Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ቀብር ላይ ሱረቱል ፋቲሃ እና ሌላን ሱራ መቅራት?

ቀብር ላይ ሱረቱል ፋቲሃ እና ሌላን ሱራ መቅራት?
የቱን ይከተላሉ አላህ ያወረደውን ወይንስ “የአባቶቻችን መንገድ” ብለው የሚጠሩትን?
.
.
.
.
.
.
.
.
.
.
.
.
.
.
.
.
መቼም እስልምናችን ውብ እና ሙሉ፣ ለየትኛውም ዘመን እና ቦታ ከበቂ በላይ የሆነ ነው፡፡ ታማኙ ነብዩ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ከአላህ የተላኩበትን ማንኛውም መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ ቀብር ስንዘይር ምን ማለት እንዳለብንም አስተምረዋል፡፡ የሚከተለው ሀዲስ ላይ እንደተዘገበው
وعن بريدة رضي الله عنه قال‏:‏ كان النبي صلى الله عليه وسلم يعلمهم إذا خرجوا إلى المقابر أن يقول قائلهم‏:‏ “السلام عليكم أهل الديار من المؤمنين والمسلمين وإنا إن شاء الله بكم للاحقون، أسأل الله لنا ولكم العافية” ‏(‏‏(‏رواه مسلم‏)‏‏)‏‏.‏
የአላህ ሰላም በናንተ የዚህ መኖሪያ (ቀብር) ባለቤቶች ላይ ይሁን፡፡ ከአማኞች እና ከሙስሊሞች፡፡ እኛ በአላህ ፍቃድ ወደ እናንተ የምንከተል (ሟቾች) ነን፡፡ አላህን ለእኛም ለእናንተ አፊያን እንዲያደርግ እንጠይቀዋለን፡፡
ከዚህ ሀዲስ የምንወስደው ዋና ቁምነገር
- በህይወት ያለ ሰው ነው ለሙታን ዱዓ የሚያደርገው፣
- ሙታን ዱዓ ይደረግላቸዋል እንጂ እነሱ አይለመኑም፣
- ዛሬ ሺርክ ላይ የወደቁ ሰዎች ህያው የሆነውን፣ ሁሉን በማድረግ ላይ ቻይ የሆነውን፣ የማይሞት አላህ ትተው ስራቸው የተቋረጠባቸውን፣ ምንም ማድረግ የማይችሉ፣ ቢጠሩ የማይሰሙ፣ ቢሰሙም ኖሮ መልስ መስጠት የማይችሉ ሙታኖችን እርዳታ ይለምናሉ፣ ቀብራቸው ላይ ሄደው ያርዳሉ፣ ቀብራቸው ላይ ጠዋፍ ያደርጋሉ፡፡
በዚህ ሀዲስ መሰረት ነብዩ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ያስተማሩን ወንድ ልጅ ቀብር ሲሄድ ይህንን ዱኣ እንዲል ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ሱረቱል ፋቲሃንም ይሁን ሌሎች ሱራዎችን በተለይ አገራችን ላይ በጀመዓ ቁርኣንን እየጮሁ የሚቀሩት ቢድዓ (በዲን ላይ የተጨመረ ፈጠራ) ነው፡፡ ከአላህ ቀጥሎ ለማንም በላይ እንወዳቸዋለን እያልን የምንጠራቸው ነብዩ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) እንዲህ ይሉናል “የእኛ ትዕዛዝ የሌለበትን ስራ የሰራ ሰው ስራው ተመላሽ ነው፡፡” (ስራው ተቀባይነት የለውም)፡፡ ቀብር ላይ ሄዶ ሱረቱል ፋቲሃንም ይሁን ሌላን ሱና በጀመዓም ይሁን በነጠላ መቅራት የታለ ነብዩ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ያዘዙበት? መልሱም አላዘዙበትም፡፡ ስለዚህ ቀብር ላይ እሳቸው ያስተማሩትን ብቻ እንበል፡፡
እኛ የነብዩ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ተከታዬች ነን ካልን በሁሉ ነገር ልንከተላቸው እና እሳቸው ያልሰሩትን ልንርቅ ይገባናል፡፡ ከዛ ውጭ የነብዩን (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ትእዛዝ ለሸሁም፣ ለኡስታዙም፣ ለአባቶቹም ሲል የተወ ሰው ከባድ አደጋ ውስጥ ገብቷል፡፡ ምክንያቱም ነብዩን (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ከማንም በላይ እኛ ዘንድ እስካልተወደዱ (እስካልተከተልናቸው እና በዲን ላይ ከሚደረግ ፈጠራ እስካልራቅን) ድረስ እውነተኛ አማኞች አልሆንም፡፡
የነብዩ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) አስተምህሮት ሱና እንዲህ ሁሉን ነገር ገላልፆ ሲያበቃ የአባቶቻችን መንገድ ብሎ ሱናን መቃረን ለከባድ አደጋ ይዳርጋል፡፡
የአባቶቻችን መንገድ የተባለው ከነብዩ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ሱና ከገጠመ በደስታ እንቀበለዋለን፡፡ ከአባት ከእናታችን በላይ ውድና በላጭ የሆኑትን የነብዩ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) መንገድ ከተቃረን አሽቀንጥረን እንወረውረዋለን፡፡ ምክንያቱም የሰይጣን መንገድ ነውና፡፡ አላህ እንዲህ ይላል
[2:170] وَإِذَا قِيلَ لَهُمُ ٱتَّبِعُوا۟ مَآ أَنزَلَ ٱللَّهُ قَالُوا۟ بَلْ نَتَّبِعُ مَآ أَلْفَيْنَا عَلَيْهِ ءَابَآءَنَآ ۗ أَوَلَوْ كَانَ ءَابَآؤُهُمْ لَا يَعْقِلُونَ شَيْـًٔا وَلَا يَهْتَدُونَ
ለእነርሱም “አላህ ያወረደውን ተከተሉ” በተባሉ ጊዜ “አይደለም አባቶቻችንን በርሱ ላይ ያገኘንበትን ነገር እንከተላለን” ይላሉ፡፡ አባቶቻቸው ምንም የማያውቁና (ወደ እውነት) የማይመሩም ቢኾኑ (ይከተሉዋቸዋልን?)
[31:21] وَإِذَا قِيلَ لَهُمُ ٱتَّبِعُوا۟ مَآ أَنزَلَ ٱللَّهُ قَالُوا۟ بَلْ نَتَّبِعُ مَا وَجَدْنَا عَلَيْهِ ءَابَآءَنَآ ۚ أَوَلَوْ كَانَ ٱلشَّيْطَٰنُ يَدْعُوهُمْ إِلَىٰ عَذَابِ ٱلسَّعِيرِ
ለእነርሱም አላህ ያወረደውን ተከተሉ በተባሉ ጊዜ አይደለም በእርሱ ላይ አባቶቻችንን ያገኘንበትን እንከተላለን ይላሉ፡፡ ሰይጣን ወደ እሳት ቅጣት የሚጠራቸው ቢሆንም (ይከተሉዋቸዋልን?)
ይሀው እነዚህ ሁለት አንቀፆች በግልፅ እንዳስቀመጡት “የአባቶቻችን መንገድ” እየተባለ አገራችን ላይ የሚነሳው የጥንቶቹም የሚያነሱት ብዥታ ነበር፡፡ ነብዩ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) እና እሳቸውን በየዘመኑ የሚከተሉ ኡለማዎች እና ተጣሪዎች የሚያዙት “አላህ ያወረደውን ተከተሉ (እንከተል)” ሲሉ ነው፡፡ የነብያትን መንገድ የሚቃረኑ ሰዎች ደግሞ በየዘመኑ መልሳቸው “አይደለም አባቶቻችንን በርሱ ላይ ያገኘንበትን ነገር እንከተላለን” የሚል ነው፡፡
አላህ ግን እንዲህ ሲል ጠየቀ
- “አባቶቻቸው ምንም የማያውቁና (ወደ እውነት) የማይመሩም ቢኾኑ (ይከተሉዋቸዋልን?)”
- “ሰይጣን ወደ እሳት ቅጣት የሚጠራቸው ቢሆንም (ይከተሉዋቸዋልን?)”
ኢናሊላሂ ወኢና ኢለይሂ ራጂኡን፡፡ አንዳንዴ የአባቶቻችን መንገድ የሚሉትን ልክ አይደለም ሲባሉ እና በማስረጃ መልስ ሲሰጠው “እናንተ ከእነ ሸህ እከሌ በላይ ታውቃላችሁን?” ሲሉም ይደመጣል፡፡ ጥያቄው እነዚህ ሸህ ተብየዎች ከነብዩ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) እና ከሰሃባዎቻቸው በላይ ያውቃሉን? በፍፁም፡፡ እኛ አላህ እና መልክተኛው በእውቀታቸው፣ በአማኝነታቸው፣ በእውነተኝነታቸው፣ በታጋሽነታቸው፣ በቁርጠኝነታቸው የመሰከሩላቸውን መልክተኛውን እና ሰሃባዎቻቸውን መንገድ ነው የምንከተለው፡፡
አላህ ያወረደውን የማይከተል ሰይጣን ወደ እሳት የሚጣራበትን መንገድ እየተከተለ ነው፡፡
አገራችን ላይ አብዛኛውን ጥፋት “የአባቶቻችን መንገድ” እየተባለ ይፈፀማል፡፡ አባቶቻችንን ሳይሆን አላህ ያወረደውን እንድንከተል ነው የታዘዝነው፡፡ መልካም ማለት እኛ መልካም ያለነው አይደለም፡፡ መልካም ማለት ዲን መልካም ያለው ነው፡፡
አምነው ለሞቱ አባቶቻችን በጠቅላላ አላህ ወንጀላቸውን እንዲምር ደረጃቸውን ከፍ እንዲያደርግ ቀብራቸውን እንዲያሰፋ እለምነዋለሁ፡፡ አላህ እኛንም ሙስሊም አድርጎ እንዲገድለን እለምነዋለሁ፡፡
አላህ እሱ ባወረደው፣ በነብዩ ሱና ከሚብቃቁት፣ ከሺርክና ከቢድኣ ከሚርቁት ያድርገን፡፡ በአላህ ቢሆን እንጂ ሀይልም ብልሀትም የለም፡፡
የአላህ ሰላት እና ሰላም በነብያት መደምደሚያ፣ በባለቤቶቻቸው፣ በቤተሰቦቻቸው፣ በባልደረባዎቻቸው እና ሀቅን በተከተለ ላይ ሁሉ ይሁን፡፡

Post a Comment

0 Comments