Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ሽብር:

ሽብር:
በሙስሊም ተፈፀመ በክርስቲያን፣ 
ሳውዲ ውስጥ ተፈፀመ ስዊድን፣ 
መስጂድ ውስጥ ሆነ ቤተ ክርስቲያን፣ 
በፈረንጅ ሆነ በዐረብ፣ 
በፂማም ወይም በኒቃብ ለባሽ ሆነ፣ በሌላ፣
በአይሲስ ተፈፀመ፣ በኩኩ ክላስ ክላን፣
በመንግስት ተፈፀመ በግለሰብ፣
በኦባማ ተፈፀመ በኡሳማ፣
.
.
.
ሁሉም ሽብር ነው። እየመረጡ ማውገዝ፣ እየመረጡ ማራገብ፣ እየመረጡ ማለፍ፣ እየመረጡ ስሙን መቀየር፣ ወንጀሉን ለመዋጋት የሚደረገውን ጥረት ፍሬው እንዲቀል ያደርገዋል።
በአሁኑ ሰዓት የምዕራብ ሃገራት ውስጥ በሙስሊም አሸባሪዎች ከሚደርሰው በላይ በሌሎች የሚደርሰው በብዙ እጥፍ የባሰ ቢሆንም የሚዲያዎች ትኩረት ግን የተገለበጠ ነው። በአሁኑ ሰዓት በምዕራብ ሃገራት ውስጥ ከሚደርሰው ሽብር በላይ በሙስሊም ሃገራት ህዝብ ላይ የሚደርሰው በብዙ እጥፍ የከፋ ቢሆንም የሚዲያዎች ትኩረት ግን የተገለበጠ ነው። በክርስቲያን ምዕራባውያን ወረራ ያለቀው ሙስሊም በሙስሊም አሸባሪዎች ከተገደለው ክርስቲያን በብዙ እጥፍ የላቀ ነው። አላማየ "የዚያ ይበልጣል የዚያ ያንሳል" አይነት ወዝ የሌለው ሙግት መቀስቀስ አይደለም። ይልቁንም የአሸባሪዎችንም ሆነ የሰለባዎችን እምነት፣ ዜግነት፣ የቆዳ ቀለም፣ ውጫዊ ነፀብራቅ መለኪያ እያደረግን ለተመሳሳይ ጥፋት የተለያየ አቋም አናንፀባርቅ ነው። ያለበለዚያ ፍትህ ይዛነፋል። ፍትህ ሲዛነፍ ወንጀለኞች አባል ለመመልመል ይጠቅማቸዋል። ሽብርን በመዋጋት ስም እምነት ማንነቱ አብሮ የሚጠለሽበት ህዝብም ወንጀሉን ከምንጩ ለማድረቅ በሚደረገው ትግል ላይ የሚኖረው ተሳትፎ ይመነምናል።
ባጭሩ እራሳችንም ሚዲያዎቻችንም ሽብርን በመዋጋትም ይሁን በመዘገብ ላይ ከተዘንባይነት የፀዳ ወጥ አቋም ሊኖረን ይገባል። አሁን ላይ በሃገራችን እንኳ ብዙሃኑ ሕዝባችን ብቻ ሳይሆን የተማረውም ክፍል ከተዘንባይነት የፀዳ አይደለም። በዚህ ሁኔታ ላይ እያለን በሌሎች ሃገራት እንደሚደርሰው ተደጋጋሚ የሽብር ጥቃት ቢደርስብን ችግሩን ለመጋፈጥ በቂ የሚዛናዊነት ዝግጅት ያለን አይመስልም። አይሲስ በሊቢያ ኢትዮጵያውያንን ባረደበት ወቅት በከፊልም ቢሆን ሲንፀባረቁ የነበሩ አዝማሚያዎች ጥሩ ማሳያ መሆን ይችላሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ ሳይሆን ሊቢያ በተፈፀመ ጥቃት ምንም ንክኪ የሌለውን አካል እስከ መነካካት ተደርሷል። ከሰልፎች ፈር የለቀቀ ጩኸት እስከ መንገድ ላይ ትንኮሳ ያለፉት ነገሮች ይህን የሚያሳዩ ናቸው።

Post a Comment

0 Comments