Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ለአቅመ አዳም ወይም ለአቅመ ሄዋን የሚደረሰው መቼ ነው?!


ለአቅመ አዳም ወይም ለአቅመ ሄዋን የሚደረሰው መቼ ነው?!

ብዙ ሰዎች ሸሪዐዊ ሃላፊነት ለመሸከም የሚደረስበትን እድሜ ሲያስቡ 15 አመት መድረስን ብቻ ነው ከግንዛቤ የሚያስገቡት፡፡ እውነታው ግን ሌሎች ተጨማሪ መለኪያዎች መኖራቸው ነው፡፡ በጥቅሉ አንድ ሰው እንደማንኛውም "አዋቂ" ሙስሊም ተቆጥሮ በሚሰራው መልካም ስራ የሚመነዳበት እና በሚሰራው ጥፋት የሚቀጣበት (ባጭሩ ስራዎቹ የሚመዘገቡበት) የእድሜ ክልል የሚደርሰው ከሚከተሉት አራት ምልክቶች ውስጥ ቀድሞ በተከሰተው ነው፡-
1. በህልምም ይሁን በውን የዘር ፈሳሽ መርጨት መጀመር
2. በብልት ዙሪያ ፀጉር መብቀል (መባለቅ)፡-
መጠኑም ፀጉሩ ለመላጨት የደረሰ ብዛት ሲኖረው ነው፡፡ እዚህ ላይ የፂም ወይም የብብት ፀጉር መለኪያ አይሆንም፡፡ የጡት መውጣት፣ የድምፅ መጎርነንና መቅጠን መለኪያ አይደሉም።
3. ለሴት የወር አበባ ማየት፡-
እነዚህ ሶስት ምልክቶች ከታዩ ልጅዎት ለሸሪዐዊ ሃላፊነት ደርሷል ወይም ደርሳለችና ያስገንዝቡ ይከታተሉ፡፡ 15 አመት መድረስን እየጠበቁ ተዘናግተው እንዳያዘናጉ፡፡ ደግሞም ከልጆችዎት ጋር ለጉዳዩ የሚያስፈልገውን ያክል ግልፅ ውይይትና መነጋገር ይኑር፡፡ ጉዳዩን ቀድሞው ካወቁ እራሳቸውን ለሃላፊነት ያዘጋጃሉና፡፡ ካላወቁ ግን እድሜያቸው ደርሶ ላይሰግዱ ላይፆሙ ይችላሉ፡፡ ልክ እንዲሁ ካላወቁ ወይም ደግሞ አጉል መተፋፈር የሚኖር ከሆነ ከነ ጀናባቸው ሊሰግዱ፣ የወር አበባ ላይ ሆነው ሊፆሙና ሊሰግዱ ይችላሉ፡፡ ይሄ ከባድ ጥፋት ነው። ስለዚህ ለልጆችዎት ወይም ደግሞ ለእህት ወንድሞችዎት በቂ ግንዛቤ ያድርሱ፡፡ መተፋፈሩ ሐቅ እንዳይሸፍንም ይጠንቀቁ፡፡
4. የመጨረሻው ምልክት 15 አመት መድረስ ነው።
ከላይ ከተራ ቁጥር አንድ እስከ ሶስት የተጠቀሱት ምልክቶች ባይታዩም 15 ከተደረሰ ቀጥታ የልጅነት የእድሜ ክልል ታልፏል ማለት ነው፡፡
ምልክቶቹ ከ 15 አመት ቀድሞ መታየት የጀመሩ ከሆነ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ እንደማንኛውም አዋቂ ሰው ሸሪዐዊ ህግጋትን በጥብቅ መከታተል ይገባል፡፡ ምልክቶቹ ቀድመው ታይተው ሳለ ሳይፆም የታለፈ የረመዳን ፆም ካለ ቀዷ ማውጣት ግድ ይላል ይላሉ ሸይኽ ኢብኑል ዑሠይሚን ረሒመሁላህ፡፡ በማህበረሰቡ ዘንድ ስለጉዳዩ ጭራሽ ግንዛቤ ከሌለ ግን ቀዷ ማውጣቱ ግዴታ እንዳልሆነ ፍንጭ የሰጡበት ፈትዋ አለ፡፡ ወላሁ አዕለም፡፡ ዝርዝር መረጃ ወይም ግልፅ እና ቀጥተኛ ፈትዋ ያገኘ ሰው ከስር ቢያሰፍረው ሁላችንንም ይጠቅማል፡፡
በነገራችን ላይ 15 አመት መድረስ ሲባል የሚፈለገው በኢስላማዊው የሂጅራ አቆጣጠር እንጂ በፀሐይ አቆጣጠር አይደለም፡፡ (የሂጅራው አቆጣጠር የጨረቃ አቆጣጠር ሲሆን የኢትዮጵያውና የፈረንጆቹ ግን የፀሐይ አቆጣጠር እንደሚባል ያስተውሉ፡፡) በጨረቃ አቆጣጠር አንድ አመት 354 ቀን ከ 9 ሰዓት አካባቢ ሲሆን በፀሐይ አቆጣጠር ግን 365 ቀን ከ 6 አካባቢ ነው፡፡ እናም አንድ ልጅ በሂጅራው አቆጣጠር 15 አመት የሚደርሰው ከፀሐዩ አቆጣጠር ቢያንስ ከ 5 ወራት በፊት ቀድሞ ነው ማለት ነው፡፡
ስለዚህ አንድ ልጅ ከ 15 ዓመት በፊት ከላይ ከአንድ እስከ ሶስት ካሉት ምልክቶች አንዱ ከታየበት ወይም ደግሞ እነዚህ ሳይታዩ ቀርተው 15 አመት ከደረሰ ጊዜ ጀምሮ እንደማንኛውም አዋቂ ሰው ለሸሪዐዊ ህግጋት ተገዥ መሆን አለበት፡፡ ከዚህ በኋላ ሴቶችን መጨበጥ፣ መመልከት፣ ከአንዲት ሴት ጋር ለብቻ ተገልሎ መቀመጥ የለበትም፡፡ በቃ ከዚህ በኋላ በደረሱ ወንዶች ላይ የሚከለከሉ ነገሮች ሁሉ ለሱም ክልክል ናቸው፡፡ የደረሱ ወንዶችን የሚመለከቱ ግዴታዎች ሁሉ ይመለከቱታል፡፡ ሴቷንም እንዲሁ፡፡ አለባበስን ጨምሮ ነገሮችን በጥንቃቄ ልትከታተል ይገባታል፡፡

(ኢብኑ ሙነወር፣ ሚያዚያ 2/2009)

Post a Comment

0 Comments