Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

“እውነቱም (ሞት) እስኪመጣህ ድረስ ጌታህን ተገዛ፡፡” (15፡99)


“እውነቱም (ሞት) እስኪመጣህ ድረስ ጌታህን ተገዛ፡፡” (15፡99)

እስከ መጨረሻ የህይወት ጠብታችን ድረስ በመታገል መኖርን የኑሯችን መርህ እናድርገው። እያልኩ ፅሁፌን እጀምራለሁ መልካም ንባብ።
ዒባዳ ከ - እስከ የሚባል ወሰን የለውም። የፈለግነውን እስክናገኝ ድረስ የምናመጨው ነዳጅም አይደለም። ይሉቁኑ እስትንፋሳችን ስትቆም የሚቆም እንጂ በደከመንና በተሰላቸን ቁጥር ከላያችን አውልቀን የምንጥለው ሸክም አይደለም። ባይሆን ይህችን የጌታችንን ንግግር ልብ በሉልኝ፡-
وَاعْبُدْ رَبَّكَ حَتَّىٰ يَأْتِيَكَ الْيَقِينُ [١٥:٩٩]

“እውነቱም (ሞት) እስኪመጣህ ድረስ ጌታህን ተገዛ፡፡” (15፡99)

የሰው ልጅ ከህይወት መጀመሪያ እስከ መኖር ጥግ አላህን በማምለክ ላይ ሊኖር ይገባል አንጂ የፈተና ዝናብ ባካፋ ቁጥር እጅና እግሩን አጣጥፎ “ያግራልኝ” እያለ ሊኖር አምልኮውን ሊያቋርጥ ወደዚህች ምድር አልመጣም። ለማጣፈጫ …
وَمَا خَلَقْتُ الْجِنَّ وَالْإِنسَ إِلَّا لِيَعْبُدُونِ [٥١:٥٦]

“ጋኔንንና ሰውንም ሊግገዙኝ እንጅ ለሌላ አልፈጠርኳቸውም፡፡” (51፡56)

በዚህ አንቀፅ ውስጥ ግልፅና በማያወላዳ መልኩ የተፈጠርንበትን አላማ አላህን ለማምለክ መሆኑን እንገነዘባለን።

በሌላም አንቀፅም …
يَا أَيُّهَا النَّاسُ اعْبُدُوا رَبَّكُمُ [٢:٢١]
“እናንተ ሰዎች ሆይ! ጌታችሁን ተገዙ” (2:21)

۞ وَاعْبُدُوا اللَّهَ وَلَا تُشْرِكُوا بِهِ شَيْئًا [٤:٣٦]
“አላህንም ተገዙ፡፡ በእርሱም ምንንም አታጋሩ፡፡” (4:36)


የጀናት ወራሽ የምንሆነው አላህን በብቸኝነት ማንንም አካል ሳናጋራበት ያለመሳነፍ ስናመልከው ብቻ ነው!
ማስተዋል የሚገባን አንድ ቁም ነገር ደግሞ አላህና መልዕክተኛው ያዘዙትን መታዘዝ ከከለከሉት ተግባራት መታቀብ ራሱ ከዒባዳ እንደሚመደብ ነው።

አላህን በብቸኝነት ስናመልክ የሚያንዣብብን ብዙ አስቸጋሪ ዳመና ይኖራል ቢሆንም ግን መከራና ጉም እያደረ እንደሚቀል ባለመዘንጋት አምልኳችንን ለአላህ ጥርት አድርገን እስከ ህወታችን ፍፃሜ በፅናት እንጓዝ። ጌታችንም እርሱን በመልካም መገናኘትን እንዲወፍቀን እንማፀነው። ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ እንዲሆንልን የምንመኝ ካለን በዚህ ርዕስ ላይ ምስኪንነት አያዋጣምና ይህችን ልብ እንበል፡-
أَحَسِبَ النَّاسُ أَن يُتْرَكُوا أَن يَقُولُوا آمَنَّا وَهُمْ لَا يُفْتَنُونَ [٢٩:٢]

“ሰዎቹ አምነናል በማለታቸው ብቻ እነሱ ሳይፈተኑ የሚተው መኾናቸውን ጠረጠሩን?” (29፡2)

ያለ መከራ አይገኝም እንጀራ አይደል ሚባለው ?

አላህ በቅጣት የሚያስፈራራን በትዕዛዙ ላይ ታግሰን በመልካም ስራ ላይ አንድንበራታ እንጂ ጌታችን በማመፃችን ነፍሳችንን በመበደላችንና ተስፋችን ተሟጦ ወደኃላ እንድናፈገፍግ አይደለም።ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ወደኛ ሊቀርብ አይደለም እንዲያማትር ልንፈቅድለት ፈፅሞ አይገባም ይልቁኑ ይህንን ማበረታቻ ክኒን እንዋጠው…

قُلْ يَا عِبَادِيَ الَّذِينَ أَسْرَفُوا عَلَىٰ أَنفُسِهِمْ لَا تَقْنَطُوا مِن رَّحْمَةِ اللَّهِ ۚ إِنَّ اللَّهَ يَغْفِرُ الذُّنُوبَ جَمِيعًا ۚ إِنَّهُ هُوَ الْغَفُورُ الرَّحِيمُ [٣٩:٥٣]

“በላቸው «እናንተ በነፍሶቻችሁ ላይ ድንበር ያለፋችሁ ባሮቼ ሆይ! ከአላህ እዝነት ተስፋ አትቁረጡ፡፡ አላህ ኃጢኣቶችን በመላ ይምራልና፡፡ እነሆ እርሱ መሓሪው አዛኙ ነውና፡፡” (39፡53)

ነገር ግን ወደ ጌታችን በንሰሃ ተመልሰን በእርሱ ትዕዛዝ ውስጥ መኖርን የወደፊት ዕቅድ አድርገን ለአሁን ግን በወንጀላችን ላይ ለመዘውተር ማሰብ አይደለም ወደ አዕምሯችን ውል ሊልብን እገባም። የዚህ አይነት ከጌታችን ትዕዛዝ ርቀን ህወታችንን በከንቱ እንድንገፋ የሚያበረታታ የሸይጧን ሽንገላ እንዳያታለን አደራ! ወደ አላህ በፀፀት የምንመለስበት ቀን በኃላ ነገ ሳይሆን አሁን ሊሆን ይገባል! ምክንቱም አላህ ይህንን ብሎናላ…

وَأَنِيبُوا إِلَىٰ رَبِّكُمْ وَأَسْلِمُوا لَهُ مِن قَبْلِ أَن يَأْتِيَكُمُ الْعَذَابُ ثُمَّ لَا تُنصَرُونَ [٣٩:٥٤]

“ቅጣቱም ወደእናንተ ከመምጣቱና ከዚያም የማትርረዱ ከመኾናችሁ በፊት ወደ ጌታችሁ (በመጸጸት) ተመለሱ፡፡ ለእርሱም ታዘዙ፡፡” (39፡54)

ስለዚህም የዚህችን ምድር ኮንትራት መቼ ጨርሰን እንደምንሄድ አናውቅምና በፀፀት ወደ አላህ ተመልሰን በአምልኳችን (ዒባዳችን) ላይ በርትተን ለመጓዝ ልንጥር ይገባናል አላህ ያግዘን።

ተፃፈ መስከረም 2/1/07

Post a Comment

0 Comments