትልልቅ ሰዎች ቤት ገብቶ ሲወገር መስማት የማያስደንቅ ሆኗል።
ኮራ ጀነን ይሉ የነበሩ ጎረምሶች ልክ እንደሴት ሲያጨበጭቡ ማየት እንደካፊር ሲደንሱ መመልከት በዝቷል። በጀለቢያ መጥቶ የጭፈራ አምሮቱን የሚወጣውን ሰርግ ይቁጠረው!
እኔማ ልበላ ሰፍ ብዬ የሄድኩበት ሰርግ ላይ የፉቅራ መአት ድቤ እየወገረ ሲያበግነኝ የመብላት ሞራሌ ባንዴ ዜሮ ወርዶ አፒታይቴ ይቆለፋል። እስቲ በአላህ ምን የመሰለ ሸበላ እንደሴት ሲያደርገው አይደለም ምግብ ዱኒያ አያስጠላም እንዴ?
ብቻ አላህ ያስተካክለን። በጭፈራ የተከፈተ ትዳር እንዴት አላህን የሚፈራ ቤተሰብ እንደሚመሰርት ግር ይለኛል። እየደለቁ ወደ ትዳር ገብቶ ሰጋጅና ጿሚ ትውልድ ማፍራት ቀላል አይመስልም።
አለኮ ደሞ 'ምን አለበት?' የሚል። ኧረ ጋሼ ብዙ ነገር አለበት! ትዳር ማለት እኮ ረጅም ህይወት ነው! እንዲህ ከመግቢያው ካጨለምነው ቀሪው እንዴት ይገፋል? ድል ተደርጎ በተደገሰ ማግስት ፍርድ ቤት የሚሄደው ስንቱ ነው?
'ያወጣሁትን መልሱ' እያለ የሚካሰሰው ስንቱ ነው?
ኧረ ነቃ እንበል! ወደ ትዳር መግቢያን ቀለል ማድረግ እኮ ብዙ ወጣቶችን ከሀራም ለመታደግ አይነተኛ ዘዴ ነው። ስንቱ መሰለህ እንዲህ ያለ ወጪን አልችልም በማለት የሚወሰልተው? ስንቱ መሰለህ ከጌታው የሚጣላው? ያውም እጅግ አፀያፊ በሆነው ዚና!
አንዳንድ እህቶችም ማሰብ ጀምሩ! (ያዙልኝ አንዳንድ ነው ያልኩት) አብዛኞቹ እንደሚያስቡ አልጠራጠርም። ጥቂቶቹ ግን የዛች ቀን እንጂ ሌላ ቀን የሌላቸው ይመስል ይህ ካልተደረገ፣ ይህ ካልመጣ፣ ይህ ካልተገዛ፣ ይህ ካልተከራየ እያሉ ቂያማ የሚያቆሙ አሉ። እያሰብን እንጂ!
ብትዳሪ እኮ ጥቅሙ ላንቺ ነው። ጥቅሙ ደግሞ ትዳሩ እንጂ ሰርጉ አይደለም። ሰርግ እኮ 'በር' ነው! ዋናው መጠለያው ቤቱኮ ትዳር ነው። እና 'ሲስቱካ ቤቱን እረስተሽ በሩን ማሰማመሩ አያዋጣም'። ነቃ በይ!
እየናቅሽ ጠያቂን በመለሽ ቁጥር አሊያም በምትጠሪው መህር እያስደነበርሽ ፈላጊሽን ስታባርሪ ጊዜሽም እየሄደ መሆኑን አስተውይ! ጊዜ ሲሄድ ደግሞ Demand መቀነሱ አይቀርም! የዛኔ የዋጋ Discount ማድረግ ለውጥ አያመጣም። ስለዚህ ጊዜሽን ተጠቀሚበት!
አንተ ደግሞ! አንተኛው! የተጠየቅከውን መኸር በማናለብኝነት የምትገፈትረው፤ ታውቆሀል ግን? በቀረው ትዳር ፈላጊ ላይ ዋጋ እያስወደድክ እንደሆነ?
አንተ ዝም ብለህ የጠየቁህ ትሰጣለህ እዚህ ምስኪኑ ፍዳውን ያያል! እነፋዙካ እኮ 'እኽ የእገሌ ልጅ እንዲህ ተከፍሎላት የለ!? የኛ ልጅ በምን ታንሳለች' እያሉ መኸር እየቆለሉ ነው። እና ባክህ ባክህ ላንተ ብቻ ሳይሆን ለቀሩትም ወንድሞችህ እያሰብክ። በልማትና በትዳር ላይ ለምናደርገው ግስጋሴ የአንተ ስራ እንቅፋት እብዳይሆንብን!
በተረፈ ትዳር ጥሩ ነው! እሱማ ግልፅ ነው። መግቢያው በሾህ ከታጠረ ግን ጥሩነቱ ሊዘነጋ ይችላል። እና ... የሚመለከታችሁ 'ባለ ድርሻ አካላት!' ይህን ካነበብን በኋላ የጉዳዩን አሳሳቢነት ተረድተን ለወጣት ትዳር ፈላጊዎች ሁኔታዎችን እንድናሳልጥ አሳስባለሁ።
ሰላም ሰርግ ይግጠማችሁ!