መልስ፦ ሐይዷ የቆመው ከፈጅር መውጣት በፊት መሆኑን እርግጠኛ ከሆነች ፆሟ ትክክለኛ ነው። ዋናው ነገር የቆመላት መሆኑን እርግጠኛ መሆኗ ነው። ምክንያቱም አንዳንድ ሴት ሳትፀዳ (ሳይቆምላት) የፀዳች ይመስላታል። ለዚህ ነው አንዳንድ የሰሃባ ሴቶች ለመፅዳታቸው ምልክት በጥጥ ይዘው ወደ አዒሻ በመምጣት ሲያሳዩዋት << ነጭ ፈሳሽ እስከምታዩ ድረስ አትቸኩሉ >> ትላቸው የነበረው። ስለዚህ ሴት መፅዳቷን እርግጠኛ እስከምትሆን ድረስ መቆየት አለባት። ከፀዳች ለመፆም ኒያ ታድርግ ፈጅር ከወጣ በኋላ እንጂ የማትታጠብ ቢሆን እንኳ ለመፆም ኒያ ማድረግ አለባት። ነገር ግን ሰላቷንም ጠብቃ መስገድ ስላለበት የፈጅርን ሰላት በወቅቱ ለመስገድ ቶሎ መታጠብ ይኖርባታል።
አንዳንድ ሴት ፈጅር ከወጣ በኋላ ወይም ፈጅር ከመውጣቱ በፊት እንደምትፀዳና በደንብ የሚያጠራና የተሟላ ትጥበት ለማድረግ በሚል ምክንያት ትጥበቱን አዘግይታ ፀሀይ ከወጣች በኋላ እንደምትታጠብ ደርሶናል። ይህ ድርጊት በረመዳን ውስጥም ሆነ ከረመዳን ውጭ ስህተት ነው። ከወር አበባ የፀዳች ሴት ግዴታዋ ቶሎ ታጥባ ሰላቷን በወቅቱ መስገድ ነውና። በወቅቱ ዋጂቡን ትጥበት ብቻ አድርጋ ሰላቷን ብትሰግድና የበለጠ ለመጥራት ከፈለገች ደግሞ ፀሀይ ከወጣች ብኋላ በድጋሚ የተሟላ ትጥበት ብታደርግ ቸችግር የለውም። ጀናብተኛ የሆነች ሴትም ፈጅር ከወጣ በኋላ ብትታጠብ ምንም ችግር የለውም። ፆሟም ትክክለኛ ነው። ወንዱም ቢሆን ፆመኛ ሆኖ ጀናባ ቢኖርበትና ፈጅር ከመውጣቱ በፊት ሳይታጠብ ቆይቶ ከፈጅር በኋላ ቢታጠብ ችግር የለውም። ነቢዩ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ጀናብተኛ ሆነው ሳይታጠቡ ፆማቸውን እንደሚጀምሩና ፈጅር ከወጣ በኋላ እንደሚታጠቡ ተዘግቧል (ቡኻሪና ሙስሊም)። ወላሁ አዕለም።
(ሸይኽ መሐመድ ኢብኑ ሷሊህ አል-ዑሰይሚን ረሒመሁላህ)